Saturday, May 25, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊከታላቁ ቤተ መንግሥት ጀርባ ያለው ኑሮ

ከታላቁ ቤተ መንግሥት ጀርባ ያለው ኑሮ

ቀን:

ታላቁ ቤተ መንግሥት ከሚገኝበት ጀርባ ጎስቋላ መንደሮች ያሉ አይመስልም፡፡ ወደ መንደሩ ሲገባ በመዲናዪቱ ያለውን እጅግ ዝቅተኛ ኑሮና ባሻገር ደሃ መኖሩን የሚዘነጉ ሀብታሞች መኖራቸውን ማሳያ የሆኑ ልዩነቶች ቁልጭ ብለው ይታያሉ፡፡

በመንደሩ ያሉ ቤቶች የተያያዙ ናቸው፡፡ ሁሉም ቁመታቸውና ርዝመታቸው ተመሳሳይ እንደሆነም ለመገመት አያዳግትም፡፡

የዚህ መንደር ነዋሪዎች ቤቶቻቸው እግር ዘርግቶ ለመቀመጥ የሚያስቸግር ነው፡፡ የአብዛኛዎቹ ቤቶች መኝታዎቻቸው ቆጥ ላይ ነው፡፡ ሰባት፣ ስምንትና ከዚያ በላይ የሆኑ ቤተሰብ ያላቸው በዚሁ ቤት እንደሚኖሩ ተነግሮናል፡፡

- Advertisement -

የጎኑ ስፋት ሁለት ሜትር፣ በሦስት ሜትር የሆኑ ቤቶች ውስጥ ከዘጠኝ ያላነሱ ቤተሰቦች ይኖሩበታል፡፡ ወደ መንደሩ ጠጋ ሲባል አፈርና ደቃቅ ከሰልን በመደባለቅ ለምግብ ማብሰያነት የሚሸጡ በርካታ እናቶች ፊታቸው በጥላሸት፣ እጃቸው በጭቃ ቢጨማለቅም ባለመሰልቸት ሥራቸውን ያከናውናሉ፡፡  

ለምግብ ማብሰያ የሚሸጡትም ጥፍጥፍ ከትርፍ ድካሙ የበዛ፣ እሱም ቢሆን ለሕመም እየዳረጋቸው መሆኑን ያስረዳሉ፡፡ ብሶትና ምሬት እንዳለበት ከገጻቸው ማንበብ አያዳግትም፡፡ በመንደሩ ይኼን ሥራ ሲሠሩ ያገኘናቸው እናት ‹‹ይኼ ኑሮ ነው ልጄ? ልጆቼ የዕለት ጉርስ እንዳያጡ እንጂ ትርፍ ኖሮት አይደለም፤›› በማለት በሐዘኔታ ይናገራሉ፡፡ የሆዳቸውን በሆዳቸው ይዘው የሚበሳጩትን ደግሞ ቤት ይቁጠራቸው፡፡

ወደ መንደሩ ባለፈው ሳምንት የገባነው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከሦስት ዓመታት በፊት ወደ ሴፍቲኔት ፕሮግራም ያስገባቸው ተጠቃሚዎች የደረሱበትን ደረጃ ለማየት ነው፡፡  

በአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 8 በሴፍቲኔት ተጠቃሚ ከሆኑት ውስጥ መጀመርያ ያነጋገርናቸው እናት ኑሯቸው እየተሻሻለ፣ ልጆቻቸውን መመገብና ማስተማር መጀመራቸውን ቢናገሩም አሁንም ችግሮቻቸው ግን እንዳልተቀረፉ ግን ከመናገር አልተቆጠቡም፡፡

እኚህ እናት ከቤተ መንግሥት ወረድ ብሎ ባለው ቦታ በጓሮ አትክልት ሰላጣ፣ ጎመንና ጥቅል ጎመን እያለሙ የዕለት ጉርሳቸውን፣ አለፍ ሲልም ለጎረቤቶቻቸው እየሸጡ ኑሯቸውን ይገፋሉ፡፡ ከሠላሳ በላይ ሆነው በቦታው ላይ ያለሙ የነበሩት ቁጥራቸው የተመናመነው ቦታው መንግሥት ለአረንጓዴ ልማት ፕሮጀክት የሚያውለው በመሆኑ ነው ይላሉ፡፡

ከዚህ ቀደም በልቶ ማደር፣ ልጆች ማስተማር የቅንጦት መሆኑን የሚናገሩት እኚህ እናት አሁን ላይ ልጆቻቸውን ከዕለት ጉርስ ባሻገር እያስተማሩ መሆኑን ይናገራሉ፡፡

ባለቻቸው አነስተኛ ቦታ ዶሮ በማርባትና በሌሎች ሥራዎች የሚተዳደሩት ሌላኛዋ እናት የሴፍቲኔት ተጠቃሚ ናቸው፡፡ እንደ አብዛኛው የመንደሩ ነዋሪዎች ከእጅ ወደ አፍ የሆነ ኑሮ ውስጥ እንዳሉ ቢናገሩም ከዚህ ቀደም ከነበረው አኗኗር እንደሚሻል  ግን ያስረዳሉ፡፡

ከመንግሥት በድጎማ ባገኙት 14 ሺሕ ብር የዶሮ ዕርባታን ቢጀምሩም፣ ገሚሶቹ በበሽታ እየሞቱባቸው ቁጥራቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እንደቀነሰባቸው ተናግረዋል፡፡ ይህም ብመሆኑ ከዚህ ቀደም ይተዳደሩበት ወደነበረውና በአዲሱ ሥራቸው ምክንያት ትተውት ወደነበረው የመንገድ ጠረጋና መሰል ሥራዎችን መመለስን ይፈልጋሉ፡፡ አሁንም የመንግሥት ድጋፍ፣ እገዛና ክትትል የሚያስፈልጋቸው መሆኑን ሁለቱም እናቶች በተደጋጋሚ ተናግረዋል፡፡

በአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 8 ነዋሪ የሆኑት ወ/ሮ ደብሪቱ ሙሉጌታ የሴፍቲኔት ተጠቃሚ መሆን ከጀመሩ ሦስት ዓመታት አልፏቸዋል፡፡ ባገኙት ሥልጠናና የሥራ ዕድል ቋሚ የመንግሥት ሠራተኛ መሆናቸውን የገለጹ ሲሆን፣ በከተማ ግብርና ላይ በመሳተፍ የዕለት ጉርሳቸውን የሚያገኙበትን ዕድል ማግኘታቸውን ጠቁመዋል፡፡

ወ/ሮ ደብሪቱ እንደተናገሩት፣ በወረዳው 105 የሚሆኑ ተጠቃሚዎች በሴፍቲኔት የታቀፉ ሲሆን፣ አሁን ላይ 99 ሰዎች በዶሮ ዕርባታ፣ በልብስ ስፌትና መሰል ሥራዎች ተሰማርተው ራሳቸውን እየደጎሙ ይገኛሉ፡፡

በሴፍቲኔት የታቀፉት በሙሉ ተለውጠዋል ማለት ባይቻልም፣ አብዛኛዎቹ ከነበሩበት የባሰ ችግር እንዲወጡ መታገዛቸውንም አክለዋል፡፡

በወረዳው የሴፍቲኔት ተጠቃሚዎች አትክልት በመሸጥና ዶሮ በማርባት ሥራዎች የተሰማሩ ሲሆን፣ ኑሯቸውን ከዚህ የበለጠ ለማሻሻል መንግሥት የብድር አገልግሎትና የሚሠሩበት ቦታ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ የምግብ ዋስትና ፕሮግራምን በመታለም በተለይ ከ2009 በጀት ዓመት ጀምሮ በመዲናዪቱ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ የማኅበረሰብ ክፍሎች ፕሮግራሙ ተግባራዊ አድርጓል፡፡  

በአዲስ አበባ 29,410 የምግብ ዋስትና ፕሮግራም ተጠቃሚዎች ሕይወታቸውን በዘላቂነት እንዲያሻሽሉ ከተቋማት ጋር በመሆን የማሸጋገርና የማረካከብ ሥራዎች መሥራቱን የከተማው አስተዳደር ማስታወቁ ይታወቃል፡፡

በመጀመርያው ዙር የምግብ ዋስትና ፕሮግራም የታቀፉ የኅብረተሰብ ክፍሎችን በደረቅ ቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ፣ በውበትና አረንጓዴ ልማት፣ በከተማ ግብርናና በመሠረተ ልማት ዘርፍ መሰማራታቸውን የከተማ አስተዳደሩ የምግብ ዋስትናና ልማታዊ ሴፍቲኔት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ አሳመነ ጌራወርቅ ተናግረዋል፡፡

የፕሮግራሙ ተጠቃሚ የሆኑት በቤተሰብ ከ29 ሺሕ በላይ መሆናቸውም ተገልጿል፡፡

ለተጠቃሚዎቹ በሴፍቲኔት ከታቀፉ በሦስተኛ ዓመት መጨረሻ ላይ በቤተሰብ ደረጃ 14,470 ብር መሰጠቱን የጠቆሙት ዳይሬክተሩ፣ በስጦታ የተሰጣቸው ገንዘብ መጠን በድምሩ 425,562,700 ነው፡፡

በፕሮግራሙና በአመለካከት ላይ ግንዛቤ በመፍጠር፣ የባንክ አካውንት በመክፈት ከሚከፈላቸው 20 በመቶ በማስቆጠብ፣ የገንዘብ አያያዝና መሰል ሥልጠናዎች እንዲያገኙ መደረጉንም ጠቁመዋል፡፡

ሕይወታቸውን በዘላቂነት እንዲያሻሽሉ ለማድረግ በመረጡትና በሠለጠኑበት ዘርፍ በመደበኛና በኢመደበኛ የሥራ ዘርፎች የሥራ ዕድል ተጠቃሚ በማድረግ ከተያዘው 29,410 ዕቅድ ውስጥ 23,616 የሥራ ዕድል ፈጠራ ማስገኘት ተችሏል ያሉት ዳይሬክተሩ፣ በዚህም 80.3 በመቶ ያህሉ የሥራ ዕድል ያገኙ ሲሆን፣ የተቀሩትን የሚሻሻሉበትና የሚታገዙበት መንገድ እየተመቻቸ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

በኢትዮጵያ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎችን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ ለመጀመርያ ጊዜ የተተገበረው በ11 ከተሞች ሲሆን፣ በተያዘው በጀት ዓመት የተሻለ ውጤት በማሳየቱ በ72 አዳዲስ ከተሞች ጭምር በአገር አቀፍ ፕሮግራምነት እንዲተገበር መደረጉ ተገልጿል፡፡  

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መረጃ እንደሚያሳየው፣ 766,800 ከድህነት ወለል በታች ከሆኑ ነዋሪዎች መካከል 415,923 (55 በመቶ) የሚሆኑ ተጠቃሚዎች ከ2009 ዓ.ም. ጀምሮ በፕሮግራሙ ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡

የመሥራት አቅም ያላቸው ግለሰቦች በማኅበረሰብ አቀፍ ልማትና የመሥራት አቅም የሌላቸውን ደግሞ በቀጥታ ድጋፉ ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉም ተወስቷል፡፡

ፕሮግራሙ በአገር አቀፍ ደረጃ እንዲተገበር ከተመደበው 450 ሚሊዮን ዶላር ውስጥ ከዓለም አቀፍ አበዳሪዎች ተቋማት 300 ሚሊዮን ዶላር ብድር የተገኘ ሲሆን፣ መንግሥት 150 ሚሊዮን ዶላር መድቧል፡፡ ለአዲስ አበባ ከተማ 70 በመቶ በመመደብ ወደ ሥራ መገባቱ ተገልጿል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የማዳበሪያ አቅርቦትና ውጣ ውረዱ

በቅፅል ስሙ “The Father of Chemical Warfare” እየተባለ የሚጠራው...

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የትርፍ ምጣኔውን ከ70 በመቶ በላይ አሳደገ

ከሁለቱ መንግሥታዊ ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ...