በቅርቡ የኢትዮጵያን ፖለቲካ የተቀላቀለውና ለዘብተኛ ሊበራሊዝም ርዕዮተ ዓለም እንደሚከተል የገለጸው ነፃነትና እኩልነት ፓርቲ (ነእፓ)፣ ለመጪው ጠቅላላ ምርጫ የሚጠቀምበትን ማኒፌስቶና የምርጫ መወዳደሪያ ምልክትን ይፋ አደረገ፡፡
የፓርቲውን የምርጫ መወዳደሪያ ምልክትና ማኒፌስቶ ይፋ ያደረጉት የፓርቲው ሊቀመንበር አብዱልቃድር አዳም (ዶ/ር) ሲሆኑ፣ ዓርብ ሚያዝያ 1 ቀን 2013 ዓ.ም. በተከናወነ ሥነ ሥርዓት ነው ማኒፌስቶውና የምርጫ ምልክቱ ይፋ ተደርጓል፡፡
በወቅቱ የፓርቲው ሊቀመንበር የማኒፌስቶውን ሐሳቦች ከማብራራት በዘለለ፣ ፓርቲያቸው በመጪው ጠቅላላ ምርጫ ዋነኛ ተፎካካሪ ለመሆን በርካታ ሥራዎች እየሠራ እንደሚገኝ በመግለጽ፣ በማኒፌስቶው የተካተቱት ሐሳቦችም ፓርቲው አሸንፎ ሥልጣን ቢይዝ ሊተገብር የሚያስባቸው ዕቅዶች እንደሆኑ ገልጸዋል፡፡
የፓርቲው ማኒፌስቶ በቀጣይ አምስት ዓመታት በፓርቲው ሊተገበሩ የታቀዱ በርካታ ዕቅዶችን ያካተተ ሲሆን፣ በዚህም መሠረት የፓርቲውን ራዕይ፣ ተልዕኮ፣ ዓላማና የትግል ሥልቶችን ያካተተ ነው፡፡
በዚህም የፓርቲውን የትግል ሥልቶች አቅርቧል፡፡ ዋነኛ የፓርቲው የትግል ሥልቶች በመግባባት ላይ የተመሠረተ፣ ከፍጥጫ፣ ከሴራና ከመጠላለፍ የራቀ የፖለቲካ ትግል፣ ሚዛናዊነትና አካታችነት፣ ተፈጥራዊ ለውጥ፣ አብሮ ማሸነፍ፣ ሕዝብን ማገልገል፣ እውነተኛነትና ታማኝነት፣ እንዲሁም በትብብር መሥራት የሚሉት ዋነኛዎቹ ናቸው፡፡
እነዚህን የትግል ሥልቶችና ዕቅዶቹን ለማሳካት ፓርቲው በዋነኛነት ትምህርት ተኮር የልማት ስትራቴጂ እንደሚከተልና ለትምህርት ከፍተኛ ሥፍራ እንደሚሰጥ ሊቀመንበሩ ገልጸዋል፡፡
‹‹ትምህርት ሰዎች በግል ሕይወታቸው እንዲያውቁ፣ እንዲሠሩና የሕይወት ግባቸውን ማሳካት እንዲችሉ የሚያግዛቸው ሲሆን፣ በማኅበራዊ ሕይወታቸው ሰላምና ጠንካራ ማኅበራዊ መስተጋብርን እንዲፈጥሩ ያስችላቸዋል፡፡ ትምህርት የለውጥ፣ የነፃነት፣ የእኩልነትና የዕድገት ቁልፍ ነው፤›› የሚል እምነት እንዳለው የፓርቲው ማኒፌስቶ ያትታል፡፡
ምንም እንኳን ፓርቲው የሚተልመውን የፖለቲካ ሥርዓት ለመገንባትና ለማሳካት የለዘብተኛ ሊበራሊዝምን ከኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ዕድገት ጋር ከግምት ውስጥ በማስገባት እንደሚከተል የገለጸ ቢሆንም፣ ነገር ግን በአንድ ርዕዮተ ዓለም እንደማይታጠር አስታውቋል፡፡ በዚህም መሠረት፣ ‹‹ነእፓ በዋነኛነት ከሚከተለው የለዘብተኛ ሊበራል ርዕዮተ ዓለም በተጨማሪ፣ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ የሶሻል ዴሞክራሲን ጨምሮ ሌሎች ርዕዮተ ዓለማዊ አስተሳሶቦችን መሠረት ያደረጉ ፖሊሲዎችን ተግባራዊ ሊያደርግ ይችላል፤›› በማለት፣ በአንድ ርዕዮተ ዓለም የታጠረና የተገደበ እንቅስቃሴ እንደማያደርግ አስታውቋል፡፡
የመንግሥት አወቃቀርን በተመለከተ ደግሞ የተሻለው የመንግሥት አወቃቀር የፌዴራል ሥርዓት መሆኑን እንደሚያምን በመግለጽ፣ ነገር ግን የሚገነባው የፌዴራል ሥርዓት የአስተዳደር ምቹነት፣ የሕዝብ ፍላጎት፣ ቋንቋና ባህልን፣ መልክዓ ምድርን፣ እንዲሁም ሌሎች የጋራ እሴቶችን ታሳቢ ያደረገ እንደሚሆን ገልጿል፡፡
የመንግሥት የሥራ ቋንቋን በተመለከተ ደግሞ ፓርቲው አሸንፎ ወደ ሥልጣን ቢመጣ ከአማርኛ በተጨማሪ፣ የኦሮሚኛ ቋንቋን የፌዴራል መንግሥቱ የሥራ ቋንቋ እንደሚያደርግ አስታውቋል፡፡