የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በመተከል ዞን ወንበራ ወረዳ ለክልል ምክር ቤት ዕጩ የነበረው አባሉ አቶ በሪሁን አስፈራው ላይ በመተከል ዞን በለስ ልዩ ቦታው ‹‹ካርባር›› ግድያ የተፈጸመበት መሆኑን አስታወቀ፡፡
በግንቦት ወር በሚደረገው አገራዊ ምርጫ ተሳታፊ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ፣ በሁሉም የአገራችን ክፍሎች በርካታ ዕጩ ተወዳዳሪዎችን ያስመዘገበ መሆኑን በመጠቆም፣ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ካድሬዎች በአባላቶቹ ላይ ተደጋጋሚ ዛቻ፣ እስርና ድብደባ እየፈተጸመ መሆኑን አስታውቋል። በተለይ በኦሮሚያና በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች በስፋት፣ እንዲሁም አልፎ አልፎ በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች በአባላቶቹ ላይ ማጉላላት፣ እስርና ድብደባ እየደረሰባቸው መሆኑን ጠቁሟል።
በተደጋጋሚ ጊዜ ሰላማዊ ዜጎችን በአሰቃቂ ሁኔታ ከመግደል እስከ ጅምላ ማፈናቀል የዘለቀው የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል፣ ቀደም ብሎ የክልሉ ካድሬዎች የተወዳዳሪዎች ምዝገባ እንዳይሳካ ለማድረግ ብዙ ጥረት ያደረጉ ቢሆንም፣ በምርጫ ቦርድ ትብብር ምዝገባው ሊከናወን መቻሉን አስታውሶ፣ የምርጫ ተወዳዳሪ ዕጩዎቹ ቅስቀሳ ላይ በነበሩበት ወቅት ያለመከሰስ መብታቸውን በጣሰ መልኩ አስሮ በማጉላላትና በማስፈራራት አላስፈላጊ ጫና ለማሳረፍ መሞከሩን ባወጣው የሐዘን መግለጫ አስታውቋል።
ይህ ሁሉ አልበቃ ብሎ የክልል ምክር ቤት ዕጩ ተወዳዳሪ የነበረው አቶ በሪሁን አስፈራው ከቻግኒ ወደ በለስ ጉዞ ላይ እያለ ልዩ ቦታው ካርባር ላይ ግድያ እንደተፈጸመበት ተናገሯል፡፡
አብን ግድያው ፖለቲካዊ መሠረት ያለውና ንቅናቄው በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል የሚያደርገውን እንቅስቃሴ ለመገደብ ሆነ ተብሎ የተደረገ እንደሆነ እንደሚያምን፣ ለዚህም የዕጩውን ግድያ ጨምሮ በአሶሳና አካባቢው በተደጋጋሚ ጊዜ በዕጩዎቹና አመራሮቹ ላይ ሲፈጽሙ የነበሩ ምክንያት አልባ እስሮችና ወከባዎች ከበቂ በላይ አስረጂዎች መሆናቸውን አስተውሷል።
በመላው ኢትዮጵያ በተለይም የግጭት ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች ምርጫ ሲቃረብ መሰል ግድያዎች፣ ጭፍጨፋዎች፣ ማፈናቀሎችና ወከባዎች እንደሚኖሩ ደጋግሞ ለመንግሥት ያሳሰበ ቢሆንም፣ ከስህተቱ መማር ያልፈለገው መንግሥት ዛሬም ድረስ ዜጎች በጅምላና በተናጥል ሲገደሉ፣ ሲፈናቀሉና ሀብት ንብረታቸው ሲወድም በዝምታ እየተመለከተ እንደሚገኝ ጠቁሞ፣ ‹‹አብን ይህ ጉዳይ ቀስ በቀስ አገር የሚያፈርስና አደገኛ ጉዳይ መሆኑን ይገነዘባል፤›› ብሏል። አስቸኳይ የዕርምት ዕርምጃ እንዲወሰድም አበክሮ የሚታገልበት መሆኑንም አስታውቋል፡፡ መንግሥት በምርጫ ዕጩ አባሉ ላይ የተፈጸመውን ግድያ በአስቸኳይ እንዲመረምርና ገዳዮችን ለፍርድ እንዲያቀርብ ጠይቋል፡፡ ለምርጫ ዕጩዎቹም ተገቢው የፀጥታ ከለላ በመንግሥት በኩል እንዲሰጥ ጠይቋዋል፡፡