የአውሮፓ ኅብረት ኮሚሽን በኢትዮጵያ በለይም ኅብረቱ በትግራይ ክልል ያለው ቀውስ እንዲያበቃ በማለት ያሳለፈው የውሳኔ ሐሳብ አፈጻጸም እንዲያጣሩ፣ የፊንላንድ መንግሥት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፔካ ሃቪስቶን ሰሞኑን ወደ ኢትዮጵያ ዳግም ልኳል።
በኅብረቱ የተወከሉት የፊንላንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፔካ ሃቪስቶ በዚህ ሳምንት ወደ ኢትዮጵያ የገቡ ሲሆን፣ በቆይታቸውም ከኢትዮጵያ መንግሥት ከፍተኛ አመራሮችና ከአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን አመራሮች ጋር በትግራይ ክልል ቀውስን ለመፍታት እየተደረገ ያለውን ጥረት በተመለከተ እንዲመክሩና ሁኔታዎችን እንዲያጣሩ ከተሰጣቸው ኃላፊነት በተጨማሪ፣ በትግራይ ክልልም በአካል በመገኘት ያለውን ሁኔታ በመቃኘት ከሁለት ሳምንት በኋላ ለሚሰበሰቡት 27 የአውሮፓ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች አባል ለሆኑበት የአውሮፓ የውጭ ጉዳዮች ምክር ቤት ሪፖርታቸውን እንዲያቀርቡ ቀጠሮ ተይዞላቸዋል።
የፊንላንዱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በኅብረቱ ምክትል ፕሬዚዳንትና የውጭ ጉዳዮች ተወካይ በሆኑት ጆሴፕ ቦሮል የተወከሉ ሲሆን፣ ጆሴፕ ቦሬል ሰሞኑን ይፋ ባደረጉት መረጃ የኅብረቱ ልዑክ በመሆን ወደ ኢትዮጵያ ከተጓዙት የፊላንዱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እንዲያጣሩ የሚጠበቅባቸውን ዋና ዋና ጉዳዮች አብራርተዋል።
የፊንላንዱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር መፈጸሙን እንዲያጣሩ ከሚጠበቅባቸው ጉዳዮች የመጀመርያው በትግራይ ክልል ያለው ግጭት በአስቸኳይ እንዲቆም በማለት፣ የአውሮፓ ኅብረት ከአንድ ወር በፊት ያወጣው የውሳኔ ሐሳብ መተግበር አለመተግበሩን የተመለከተ እንደሆነ ጆሴፕ ቦሬል ገልጸዋል።
በሁለተኛ ደረጃ የሚያጣሩት በትግራይ ክልል በሁሉም አካባቢዎች የሰብዓዊ ዕርዳታ ለማቅረብ የሚያስችል ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን የሚመለከት ሲሆን፣ በሦስተኛ ደረጃ የተሰጣቸው ኃላፊነት በትግራይ ክልል የተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን በገለልተኛ አካል ለማጣራት ከተደረሰው ስምምነት በተጨማሪ፣ ምርመራውን ለመጀመር የሚያስችል አደረጃጀትና የቅድመ ዝግጅት ተግባራት መከናወናቸውን ማጣራት ነው።
በአራተኛ ደረጃ የተሰጣቸውና የአውሮፓ ኅብረት በዋና አጀንዳነት የሚመለከተው ጉዳይ፣ በትግራይ ክልል ግጭት የተሳተፉ የኤርትራ ወታደሮች ከክልሉ መውጣት አለመውጣታቸውን ማጣራት እንደሆነ የኅብረቱ ምክትል ፕሬዚዳንት ጆሴፕ ቦሬል ገልጸዋል።
‹‹የኤርትራ ወታደሮች ከክልሉ እንዲወጡ ስምምነት መደረሱን የተመለከተ መግለጫ በኢትዮጵያ መንግሥት በኩል በቅርቡ የወጣ ቢሆንም፣ ወታደሮቹ መውጣት አለመውጣታቸውን በተመለከተ ግን ማረጋገጫ እስካሁን አላገኘንም። በመሆኑም የኤርትራ ወታደሮች ከክልሉ ወጥተው መመልከት እንፈልጋለን፤›› በማለት ይህ ጉዳይ የአውሮፓ ኅብረት በዋናነት ትኩረት የሚያደርግበት ጠቃሚ ጉዳይ እንደሆነ ጆሴፕ ቦሬል ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ወቅታዊ የፖለቲካ ሁኔታ የአውሮፓ ኅብረት ትኩረት ከሚያደርግባቸው አንኳር የውጭ ፖሊሲ ጉዳዮች ቀዳሚ እንደሆነ የተናገሩት ጆሴፕ ቦሬል፣ ይህ የሆነበት ምክንያት አንዱ ኢትዮጵያ ለአውሮፓ ኅብረት ባላት ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ በመሆኑና የኢትዮጵያ አለመረጋጋት መላ አካባቢውን ትርምስ ውስጥ የመክተት አቅም ያለው ከመሆኑ የተነሳ እንደሆነ አስታውቀዋል።
በመሆኑም ኅብረቱ እንዲሻሻሉ የሚፈልጋቸውና ኢትዮጵያን ወደ ሰላም ለመመለስ ጠቃሚ ናቸው ያላቸው ነጥቦች መፈጸም አለመፈጸማቸውን የኅብረቱ ልዑክ አጣርተው፣ ከሁለት ሳምንት በኋላ በሚያቀርቡት ሪፖርት ላይ ተመሥርቶ የዕርምጃ ውሳኔዎችን እንደሚያሳልፍ ተናግረዋል።
የኅብረቱ ልዑክ የሚያቀርቡትን ሪፖርት መሠረት አድርጎ ኅብረቱ በኢትዮጵያ ላይ ዕርምጃ እንደሚወስድ ያስታወቁት ጆሴፕ ቦሬል፣ ‹‹በትግራይ ክልል ኢሰብዓዊ ጥሰቶች በፈጸሙ ላይ የአውሮፓ ኅብረት ሁሉንም የውጭ ግንኙነት መሣሪያዎቹን ለመጠቀም ዝግጁ ነው፤ ብለዋል።
የአውሮፓ ኅብረት ዕርምጃ ምን ሊሆን ይችላል?
የአውሮፓ ኅብረት በኢትዮጵያ ላይ ዕርምጃ ለመውሰድ ተፅዕኖ መፍጠሪያ የሆነትን ሁሉንም የውጭ ግንኙነት መሣሪያዎቹን እንደሚጠቀም ቢገልጽም፣ እወስዳለሁ ያለውን ዕርምጃ ለመጀመር መነሻ ሊሆኑ የሚችሉት በፊንላንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እንዲጣሩ የተባሉት አራቱ ዋነኛ ነጥበች ናቸው።
ከዚህ ውስጥ አንዱ ግጭት መቆሙን የሚጠይቅ ሲሆን፣ የኅብረቱ ልዑክ አዲስ አበባ በተገኙበት ወቅት ከፍተኛ ውጊያ በክልሉ እየተካሄደ መሆኑን መረጃዎች ያመላክታሉ ተብሏል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ቅዳሜ መጋቢት 25 ቀን 2013 ዓ.ም. የደመና ማዝነብ ፕሮጀክትን በይፋ ባስጀመሩበት ወቅት ባደረጉት ንግግርም፣ የመከላከያ ሠራዊቱ ከፍተኛ ኦፕሬሽን ላይ እንደሚገኝ ጠቁመው ነበር።
የኤርትራ ጦር ከትግራይ ክልል እንዲወጣ በተደረገው ስምምነት መሠረት የኤርትራ ጦር ከሠፈረባቸው የትግራይ ክልል አካባቢዎች መውጣት መጀመሩን የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ላይ ባወጣው መግለጫ ያስታወቀ ሲሆን፣ የአውሮፓ ኅብረት ግን ከመግለጫ ባለፈ የኤርትራ ጦር መውጣቱን ማረጋገጥ ይፈልጋል።
በመሆኑም ከላይ የተቀመጡት ሁለት ነጥቦች አለመሟላት ኅብረቱን እወስዳለሁ ወዳለው ዕርምጃ ለማለፍ ሊያስችለው እንደሚችል ይጠቀሳል።
ኅብረቱ እወስዳለሁ ያለው ዕርምጃ በዋናነት የሚገናኘው ከሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ጋር በመሆኑ፣ ኅብረቱ በታኅሳስ 2013 ዓ.ም. ያወጣው የሰብዓዊ መብቶች ጥሰትን ለመከላከል ያወጣው የማዕቀብ ሕግ በኢትዮጵያ ላይ ተግባራዊ እንዲደረግ ሊወስን እንደሚችል ጠቋሚ አዝማሚያዎች እየተስተዋሉ ናቸው።
የኢትዮጵያ መንግሥት በትግራይ ክልል ባከናወነው ‹‹የሕግ ማስከበር ዘመቻ›› መቀሌ ከተማን መቆጣጠሩን ተከትሎ የሕግ ማስከበር ዘመቻውም መጠናቀቁን ካሳወቀ በኋላ የወጣው ይህ የአውሮፓ ኅብረት አዲስ ሕግ፣ በፍጥነት ወደ ሥራ ገብቶ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ፈጽመዋል በማለት በለያቸው የሩሲያ፣ የሚያናማር፣ የሊቢያ፣ እንዲሁም የኤርትራ መንግሥታት የመከላከያና የደኅንነት መሥሪያ ቤት ኃላፊ በሆኑ ግለሰቦች ላይ የጉዞና የሀብት ዕገዳ ማዕቀቦችን ለመጣል ተጠቅሞበታል።
ይህ ሕግ ጥቅም ላይ የሚውለው ሰብዓዊ ጥሰቶችን ፈጽመዋል በተባሉ የመንግሥት አመራሮች ላይ በግለሰብ ደረጃ፣ እንዲሁም ጥሰቱ የተፈጸመው ሰፋ ባለ ደረጃ ከአንድ ተቋም ወይም ፖሊሲ አስፈጻሚ ተቋም ጋር የሚገናኝ ከሆነ በተቋሙ ላይና በተቋሙ የበላይ አመራሮች ላይ የሀብት ዕቀባን ጨምሮ የጉዞ ማዕቀብ ሊጥል እንደሚችል የኅብረቱ መረጃዎች ያመለክታሉ።
ዕርምጃ ለመውሰድ ምክንያት የሆነው የሰብዓዊ መብቶች የተፈጸመው በተቀናጀ መንገድ ወይም ዕቅድ ወጥቶለት በሥነ ሥርዓት በርካታ የመንግሥት ተቋማትን ባሳተፈ ደረጃ ከሆነ፣ ኅብረቱ ይህንን ባደረጉ የመንግሥት ኃላፊዎች ላይ ከሚጥለው ማዕቀብ በተጨማሪ በሚመሩት መንግሥት ላይ ትኩረት በማድረግ የኢኮኖሚ ማዕቀብ ጭምር ሊጥል እንደሚችል መረጃው ያመለክታል።
ይህ ከሆነም የኢኮኖሚ ማዕቀቡን የማስፈጸም ግዴታ በሁሉም የኅብረቱ አገሮች ሕግ መሠረት የተቋቋሙ ተቋማት በሙሉ፣ በኅብረቱ የአስተዳደር ወሰን ውስጥም ሆነ ውጪም ቢገኙ የተመግበር ግዴታ ይጣልባቸዋል።
በመሆኑም የኢኮኖሚ ማዕቀቡ ከተጣለበት መንግሥት ወይም ከሚመለከተው አካል ጋር ምንም ዓይነት የኢኮኖሚ ግንኙነት መፈጸም፣ ወይም የተጀመረ የኢኮኖሚ ግንኙነትን ማድረግ፣ ክፍያዎችን መፈጸም፣ ወይም የባንክ ሒሳብ እንዲንቀሳቀስ ማድረግ አይችሉም።
ሌላው ጉዳይ የአውሮፓ ኅብረት በተጠቀሰው ሁኔታ የሚጥለው ማዕቀብ የተፈጻሚነት ወሰን ከ27 የአውሮፓ ኅብረት አባል አገሮች ውጪም ሊፈጸም የሚችል መሆኑ ነው።
ከእነዚህም መካከል የአውሮፓ ኅብረትን ለመቀላለቀል ዕጩ የሆኑ እንደ ቱርክ፣ ኖርዌይ፣ ዩክሬንን ጨምሮ 14 የሚጠጉ አገሮች ማዕቀቡን ተቀብሎ መፈጸም የሚጠበቅባቸው እንደሆነ መረጃው የሚያመለክት ሲሆን፣ ይህን አለማድረግ አገሮቹ ኅብረቱን ለመቀላቀል የሚያደርጉትን ጉዞ ሊያደናቅፍ ይችላል።
ከኅብረቱ አባል አገሮችና ዕጩ አገሮች በተጨማሪ፣ ኅብረቱ ከሚያራምደው የውጭ ፖሊሲና የሰብዓዊ መብቶች መርህ ጋር ስምም የሆኑ አገሮች ናቸው የሚላቸው አገሮች ማለትም አሜሪካ፣ ካናዳ፣ ጃፓን፣ ኒውዚላንድ፣ ደቡብ ኮሪያ፣ ስዊዘርላንድና ኖርዌይ የኅብረቱን ማዕቀብ ተቀብለው የሚተገብሩ መሆኑን፣ በእነዚህ አገሮች የሚጣል ማዕቀብንም ኅብረቱ ተቀብሎ በራሱ መንገድ ተግባራዊ እንደሚያደርግ መረጃው ያመለክታል።
ይህንን ጉዳይ በተመለከተ የአውሮፓ ኅብረት የምክትል ፕሬዚዳንት ጆሴፕ ቦሬል ሰሞኑን ከአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ጋር ምክክር ማድረጋቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ማክሰኞ መጋቢት 28 ቀን 2013 ዓ.ም. በኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች አያያዝን የተመለከተ ሰፊ ሪፖርት ያወጣ ሲሆን፣ በዚህ ሪፖርትም የኢትዮጵያ መንግሥት በተለይም የፀጥታ ተቋማት ከፍተኛ የሰብዓዊ መብትና የፖለቲካ መብት ጥሰቶችን በኢትዮጵያዊያን ላይ ፈጽመዋል ብሏል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ወደ ሥልጣን መምጣታቸውን ተከትሎ በኢትዮጵያ የተጀመሩ ተስፋ ሰጪ የዴሞክራሲያዊ አስተዳደር ሥራዎች፣ በአሁኑ ወቅት በመንሸራተት ላይ ስለመሆናቸውም አመልክቷል።