Monday, February 26, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልምዕት ዓመት የሞላው ‹‹ፋቡላ›› ያውሬዎች ኮሜዲያ

ምዕት ዓመት የሞላው ‹‹ፋቡላ›› ያውሬዎች ኮሜዲያ

ቀን:

ከፋቡላ በፊት ማን ነበር?

በዳግማዊ ምኒልክ ዘመን (1881-1906) መገባደጃ ላይ በአዲስ አበባ ከተማ ዘመናዊ ትምህርት ቤት (አስኳላ) መከፈቱን ተከትሎ ተማሪዎች ተውኔት መጫወት መጀመራቸው ይወሳል፡፡ የዚህም አጀማመር ‹‹በኢትዮጵያ የመጀመርያው ቴአትር›› እየተባለ ከሚነገርለት በ1913 ዓ.ም. በበጅሮንድ (በኋላ ፊታውራሪ) ተክለ ሐዋርያት  ተክለማርያም ከተደረሰው ፋቡላ አስቀድሞ ነው፡፡

ፋቡላ ያውሬዎች ኮሜዲያ ከተደረሰና ለመድረክ ከበቃ ደግሞ ዘንድሮ አንድ መቶ ዓመት ሞልቶታል፡፡ ይህንኑ የቴአትር ክስተት የኢትዮጵያ ቴአትር ባለሙያዎች ማኅበር ከባለ ድርሻ አካላት ጋር ለማክበር መዘጋጀቱን ባለፈው ረቡዕ መጋቢት 29 ቀን 2013 ዓ.ም. በሰጠው መግለጫ አስታውቋል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

‹‹አውሮፓዊ ቅርፅ ያለው ዘመናዊ ቴአትር በኢትዮጵያ የተጀመረበትን 100ኛ ዓመት›› በልዩ ልዩ መርሐ ግብሮች ለማክበር መዘጋጀቱን የገለጸው ማኅበሩ፣ የበዓሉ መክፈቻ ሚያዝያ 5 ቀን 2013 ዓ.ም. በሸራተን አዲስ ይሆናል ብሏል፡፡

 የኢዮቤልዩ በዓሉ፣ ቴአትርን የማነቃቃት እንቅስቃሴ እንደሚኖረው በተለይም የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከሰትን ተከትሎ በሙያው ላይ የተፈጠረውን መደበትና የቴአትር ቤቶችን በተለያዩ ምክንያቶች ሥራ ላይ አለመሆን የፈጠረውን መቀዛቀዝ በመገንዘብ፣ ሙያው ላይ ያሉትን ችግሮች በዘላቂነት ለመፍታት የታለመበት ነው፡፡

በቴአትር ሙያ ላይ ያሉትን ችግሮች ለመቅረፍ የሚያስችሉ ውይይቶችና ንግግሮች ለመፍጠር የሚያስችሉ ዓውደ ርዕዮች፣ በአገር አቀፍ ደረጃ 100 ቴአትሮች የሚቀርብባቸው ፌስቲቫሎች፣ የምዕት ዓመቱን የኢትዮጵያ ቴአትር ታሪክ የሚዘክሩ ኅትመቶች፣ እንዲሁም አንጋፋ ባለሙያዎችን የሚያከብር የዕውቅናና የምስጋና ምሽት ለማከናወን እንቅስቃሴውን መጀመሩን ማኅበሩ አስታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ ቴአትር ባለሙያዎች ማኅበር ክብረ በዓሉን የሚያካሂደው ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቴአትር ትምህርት ቤት፣ ከባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር፣ ከአዲስ አበባ ባህል ኪነጥበብና ቱሪዝም ቢሮ እንዲሁም በግላቸው ቴአትርን ከሚሠሩ ባለሙያዎች ጋር መሆኑንም አስታውቋል፡፡

ፋቡላ ለምን ተጻፈ?

ፋቡላ የአውሬዎች ኮሜዲያን የደረሱት በጅሮንድ ተክለ ሐዋርያት  ተክለማርያም ናቸው፡፡ በአፄ ምኒልክ ዘመን ትምህርታቸውን በመስኮብ የተከታተሉት ደራሲው ፋቡላን ለምንና እንዴት እንደጻፉት ‹‹ኦቶባዮግራፊ (የሕይወቴ ታሪክ)›› ባሉት ግለ ታሪካቸው ላይ አቅርበውታል፡፡  

የዳግማዊ ምኒልክ አልጋ ወራሽ ሆነው የተቀመጡትን ልጅ ኢያሱ አካሄድ እንዳላማራቸው በመረዳት ማረቂያ ይሆን ዘንድ ድርሰቱን መድረሳቸውን ይገልጹታል፡፡

‹‹ዐፄ ምኒልክ በመጨረሻ ዘመናቸው አንደበታቸው ተዘግቶ፣ ከልፍኛቸው ውስጥ አይወጡም… ልጅ ኢያሱ ግን አልጋወራሽ እየተባሉ ይቦርቃሉ፡፡ …እንደዚህ በአንድ ወገን፣ ያኔ ምኒልክን፣ በሌላው የልጅ ኢያሱን አጉል አኳኋን እያሰብኩ መተከዝ አልቀረልኝም፡፡ ይልቁንም ያለፈውን፣ ያሁኑንም የወደፊቱንም የአገራችንን ሁኔታ እየተመለከትኩ ጠሊቅ ሐዘን ተሰማኝ፤›› በማለት የገለጹት ፊታውራሪ ተክለ ሐዋርያት  መፍትሔ አድርገው የወሰዱት ወጣቱን አልጋወራሽ እጎዳናው ውስጥ ለማግባት የልጅ ኢያሱን ልቡና ለመማረክ የጨዋታ ድርሰት ማዘጋጀት ነው፡፡

‹‹እንግዲያስ የልጅ ኢያሱን ልቡና መማረክ ያስፈልጋል፤ ታዲያ አዕምሮውን መኮትኮት ይቻላል፡፡ እስቲ ልሞክረው፣ ቢሆን መልካም፣ ያልሆነ እንደሆነ ይቀራል፡፡ ኢትዮጵያ እንደ ዕድሏ ትሆናለች፡፡ …ለልጅ ኢያሱ ቁም ነገር የተሞላበት ጨዋታ ላሰናዳላቸው እያልኩ ተመኘሁ፡፡ …እነ ኤዞፕ፣ እነ ላፎንቴን፣ እነ ኪሪሎፍ የጻፉት የአውሬዎች ተረት (ፋብል) ለምሳሌነት ይረዳኛል፡፡ በዚህ ዓይነት በአማርኛ ተረት ለማሰናዳት አሰብኩ፣ ያውሬዎች ተረት የተባለ ግጥም ጻፍኩ፡፡ ይህን በኋላ በንግሥት ዘውዲቱ ጊዜ አሳተምኩት፣ ደግሞ በኋላ በቲያትር ለማሳየት እንዲመች አድርጌ አዛወርኩት፡፡

በግጥም ያሰናዱትን ተረት ለወንድሞቻቸውና ለወዳጆቻቸው እንዲሁም በነጋድራስ ተሰማ እሸቴ አማካይነት ለልጅ ኢያሱ እንዳነበቡላቸው ፊታውራሪ ተክለ ሐዋርያት  ገልጸዋል፡፡ ልጅ ኢያሱ በወንበር ላይ ተቀምጠው አሽከሮች ባለሟሎቻቸው የሆኑት ቆመው የአውሬዎች ተረትን ያዳምጣሉ፡፡

ሁሉም እያዳመጡ ማድነቅ መሳሳቅ አበዙ፡፡ ልጅ ኢያሱ፡ ‹‹አባባ ይሙት ይገርማል፣ አባባ ይሙት እንዲህ ነዋ የተማረ ሰው እንዲህ ነው…›› ብለው ይናገሩና ለአባቴ አንብላቸው ይሏቸዋል፡፡

ደራሲው ለራስ ሚካኤልና አሥር ያህል ለሚሆኑ መኳንንቶቻቸውም ድርሰታቸውን ያቀርቡላቸዋል፡፡ አቀባበሉንም እንዲህ ገልጸውታል፡፡

‹በል ስቲ ንገረንማ እንስማው እንጂ› አሉና ዓይኖቻቸውን እኔ እላይ ተከሉ፡፡ ገና ማንበብ ስጀምር፣ ራስም መኳንንቶቻቸውም ተሳሳቁ፡፡ ‹ኧረገኝ ኽጡብ! አሁን አያችሁ!› እያሉ ተደነቁ፡፡ አንብቤ ከጨረስኩ በኋላ ራስ ጠየቁኝ፡፡ ‹በልማ ልዤዋ ባገራችሁ፣ ጉንዳንና ፌንጣ እንደዚህ መነጋገር ይችላሉን?› አሉ፡፡ እኔም ምሳሌ መሆኑን አስረዳኋቸው፡፡

‹‹ለጌታዬ ማጫወቻ እንዲሆን፣ ወዲያውም ወደ ቁም ነገር እንዲመራቸው አስቤ ለምሳሌ ጻፍኩላቸው፡፡ ቁም ነገሩን በጨዋታ እያስመሰልኩ ማሳየቴ ነው፡፡ በጨዋታም ውስጥ ፍሬ እንዲገኝበት ያስፈልጋል፡፡ ገለባ ብቻ የሆነ እንደሆነ ጥቅም አይገኝበትም እያልኩ ምስጢሩን እያጎላሁ ገለጥኩላቸው፡፡

ፊታውራሪ በወቅቱ ካቀረቧቸው ተረቶች መካከል አንዱ ‹‹ሉልና አውራ ዶሮ›› ነው፡፡

አንድ ሉል ከዘውድ ውስጥ ጠብ ብሎ ኖሮ

አውራ ዶሮ አገኘው ሲጫጭር ከጓሮ

የሚበላ መስሎት ለቀም አደረገው

ኋላ ግን አየና ታፉ አውጥቶ ጣለው

ይህን ገንዘብ ብዬ ደርሶ ላልቸገር

ያተር ፍሬ መስሎኝ ቋምጨለት ነበር

እሱስ ከንቱ ኖሯል ጥቅም የሌለበት

መልኩን አሳምሮ እኔን ሊያሞኝበት

እንደዚህ እያለ ጌታው አቶ ዶሮ

ሉሉን ጥሎ ሄደ – ኩኩሪኩ ብሎ

ስለዚህ ይመኙዋል – አስቀድሞ እውቀትን

እውቀት ታለ ወዲያ በኋላ ማግኘትን፡፡

ፊታውራሪ ተክለ ሐዋርያት  በፋቡላ አማካይነት ልጅ ኢያሱን ለማቃናት የሞከሩት ሁሉ እንዳልተሳካላቸው በግለታሪካቸው ጠቁመዋል፡፡

በ‹‹ያውሬዎች ተረት – ፋቡላ›› ድርሰታቸው መቅድም እንደገለጹት ልጅ ኢያሱ ከሥልጣናቸው ከተሻሩ በኋላ በልዑል ራስ ተፈሪ የኢትዮጵያ አልጋወራሽ ባለሙሉ ሥልጣን እንደራሴ አማካይነት መጽሐፉ እንዲታተም ተደርጓል፡፡

ፋቡላ ለቴአትር መድረክ እንዴት ለመቅረብ ቻለ?

የፋቡላ ድርሰት የአውሬዎች ኮሜዲያ በንግሥት ዘውዲቱ ዘመነ መንግሥት በ1913 ዓ.ም. አካባቢ ነበር ለመድረክ በሚመች መልኩ የቀረበው፡፡  

የአውሬዎች ኮሜዲያ (መሳለቂያ) የጻፉበት ምክንያት ደራሲው በግለታሪካቸው እንደሚከተለው ተገልጿል፡፡

…ካቶ ኅሩይ የአዲስ አበባ ሙኒሲፖሊቴ ዲሬክተር የጥሪ ወረቀት… ዛሬ ማታ በራስ ሆቴል የቴአትር ጨዋታ ለማሳየት ተደራጅተናልና መጥተው እንዲያዩልን የሚል ነው (መጣልኝ) …ለማየት ቸኩዬ ሄድኩ… ግን ክፉኛ ተሳቀቅሁ አዝማሪዎች፣ ዘፋኞች ተሰብስበው አታሞ መሰንቆ ክራር እየመጡ ሲዘፍኑና ሲጨፍሩ አየሁ፤ የልጅ ኢያሱ አስተዳደር በምን ዓይነት እንደተመራ አይቼ አዝኜ አልነበረም? አሁን ደግሞ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ በምን ዓይነት ወደ ሥልጣኔ እንደሚመራ አየሁና የባሰውን አዘንኩ… ወዲያው አንድ የቴአትር ጨዋታ ለምሳሌ ያህል ለማሰናዳት ተመኘሁ…››

ደራሲው ምኞታቸውን ወደ ተግባር የለወጡት ፋቡላ (ተረት) በተባለው ድርሰታቸው ውስጥ የተመሰሉትን አውሬዎች እርስ በራሳቸው ተነጋጋሪዎች አድርገው በማስመሰል በጥቂት ጊዜ ውስጥ በማሰናዳት ልሁል አልጋ ወራሽ ራስ ተፈሪና መኳንንቶች በነበሩበት በራስ ሆቴል ማሳየታቸውን በድርሰቱ መቅድም ተመልክቷል፡፡

በያውሬዎች ኮሜዲያ በጎች ከበረት ውስጥ ተኝተው አድረው ሲነጋጋ እየተነሱ እየተንጠራሩ የሚነጋገሩበት ትዕይንት አለ፡፡ አንደኛው በግ እንዲህ ትላለች፡-

እንቅልፍ አዘንግቶኝ ብቻዬን ተኝቼ

ታባቴም ተናቴም ቀረሁ ተለይቼ

እንግዲህ እናቴን የት አገኛታለሁ?

ከዱር ስንከራተት እቀርባታለሁ

መንገዱን አላውቀው ሄጄ እንዳልፈልጋት

ይህን ጊዜ ለሷም ሆኖባታል ሥጋት

ጡት እንኳ አልጠገብኩም ዋጥም ይዞኛል

በዚህ በኩል ውኃ ይገኝ ይመስለኛል

እስቲ በፊት ሄጄ ጥማቴን ላስወጣ

ወንዙን ተከትዬ አሻቅቤ ልውጣ፡፡

ከፋቡላ በፊት ማን ነበር?

ከፋቡላ በፊት የቴአትር ጨዋታ እንደነበር የተለያዩ ማስረጃዎች መኖራቸው የሚገልጹ ጽሑፎች አሉ፡፡ አንዱ ራሳቸው በጅሮንድ ተክለ ሐዋርያት ናቸው፡፡ ምንም እንኳን ለአቅመ ቴአትር የደረሰ አይደለም ቢሉም፡፡ የቴአትር ባለሙያዎች ማኅበር የፋቡላን መቶኛ ዓመት ላከብር ነው የሚለውን ማስታወቂያ የተመለከቱት የቴአትር ባለሙያና የፐርፎርማንስ ሒስቶሪግራፊ (Performance Historiography) ምሁር ሱራፌል ወንድሙ (ዶ/ር) በጻፉት መጣጥፍ፣ ‹‹”መቶ ዓመት” የሚለው የታሪክ መነሾ እንደ ርዕስ ብዙም የሚደላኝ አይደለሁም። ምክንያቱምየመቶ ዓመት ታሪክየሚለው ጉዳይ ብዙ አውሮፓዊ ዕውቀቶችን እየገለበጥን የምንቀጥልባቸውን ሒደት ያለበቂ ሒስ የሚያስቀጥል ሊሆን ይችላል፤›› ብለው ይህ ሐሳብ፣ ‹‹የኢትዮጵያ የዘመናዊ ቴአትር ጅማሬ የሚነሳው ከበጅሮንድ ተክለ ሐዋርያት በአውሮፓዊ ቅርፅ (ከዚያ ቀደም በፃፉት ተረት ላይ ተመሥርተው በገፀባህሪያት ንግግር አዋቅረው በሠሩት ቴአትር) ላይ አተኩሮ የተሠራ ስለሆነ ነው፤›› ከሚል መነሻ ነው የሚመጣው በማለት ያትታሉ። የኢትዮጵያም እንዲሁም በአፍሪካ ቴአትር ውስጥ ኢትዮጵያ እንድትገባ በተደረገበት አካዴሚያዊ  ትርክት ይህ እውቀት እስከዛሬ ገንኖ የወጣ መሆኑን የሚገልጹት ዶ/ር ሱራፌል፣

ከፋቡላ በፊት የብዙ ዘፈኖችና እንቅስቃሴአዊ ክንውኖችን (ድራማዊ ድርጊያዎችን) ይዞ የተሠራውና ‹‹የኢትዮጵያ ልጆች የቲአትር ማኅበር›› ተዘጋጅቶ በወቅቱ የማዘጋጃ ቤት ዳይሬከተር (ከንቲባ) በነበሩት ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደሥላሴ ጥሪ ለሕዝብ የቀረበው ትርኢት የቀረበበት ትክክለኛ ዕለት ነሐሴ 2 ቀን 1912 ዓ.ም. መሆኑን ያብራራሉ የማኅበሩ ዋና አለቃ ኪዳነ ማርያም፣ ምክትላቸው አቶ ፀጋዬ ገብረ ፃዲቅ እንደነበሩም ያስታውሳሉ፡፡

ዛሬ መቶኛ ዓመቱን የምናከብርለት ብቻ ሳይሆን የቴአትርን ጅማሬ መነሻ እንዲደነግግ ያደረግንለት ቴአትር ትክክለኛ ቀኑ አይታወቅም።

ዶ/ር ሱራፌል ሐቲታቸውን ይቀጥላሉ፡- ‹‹በጅሮንድ ተክለ ሐዋርያት የኢትዮጵያ ልጆች የቴአትር ማኅበር ያቀረባቸውን ትርኢቶች ተችተው ከተነሱ በኋላየኔን ወዲያው አቀረብሁትይላሉ። የሳቸውየቴአትር ጨዋታቁርጥ ያለው ቀን እስከዛሬ ባይታወቅምጳጉሜን ወር ላይ እንደነበረ ግን በራሳቸው ተገልፆአል። የቀደመውና በእነኪዳነማርያምየቴአትር ጨዋታ› የተሰኘው ትርዒት ነሐሴ መጀመሪያ መቅረቡን ይዘን በጅሮንድ ጽሑፉን እንደአዲስ አዘጋጅተው፣ ተዋንያኑን አሠልጥነው ልክ በአንድ ወሩ አደረሱት ካልን የእሳቸውምየቴአትር ጨዋታ› 101 ዓመቱ ሊሆን ይችላል። ነገር ግን ጳጉሜን 1913 ብለው መጻፋቸውን ልብ እንላለን።

ሁሉን ታሪክ ማምጣታቸው የኢትዮጵያ ዘመናዊ ቴአትር ጅማሬ 101 ዓመቱ እንጂ 100ኛው ዓመት አይደለም የሚል ክርክር ለማምጣት አይደለም የሚሉት ባለሙያው ትንተናቸውን ይቀጥላሉ፡፡

‹‹ይልቁንም ዘመናዊነትን እንደዓለምአቀፋዊ ሁኔታ (ኮንዲሽን) የምናይና የጥበቡንም ዘመናዊነት መመርመር የምንፈልግ ከሆነ ጥያቄያችንን በምን የዕውቀት መሠረት ላይ አንተርሰን ነው የምንጠይቀው? ሕይወታችንን እና ጥበባቱን የምንተነትነው? የሚለውን ልብ እንድንል ነው። ቀናትን ማወቁ ጥሩ ቢሆንም ቀናትን ማወቅንና መነሾን (ኦሪጅን) መፈለግን የዕውቀት ጥግ የምናደርግ ከሆነ የጥያቄዎቻችን አድማስና የምናውቃቸውም ነገሮች ውሱን ብቻ ሳይሆኑ ብዙ ልምዶችን፣ ጥበባትንና ሕይወቶችን ቆርጠን እንድንጥል ሊያደርጉን ይችላሉ።

‹‹ይህንን የቴአትር ጥበብ ክብረ በዓል የምናከብርበት የዘመን ስሌት ወደድንም ጠላንም አንድን ዕውቀት ከፍ አድርጎ፣ አንዱን በማንገዋለል ብዙ ነገሮቻችንን እንዳናውቅ ሊከልለንም መቻሉን በማንሳት ነው ንግግራችንን መቀጠል ያለበን።

‹‹እናም ቴአትርን በስፋት ከፖለቲካም ሆነ ከጥበቡ ዘመናዊነት እንዲሁም የኢትዮጵያን የተበጣጠሰ (ፍራግመንታሪ) እ የሟሟ (ፍሉድ) ታሪክ ተከትለን፣ ከተገደገደ የሀገረ መንግሥት ኦፊሴሊያዊ እንዲሁም አውራ (ሜይንስትሪም) ትርክት አውጥተን ከባለሙያዎቹ እስከ ተገፊና ገፊ ኢትዮጵያውያን ብሎም እስከ ቴአትር ጥበባቱ ቅርፅና ይዘት በመተንተን ስለ ጥበባችን ፖለቲካ ኢኮኖሚም ሆነ ስለ ፖለቲካውና ኢኮኖሚውጥበብድረስ ለመረዳት መሞከር ለተሻለ ሰብአዊ ዓለም ግንባታ ያግዘናል ብዬ አስባለሁ።

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመጣንበትና አብረን የምንዘልቅበት የጋራ እሴታችን ለመሆኑ ነጋሪ ያስፈልጋል ወይ?

በኑረዲን አብራር በአገራችን ለለውጥ የተደረጉ ትግሎች ከመብዛታቸው የተነሳ ሰላም የነበረበት...

አልባሌ ልሂቃንና ፖለቲከኞች

በበቀለ ሹሜ በ2016 ዓ.ም. ኅዳር ማክተሚያ ላይ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ...

አሜሪካ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ተገቢነት ቢኖረውም ከጎረቤት አገሮች ጋር በሚደረግ ንግግር መሆን አለበት አለች

መንግሥትን ከፋኖና ከኦነግ ሸኔ ጋር ለማነጋገር ፍላጎቷን ገልጻለች የኢትዮጵያ የባህር...