- እስኪ ካቆምክበት ሐሳብ ጀምርልኝ፡፡ የሰሞኑ ድርድር አዲስ ጉዳይ ምን ነበር?
- ክቡር ሚኒስትር ለድርድር ብንቀመጥም በዋና ጉዳይ ላይ መወያየት አልቻልንም።
- ለምን?
- በግብፅ በኩል አዲስ የክርክር አጀንዳ ተመዟል፡፡
- ከዚህ ቀደም ያልነበረ ነው?
- አዎን ክቡር ሚኒስትር፡፡
- አዲሱ ክርክር ምንድነው?
- ድርሻዬ መነካት የለበትም ነው የምትለው።
- ግብፅ ነች?
- አዎ።
- የከረምንበት ክርክር አይደለም እንዴ ምኑ ነው አዲስ?
- አዲስ የድርሻ ጥያቄ ነው የተነሳው ክቡር ሚኒስትር፡፡
- የምን ድርሻ?
- የደመና ድርሻ፡፡
- ምን?
- በኢትዮጵያ ላይ የደመና ድርሻ አለኝ እያለች ነው።
- ወይ ግብፅ? እና ምን ይሁን አለች?
- ስምምነት ሳይደረስ መጀመር የለበትም።
- ምኑ?
- ደመና ማዝነቡ።
- እናንተ ምን ምላሽ ሰጣችሁ?
- ስለደመና ለመደራደር ሥልጣን እንዳልተሰጠን አሳውቀናል፡፡
- ሥልጣን ቢሰጣችሁስ?
- እንደማይሰጠን እናውቃለን ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ለምን?
- በበላይ አካል በጥብቅ የተያዘ መሆኑን እናውቃለን።
- ሌላ ያነሱት ነገር አለ?
- ግብፆች ካዳመጧቸው የማያነሱት ነገር የለም፡፡
- ምን አነሱ?
- በእረፍት ሰዓት ከደመና ማዝነቡ ጋር በተያያዘ ሲጠይቁን ነበር፡፡
- ምን አሉ?
- ደመና እንድታዘንቡ ብንስማማ እንኳን እንዲቀላቀል አንፈቅድላችሁም ይላሉ።
- ምኑ ከምን እንዳይቀላቀል?
- የደመናው ዝናብ ከዓባይ ወንዝ ጋር።
- ለምን?
- የዓባይ ድርሻችንን ለመለየት እንቸገራለን ነው የሚሉት፡፡
- ወይ ግብፅ. . .
- አንዳንዶቹ ደግሞ የዓባይ ወንዝን የምናውቀው ብቻውን ነው፡፡ ከሰው ሠራሽ ደመና ዝናብ እንዲቀላቀል አንፈልግም ይላሉ።
- ከሰው ከሠራሽ ደመና አንፈልግም አሉ?
- አዎ።
- ምን ይሁን ይላሉ?
- ኦርጋኒክ ደመና፡፡
- ደመና ማዝነቡን ወደፊት ብንሞክረው ሳይሻል አይቀርም?
- ይኼማ መንበርከክ ነው ክቡር ሚኒስትር. . . መሆን የለበትም፡፡
- እኔ ከግብፅም ሆነ ከማንም ጋር አታካራ ውስጥ መግባት አልፈልግም፣ ሰላም ነው የምፈልገው፡፡
- ክቡር ሚኒስትር ይህንን እንዳይወስኑ፡፡
- ነገርኩህ እኮ ሰላም ነው የምፈልገው። ደመና ማዝነቡን ወደፊት እንደርስበታለን።
- ክቡር ሚኒስትር ሕዝቡ ምን ይለናል?
- ሕዝቡ ያለንበትን ሁኔታ ይረዳል።
- እሺ ሕዝቡ ተረዳን እንበል፣ ፓርላማውስ ምን ይለናል?
- ፓርላማው ምንም አይለንም፡፡
- እንዴት?
- ባልፈቀደልን በጀት ሊቆጣጠረን አይችልም፡፡
- ለነገሩ እሱስ ባልፈቀደው በጀት ምን ብሎ ይጠይቃል ልክ ነዎት!
[ክቡር ሚኒስትሩ ወደ ቢሯቸው እንደገቡ አጀንዳቸውን ተመልክተው ለዕለቱ ቀጠሮ የተያዘላቸው አንድ የሚዲያ ባለሙያ እንዲገባ አዘዙ]
- ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- እንደምን አለህ? እስኪ አረፍ በል፡፡
- ክቡር ሚኒስትር ለሚዲያ ዘርፉ ዕድገት ባለዎት ቀና አመለካከትና ከእኛ ጋር ለመወያየት ቢሮዎ ዘወትር ክፍት መሆኑን አደንቃለሁ።
- ለአገራችንና ለሕዝባችን ዴሞክራሲ አስፈላጊ በመሆኑ ነው ዘርፉን የምንደግፈው።
- ዛሬ የመጣሁት ግን ቅሬታ ለማቅረብ ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ምን ገጠመህ?
- በግሌ ደህና ነኝ፣ ለዘርፉ ዕድገት ትርጉም ያለው አስተዋጽኦ ይኖረዋል ያልነው የሕግ ማሻሻያ በፓርላማ ቢፀድቅም እስካሁን ወደ ሥራ አለመግባቱ አሳስቦናል።
- ምን አሳሰባችሁ?
- ክቡር ሚኒስትር ሕጉ ወደ ሥራ ያልገባው በመንግሥት በኩል የአቋም መንሸራተት በመኖሩ ነው የሚሉ መረጃዎች እየደረሱን በመሆኑ ነው ሥጋት የጫረብን።
- ሃሃሃ. . . ሥጋት አይግባችሁ፣ ሕጉ በነጋሪት ጋዜጣ ኅትመት ላይ እያለ መጠነኛ ችግር ስለገጠመን ነው የዘገየው።
- ነጋሪት ጋዜጣ ላይም ተበላሽቶ እንዳይሆን?
- ምኑ?
- የኅትመት ማሽኑ፣ የኅትመት ሚዲያዎችን ያሰቃየው አንዱ ችግር አንድ ለእናቱ የምንለው የኅትመት ማሽን በተደጋጋሚ መበላሸት ነው።
- አይ እንደዚያ እንኳን አይደለም።
- እሱ ካልሆነ ወረቀት ወይም ቀለም አልቆ ነው የሚሆነው፡፡
- አይደለም ስልህ።
- ታዲያ ምን ተፈጥሮ ነው?
- ኅትመቱ እንዲዘገይ ታዞ ነው።
- ለምን ክቡር ሚኒስትር?
- አዋጁ በነጋሪት ታትሞ ከመውጣቱ በፊት ሹመቶች ለመስጠት ታስቦ ነው።
- ሹመት?
- አዎ፣ ከአዋጁ በፊት የሚዲያ ዘርፉን ለሚቆጣጠረው መሥሪያ ቤት ባለሥልጣናትን ለመሾም ነው።
- ምን?
- ምነው ደነገጥክ?
- እንዴት ይሆናል ይኼ ክቡር ሚኒስትር? መሆን የለበትም፡፡
- ለምን?
- የሕግ ማሻሻያው ተስፋ የሰጠን አንዱ ጉዳይ እኮ ይኼ ነው።
- የምን ተስፋ?
- ለባለሥልጣኑ የሚሾሙ ኃላፊዎች በገለልተኛ ቦርድ ታጭተው መቅረብ እንዳለባቸው ነው ፓርላማው ያፀደቀው ሕግ የሚደነግገው።
- አዎ ልክ ነህ።
- ታዲያ የአዋጁ ኅትመት እንዲቆም ተደርጎ ከሕጉ ውጪ ባለሥልጣን መሾም ትክክል ነው ክቡር ሚኒስትር? እንዴት ይሆናል?
- ግዴለህም ተረጋጋ. . . የሳትከው ነገር አለ፡፡
- ምንም የሳትኩት የለም ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ይኸውልህ አዋጁ ፀደቀ እንጂ ተፈጻሚ አልሆነም።
- እ. . .
- አድምጠኝ! አዋጁ ተፈጻሚ መሆን የሚጀምረው መቼ እንደሆነ አልተገነዘብክም።
- እንዴት?
- አዋጁ ተፈጻሚ የሚሆነው በነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ ይፋ ከተደረገበት ቀን አንስቶ እንደሆነ በአዋጁ የመጨረሻ አንቀጽ አልተደነገገም?
- እውነት ነው ተደንግጓል፡፡
- ታዲያ በነጋሪት ታትሞ ከመውጣቱ በፊት ሹመት መስጠት ምን ችግር አለው?
- የሆነው እንደዚያ አይደለማ?
- ምንድነው የሆነው?
- የነጋሪት ጋዜጣው ኅትመት ቆሞ ሹመቱ ተካሄደ።
- ያው ነው።
- እንዴት ያው ይሆናል?
- አዋጁ ካልታተመ ተፈጻሚ አይሆንም፡፡
- የተሾሙት ኃላፊዎች እንዴት ናቸው? ልምድ አላቸው ክቡር ሚኒስትር?
- ስለሱ አታስብ። ዋና ዳይሬክተሩ በመረጃ መረብ ደኅንነት ባልደረባ የነበሩና ጥሩ ልምድ ያላቸው ናቸው፡፡
- ከመረጃ መረብ ደኅንነት ነው ያሉኝ?
- አዎ።
- ጉድ ፈላ በሉኛ?
- ምን አልክ?
- አለቀልን፡፡
- ሌላው ያልነገርኩህ. . .
- ምን?
- የነጋሪት ጋዜጣው ኅትመትም እንዲፋጠን ተወስኗል፡፡
- ምን ዋጋ አለው አሁን። ከተበላሸ…
- ምኑ?
- ማሽኑ!