Monday, April 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርት‹‹የጨዋታው መጠናቀቂያ ፊሽካ እንደተሰማ ነው ስለ ቀጣይ ዝግጅታችን ማሰብ የጀመርነው›› ውበቱ አባተ፣...

‹‹የጨዋታው መጠናቀቂያ ፊሽካ እንደተሰማ ነው ስለ ቀጣይ ዝግጅታችን ማሰብ የጀመርነው›› ውበቱ አባተ፣ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ብሔራዊ ቡድን አሠልጣኝ

ቀን:

በኢትዮጵያ እግር ኳስ የአሠልጣኞች ስም ዝርዝር ውስጥ በቀዳሚነት ከሚጠቀሱት መካከል አንዱ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ስኬታማ ጊዜና ድልን መጎናፀፍ ከቻሉ አሠልጣኞች ውስጥም ይጠቀሳል፡፡ በተለይ የአንድን ክለብ ጥንካሬና ድክመትን አቻችሎ ለድል መብቃትን እንደተካነበት ይነገርለታል፡፡ የሚከተለው የአጨዋወት ዘይቤ በበርካቶች ይወደዳል፡፡ 14 ዓመታት በእግር ኳስ ተጫዋችነት አሳልፎ፣ በአሠልጣኝነቱም ስኬታማ ጊዜን እያሳለፈ ይገኛል፡፡ የእግር ኳስ ሕይወቱ በትውልድ ከተማው አዳማ የጀመረው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ብሔራዊ ቡድን አሠልጣኝ ውበቱ አባተ፣ 1997 .. ጀምሮ አዳማ ከነማን፣ ደደቢትን፣ ኢትዮጵያ ቡናን፣ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን እንዲሁም የሱዳኑ አል አል ሼንዲ፣ ሐዋሳ ከነማ፣ ፋሲል ከነማ፣  በመጨረሻም ከሰበታ እግር ኳስ ክለብ ጋር ስኬታማ የሚባሉ ጊዜዎችን ማሳለፍ ችሏል፡፡ ከስድስት ወራት በፊት የኢትዮጵያ አግር ኳስ ብሔራዊ ቡድንን ለማሠልጠን ኃላፊነት የተረከበው አሠልጣኙ፣  ከስምንት ዓመት በኋላ ብሔራዊ ቡድኑን ለአፍሪካ ዋንጫ ማሳለፍ ችሏል፡፡ አሠልጣኙ ያሳለፈውን የአሠልጣኝነት ጉዞና ብሔራዊ ቡድኑ በቀጣይ ስላለበት የአፍሪካ ዋንጫ ጨዋታና የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ዝግጅት ጋር በተያያዘ ዳዊት ቶሎሳ አነጋግሮታል፡፡

ሪፖርተር፡ ወደ አሠልጣኝነት እንዴት እንደገባህ አስታውሰን?

ውበቱ አባተ፡ የአሠልጣኝነት ጉዞዬ የጀመረው አዳማ የሠፈር ወጣቶችን በመሰብሰብና በበጎ ፈቃደኝነት በማሠልጠን ነበር፡፡ ከዛም አዳማ ፖሊስ የሚባል ክለብ ሲቋቋም ከእኔ ሲሠለጥኑ የነበሩ ወጣቶችን ይዤ 1997 ..  በነፃ ማሠልጠን ቀጠልኩ፡፡ በጊዜው የወጣቱ፣ እንዲሁም የፖሊስ ክለቡ የዞን ሻምፒዮን መሆን ችሎ ነበር፡፡ በወቅቱ የአዳማ ከነማ እግር ኳስ ክለብ ዋና አሠልጣኝ ለነበረው ሥዩም ከበደ በምክትል አሠልጣኝነት እንዳገለግል ጥሪ ቀረበልኝ፡፡ 1998 .. ሥዩም መልቀቁን ተከትሎ አቶ ጸጋዬ ደስታ ወደ ክለቡ ሲመጡ በምክትል አሠልጣኝነቴ ቀጥዬ አንደኛው ዙር መጠናቀቁን ተከትሎ ውጤቱም ጥሩ ባለመሆኑ እሳቸው ክለቡን በገዛ ፈቃዳቸው ሲለቁ የክለቡ ዋና አሠልጣኝ ሆኜ በይፋ የአሠልጣኝነቴን ሥራ ጀመርኩ፡፡ በወቅቱ አዳማ እግር ኳስ ክለብ በሊጉ ከሚሳተፉት 16 ክለቦች 15ተኛ ደረጃ ላይ ነበር የሚገኘው፡፡ ከዚያም ቀሪ ጨዋታዎችን ካደረግን በኋላ አሥረኛ ደረጃን በመያዝ ማጠናቀቅ ቻልን፡፡ 1999 .. ጀምሮ በይፋ የአዳማ እግር ኳስ ክለብ ዋና አሠልጣኝ ሆኜ ተሾምኩ፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ሪፖርተር፡ከአዳማ ጋር ከተለያየህ በኋላ ደደቢት፣ ኢትዮጵያ ቡናንና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ክለቦችን ካሠለጠንክ በኋላ ቀጥታ ወደ ሱዳን ሊግ ነበር ያመራኸው? አጋጣሚውን እንዴት ተገኘ?

ውበቱ አባተ፡ በጊዜው በኢትዮጵያ ዜግነታቸው ሱዳናዊ የሆኑ በርካታ ሱዳናዊያን  እግር ኳስ ያዘወትሩ ነበር፡፡ ከእዚያም ወደ ሱዳን ሄዶ ማሠልጠን የሚፈልግ አሠልጣኝ ሲጠይቁ ከእኔ ጋር ከተገናኘን በኋላ ፍላጎት ካለኝ ሊቀጥሩኝ እንደሚችሉ አሳወቁኝ፡፡ ልክ ወደ ሱዳን እንዳመራሁ የተቀጠርኩት በምክትል አሠልጣኝነት ነበር፡፡ ከእዚያም ለስድስት ወራት በዋና አሠልጣኝነት መምራት ችያለሁ፡፡ 2006 .. ጀምሮ የነበረኝ የሁለት ዓመት ቆይታዬ ጥሩ ነበር፡፡ ክለቡ ሁለት ጊዜ የካፍ ኮንፌዴሬሽን ውድድር መሳተፍ ችሏል፡፡ ከዛም ባሻገር በግሌ ያገኘሁት ልምድ ቀላል የሚባል አይደለም፡፡ ምክንያቱም በሊጉ በርካታ የውጭ አገር የእግር ኳስ ባለሙያዎች ይገኛሉ፡፡ ከጋና፣ ከብራዚል፣ ከፈረንሣይና ከአልጄሪያ የመጡ አሠልጣኞች ነበሩ፡፡ ከእነሱ ጋር የማውራትና የመወያየት ልምድም የመቅሰም አጋጣሚ ነበረኝ፡፡ ወደ አገር ቤት ከተመለስሁ በኋላም  ተመልሼ እንዳሠለጥን  ሦስት ጊዜ ጠይቀውኛል፡፡ በጊዜው እኔ ሌላ ኮንትራት ስለተፈራረምኩ፣ ልቀበላቸው አልቻልኩም፡፡

ሪፖርተር፡ ወደ አገር ቤት ከተመለስህ በኋላ ከሐዋሳ፣ ፋሲልና ሰበታ እግር ኳስ ጋር ቆይታ አድርገሃል። ራስህን እንዴት ትገመግማለህ?

ውበቱ አባተከሱዳን ከተመለስኩ በኋላ 2007 .. አጋማሽ ጀምሮ እስከ 2010 .. ድረስ ሐዋሳ ነበር ቆይታዬ፡፡ በሐዋሳም ከሞላ ጎደል ጥሩ ጊዜ ነበረኝ ማለት ይቻላል፡፡ ግን ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ የተጫዋቾች ዝውውርን አስመልክቶ ካወጣው ፖሊሲ ጋር ተያይዞ፣ በፈለግነው መንገድ ቡድኑን መገንባት አልቻልንም ነበር፡፡ ምክንያቱም እንደ ቀድሞ ተጫዋችን መርጦ ማስፈረም፣ ያሉትን ማቆየትና አዳዲስ ማስፈረም አስቸጋሪ ነበር፡፡  ጥሩ ጥሩ ተጫዋቾች ወደ ትልልቅ ክለቦች ወይም ሙሉ በሙሉ ከፍተኛ ክፍያ ወደ ሚከፍሏቸው ክለቦች ነበር ሲያመሩ የነበሩት፡፡ የደመወዝ ጣራ መጠን መቀመጡ ተጫዋቾችን በደንብ ወደ ሚከፍሉ ክለቦች ትኩረታቸውን እንዲያደርጉ ጫና ፈጥረዋል፡፡ እንደዛውም ሆኖ አዳዲስና ታዳጊ ተጫዋቾችን ወደ ላይ በማሳደግ በሊጉ  ላይ ጥሩ ተፎካካሪ መሆን ችለን ነበር፡፡ 2010 .. በኋላም በፋሲል ጥሩ ቆይታ ነበረኝ፡፡ ክለቡ 2011 .. ላይ አንድ ጨዋታ እስኪቀር ድረስ ከሊጉ አሸናፊ ጋር ተናንቆ ሁለተኛ ሆኖ አጠናቋል፡፡ ለመጀመርያ ጊዜም በካፍ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ላይ መሳተፍ ችሏል፡፡ ከፋሲል ጋር የተለያየሁት ባለቤቴ የልብ ሕመም አጋጥሟት ስለነበር፣ ከእሷ አጠገብ መሆን ስለነበረብኝ ነው፡፡

ሪፖርተር፡የኢትዮጵያ አግር ኳስ ክለቦች ሁሌም የሚተቹበት ችግር እንዳለ በተደጋጋሚ ይነሳል፡፡ ይሄ መቀረፍ ያልቻለና በሁሉም ክለቦች ላይ የሚስተዋለው ችግር ምንድነው?
ውበቱ አባተ፡ በርካታ የኢትዮጵያ ክለቦች ላይ የሚስተዋል ሁለት አንኳር ችግር አለ፡፡ አንደኛው የገንዘብ ችግር ሲሆን፣ ሌላኛው የመዋቅር ችግር ነው፡፡ ይኼ ችግር ተለዋዋጭ ነው፡፡ አንደኛው ክለብ አንዱን ያሟላል አንደኛው ሌላ ያጎላል፡፡ በርካቶቹ ውጤት ላይ ከማተኮር ባሻገር መዋቅራቸውን ማዘመኑ ላይ እምብዛም ናቸው፡፡ የገንዘቡ ችግር መንስዔ በርካቶቹ ክለቦች የመንግሥት ካዝና ስለሚጠብቁ ነው፡፡
ሪፖርተርከፋሲል ከነማ ጋር እንደተለያየህ ለሰበታ ከነማ ፊርማህንን ካኖርህ ከአሥር ወራት በኋላ የብሔራዊ ቡድን ዋና አሠልጣኝ ተደርገህ መሾምህ ይታወሳል፡፡ በአንፃሩ ከሰበታ ጋር ግን ውዝግብ ውስጥ መግባታችሁ ይታወቃል፡፡ በመካከላችሁ የተፈጠረው አለመግባባት ምንድነው?

ውበቱ አባተ፡ ከፋሲል ከተለያየሁ በኋላ ሰበታ እግር ኳስ ክለብን ለማሠልጠን የሁለት ዓመት ውል ተዋውለን ነበር፡፡ ለሁለት ዓመት ቆይታዬም 3.4 ሚሊዮን ብር ከፍለውኛል፡፡ አንድ ዓመት ከሁለት ወር ከሠራሁ በኋላ የብሔራዊ ቡድን አሠልጣኝ እንድሆን ተመረጥኩ፡፡ ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጋር ከመፈራረሜ በፊት ከሰበታ ጋር ቀሪ ውል ስለሚቀረኝ እንዴት ማድረግ እንዳለብኝ ለፌዴሬሽኑ አሳውቄ ነበር፡፡ ክለቡ ደግሞ ከሁለት ዓመት ኮንትራት ቀሪ አሥር ወራት አላገለገልክም  የሚል መከራከሪያ እያቀረበ ይገኛል፡፡ በአንፃሩ እኔ ክለቡን ማሠልጠን  አልፈልግም ብዬ ብለቅ፣ ያልሠራሁበትን መመለስ እንዳለብኝ ውል ላይ ተቀምጧል፡፡ ስለዚህ አሁን ፌዴሬሽኑ ጉዳዩን እንደሚፈታ ቃል ገብቶ ነበር፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ እየተከራከርን የማዳጋስካር ጨዋታ መጣ፡፡ በተቻለ መጠን ትኩረታችንን በጨዋታው ላይ ማድረግ ስለነበረብን ጨዋታው ላይ ትኩረት ማድረግ እንዳለብን ተነጋገርን፡፡ ስለዚህ ብሔራዊ ቡድኑ ያለበትን ውድድር እሰኪያጠናቅቅ ጉዳዩ እንዲቆይና ከእዚያ በኋላ የሚፈታ ይሆናል የሚለው ስምምነት ላይ ደርሰናል፡፡

ሪፖርተርከዚህ ቀደም ብሔራዊ ቡድኑ ጨዋታ ሲኖረው አሠልጣኞች ፌዴሬሽኑን ሲተቹ መመልከት የተለመደ ነው፡፡ አሁን ያለው የእግር ኳሱ አስተዳዳሪ ቡድኑ የሚፈልገውን ነገር እያሟላ ነው ማለት ይቻላል?

ውበቱ አባተ፡ በተለያዩ ጊዜያት ብሔራዊ ቡድኑን በተመለከተ የተለያዩ አከራካሪ ጉዳዮች ሲነሱ ማስተዋል የተለመደ ነው፡፡ አሠልጣኞቹ ችግር ሳይገጥማቸው ቀርቶ አይደለም፣ ችግሮች ነበሩ፡፡ ግን በእኔ አመለካከት ስለችግሮቹ አጉልቶ ከማውራት ጥሩ ጥሩ ንግግሮችን እያነሱና እያደነቁ መጓዝ ይሻላል ባይ ነኝ፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ብዙ ነገሮች እየተደረጉልን ነው፡፡ ከዚህ ቀደም የወዳጅነት ጨዋታ ማግኘት ከባድ ነበር፡፡ አሁን ግን እየተመቻቸልን ነው፡፡ ቡድኑ በተለያዩ የክልል ከተሞች ዝግጅቱን ሲያደርግ ፌዴሬሽኑ አስፈላጊውን ድጋፍ ሁሉ አድርጎልናል፡፡ ስለዚህ ከድሮ ጋር ሲነፃፀር አሁን የተሻለ ነው፡፡ ምንም እንከን የለም ማለት ባይቻልም መልካም ጎኖችን ማድነቅ ያስፈልጋል፡፡
ሪፖርተርየኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከስምንት ዓመት በኋላ 33ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ጨዋታ ማለፉን አረጋግጧል፡፡ በቀጣይ የአፍሪካ ዋንጫ ጨዋታን ጨምሮ ለዓለም ዋንጫም የማጣሪያ ጨዋታ ይጠብቀዋል፡፡ ቀጣይ የሚኖራችሁ ዝግጅት ምን ይመስላል?
ውበቱ አባተ፡ በቀጣይ የአፍሪካ ዋንጫና የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታ ይጠብቀናል፡፡ የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታ ግንቦት ላይ ነው የሚጀምረው፡፡ የመጀመርያ ጨዋታችን ከጋና ጋር ነው።  ስለዚህ ከግንቦት 28 በፊት ተጫዋቾቹን ጠርተን ዝግጅት እንጀምራለን፡፡ ስለዚህ እነማን ይጠራሉ፣ ይቀነሳሉ የሚለውን በቀጣይ የምናደርገው ዝግጅት ይወስናል፡፡ የወዳጅነት ጨዋታም ይኖረናል፡፡ ብሔራዊ ቡድኑን ለአፍሪካ ዋንጫ እናሳልፋለን ብለን ነበር የተነሳነው፣ ከዚህ በኋላ ደግሞ በውድድሩ ላይ ጥሩ ውጤት ማምጣቱ ላይ ትኩረት ሰጥተን እንሠራለን፡፡ የጨዋታው መጠናቀቂያ ፊሽካ እንደተሰማ ነው ስለቀጣይ ዝግጅታችን ማሰብ የጀመርነው፡፡ ስለዚህ በቂ ዝግጅት እናደርጋለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር የጨረታ ማስታወቂያ

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር በገቢ እና በውጭ ንግድ እንዲሁም...

ያልተቃናው የልጆች የንባብ ክህሎት

አንብቦና አዳምጦ መረዳት፣ የተረዱትን ከሕይወት ጋር አዋህዶ የተቃና ሕይወት...

እንስተካከል!

ሰላም! ሰላም! ውድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ እንዲሁም የሰው ዘር በሙሉ፣...

የሙዚቃ ምልክቱ ሙሉቀን መለሰ ስንብት

የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ በ1950ዎቹ እና በ1960ዎቹ በኪነ ጥበባትም ሆነ...