ቀለንቶናችን (ካላንደራችን) ይለያል። እንዴት ቢሉ ሚያዝያ 1 ላይ መስከረም 1 ቀን ተመልሶ ይመጣልና! ‹‹በዘይሠርቅ መስከረም ይሠርቅ ሚያዝያ›› — መስከረም በባተበት ሚያዝያ ይብታልና እንዲል። የሚያዝያ ወጌን በከፊል ላወጋችሁ ወደድሁ፡፡
ጓደኛሞች ካፌ ደጃፍ ላይ ሆነው ወግ ይዘዋል፡፡ አንደኛው ‹‹ጊዜው እንዴት ይነጉዳል ጃል፣ ሳናውቀው መንፈቁን ተሻግረን ከሁለተኛው መንፈቅ አንዱን ወር አነሳንለት ኮ›› ሲል፣ ሌላኛው ቀበል አድርጎ ‹‹መንፈቁን ብንሻገርም መስከረም ራሱ ዞሮ ነው ሚያዝያ ላይ የመጣው፤ አይገርምም?›› ብሎ ይመልስለታል፡፡
‹‹የምን መስከረም ነው፣ እንዴት ሆኖ?›› ብሎ ለጠየቀውም ‹‹መስከረም 1 ቀን የዋለው ዓርብ ነበር፣ አሁን ያሳለፍነው ሚያዝያ 1 ቀን የዋለውም ዓርብ ነው፡፡ ወሮቻችን ከሌሎቹ በተለየ ተመሳሳይነት አላቸው፤” ሲል ያብራራለታል፡፡
ኢትዮጵያ ከሌሎች አገሮች የሚለያት፣ ልዩ የሚያደርጋት ምድረ ቀደምት ካሰኛት አንዱ የዘመን አቆጣጠሯ ባሕረ ሐሳቧ (ቁጥር ያለው ዘመን) ነው፡፡ 13 የፀሐይ/ጸጋ ወራት (ሠርቲ መንዝስ ኦቭ ሠንሻይን) ያሰኛትም ቀለንቶኗ፣ ባሕረ ሐሳቧ ነው፡፡ እንደ ጎርጎርዮሳዊ/ ዩሎሳዊ ቀመር (በዘልማድ ያውሮፓውያን አቆጣጠር የሚባለው) የወር አመዳደቧ ወጣ ገባ አይደለም፡፡ አሥራ ሁለት ወሮቿ እያንዳንዳቸው ሠላሳ ሠላሳ ቀኖች ሲኖራቸው (አምስት ተሩብ ተጨማሪ ቀናት ለብቻቸው 13ኛ ወር ሆነው)፣ ያውሮፓው ቀመር ግን በ31፣ 30፣ 28 ቀኖች የተመደበ ነው፡፡ ይህን የኢትዮጵያ የ30 ቀን የወር አመዳደብ፣ የጥንት ግብፃውያን አሁን ደግሞ ኮፕቶች ጨምሮ የሚጠቀሙበትና መሳ መሳ የሆነውን ዐውደ ወር የተመለከቱ እንደ ኦቶ ኒጉባር ያሉት ምሁራን አቆጣጠሩን “ፐርፌክት ካላንደር” ሲሉ ይጠቅሱታል፡፡
እናማ አንዱ ማሳያ መስከረም በባተበት (በገባበት) ሚያዝያ እንደሚብተው ጥቅምት ከግንቦት፣ ኅዳር ከሰኔ፣ ታኅሣሥ ከሐምሌ፣ ጥር ከነሐሴ፣ የካቲት ከጳጉሜን ጋር መግጠማቸው ነው፡፡ መሳ ለመሳ ናቸው፡፡ የሚገቡበት ዕለት ይመሳሰላል፡፡ መጋቢት ግን ከማንም አይገጥምም ማዕከላዊ ነውና፡፡ በግራና በቀኝ ስድስት ስድስት ወሩን ያሰልፋልና፡፡
– ሔኖክ መደብር