Thursday, June 8, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

አገር ተጨንቃ መቀለድ የታሪክ ተጠያቂ ያደርጋል!

ግብፅ ሱዳንን ከፊት ቃፊር አድርጋ ለአደገኛ ጥፋት ዝግጅት ማድረግ ከጀመረች ሰነባብታለች፡፡ ከሱዳን፣ ከደቡብ ሱዳን፣ ከኬንያና ከኡጋንዳ ጋር የፀጥታና የደኅንነት ስምምነቶች በመፈራረም ኢትዮጵያን ፋታ ለመንሳት እያሴረች ነው፡፡ ታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታን በማስቆም የኢትዮጵያን ተፈጥሯዊ መብት ለመገደብ ታጥቃ ተነስታለች፡፡ ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ ማኅበረሰቡ ዘንድ እንቢተኛና ጨካኝ ለማስመሰል ተከታታይ ዘመቻ ከፍታባታለች፡፡ ታላቁ የህዳሴ ግድብ የኤሌክትሪክ ኃይል ከማመንጨት ውጪ ሌሎች ፕሮጀክቶች እንደማይከናወኑበት ግልጽ መሆኑ እየታወቀ፣ በግብፅ የተቀነባበረ ፕሮፓጋንዳና የዲፕሎማሲ ዘመቻ ኢትዮጵያ ነውጠኛ ተደርጋ እየቀረበች ነው፡፡ ኢትዮጵያ ግን አቅመ ቢስ መስላ እየታየች ነው፡፡ ሰሞኑን በኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ዋና ከተማ ኪንሻሳ የተካሄደው የሦስቱ አገሮች ድርድር ከመጀመሩ በፊት፣ የግብፅ ፕሬዚዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲ ይህ ድርድር የመጨረሻው እንደሚሆን፣ ከግብፅ የውኃ ድርሻ ጠብታ ለመንካት መሞከር አጠቃላይ ቀጣናውን ቀውስ ውስጥ እንደሚከት ማስጠንቀቃቸው ይታወሳል፡፡ ኢትዮጵያ በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል በቅርቡ ባካሄደችው ውጊያና በተለያዩ አካባቢዎች እየተከናወኑ ባሉ ጥቃቶች በሚደርሱ ግድያዎችና ውድመቶች ሳቢያ፣ ከመቼውም ጊዜ በላይ ተዳክማለች ተብሎ በመታመኑ ግብፅ ሱዳንን በማስከተል አጋጣሚውን ለመጠቀም አሰፍስፋለች፡፡ የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች ደግሞ ከመቼውም ጊዜ በላይ ውስጣዊ ችግሮቻቸውን በሰላማዊ መንገድ መፍታት ተስኗቸው፣ በታሪካዊ ጠላቶች ፊት የተፍረከረኩ መስለው አገራቸውን አስንቀዋል፡፡ በጥንካሬ የታጀበ አንድነት በሚያስፈልግበት በዚህ ወሳኝ ወቅት፣ ግላዊና ቡድናዊ ጉዳዮች ላይ ብቻ በማተኮር አገርንና ሕዝብን አሳልፎ መስጠት የታሪክ ተጠያቂ ያደርጋል፡፡

ኢትዮጵያ ጥቅሟን ለማስከበር የምታደርገው ጥረት በበርካታ ፈተናዎች የተከበበ ለመሆኑ፣ የኢትዮጵያ ወቅታዊ ተጨባጭ ሁኔታዎችን የሚከታተሉ ዜጎች በሚገባ ይረዳሉ፡፡ በህዳሴ ግድቡ ምክንያት ከግብፅ ጋር እየተደረገ ያለው መደነቃቀፍ የበዛበት ድርድር፣ ምን ያህል ከባድና ፈታኝ እንደሆነ በግልጽ ይታወቃል፡፡ በዚህ ወሳኝ ወቅት የኢትዮጵያን ሕዝብ ከዳር እስከ ዳር በአንድነት ማሠለፍ ካልተቻለ፣ ፈተናው የበለጠ እየከበደ ይሄዳል፡፡ ፈተናውን ማቅለል ካልተቻለ ደግሞ የኢትዮጵያን ጥቅም አሳልፎ መስጠት ውስጥ ይገባል፡፡ ኢትዮጵያ አሁን ያለችበት አሳሳቢ ሁኔታ ብርቱ ምክክር ያሻዋል፡፡ የፖለቲካ ልሂቃን በሚፈጥሩት ሽኩቻ ምክንያት ታይቶ የማይታወቅ ከፍተኛ መከፋፈል እየተፈጠረ ነው፡፡ ኢትዮጵያ በታሪኳ ዓይታው የማታውቀው ክፍፍል ሲፈጠርና ልዩነቱ ከመጠን በላይ ሲለጠጥ፣ እንኳንስ ጥቅሟን ማስከበር ቀርቶ ህልውናዋም በጣም ያጠራጥራል፡፡ ለአገራቸው ባላቸው ከፍተኛ ፍቅር ምክንያት ጥቅሟን ለማስከበር ሌት ተቀን የሚለፉ እንዳሉ ሁሉ፣ የባዕዳን ተላላኪ ሆነው ሕዝቡን በተገኘው አጋጣሚ የሚያጋጩና ጠላትነትን የሚያበራክቱም እንደ አሸን ፈልተዋል፡፡ አንገቷን አሸዋ ውስጥ እንደምትቀብር ሰጎን በደንታ ቢስነት ራሳቸውን የሚሰውሩም እንዲሁ፡፡ አሁን የሚያዋጣው ግን ልዩነትን ወደ ጎን በማድረግ ለኢትዮጵያ ጥቅም አብሮ መሥራት ነው፡፡ ኢትዮጵያን ከድህነት ውስጥ ለማውጣት ልጆቿ ጠንካራ ሠራተኞች መሆን አለባቸው፡፡ ይህ ጥንካሬ ሊኖር የሚችለው ግን ከግላዊና ከቡድናዊ ፍላጎቶች በመላቀቅ፣ ለኢትዮጵያ በአንድነት መቆም ሲቻል ብቻ ነው፡፡

ኢትዮጵያ በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚ፣ በዲፕሎማሲና በወታደራዊ መስኮች የተጠናከረች አገር መሆን ሲገባት፣ የሚያደነቃቅፏት በርካታ ችግሮች ተጋርጠውባታል፡፡ ድንበር ተሻጋሪ ወንዞችን በፍትሐዊ መንገድ ለመጠቀም፣ ጥቅም ላይ ያልዋሉ ሰፋፊ የእርሻ መሬቶቿን ለማልማት፣ የከበሩ ማዕድናቷን ለማውጣት፣ ወዘተ. ሰላም ያስፈልጋታል፡፡ ይህ ሰላም ግን ዕውን የሚሆነው ኢትዮጵያውያን በተባበረ ድምፅ በአንድነት መቆማቸውን ሲያረጋግጡ ብቻ ነው፡፡ በህዳሴ ግድቡ ግንባታ ምክንያት ግብፅ ከመቼውም ጊዜ በላይ ኢትዮጵያን ለማተራመስ ስለተነሳች፣ አሜሪካና የአውሮፓ ኅብረት ጀርባቸውን እንዲሰጧት ማድረግም ችላለች፡፡ በትግራይ ክልል በተካሄደው ዘመቻና በተለያዩ አካባቢዎች በሚፈጸሙ ግድያዎችና ውድመቶች ምክንያት፣ ኢትዮጵያን ከጨነገፉ አገሮች ተርታ ተሠልፋ እንድትታይ ርብርብ እያደረገች ነው፡፡ የአገር ውስጥ ተላላኪዎችን በማሰማራት ለመስማት የሚዘገንኑ ጭካኔዎችን እያስፈጸመች ነው፡፡ ይህ ወቅት እጅግ በጣም ከፍተኛ የሆነ ትዕግሥት፣ ብልኃትና አስተዋይነት ይፈልጋል፡፡ የኢትዮጵያን ህልውና መታደግ የወቅቱ የማይታለፍ ጥያቄ ነው፡፡ ካልሆነ ግን የታሪክ ተጠያቂነት ይከተላል፡፡

ኢትዮጵያዊያን ስለፍትሐዊነትና ስለምክንያታዊነት ሲጨነቁና ሲጠበቡ ምላሹ እንዲህ ዓይነት ነውረኛ ሴራ ከሆነ፣ አሁን ማሰብ ያለባቸው የቅኝ አገዛዝ ዘመን ውርስ የሆነውን የበላይነት መንፈስ መስበር እንደሚገባ ነው፡፡ ግብፅ ግትር ሆና ውኃውን በቁጥጥሯ ሥር ለማዋል ላይ ታች የምትለው፣ ቅኝ ገዥዎች በአፍሪካ ምድር የተከሉትን የማበጣበጥ ስትራቴጂ በማስፈጸም የበላይነቷን ለማፅናት ነው፡፡ ኢትዮጵያ ደግሞ የቅኝ አገዛዝ መንፈስን በታላቁ የዓድዋ ጦርነት በመስበር ለዓለም ጥቁር ሕዝቦች አርዓያ ስለሆነች፣ ግድቧን በያዘችው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት የመጀመሪያውን ምዕራፍ ሁለተኛ ዙር መሙላት በመጀመር ተምሳሌትነቷን ማጠናከር አለባት፡፡ በጀግንነቱ የማይታማው የኢትዮጵያ ሕዝብ ከዚህ ክቡር ዓላማ ጀርባ ተሠልፎ በዚህ ዘመንም አንፀባራቂ ገድል እንደሚፈጽም ይታመናል፡፡ ከእነ ግብፅ ጀርባ የተሠለፉ ኃይሎች ሊረዱት የሚገባው ተፈጥሯዊ መብት ለድርድር እንደማይቀርብ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ጨዋ፣ አስተዋይና ደግ በመሆኑ ጎረቤቶቹን ለመጉዳት እንደማይፈልግ የታወቀ ነው፡፡ ነገር ግን ትዕግሥትም ገደብ አለውና አጉል ድርጊት ሲፈጸምበት እጁን አጣጥፎ እንደማይቀመጥ መታወቅ አለበት፡፡ በገዛ ገንዘቡና ጉልበቱ የሚገነባውን ግድብ መቼ መሙላትና ማጠናቀቅ እንዳለበት ነጋሪም አያሻውም፡፡ ግድቡን በማንም ላይ ጉዳት ሳያደርስ እንዴት መሙላት እንደሚችል በሚገባ ያውቀዋል፡፡ ከዚህ ውጪ ማንም ሊያስፈራራው አይችልም፡፡ ከተሞከረም ምላሹ ምን እንደሆነ በሚገባ ማሳየት ይችላል፡፡ ፖለቲከኞችም የማይረባ ሽኩቻችሁን አቁማችሁ በዚህ መንፈስ ካልተመራችሁ ታሪክ ይፋረዳችኋል፡፡

የዓባይ ውኃ ጉዳይ አሁን ከመቼውም ጊዜ በላይ ጣልቃ ገብነትን እየጋበዘ ነው፡፡ የዓባይ ተፋሰስ የራስጌ አገሮችን ተፈጥሯዊ የመጠቀም መብትን የሚጋፉ ድርጊቶች እየበዙ ነው፡፡ የኢትዮጵያን የፍትሐዊነትና የምክንያታዊነት መርህ በመጣስ፣ በገዛ ሀብቷ የበይ ተመልካች ለማድረግ የሚደረጉ ጥረቶች ትዕግሥትን የሚፈታተኑ ሆነዋል፡፡ የመካከለኛው ምሥራቅ ፖሊሲዋን በግብፅ አማካይነት የምታስፈጽመው አሜሪካም ሆነች ሌሎች፣ የታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የውኃ ሙሌት ለማስቆም የሚያደርጉትን ጥረት ማክሸፍ ይገባል፡፡ ይህ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት የመዳፈር አጉል ድርጊት መሆኑን ማስገንዘብ ተገቢ ነው፡፡ ለዓባይ ውኃ ምንም ዓይነት አስተዋፅኦ የሌላትን ግብፅ በመደገፍ፣ ለውኃው 86 በመቶ የምታበረክተውን ኢትዮጵያን እጅ ለመጠምዘዝ የሚደረገው ሴራ መቆም አለበት ይባል፡፡ 300 ሚሊዮን በላይ አፍሪካውያን የሚኖሩባቸውን የተፋሰሱን አገሮች መብት እስከ ወዲያኛው ለመገደብ ማንም ጣልቃ ሲገባ፣ ኢትዮጵያውያን በአንድነት በመቆም እንዲህ ዓይነቱን ዓይን አውጣ ድርጊት ማጋለጥና ማስቆም አለባቸው፡፡ ኢትዮጵያ ግድቧን በተገቢው ጊዜ እንዳትሞላ ለማስቆም የሚደረገውን አጉል ሙከራ ማምከን ይገባል፡፡ ኢትዮጵያዊያን ውኃውን በፍትሐዊነትና በምክንያታዊነት እንጠቀምበት በማለት ለዘመናት ያሳዩት ደግነት ተዘንግቶ፣ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብ ሲገነቡ ግብፅ ያሳየችው ክፋት መቼም ቢሆን አይረሳም፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን ሌሎችም የገዛ ጥቅማቸውን ብቻ በማሥላት በግድቡ ላይ የጀመሩት ዘመቻም እንዲሁ አይረሳም፡፡ ኢትዮጵያዊያን ይህንን እኩይ ድርጊት ተባብረው ማስቆም አለባቸው፡፡ የኢትዮጵያ ተፈጥሯዊ የመጠቀም መብት ለድርድር እንደማይቀርብ በተባበረ ድምፅ ማሰማት የግድ ነው፡፡

የያዝነው ዓመት ምርጫ ይካሄድበታል ተብሎ ለወርኃ ግንቦት መጨረሻ ቀጠሮ ተይዟል፡፡ ምርጫ እንኳንስ ሰላምና መረጋጋት ጠፍቶ ሰላም በሰፈነበትም ሒደቱ በጣም አስቸጋሪ ነው፡፡ ለአገር እናስባለን የሚሉ ወገኖች ኢትዮጵያ ከእነ ግብፅ ጋር የገባችበትን አለመግባባት ከተቻለ በሰላማዊ መንገድ አጠናቅቃ፣ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ መሠረት የሚጥለውን ምርጫ በሰላማዊ፣ በፍትሐዊና ሁሉንም በሚያግባባ መንገድ እንድታከናውን ይተባበሩ፡፡ ሰላማዊ የፖለቲካ ፉክክር የሚኖረው ምርጫው ሒደቱ የሰመረ ሲሆንና ሁሉም ወገኖች ኃላፊነታቸውን ሲወጡ ብቻ ነው፡፡ ከሒደቱ ማማር በፊት ውጤት ላይ እየተተኮረ ሴራ መጎንጎን ከተጀመረ ታጥቦ ጭቃ መሆን ይከተላል፡፡ ኢትዮጵያ በታሪኳ ለመጀመርያ ጊዜ ዓለም አቀፍ መሥፈርቶችን ያሟላ ምርጫ እንድታካሂድ ከተፈለገ፣ ለልዩነቶች ዕውቅና በመሰጣጠት በእኩልነት ለመፎካከር የሚያስችል የፖለቲካ ምኅዳር በጋራ ማዘጋጀት የግድ ይሆናል፡፡ እልህ፣ ግትርነት፣ ሕገወጥነትና ጉልበተኝነት ከዴሞክራሲ ጋር ፀብ እንጂ ዝምድና የላቸውም፡፡ ተፎካካሪዎች በሕዝብ ድምፅ ለመዳኘት የፖለቲካ የጨዋታ ሕግ በሚፈቅደው መሠረት የቤት ሥራቸውን ጨርሰው ብቻ ነው መገኘት ያለባቸው፡፡ በሴራና በመሰሪነት የሚገኘው አምባገነንነት ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ደግሞ አምባገነንነት ሰልችቶታል፡፡ ኢትዮጵያም ድህነት ውስጥ የተዘፈቀችው የአምባገነንነት መጫወቻ ስለሆነች ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ በስሙ የሚነግዱትንና የሚቆምሩትን አይፈልግም፡፡ ይህ ለአገሩ ከፍተኛ ክብርና ፍቅር ያለው ሕዝብ ጥቅሟ ተከብሮ እንዲያልፍላት ይፈልጋል፡፡ መፍትሔው የኢትዮጵያ ጥቅም እንዲከበር በአንድነት መቆም ብቻ ነው፡፡ አገር ተጨንቃ መቀለድ የታሪክ ተጠያቂ ያደርጋል!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

በኦሮሚያ ክልል በስድስት ከተሞች የተዋቀረውን ሸገር ከተማን የማደራጀት ሥራ ተጀመረ

በአዲስ አበባ ዙሪያ በሚገኙ ስድስት ከተሞች የተዋቀረው ሸገር ከተማን...

የኦሮሞን ሕዝብ ታሪክ አልባ በማድረግ ታሪክ አይሠራም

በኢተፋ ቀጀላ​​  ከዛሬ ሃምሳ ዓመት ወዲህ ከተፈጠሩት የኦሮሞ ድርጅቶች መካከል ከኢጭአት በስተቀር፣...

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ከተለመደው አሠራር ወጣ ያለውን ‹‹የወደፊት ግብይት›› ሥርዓት በይፋ አስጀመረ

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ከተለመደው የማገበያየት ተግባሩ ወጣ ያለና በኢትዮጵያ...
- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

ከቀጣዩ ዓመት በጀት ውስጥ 281 ቢሊዮን ብሩ የበጀት ጉደለት ነው ተባለ

ለቀጣዩ በጀት ዓመት ከቀረበው 801.65 ቢሊዮን ብር አጠቃላይ በጀት...

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ከተለመደው አሠራር ወጣ ያለውን ‹‹የወደፊት ግብይት›› ሥርዓት በይፋ አስጀመረ

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ከተለመደው የማገበያየት ተግባሩ ወጣ ያለና በኢትዮጵያ...

የባንክ ማቋቋሚያ መሥፈርት እንደሚጠነክር ሚኒስትሩ ተናገሩ

 ባንኮች ስለውህደት እንዲያስቡም መክረዋል በኢትዮጵያ ውስጥ ባንክ ለማቋቋም የሚያስፈልገው መሥፈርት...

ማን ይቻለን?

በጠዋት የተሳፈርንበት ታክሲ ውስጥ በተከፈተው ሬዲዮ፣ ‹‹ይኼኛው ተራራ ያን...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

አገር አጥፊ ድርጊቶች በአገር ገንቢ ተግባራት ይተኩ!

ኢትዮጵያ ውስጥ በስፋት የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት በመንስዔዎች ላይ መግባባት ያስፈልጋል፡፡ መግባባት ሊኖር የሚችለው ደግሞ በሠለጠነ መንገድ ለመነጋገር የሚያስችል ዓውድ ሲፈጠር ነው፡፡ ለዚህ ስኬት ዕውን...

ሕገ መንግሥት ለማሻሻል ባህሪን መግራት ያስፈልጋል!

በሥራ ላይ ያለው አወዛጋቢ ሕገ መንግሥት ከፀደቀበት ከ1987 ዓ.ም. ጀምሮ እስካሁን ድረስ ከተለያዩ አቅጣጫዎች ወቀሳዎችና ተቃውሞዎች ይቀርቡበታል፡፡ ከተቃውሞዎቹ መካከል በሕገ መንግሥቱ መግቢያ ላይ ኢትዮጵያዊነትን...

የፖለቲካ ምኅዳሩ መላሸቅ ለአገር ህልውና ጠንቅ እየሆነ ነው!

የኢትዮጵያ ፖለቲካ ምኅዳር ከዕለት ወደ ዕለት የቁልቁለት ጉዞውን አባብሶ እየቀጠለ ነው፡፡ በፖለቲካ ፓርቲዎች የእርስ በርስ ግንኙነትም ሆነ በውስጠ ፓርቲ ዴሞክራሲ የሚታየው መስተጋብር፣ ውል አልባና...