Thursday, November 30, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዓለምየመዘጊያ ቀነ ገደባቸው ያበቃው የኬንያ የስደተኛ መጠለያዎች

የመዘጊያ ቀነ ገደባቸው ያበቃው የኬንያ የስደተኛ መጠለያዎች

ቀን:

ኬንያ በአገሯ የሚገኙትንና በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ስደተኞችን የያዙትን መጠለያዎች ለመዝጋት ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የስደተኞች ኮሚሽን የሰጠችው የሁለት ሳምንታት ቀነ ገደብ ትናንት መጋቢት 28 ቀን 2013 ዓ.ም. አብቅቷል፡፡

በሰሜን ምዕራብና በምሥራቅ ኬንያ የሚገኙት የዳዳብና የካኩማ የስደተኛ መጠለያዎች ከ410 ሺሕ በላይ ስደተኞችን ያስጠለሉ ናቸው፡፡ ከእነዚህ ውስጥ የደቡብ ሱዳን ስደተኞች በቁጥር አነስተኛ ሲሆኑ፣ የሶማሊያ ስደተኞች ደግሞ በርካታ መሆናቸውን የኮሚሽኑ መረጃ ያሳያል፡፡

የኢትዮጵያ፣ የታንዛኒያ፣ የኡጋንዳና የቡሩንዲ ስደተኞች የሚገኙባቸውን የስደተኛ መጠለያዎች ኬንያ እንደምትዘጋ የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ የሰጠችው የደኅንነት ሥጋት አለብኝ በሚል ነው፡፡

የኬንያ መንግሥት ለሶማሊያ ድንበር ቅርብ የሆነው ዳዳብ የስደተኞች መጠለያ እንዲዘጋ እንደሚፈልግና የደኅንነት ሥጋት እንዳለበት በመጀመርያ ያስታወቀውም እ.ኤ.አ. በ2016 ነው፡፡ ከዚህ በማስከተልም የካኩማ የስደተኞች መጠለያ እንዲዘጋ ማሳሰቡ አይዘነጋም፡፡

የኬንያ አገር ውስጥ ሚኒስትር ፍሪድ ማታኒ የተመድ ስደተኞች ኮሚሽን ሁለቱንም መጠለያዎች እንዲዘጋ የ14 ቀናት ጊዜ ገደብ መስጠታቸውንና ከዚህ በኋላ አጀንዳው ላይ ምንም ተጨማሪ ውይይት እንደማይደረግ ያስታወቁት ከሁለት ሳምንት በፊት ነበር፡፡

የመዘጊያ ቀነ ገደባቸው

 

ኮሚሽኑም ጥበቃ የሚያስፈልጋቸው ስደተኞች ያገኙ የነበረውን አገልግሎት እንዳያጡ ከኬንያ መንግሥት ጋር ውይይት ለማድረግ ቃል ገብቶ፣ የመጠለያዎቹ መዘጋት የኮቪድ-19 ተፅዕኖን መቋቋምን ጨምሮ ሌሎች ጥበቃዎች ላይ የሚኖረውን አሉታዊ ተፅዕኖም አንስቷል፡፡

ዴይሊ ኔሽን ጋዜጣ እንዳሰፈረው፣ የስደተኛ መጠለያዎቹ የማይዘጉ ከሆነ የኬንያ መንግሥት ስደተኞቹን ወደ ሶማሊያ ድንበር የሚያስጠጋ ይሆናል፡፡ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ሥርጭት ለመከላከል ዓምና ወደ ዳዳብም ሆነ ካኩማ የስደተኞች መጠለያ መግባትም ሆነ መውጣት እንደማይቻል ያስታወቀው የኬንያ መንግሥት በዓመቱ ደግሞ መጠለያዎቹ እንዲዘጉ ብሏል፡፡

በመጠለያዎቹ የሚኖሩ ስደተኞች ሥጋት

አልጀዚራ ከሥፍራው ተገኝቶ እንደዘገበው፣ በሁለቱ ስደተኛ መጠለያዎች ካሉት 410 ሺሕ ያህል ስደተኞች አብዛኞቹ የሚያውቁት ይህንኑ መጠለያ ብቻ ነው፡፡ በመሆኑም የኬንያ መንግሥት ውሳኔ አስደንጋጭ ሆኖባቸዋል፡፡

በሁለቱም መጠለያ ጣቢያዎች የተናፈሰው ‹‹የይዘጋል›› መረጃም በስደተኞች ላይ ፍርሃትን አንግሷል፣ ተስፋም አስቆርጧል፡፡ በካኩማ መጠለያ የሚገኘው የ26 ዓመቱ ደቡብ ሱዳናዊ ‹‹ከመጠለያው ውጪ የምናውቀው ሌላ ቤት የለንም፤›› ብሏል፡፡

ላለፉት አሥር ዓመታት በካኩማ ስደተኛ መጠለያ ውስጥ የኖረችው ሶማሊያዊቷ ሂቦ ሞሐመድ፣ ‹‹የኬንያ መንግሥት የስደተኛ መጠለያዎቹን እዘጋለሁ ማለቱን ስሰማ ተረብሻለሁ፡፡ ሶማሊያ ያልተረጋጋች አገር ናት፡፡ አሁንም የሽብር ጥቃት በተደጋጋሚ ይፈጸምባታል፡፡ ካኩማ የእኔ ቤት ነው፣ ሰላም ያገኘሁበት ቤት፤›› ብላለች፡፡ ስደተኞቹ ምን እንደሚመጣ፣ የት እንደሚሄዱም አለማወቃቸው ሥጋት ውስጥ እንደከተታቸው ተዘግቧል፡፡

ስደተኞቹ የት ይሄዳሉ?

የኬንያ መንግሥት፣ ለተመድ ስደተኞች ኮሚሽን ላቀረበው ጥያቄ ምላሽ የማያገኝ ከሆነ ስደተኞቹን ወደ ሶማሊያ ድንበር ለማስጠጋት እንደሚገደድ አስታውቋል፡፡ ከ190 ሺሕ በላይ ስደተኞች የሚገኙበት የካኩማ መጠለያ ጣቢያ ከኬንያ በሰሜን ምዕራብ ይገኛል፡፡ ዳዳብ ደግሞ በምሥራቅ ኬንያ የሚገኝ ሲሆን፣ ይህ ለሶማሊያ ድንበር ቅርብ ነው፡፡ ሆኖም በርካታ የሶማሊያ ስደተኞች ሁለቱም ስደተኛ መጠለያዎች እየተመላለሱ የሚኖሩ ናቸው፡፡

በሁለቱም ጣቢያዎች ሕይወት ከባድ እንደሆነ ስደተኞቹ ይገልጻሉ፡፡ ሩቅና ገጠራማ አካባቢ መገኘታቸው፣ ለመንቀሳቀስ አለመፈቀዱ፣ ሙስና እና ደካማ አገልግሎት አለ ቢሉም፣ ከቀያቸው የተሻለ ሰላምና ደኅንነት እንዳገኙና በንግድ ሥራ ዕድልም ሆነ በትምህርት ተጠቃሚ እንደሆኑ ይናገራሉ፡፡

የስደተኛ መጠለያዎቹ ሲዘጉ በቀጣይ ምን እንደሚሆን በተለይም የት እንደሚሄዱ አለማወቃቸው ሐሳብ እንደሆነባቸው እ.ኤ.አ. ከ2005 ጀምሮ ከኢትዮጵያ የተሰደደውና በሁለቱም መጠለያዎች የኖረው የ26 ዓመቱ ኢትዮጵያዊ ዴቪድ ኦሞድ ተናግሯል፡፡

‹‹የት እንሄዳለን›› የሚለው ዴቪድ፣ በርካቶች በትንሹ 20 ዓመትና ከዚያ በላይ ኖረዋል፣ እዛው የተወለዱም አሉ፡፡ ከወጡበት አገር ምንም ዓይነት ሀብት የላቸውም፡፡ ወጣት ስደተኞች ደግሞ በኬንያ ትምህርት ጀምረዋል፣ ለበርካታ ዓመታት ከተኖረበት ሥፍራ ተነስቶ በአዲስ ቦታ ሕይወት መጀመርም ከባድ ነው ብሏል፡፡

ከሶማሊያ ተሰዶ በካኩማ ካምፕ መኖር ከጀመረ አሥር ዓመታትን ያስቆጠረው አብድራህማን አህመድ ደግሞ ‹‹ማንም ሰው ስደትን መርጦ ወደ ሌላ አገር የሚሄደው በአገሩ ምርጫ ስላጣ ነው፤›› ይላል፡፡ የኬንያ መንግሥትን ውሳኔም ‹‹ሰብዓዊነትን ማግለል›› ይለዋል፡፡

የቀድሞ የሶማሊያ የደኅንነት ባለሙያ አብዱላህ ሞሐመድ፣ ከስደተኛ መጠለያዎቹ ጋር በተያያዘ ‹ኬንያ የደኅንነት ሥጋት አለብን› የምትለው የተጋነነ ነው ይላል፡፡ አል ሻባብ ምናልባት በስደተኛ ጣቢያዎቹ ሰርጎ ገብቶ ተዋጊ ሊመለምል ይችላል፡፡ ነገር ግን ስደተኞች በሙሉ በዚህ ሊፈረጁ አይገባም፡፡ ሁሉም ስደተኞችም ጉልህ የደኅንነት ሥጋት አይደሉም፡፡

በዳዳብ እና ካኩማ የስደተኛ መጠለያ የሚኖሩ በርካታ ስደተኞች ወደ ምዕራባውያን አገሮች እንሄዳለን በሚል ተስፋ ዓመታትን ያስቆጠሩ ናቸው፡፡ የቀናቸው ሲያቀኑ፣ ያልቀናቸው ተስፋ ሰንቀው ዓመታትን በመጠለያዎቹ አሳልፈዋል፡፡ ትዳር መሥርተዋል፣ ወልደዋል፡፡ በንግድ ሥራ የተሰማሩ፣ የሚማሩና ሌላም ሥራ የሚከውኑም አሉ፡፡ ከዚህ ቀደም የቀድሞ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የአሜሪካን በር ለስደተኞች ዝግ ሲያደርጉ በርካቶች ራሳቸውን ማጥፋታቸውንም ዘገባው ያሳያል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመቃወም ነፃነት ውዝግብ በኢትዮጵያ

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የሾላ አካባቢ...

የሲሚንቶን እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አጓጊ ጥረት

በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆን ከሚጠቀሱ ምርቶች...

የብሔር ፖለቲካው ጡዘት የእርስ በርስ ግጭት እንዳያባብስ ጥንቃቄ ይደረግ

በያሲን ባህሩ በሪፖርተር የኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም “እኔ...