የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን (ዋሊያዎቹ) ዋና አሠልጣኝ ውበቱ አባተ፣ ያሳኩት ውጤት በዕቅድና በሥራ የተገኘ ነው ሲሉ ከትናንት በስቲያ ሰኞ መጋቢት 27 ቀን 2013 ዓ.ም. በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አብራርተዋል፡፡
ጋዜጣዊ መግለጫው በዋናነት አሠልጣኙ ብሔራዊ ቡድኑን በኃላፊነት ከተረከቡ በኋላ ያደረጓቸውን የመጨረሻዎቹን ሁለት ጨዋታዎችና ቀደም ሲል በሰበታ ከነማ እግር ኳስ ክለብ በነበሩበት ወቅት የነበራቸውን የውል ስምምነት የተመለከተ ነበር፡፡
ከቀድሞ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አሠልጣኝ ኢንስትራክተር አብርሃም መብርሃቱ ምትክ በ2012 የውድድር ዓመት መጨረሻ ዋሊያዎቹን የተረከቡት አሠልጣኝ ውበቱ አባተ፣ ኢትዮጵያ ከስምንት ዓመት በኋላ ለአፍሪካ ዋንጫ የበቃችበትን ውጤት አሳክተዋል፡፡ አንዳንዶች የኢትዮጵያ ቡድን ለዚህ ስኬት የበቃበትን መንገድ ከዕድል ጋር የሚያያይዙት ቢኖሩም፣ አሠልጣኝ ውበቱ በዚህ አይስማሙም፡፡ ለዚህም የቡድኑን ኃላፊነት ተረክበው መደበኛ ዝግጅት ከመጀመራቸው በፊት ከተጫዋቾቻቸው ጋር ያቀዷቸውን ዕቅዶችና ውይይቶች ተመልክቶ እውነታውን መረዳት እንደሚቻል ጭምር ነው በመግለጫቸው ያብራሩት፡፡
አሠልጣኙ ለመጀመሪያዎቹ የቡድናቸው ስብስብ ‹‹እመኑኝ ለካሜሩን የአፍሪካ ዋንጫ እንበቃለን፤›› ብለው እንደነገሯቸው፣ ይህ ደግሞ በምኞት ብቻ ሳይሆን ሊተገበሩ የሚችሉ ዕቅዶች አቅደው መሥራት በመቻላቸው እንደሆነም አስረድተዋል፡፡
አሠልጣኝ ውበቱ ብሔራዊ ቡድኑን ለማሠልጠን ኃላፊነቱን የተረከቡት፣ የቀድሞ አሠልጣኝ ኢንስትራክተር አብርሃም ብሔራዊ ቡድኑን ይዘውና በምድቡ ከጠንካራዋ አይቮሪኮስት ጋር በባህር ዳር ስታዲየም ተጫውተው 2ለ1 በሆነ ውጤት የረቱበት ወቅት መሆኑ የበረታ ተቃውሞ በሚደመጥበት ወቅት እንደነበር ይታወሳል፡፡
ለአሠልጣኝ ውበቱ ሌላው የተነሳላቸው ጥያቄ፣ ዓምና ከፋሲል ከነማ ጋር የነበረው ውል እንደተጠናቀቀ ሰበታ ከነማን ለማሠልጠን የሁለት ዓመት ኮንትራት የተፈራረሙበት ጊዜ እንደመሆኑ መጠን ከክለቡ ጋር የተለያዩበት ሁኔታና የሕግ አካሄድ ምን እንደሚመስል የተመለከተ ነበር፡፡
አሠልጣኙ ብሔራዊ ቡድኑን ለማሠልጠን ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የሁለት ዓመት ኮንትራት ሲቀበሉ፣ በክለቡ ያልሠሩበትን የአንድ ዓመት የፊርማ ክፍያ ለክለቡ እንደመለሱ፣ ሆኖም ግን ከክለቡ ሊከፈላቸው የነበረውን ክፍያ በተመለከተ ግን ከፌዴሬሽኑ እንደሚያገኙ ቃል እንደተገባላቸው አውስተዋል፡፡
ከአሠልጣኝ ውበቱ አባተ ጋር በጋዜጣዊ መግለጫው ለተገኙት የብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ባህሩ ጥላሁን ከብሔራዊ ቡድኑ ቀጣይ ጉዞና ተያያዥ ጉዳዮችን በተመለከተ ለተነሱ ጥያቄዎች ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
በካሜሩን አስተናጋጅነት ለመጀመሪያ ጊዜ 24 ቡድኖችን ለሚያሳትፈው የአፍሪካ ዋንጫ አስተናጋጇ ካሜሩን፣ ኢትዮጵያ፣ አልጀሪያ፣ ቡርኪና ፋሶ፣ ኬፕቨርዴ፣ ኮሞሮስ፣ አይቮሪኮስት፣ ግብፅ፣ ኢኳቶሪያል ጊኒ፣ ጋቦን፣ ጋምቢያ፣ ጋና፣ ጊኒ፣ ጊኒ ቢሳዋ፣ ማላዊ፣ ማሊ፣ ሞሪታኒያ፣ ሞሮኮ፣ ናይጀሪያ፣ ሴኔጋል፣ ሱዳን፣ ቱኒዚያ፣ ዚምባቡዌና ቤኒን ተሳታፊዎች ይሆናሉ፡፡