ኢትዮጵያ ዓምና መጋቢት 27 ቀን 2012 ዓ.ም. በኮቪድ-19 ቫይረስ ምክንያት የመጀመርያውን ሞት አስመዝግባ ነበር። ዘንድሮ በተመሳሳይ ቀን በ24 ሰዓት ውስጥ 37 ሰዎች በኮቪድ-19 ቫይረስ ሕይወታቸውን ማጣታቸውን የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ሳይንስ ኢንስቲትዩት አስታውቋል። ይህም ወረርሽኙ ወደ አገር ውስጥ ከገባ ጊዜ ጀምሮ ከፍተኛው የሞት ቁጥር ሆኖ ተመዝግቧል። መጋቢት 28 ቀን 2013 ዓ.ም. በወጣው ዕለታዊ መረጃ 8190 ሰዎች ተመርምረው 2054 ሰዎች ቫይረሱ ተገኝቶባቸዋል፡፡ 25 ሰዎች ሕይወታቸው ሲያልፍ፣ 850 ሰዎች ጽኑ ሕሙማን ክፍል ውስጥ ይገኛሉ፡፡
እስከ ተጠቀሰው ዕለት ድረስ በጠቅላላው ሕይወታቸውን ያጡት ቁጥር 3025 ሆኗል፡፡
‹‹ሁላችንም ራሳችንን እና የምንወዳቸውን ስዎች በኮቪድ-19 ምክንያት እንዳናጣ የመከላከያ መንገዶችን እንተግብር፤›› ሲል ኢንስቲትዩቱ አሳስቧል፡፡››
የጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ማብራርያ
ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ኮቪድ19ን ለመከላከል ከወጣው መመርያ ጋር በተያያዘ በመሠረታዊ ጉዳዮች ላይ የሰጠው ማብራሪያ እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡
- ስለ ስብሰባ፤
ስለ ስብሰባ የሚደነግገው አንቀጽ ውይይት ማድረግ የሚፈልግ የትኛውም ተቋም የተሳታፊዎቹን ቁጥር ከ50 እንዳይበልጥ የሚከለክል ሲሆን፣ ከ50 በላይ ተሳታፊዎችን የሚያቅፉ ውይይቶች አስገዳጅ ከሆኑ የአዳራሹን ወይም የመወያያውን ስፍራ ሰው የመያዝ አቅም አንድ አራተኛውን በመጠቀምና ለሰላም ሚኒስቴር በማሳወቅ፣ እንዲሁም በተሳታፊዎቹ መካከል የሚኖረው አካላዊ ርቀት ከሁለት የአዋቂ እርምጃ ሳያንስ እንዲሁም የአፍ እና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል እንዲጠቀሙና የእጅ ንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁስ እንዲሟላ በማድረግ ማከናወን የሚቻል መሆኑን ይደነግጋል፡፡
ከዚህና መመርያው ላይ የተቀመጡት ድንጋጌዎች ድርጊትን የሚከለክሉ ሳይሆኑ ገደብ የሚጥሉ በመሆናቸው ገደቦቹን በማክበር የተፈለገውን ዓላማ ማሳካት የሚያስችል ሕግ ነው፡፡ በምርጫ ቅስቀሳና መሰል የሕዝብ ስብሰባዎች አካሄድ ላይ ገዢውም ሆነ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ይህንን መመርያ ባከበረ ሁኔታ መከወን አለባቸው፡፡ ከዚህ በዘለለ ፓርቲዎች ደጋፊዎቻቸውን ወይም ሕዝቡን አግኝተው ዓላማቸውን መግለጽ መቻላቸው ለፓርቲዎቹ ብቻ ሳይሆን ለመራጩ ሕዝብ በዕውቀት ላይ የተመሠረተ ምርጫ ለማካሄድ የሚረዳው በመሆኑ የምርጫ ቅስቀሳና ውይይቶች መደረጋቸው የሚፈለግ ነውና የወረርሽኙን ሥርጭት ለመቆጣጠር የሚያስችሉ በመመርያው ላይ የተቀመጡ ክልከላዎችን በማክበር መንቀሳቀስ በሕግ የሚደገፍ ተግባር ነው፡፡
- ሌላው ከላይ የተጠቀሰውን የምርጫ ቅስቀሳና ውይይት ለማድረግ የፈለገ አካል ወይም ፓርቲ ስብሰባውን ለማድረግ ፈቃድ የሚጠይቀው አካል አለመኖሩ ነው፡፡ በዚህ መመርያ መሠረት የኮቪድ-19ን ሥርጭት ለመከላከል የተቀመጡትን ገደቦች እስካልጣሰ ድረስ ፓርቲው ስብሰባ ለማካሄድ፣ ከየትኛውም የመንግሥት አካል ፈቃድ እንዲሰጠው የመጠየቅ ግዴታ የሌለበት ሲሆን፣ የሰላም ሚኒስቴር የተጣለበትን በሽታውን የመዋጋት ኃላፊነት በሚገባ መወጣት እንዲችል ስብሰባው እንደሚደረግ አስቀድሞ ሚኒስቴሩ እንዲያውቅ ማድረግ ግን ግዴታ ነው፡፡
- መመርያው በመንግሥት ተቋማት ላይም ተፈጻሚነት ያለው ስለመሆኑ፤ ለተቋማችን እየቀረቡ ካሉት ጥያቄዎች መካከል አንዱ መመርያው በመንግሥት ተቋማት ቢጣስ ተጠያቂነትን ያስከትላል ወይ የሚል ነው፡፡ ከዚህ አንጻር ከመመርያው የምንረዳው የወጣበት ዓላማ ሁሉንም የማኅበረሰብ አካል በእኩል ለመግዛት ነው፡፡ ይህ ማለት በመመርያው የተጣሉትን ገደቦችም ሆነ ግዴታዎች ጥሶ የሚገኝ ማንኛውም የመንግሥት ተቋም እንደ የግል ተቋማትና ግለሰቦች ሁሉ በሕግ ከመጠየቅ የሚድንበት ሁኔታ አይኖርም ማለት ነው፡፡ የመንግሥት ተቋማት፣ የግል ድርጅቶችና ግለሰቦች በሕጉ የተጣለባቸውን ግዴታ እንዲወጡ ምሳሌ ሆነው መቅረብ አለባቸው፡፡ ቀድመው የታቀዱ ውይይቶቻቸውን እየሰረዙ ወይም ላልተወሰነ ጊዜ እያራዘሙ ወይም በበይነ መረብ ለማካሄድ በመወሰን ላይ ላሉ ተቋማት ኮሚቴው ምስጋናውን ያቀርባል፡፡
- ስለ ቅጣት፤
የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ካለው በቀላሉ የመሠራጨት ዕድል የተነሳ ሰዎችን ማሰር አማራጭ አይሆንም፡፡ በመሆኑም ወደ እስር ከመገባቱ በፊት ሕዝቡን ማስተማርና ማስጠንቀቅ የግድ ይላል፡፡ ሆኖም ትምህርቱንና ማስጠንቀቂያውን ችላ ብለው በወንጀል ተግባር ተሰማርተው የሚገኙ ሰዎችን በወንጀል መጠየቅ ያስፈልጋል፡፡
መመርያው ያመላከተው የወንጀል ሕጉም አንቀጽ 522 በድርጊቱ ጥፋተኛ የተባለ ሰው እስከ ሁለት ዓመት ቀላል እስራት ይቀጣል ይላል፡፡ ይህ ማለት አንዳንድ ሚዲያዎች እንደሚሉት በኢትዮጵያ ማስክ አለማድረግ ሁለት ዓመት ያስቀጣል በሚል መረዳት አደጋ አለው፡፡ ድንጋጌው ቀላል እስራቱ እስከ ሁለት ዓመት ቀላል እስራት ነው የሚለው እስከ ተባለ ሁለት ዓመት ጣራው ሆኖ መነሻ የእስራት መጠን አለው ማለት ነው፡፡ በወንጀል ሕጋችን ጠቅላላ ክፍል ቀላል እስራት መነሻው 10 ቀን እንደሆነ ይደነግጋል፡፡ በመሆኑም ወንጀሉ የሚያስጠይቀው በ2 ዓመት ሳይሆን ከ10 ቀን እስከ 2 ዓመት ሊደርስ በሚችል ቀላል እስራት ነው ማለት ነው፡፡ በመሆኑም ተፈጸመ የተባለው የሕግ ጥሰት ውስጥ ያሉ የድርጊትና የሐሳብ ክፍል ከግምት ገብቶ እንደ ወንጀሉ ክብደት ደረጃ ወጥቶለት የሚወሰን ነው ማለት ነው፡፡
በቀላል ምሳሌ ለማስረዳት አንድ አጠገቡ ካለ ሰው ከ2 ሜትር በታች በሆነ ርቀት ውስጥ ተጠግቶ የቆመ ሰውና በሽታው እንዳለበት እያወቀ ከሌሎች ጋር የተቀላቀለ፣ አብሮ የተንቀሳቀሰ ወይም ምግብ የተመገበ ሰው የወንጀል ባህሪ (አደገኝነታቸው) እኩል ሊሆን አይችልም፡፡ በመሆኑም ሰው መቀጣት ያለበት ባጠፋው ልክ በመሆኑ ቅጣት ሲጣል ይህንን ከግምት የሚያስገባ ይሆናል፡፡