ከካፍ የተረከበው ስፖርት ኮሚሽን ማብራሪያ አለመጠየቁን ገልጿል
የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) ከ13 ዓመታት በፊት በአዲስ አበባ አያት አካባቢ ላስገነባው የምሥራቅና የመካከለኛው አፍሪካ አገሮች ታዳጊ ወጣቶች የእግር ኳስ አካዴሚ ማስፋፊያ የተፈቀደው ቦታ፣ በፍርድ ቤት ትዕዛዝ መታገዱን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታወቀ፡፡ የአካባቢው አርሶ አደሮች ከ13 ዓመታት በኋላ እንደ አዲስ ግብር እንዲገብሩበት ስለመደረጉ ጭምር ተነግሯል፡፡
በ2000 ዓ.ም. ለአካዴሚው ማስፋፊያ እንዲሆን ቀድሞ በነበረው 30 ሺሕ ካሬ ሜትር ቦታ በተጨማሪ 20 ሺሕ ካሬ ሜትር በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ተሰጥቶ የነበረ ቢሆንም፣ ለማስፋፊያ በተሰጠው ቦታ ላይ በተነሳ ክርክር ከሥፍራው የተነሱ አርሶ አደሮች ለፍርድ ቤት አቤት ማለታቸውን ተከትሎ ነው ፍርድ ቤት ዕግዱን ያወጣው፡፡ ለማስፋፊያው ተጨማሪ የተሰጠው መሬት ላይ ለዓመታት ተቋርጦ የነበረውን ግብር ከዚሁ ዓመት ጀምሮ አርሶ አደሮቹ እንዲገብሩ በመደረጉ፣ ፍርድ ቤቱ ዕግዱን እንዲጥል መነሻ እንደሆነው ፌዴሬሽኑ አስታውቋል፡፡
እንደ ፌዴሬሽኑ ከሆነ ገበሬዎች ከ13 ዓመታት በኋላ ግብር እንዲከፍሉ ከተደረገ በኋላ ወደ ፍርድ ቤት ሄደው አቤቱታ አቅርበው የዕገዳ ውሳኔ ከመተላለፉ በፊት፣ የአካዴሚውን ካርታና የሳይት ፕላን ከካፍ የተረከበው ስፖርት ኮሚሽን፣ በጉዳዩ ማብራሪያ እንዲሰጥ አልተደረገም፡፡ በዚያ ላይ ኮሚሽኑ አካዴሚውን ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ለማስረከብ በሒደት ላይ ባለበት በዚህ ወቅት እንዲታገድ መደረጉ አግባብ እንዳልሆነ ጭምር፣ የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
ካፍ በአዲስ አበባ የገነባው አካዴሚ የምሥራቅ አፍሪካ ታዳጊዎች የእግር ኳስ ልህቀት ማዕከል እንዲሆን ታሳቢ ተደርጎ የተገነባ ሲሆን፣ ማስፋፊያውም ይኼንን ተግባር በስፋት ለማከናወን ያስችላል ተብሎ የተወሰነ ነበር፡፡
ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ በታገደው ቦታ ላይ አንድ የተፈጥሮ ሳርና ሁለተኛውን ደግሞ በሰው ሠራሽ ሳር ሁለት ሜዳዎችን ለማስገንባት ስፖንሰር ተገኝቶ ተቋራጮችን ለማወዳደር በዝግጅት ላይ እንደነበርም ፕሬዚዳንቱ አክለዋል፡፡
አካዴሚውን ያስገነባው ካፍ ከሁለት ዓመት በፊት ቀድሞ የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስትር ለነበሩት አቶ ርስቱ ይርዳው የአካዴሚውን ሙሉ ሰነድ እንዳስረከበ ያስረዱት አቶ ኢሳያስ፣ ፌዴሬሽኑ ሁለቱን ሜዳዎች ማስገንባት ይችል ዘንድ ከሁለት ወራት በፊት የመሬት መጥረጊያ ማሽኖችን በማስገባት ዋናውን ሥራ ጀምሮ ነበር፡፡
ችግሩን ተከትሎ ከወር በፊት ከተመረጡት የካፍ አመራሮች መካከል ከጽሕፈት ቤት ኃላፊውና ከፕሬዚዳንቱ ጋር መነጋገራቸውን ያስረዱት አቶ ኢሳያስ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ይህን ጉዳይ በጥሞና ተመልክተው አፋጣኝ የመፍትሔ አቅጣጫ ሊያበጁለት እንደሚገባ ጠይቀዋል፡፡
አካዴሚው ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ የተለያዩ ቢሮዎችና የስብሰባ አዳራሾች፣ ስፖርተኞች የሚተኙባቸው 42 ክፍሎችና የላውንደሪ ማሽኖች፣ እንዲሁም አንድ ዓለም አቀፍ አካዴሚ ሊያሟላቸው የሚገቡ ጅምናዚየሞችን አሟልቶ የያዘ በመሆኑ፣ ለብሔራዊ ቡድኖች ዝግጅት አገልግሎት መስጠት ከጀመረም ሰነባብቷል፡፡
የዓለም አቀፍ እግር ኳስ ማኅበር (ፊፋ) ከዓመት በፊት በአዲስ አበባ የከፈተውን ቀጣናዊ ጽሕፈት ቤት ምክንያቱን ሳያሳውቅ ወደ ሩዋንዳ ማዛወሩ ይታወሳል፡፡