Wednesday, February 28, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ወጪ ንግዱን የፈተነው የውጭ ምንዛሪ አጠቃቀም

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ የወጪ ንግድ ገቢና የውጭ ምንዛሪ አጠቃቀም በየወቅቱ የተለያ አቤቱታዎች የሚሰነዘሩበት ነው፡፡ የኢትዮጵያ የወጪ ንግድ ከዓመታት በኃላም በዓመት እየተገኘበት ያለው የውጭ ምንዛሪ ገቢ ከሦስት ቢሊዮን ዶላር በታች ነው፡፡ ይህንን የወጪ ንግድ ገቢ ለማሳደግ የተለያዩ ጥረቶች ቢደረጉም፣ ውጤቱ ብዙም ለውጥ አላመጣም፡፡

ዘርፉን ለማበረታታት ተብሎ የሚወሰዱ ዕርምጃዎች ቢኖሩም፣ ውጤት ያልተገኘበት ምክንያት በተለያየ መልክ ይገለጻል፡፡ የወጪ ንግዱ ብቻውን አትራፊ አይደለም የሚለው ምልከታም የብዙዎች ነው፡፡ የውጭ ምንዛሪ አጠቃቀምን የተመለከቱ ሁለት መመርያዎችና በጥሬ ገንዘብ ከባንክ በዕለት መውጣት ያለበት የገንዘብ መጠንን በሚደነግገው መመርያ ዙሪያ በተደረገ ውይይት ላይ የወጪ ንግድ ብቻውን አትራፊ አይደለም የሚለው ምልከታ ከንግዱ ኅብረተሰብ ተንፀባርቋል፡፡

የወጪ ንግዱ አሁን ባለው ደረጃ አትራፊ ነው ተብሎ እንደማይታመን የሚገልጹ አስተያየቶች ጠንከር ብለው በወጡበት በዚህ መድረክ፣ በተለይ በወጪ ንግድ ላይ የተሰማሩ ላኪዎች አሁን ባለው ሁኔታ የወጪ ንግዱ አትራፊ የሚሆነው በገቢ ንግድ ሲደገፍ ነው ብለውም ያምናሉ፡፡

መንግሥት በወጪ ንግድ የተሰማሩ ላኪዎች ከሚያስገኙት የውጭ ምንዛሪ የተወሰነውን ለገቢ ዕቃዎች እንዲጠቀሙበት ባይፈቅድ፣ በሚያገኙት የውጭ ምንዛሪ በተወሰነው የገቢ ለራሳቸው ግብዓት የሚሆኑ ምርቶችን ባያስመጡበት አብዛኛው ላኪ ወጪ ንግድ ላይ አይቆይም የሚል አመለካከትም አላቸው፡፡

ከወጪ ንግድ ገቢ የሚገኝ ውጭ ምንዛሪ አጠቃቀምን በተመለከተ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መመርያዎችም ኤክስፖርተሩን ለማበረታታት ተብለው የተሰናዱ ናቸው፡፡ አሁን ላይ ላኪዎች ከሚያገኙት ውጭ ምንዛሪ ገቢ 45 በመቶን የፈለጉትን ዕቃ በማስመጣት እንዲጠቀሙበት የተደረገው በዚሁ ምክንያት ነው፡፡

በተደጋጋሚ የተደረጉ የብር ምንዛሪ ለውጦችም በዋናነት ኤክስፖርቱን ያበረታታሉ ተብሎ የሚወሰድ ነው፡፡ የወጪ ንግድ አትራፊ አይደለም የሚለውን ዕሳቤ ያጠናከሩት የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት መላኩ ዕዘዘው (ኢንጂነር)፣ የወጪ ንግድ ብቻውን አያተርፍም የሚባልበትን ምክንያቶች ገልጸዋል፡፡ መንግሥት ሁልጊዜ ኤክስፖርት ዘርፍ ብቻውን ማትረፍ አለበት ቢልም፣ እሳቸው ግን የኤክስፖርት ዘርፉ ብቻውን በቅርብ ጊዜ ያተርፋል ብለው እንደማያምኑም ተናግረዋል፡፡

በቅርብ ጊዜ አትራፊ የማይሆንበት ብዙ ምክንያቶች እንደሚኖሩት የገለጹት ፕሬዚዳንቱ፣ የኢትዮጵያ የግብርና አመራረት ሒደት ኋላቀርነት፣ የምርት ብክነት፣ ገበያው በደላላ የሚመራ መሆኑ፣ መሠረተ ልማቱ፣ ሎጂስቲክስ፣ የጫኝና አውራጅ ጉዳዮችም የወጪ ንግዱን አትራፊ ከሚያደርጉ ምክንያቶች ተርታ የሚቀመጡ ናቸው፡፡

በአገር ደረጃ ያለው የሰላም ጉዳይም ሌላው ችግር ነው ብለው እንደሚያምኑ ያክላሉ፡፡ ኢትዮጵያን ከምርትና ምርታማነት አንፃር በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ እያደረጋት አይደለም ብለዋል፡፡ የሰሊጥ ምርትን በምሳሌነት የጠቀሱት በኢትዮጵያ በአንድ ሔክታር  የሚመረተው ሰሊጥ፣ በህንድና በቻይና ከሦስት እጥፍ በላይ መመረቱን ነው፡፡  

ሌላው እንደማሳያ ይሆናል ብለው ያቀረቡት የጥጥ ምርትን ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ጥጥ እየተገዛ ያለው በኪሎ ግራም 110 ብር ነው፡፡ በዓለም ገበያ ግን 76 እና 77 ብር ነው፡፡ ስለዚህ የእኛን አገር ጥጥ ኤክስፖርት አድርጎ ማትረፍ አይቻልም ወይም በራሱ አትራፊ ሆኖ ሊቀጥል አይችልም፡፡

ምክንያቱም ከመጀመርያው ጥጡ ሲመሠረት ከፍተኛ ወጪ የወጣበት ስለሆነ እነዚህ ሁኔታዎቹ ባልተስተካከሉበት መንገድ ኤክስፖርቱ ብቻውን አትርፎ ለመሄድ ብዙ ችግሮች አሉበት ብለው ይሞግታሉ፡፡ ስለዚህ የኢትዮጵያ ወጪ ንግድ አሁን ባለው የአመራረት ዘዴ፣ የግብይት ሥርዓት ባህልና የማምረት አቅም አንፃር የዓለም ገበያን ሰብሮ ብቻውን ሊያተርፍ የማይችል መሆኑን የተለያዩ መረጃዎችን ጠቅሰው ተናግዋል፡፡

በአመዛኙ ከላኪዎች ወገን በሚነሳው፣ ‹‹ወጪ ንግድ ዘርፍ ብቻውን አያተርፍም›› የሚለውን ምልክታ በተመለከተ ያነጋገርናቸው አንድ የማክሮ የኢኮኖሚ ባለሙያ ግን እንዲህ ያለውን አመለካከት አይቀበሉትም፡፡ ባያተርፉ እንዴት ሊሠሩ ይችላሉ? ብለውም ይጠይቃሉ፡፡

‹‹ኤክስፖርተሮች ለማሳመን ሲሉ እንደዚህ ዓይነት ምክንያቶችን ያቀርባሉ እንጂ፣ አትራፊ ካልሆኑ አይንቀሳቀሱም፤›› የሚሉት እኚሁ የማይክሮ ኢኮኖሚ ባለሙያው፣ ላኪዎች የውጭ ምንዛሪ ትርፍ ስላላቸው ይህንንም የሚጠቀሙበት በመሆኑ ይህ እንዳይቀየርባቸው ከመፈለግ አንፃር እንጂ፣ አትራፊ አይደለም የሚለውን ብዙም የማይቀበሉት መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ምርቱን ወደ ውጭ ከመላክ እዚህ አገር ብንሸጠው ይሻላል ከሚልም ነው፡፡ ምክንያቱም የዋጋ ግሽበቱ ትልቅ ሲሆን አንድ አገር ውስጥ ተወዳዳሪነት እየቀነሰ ይመጣል፡፡ ስለዚህ ሰዎች ወደ ውጭ ከሚልኩ አገራቸው ውስጥ ቢሸጡ ትርፋቸው ይበልጣል ከሚል መነሻ አስተያየቶችን ይሰነዝራሉ እንጂ ሙሉ ለሙሉ የወጪ ንግዱ ትርፋማ አይደለም ማለት አይደለም የሚል አመለካከት አላቸው፡፡

በእኚሁ ባለሙያ እምነት የወጪ ንግዱ ትርፋማ ነው፡፡ ግን ይህ ትርፍ ከሌሎች ዘርፎች ጋር ሲወዳደር አነስተኛ ሊሆን ይችላል፡፡ ኮንስትራክሽን የሚያተርፈው ከውጭ አስገብተው ከሚሸጡ አስመጪዎች ሲነፃፀር ያነሰ ነው የሚለው ግን ሊያስማማ ይችላል እንጂ አያተርፍም የሚለው ላይ አይስማሙም፡፡

የውጭ ምንዛሪው መጠን ከሚያድግበት ፍጥነት አንፃር በኢትዮጵያ ያለው ዋጋ ማደጉንም አንስተዋል፡፡ የምንዛሪው መጠኑ አሁንም መፍጠን አለበት የሚባለውም ኤክስፖርተሮች አሁን የሚያገኙን ትርፍ ለማሻሻል ታስቦ ነው ያሉት የማክሮ ኢኮኖሚ ባለሙያው፣ ኤክስፖርተሩ በሚልከው ምርት የተሻለ ተጠቃሚ የሚሆነው የውጭ ምንዛሪው በገበያ ዋጋ ሲወሰን ነው ብለዋል፡፡ የምንዛሪ መጠኑ ከፍ ካለላቸው የሚያገኙት ውጭ ምንዛሪ ወደ ብር ተቀይሮ እጃቸው ላይ ሲገባ ከፍ ይልና እንዲህ ዓይነቱ አመለካከቶች ሊወገዱ ይችላሉ፡፡ ስለዚህ ዘለቄታዊ መፍትሔው የውጭ ምንዛሪው በገበያ ዋጋ ሲስተናገድ ብቻ መሆኑንም ባለሙያው አስረድተዋል፡፡   

ላኪዎች የወጪ ንግዱ ብቻውን አያተርፋቸውም የሚባልበት ምክንያት እዚህ አገር ዕቃ አምጥቶ ለመሸጥ ውጭ ምንዛሪን በማግኘት ዕቃ አምጥተው መሸጣቸው የበለጠ ስለሚያተርፋቸው ነው፡፡

ከወጭ ምንዛሪ አጠቃቀም ጋር በተያያዘ በወጡ መመርያዎች ዙሪያ ከሰሞኑ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችና የንግድ ኅብረተሰቡ ባደረጉት የምክክር መድረክ ላይ የተነሳው ኤክስፖርቱ በሒደት ራሱን መቻል እንደሚኖርበት ነው፡፡ ለዚህም የውጭ ምንዛሪ ሥርዓትን መዘርጋት ያስፈልጋል የሚለውን የኢኮኖሚው ባለሙያው ይስማሙበታል፡፡

እንደ ኢንጂነር መላኩ ገለጻ፣ የወጪ ንግዱን አትራፊ ለማድረግ አሁንም ብዙ ሥራ ይጠበቅብናል የሚል እምነት አላቸው፡፡ አትራፊ ለመሆን ደግሞ መሠራት አለባቸው ብለው ካስቀመጧቸው ዋና ዋና ነጥቦች መካከል ምርታማነትን ማሳደግ፣ ወደ ዘመናዊ እርሻ መግባትና በመስኖ በዓመት ሁለትና ሦስት ጊዜ በማምረት የምርት መጠን መጨመር የሚሉት ይገኙባቸዋል፡፡

የአገሪቱ የግብርና ምርምር ተቋማትም ወጪ ንግድ የእርሻ ምርቶችን የምርት መጠን የሚጨምሩ ዝርያዎችን ማውጣት እንዲችሉ መሥራት አለባቸው፡፡ እንዲህ ባለው መንገድ ምርትን ማሳደግ ከተቻለ ተወዳዳሪ መሆን ይቻላል፡፡ ምክንያቱም በኢትዮጵያ የሚመረቱ ምርቶችን ሌሎች አገሮች በሔክታር የሚያመርቱት እጅግ ብዙ ስለሆነና በዓለም ገበያ ዋጋ ቀንሰው ስለሚሸጡ ኢትዮጵያ በውድ ዋጋ ያመረተውን ምርት በእነሱ ዋጋ መሸጥ ስለማይቻል የንግድ ምርትን ማሳደግ ዓይነተኛ መፍትሔ ነው ይላሉ፡፡ የኢትዮጵያን የወጪ ንግድ ምርቶች ተወዳዳሪ ከሚያደርጓቸው ሌሎች ምክንያቶች ውስጥ የሎጂስቲክስና የመሠረተ ልማት መወደድ ስለሆነ እዚህ ላይም መሠራት የግድ ይላል፡፡

በጥቅል ሲታይ ኢትዮጵያ ወጪ ንግድ አትራፊ የማይሆነው ምርቱ ከመነሻው ጀምሮ ያለው ወጪ መደራረብ ስለሆነ ይህንን ወጪ በከፍተኛ ሁኔታ የሚቀንስ አሠራር መዘርጋት አለበት፡፡ ይህ ካልሆነ አሁን ባለው የኢትዮጵያ የግብይት ሥርዓትና ከፍተኛ ወጪ በሚጠይቅ የአመራረት ሒደት ተወዳዳሪ መሆን ስለማይቻል ወጪ ንግዱን አትራፊ ማድረግ ይከብዳል የሚል እምነት አላቸው፡፡

ከውጭ ምንዛሪ አጠቃቀምና በቅርቡ በወጡ መመርያዎች ዙሪያ በተደረገው የውይይት መድረክ ላይ ኢንጂነር መላኩ በሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ተጨማሪ አስተያየት የሰጡበት ነበር፡፡ 

ከመመርያዎች ጋር በተያያዘ ካነሷቸው ነጥቦች መካከል በብሔራዊ ባንክ በኩል እየወጡ ያሉት መመርያዎች እንደ አገር በጣም ጥሩዎች ቢሆንም፣ በመመርያዎቹ ዙሪያ ባለድርሻ አካላት ጋር ያለመመካከርና ያለመናበብ ችግር መኖሩን አሳይተዋል፡፡ ሌላው መመርያዎች ሲወጡ ተፅዕኗቸው ምንድነው? ብሎ የማየትም ክፍተት እንዳለ ጠቁመዋል፡፡ ‹‹እናንተ ብቻችሁን በምትወስዷቸው ዕርጃዎች ለምሳሌ የዳያስፖራ አካውንትን ስቶክ በማድረጋችሁ ምክንያት ባለፈው አንድ ወር ሁሉም በሚባል ደረጃ ዕቃዎች ከ20 እስከ 50 በመቶ ጨምሯል፤›› ያሉት ኢንጂነር መላኩ፣ አብዛኛዎቹ ዕቃዎች ይገቡ የነበረው በዳያስፖራ አካውንት ስለነበር የአካውንቱ ባለቤቶች ዕቃውን ካስመጡ በኋላ ጂቡቲ ላይ ስለያዙት የዋጋ ጭማሪ መከሰቱን አመልክተዋል፡፡ ምክንያቱም ይህንን ዕቃ ድጋሚ ለማምጣት ዕድሉ ስለማይኖር ብለው እንደሆነም በመጥቀስ አንዳንድ መመርያዎች ሲወሰኑ እንዲህ ያለው ያልተጠበቀ ችግር ሊከሰት እንደሚችል መታሰብ ነበረበት ብለዋል፡፡

‹‹አንድ የቴክስታይል ፋብሪካ ትልቅ ጨረታ አሸንፎ አድቫንስ ክፍያ ተከፈለው፡፡ ይህ ክፍያ አንድ ሚሊዮን ዶላር ነው፡፡ አሁን በወጣው መመርያ መሠረት እጁ ላይ ሊገባ የሚችለው 300 ሺሕ ዶላር ነው፡፡

አንድ ሚሊዮን ዶላር የተከፈለው ጥሬ ዕቃ ገዝቶ፣ አምርቶ ሊሸጥላቸው ነው፡፡ ግን የቅድመ ክፍያው አንድ ሚሊዮን ዶላር ተከፍሎ፣ 300 ሺሕ ዶላሩ ጥሬ ዕቃውን ሊገዛለት ስላልቻለ ይኼው በየመንግሥት መሥሪያ ቤቱ እየጮኸ ይገኛል፤›› ብለው መመርያው ጫና መፍጠሩን በምሳሌ አስረድተዋል፡፡ ይህ የሚሆነው በአዲሱ መመርያ ለጥሬ ዕቃ መግዣ መጠቀም የሚቻለው 300 ሺሕ ዶላሩን ብቻ በመሆኑ ነው፡፡

ስለዚህ እንዲህ ዓይነት መመርያ ሲወጣ እናቀነቅንለታለን የምንለውን የአምራቹን ዘርፍ የሚጎዳ ከሆነ ችግሩ እየበዛ ስለሚሄድ ከዚህ አንፃር ማየትን ይጠይቃል፡፡

በአጠቃላይ ሕግ ሲወጣ ሕገወጦችን ለመከላከል ታሳቢነት ተደርጎ ነው ቢባልም ወደ ተግባር ሲለወጥ ግን ችግሮች ሲያስከትል ይታያል፡፡ ሕጋዊዎችን ሊሸፍን በሚችል መንገድ መታየት አለበት ብለው እንደሚያምኑም በወቅቱ ለነበሩ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የሥራ ኃላፊዎች ገልጸዋል፡፡

እንደ አበባና ሌላም የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉም የአገሪቱ ወሳኝ ምርቶች ናቸው ከተባለም  የውጭ ምንዛሪ ግኝቱን በተመለከተ በተለይ ከዚህ መመርያ አንፃር ብሔራዊ ባንክ በቶሎ ቢያጤነው መልካም ነው ብለዋል፡፡

በዕለት የሚወጣ የገንዘብ መጠን ላይ የተጣለውን ገደብና በአማራጭ የገንዘብ ማዘዋወሪያዎች መጠቀም የሚችል ስለመሆኑ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የሥራ ኃላፊዎች የተሰጠውን ገለጻ በማንሳትም ኢንጂነር መላኩ በአማራጭ የገንዘብ ማዘዋወሪያ ዘዴዎች ይጠቀም መባሉ ምን ያህል ውጤታማ ነው የሚለውን ጠይቀዋል፡፡

ምንም እንኳን የገንዘብ መለዋወጫ መንገዶች ባንክ ለባንክ ትራንስፈር፣ የኢንተርኔት፣ የሞባይል ባንኪንግ የመሳሰሉ አሠራሮች በአገራችን እያደጉ የመጡ ቢሆንም፣ የሚቀራቸው ነገር እንዳለ የጠቆሙት ኢንጂነር መላኩ፣ የገንዘብ መለወጥን ገደብ በተመለከተ አብዛኛው የንግድ ኅብረተሰብ የሚስማሙበት ቢሆንም ችግር የፈጠረው የመሠረተ ልማት አለመሟላት መሆኑንም አስረድተዋል፡፡

ባንኮችም መሠረተ ልማት ማሟላት እንዳለባቸው ያመለከቱት ፕሬዚዳንቱ፣  አንዱ ባንክ የኤቲኤም ካርድ፣ ሌላው ባንክ ኤቲኤም ላይ ይሠራል ይባላል እንጂ በአብዛኛው ሲሠራ አለመታየቱን እንደ ችግር አንስተዋል፡፡

ለምሳሌ አበባ ኤክስፖርተሮች ከባንክ ባንክ ገንዘብ ሲያዘዋውሩ 24 ሰዓታት የሚፈጅባቸው ከሆነ የአየር መንገዱ ካርጎ ጥሏቸው ሊሄድ ይችላል፡፡ ስለዚህ መሠረተ ልማቱ መሟላት ላይ ባንኮች ሥራ መሥራት ይገባቸዋል ብለዋል፡፡  

የመረጃ አያያዛችን በተለይ በአጠቃላይ እንደ አገር ዲጂታላይዜሽን ባላደገበት ሁኔታ በቀን ከ50 ሺሕ ብር በላይ በጥሬ አይውጣ የተባለው መተግበሩ ምን ያህል ውጤታማ ይሆናል? የሚለውም ያሳስባቸዋል፡፡ ማሳሰብ ብቻ ሳይሆን መመርያው የወጣበትን ዓላማ ላያሳካ ይችል ይሆናል የሚል ሥጋትም አላቸው፡፡ በዚህም አንድ ምሳሌ አስቀምጠዋል፡፡ ይህም አንድ ሰው በአንድ ባንክ በተለያየ ቅርንጫፍ በተለያዩ ባንክ አድርጎ አሥርም መቶም አካውንት ከፍቶ እናንተ (ብሔራዊ ባንክን) ካላችሁት በላይ አካውንት እየፈጠረ ሊሄድ መቻሉን ነው፡፡

ስለዚህ ናሽናል አይዲ በሌለበት ወይም የእያንዳንዱ ሰው የባንክ አካውንት ከቲን ነምበር ጋር ባልተሳሰረበት ሁኔታ እንዴት የምትፈልጉትን ዓላማ ማሳካት ይቻላል? ብለዋል፡፡

ባንክ መመርያ ሲያወጣ በአግባቡ መረጃ የማይሰጥ መሆኑን በማስመልከት፣ ‹‹ባንኩ መመርያ ያወጣል ለ17ቱም ባንኮች ተብሎ ይላካል ከዚህ በኋላ የንግዱ ኅብረተሰብ መረጃውን በሌላ መንገድ ማፈላለግ ይገደዳልና እንዲህ ያለው አሠራር መስተካከል አለበት፤›› ብለዋል፡፡

‹‹ንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ይህንን መመርያ ስታወጡ ያውቃል ወይ? እኔ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ከፍተኛ አመራሮችን አነጋግሬያቸዋለሁ፡፡ ይህንን መመርያ የሰሙ አንደኛ እንደ ነጋዴዎቹ አንድ ላይ ነው፤›› በማለት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መመርያውን ለንግድ ሚኒስቴር ያለማሳወቁንም ፕሬዚዳንቱ ገልጸዋል፡፡ ስለዚህ መመርያዎች ሲወጡ በተቻለ መጠን ባለድርሻ የሚባሉ የመንግሥት ተቋማት ጋር የመናበብ ባህሉ ቢኖር በጣም ጥሩ ነው ብለው እንደሚያምኑም አመልክተዋል፡፡ እኛም መድረክ አመቻችተን ብንነጋገር ከንግዱ ኅብረተሰብ መፍትሔም ሊመጣ ይችላልና እንዲህ ያለው ባህል ቢዳብር የሚለው አመለካከታቸውን ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የሥራ ኃላፊዎች አሳውቀዋል፡፡  

በዚህ የውይይት መድረክ ላይ በቅርቡ በወጡ መመርያዎች ላይ ማብራሪያ ሰጥተው የነበሩ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዥዎች አቶ ፈቃዱ ደግፌና አቶ ሰለሞን ደስታ እንዲሁም የባንኩ ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ሀብታሙ ወርቅነህ መሆናቸው አይዘነጋም፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች