Wednesday, May 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊኮቪድ-19 እንዲሠራጭ ምክንያት የሆኑ አመለካከቶች

ኮቪድ-19 እንዲሠራጭ ምክንያት የሆኑ አመለካከቶች

ቀን:

በኢትዮጵያ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በከፍተኛ ሁኔታ በመሠራጨቱ የብዙ ሰዎች ሕይወትን እየቀጠፈ ይገኛል፡፡ ወረርሽኙን ለመከላከል መንግሥት ከዚህ በፊት የወጡ መመርያዎችን እንደ አዲስ እንዲተገበሩ ቢያደርግም፣ በማኅበረሰቡ ዘንድ ግን ችላ ማለት ይታያል፡፡

ይኼንንም ለማስቆም በሚደረገው ጥረት መንግሥት ለወረርሽኙ ትኩረት በመስጠትና የወጡ መመርያዎችን ተግባራዊ እንዲሆኑ በማድረግ መሥራት እንደሚጠበቅበት፣ የሙያ ማኅበራት ረቡዕ መጋቢት 29 ቀን 2013 ዓ.ም. በጋራ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቀዋል፡፡

ጥሪውን አስመልክቶ የኢትዮጵያ ጤና አጠባበቅ ማኅበር ዋና ዳይሬክተር ዓለማየሁ መኮንን (ዶ/ር) እንደገለጹት፣ አዲስ አበባን ጨምሮ በ15 ክልሎችና በ48 ትምህርት ቤቶች ላይ ካለፈው ጥቅምት ወር ጀምሮ ባሉት ተከታታይ 20 ሳምንታት በተደረገው የዳሰሳ ጥናት፣ የእጅ ንፅህና አጠባበቅ ከአምስት በመቶ በታች፣ አካላዊ መራራቅ ትግበራ ከ20 በመቶ በታች፣ ተገቢ የመተንፈሻ አካል ንፅህና አጠባበቅ ከ40 በመቶ በታች፣ የአሽከርካሪዎችና የረዳቶች የአፍና አፍንጫ ጭንብል አጠቃቀም ከ35 በመቶና ከ20 በመቶ በታች መሆኑ ታውቋል፡፡ ይህም ወረርሽኙ በፍጥነት እንዲዛመት እንደምክንያት ተነስቷል፡፡

- Advertisement -

በአሁኑ ወቅት በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ የመጣውን ወረርሽኝ ለመቆጣጠር ዘላቂ የሆኑ መመርያዎችን በማውጣት መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ መሥራት እንዳለበት  ዶ/ር ዓለማየሁ  አስረድተዋል፡፡

በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በመምጣቱ የጤና ባለሙያዎች ትልቅ ፈተና ውስጥ መግባታቸውን፣ በተለይም የሕክምና አገልግሎቱን እንደ ልብ ማግኘት አለመቻሉንና የሟቾች ቁጥር መብዛቱን ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡

በፊት በየቦታው አገልግሎት ይሰጡ የነበሩ የእጅ መታጠቢያዎች ወደ ቦታቸው በመመለስ አገልግሎት እንዲሰጡ ማድረግ፣ በገበያ ላይ የሚታዩ ከፍተኛ የሆነ መተፋፈንን መቀነስ፣ የምሽት ጭፈራ ቤቶችን መዝጋትና ሌሎች ለቫይረሱ መስፋፋት ምክንያት ይሆናሉ የሚባሉ ቦታዎችን በመለየት መሥራት ይገባል ብለዋል፡፡  

መንግሥት ጠንከር ያለ ዕርምጃ በመውሰድና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት በመሥራት በከፍተኛ ፍጥነት እየተዛመተ የሚገኘውን የኮሮና ወረርሽኝ መከላከል ያስፈልጋል ያሉት የኢትዮጵያ ጤና አጠባበቅ ማኅበር ቦርድ አባል አዳሙ አዲሴ (ዶ/ር) ናቸው፡፡

ወረርሽኙ አሳሳቢ በሚባል ደረጃ በተለያዩ ክልሎች እየተዛመተ መሆኑን የገለጹት ዶ/ር አዳሙ፣ የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል ማድረግ፣ አካላዊ ርቀትን መጠበቅና እጅን በሳሙና መታጠብ ዕለት ከዕለት ተግባራዊ መሆን እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡

የጤና ሚኒስቴር ከጤና ሙያ ማኅበራት፣ ከሲቪል ማኅበራት ድርጅቶችና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር የተቀናጀና የተናበበ አሠራሮችን በመዘርጋት የወረርሽኙን ሥርጭት በከፊልም ቢሆን ማቆም እንደሚቻል አስታውሰዋል፡፡

ከዚህ በፊት በሌሎች አገሮች የተከሰተውና በፈጣን መንገድ ይሠራጫል ተብሎ የሚታመነው አዲሱ የኮቪድ-19 ልውጥ ዝርያ፣ ወደ ኢትዮጵያ ገብቶ በማኅበረሰቡ ውስጥ እየተሠራጨ ሊሆን እንደሚችልም በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ ተነግሯል፡፡

በኢትዮጵያ የኮቪድ-19 ክትባት በተገቢው መንገድ ለማኅበረሰቡ ለማድረስ በሚደረገው ጥረት ስለክትባቱ አሰጣጥ የተዛቡና የተጋነኑ መረጃዎች እየወጡ መሆኑና ይኼንንም ማቆም እንደሚያስፈልግም ተገልጿል፡፡   

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የማዳበሪያ አቅርቦትና ውጣ ውረዱ

በቅፅል ስሙ “The Father of Chemical Warfare” እየተባለ የሚጠራው...

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የትርፍ ምጣኔውን ከ70 በመቶ በላይ አሳደገ

ከሁለቱ መንግሥታዊ ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ...