ከክልሉ ውጪ የሚኖረው የሐረሪ ክልል ከሕዝብ ባለፉት አምስት ምርጫዎች የመምረጥ መብት ተሰጥቶት የመረጠ ቢሆንም፣ ግንቦት 28 ቀን 2013 ዓ.ም. በሚካሄደው ምርጫ ላይ መሳተፍ እንደማይችል የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ዓርብ ሚያዝያ 1 ቀን 2013 ዓ.ም. አስታወቀ፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ከክልሉ ውጪ የሚኖው ሕዝብ መምረጥ የሚያስችለው የሕግ መሠረት ስለሌለ መሆኑን ጠቁሟል፡፡
የሐረሪ ሕዝብ ክልል ምክር ቤት፣ ብሔራዊ ጉባዔ፣ የፕሬዚዳንት ጽሕፈት ቤትና የብልፅግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ለቦርዱ በጻፉት ደብዳቤ እንደገለጹት፣ ከክልሉ ውጪ የሚኖረው የሐረሪ ሕዝብ የክልሉ ምክር ቤት አካል ለሆነው ብሔራዊ ጉባዔ የመምረጥ መብት ተሰጥቶታል፡፡ መብቱን የሰጠው የሽግግር መንግሥት ምክር ቤት መጋቢት 6 ቀን 1987 ዓ.ም. ባካሄደው 102ኛ መደበኛ ስብሰባ መሆኑን ገልጿል፡፡
በዚህም መሠረት ባለፉት አምስት አገራዊ ምርጫዎች ከክልሉ ውጪ የሚኖሩ የብሔረሰቡ አባላት በመምረጣቸው፣ በዚሁ መሠረት በስድስተኛውም አገራዊ ምርጫም እንዲሳተፉ ያቀረቡትን ጥያቄ ተቀብሎ ቦርዱ ሒደቱንና የሕግ መሠረቱን መመርመሩን አስታውቋል፡፡
በሕገ መንገግሥቱ ድንጋጌ መሠረት በአንድ ክልል የመንግሥት አወቃቀር ውስጥ የሚገኙ የምክር ቤት አባላት የሚመረጡት፣ በክልሉ ድምፅ መስጠት በሚችሉ ነዋሪዎች ብቻ መሆኑን ያስታወሰው ቦርዱ፣ ከዚህ ውጪ ከክልሉ ውጪ ያሉ አነስተኛ የሆነ ብሔረሰብ አባላት እንዲመርጡ የተደነገገም ሆነ የተለየ አሠራር መተግበር የሚያስችል ድንጋጌ በምርመራው እንዳላገኘ ገልጿል፡፡
የሽግግር መንግሥት ምክር ቤት መጋቢት 6 ቀን 1987 ዓ.ም. ባካሄደው 102ኛ መደበኛ ስብሰባ፣ ‹‹የሐረሪ ብሔራዊ ጉባዔ ከክልሉ ውጪ ነዋሪ በሆኑ የብሔረሰቡ አባላት ይመረጣል›› የሚለው ውሳኔ ሕገ መንግሥቱን መሠረት ያደረገ አለመሆኑን ጠቁሟል፡፡ እንዲያውም ውሳኔው አግባብነት እንደሌለው ከሚያሳዩ ሁኔታዎች አንዱ፣ በውሳኔ ሰነዱ ላይ የምክር ቤቱ ማኅተም ያላረፈበት መሆኑንም አክሏል፡፡
ክልሉ በጻፈው ደብዳቤ ባለፉት አምስት ምርጫዎች ስለተሳተፉት የብሔረሰቡ አባላት፣ የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ መመርያ እንደሚያሳይ ቢጠቀስም፣ የተባለውን መመርያ በቦርዱ ጽሕፈት ቤት አለማግኘቱንም በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ውብሸት አየለ ፊርማ ወጪ የተደረገው የመልስ ደብዳቤ ያብራራል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ባለፉት አምስት ምርጫዎች ከክልሉ ውጪ የሚኖሩ የብሔረሰቡ አባላት ለሐረሪ ብሔራዊ ጉባዔ እንዲመርጡ ሲያደርግ የቆየ ቢሆንም፣ የስድስተኛውን አገራዊ ምርጫ ሒደት እያከናወነ የሚገኘው ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የተለያዩ ማሻሻያዎችን ሲያደርግ የቆየው፣ የሕገ መንግሥትና የምርጫ ሕግ መሠረት የሌላቸውን ልምዶችና አሠራሮችን እንዳይቀጥሉ ለማድረግ መሆኑን ገልጿል፡፡
ባለፉት አምስት ምርጫዎች ያለ ሕገ መንግሥት ድጋፍ ከክልሉ ውጪ ያሉ የብሔረሰቡ አበላት ሲመርጡ መቆየታቸውን መሠረት አድርጎ እንዲቀጥል ቢደረግም፣ ሌሎች አነስተኛ ቁጥር ያላቸው ብሔረሰቦች ከክልላቸው ውጪ ያሉ አባሎቻቸውን በምርጫው እንዲሳተፉ ጥያቄ ቢያቀርቡና ቦርዱ ቢከለክላቸው፣ የቦርዱን ፍትሐዊነትና ገለልተኛነት፣ እንዲሁም ምርጫን የማስተዳደር ጉዳይ አደጋ ላይ እንዲወድቅ እንደሚያደርገው አስታውቋል፡፡
ምርጫው ፍትሐዊ እንዲሆንና ሁሉም በእኩልነት የሚገለገልበት ሥርዓት ለመዘርጋት ሕገ መንግሥታዊ ድጋፍ ያላቸውን ልምዶችና አሠራሮች ብቻ እንደሚወስድም ገልጿል፡፡ በመሆኑም ክልሉ ያቀረበውን ጥያቄ እንደማያስናግድም አስታውቋል፡፡