Saturday, December 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉአገራዊ መንገጫገጭ ያደበዘዘው ምርጫና ሒደቱ

አገራዊ መንገጫገጭ ያደበዘዘው ምርጫና ሒደቱ

ቀን:

በንጉሥ ወዳጅነው

ምርጫ 2013 እንደሚፈለገውም ባይሆን በቅስቀሳ፣ በዜጎች ምዝገባና በተለያዩ የምርጫ ተግባራት እንደነገሩ እየተከናወነ ይመስላል፡፡ በዚያው ልክ ምርጫው ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዳይካሄድ የተለያዩ መሰናክሎች እያጋጠሙ ነው፡፡ በእርግጥ በአገራችን ለውጥ ከተጀመረ ካለፉት ሦስት ዓመታት ወዲህ እየገጠሙን ያሉት ፈተናዎችና የፖለቲካ ውዝግቦች ናቸው፡፡ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ጉዞው ሥር በሚሰድበት ምዕራፍ ላይ ተጠናክረው እንቅፋት እየሆኑ ያሉት ጉዳዮችን ማየት ጠቃሚ ይሆናል፡፡

አገራችን በተለያዩ ጊዜያት ፈተና ሲገጥማት ነበር፡፡ ይነስም ይብዛም የሚገጥሟት ፈተናዎችና ችግሮችም የሚያደርሱትን ጉዳት እያደረሱ ታልፈዋል፡፡ በምንገኝበት ወቅትም ቢሆን ምንም እንኳን የለውጥ ጅምር መታየቱ እንደተስፋ ቢወሰድም፣ ለውጡ እያገጠመው ያለው ተግዳሮትና ፈተና ግን እስካሁን ሊያባራ አለመቻሉ ብዙዎችን በማሳዘን ላይ ይገኛል፡፡ በተለይ በእርስ በርስ ግጭት እያለቁ ያሉና በማንነታቸው ብቻ የጥቃት ሰለባ እየሆኑ ያሉ ዜጎች ጉዳይ፣ የድንበር ፍጥጫ (በተለይ ከሱዳን ጋር)፣ እንዲሁም በትግራይ ክልል ያለው አስከፊ ሁኔታ ዘላቂ መፍትሔ አለማግኘቱ አሳሳቢ እውነታዎች ሆነዋል፡፡

ከእነዚህ የማኅበረ ፖለቲካዊ ጫናዎች ተነጥለው የማይታዩት የዋጋ ንረት፣ የገበያ አለመረጋጋትና የብር የመግዛት አቅም መዳከም፣ በምጣኔ ሀብቱ መስክ የተጋረጡ ፈተናዎች ናቸው፡፡ በተለይ በከተሞች በምግብ እህል፣ በማጣፈጫና በቅመማ ቅመም፣ እንዲሁም በአልባሳትና መሰል የፍጆታ ዕቃዎች ላይ በፍጥነት የሚያሻቅብ ተለዋዋጭ ዋጋ እየታየ መሆኑ፣ የዝቅተኛው የኅብረተሰብ ክፍል ራስ ምታት በመሆን ላይ ነው፡፡ የኮንስትራክሽን ዘርፉን እግር ከወርች ሊይዘው የሚገዳደረው የሲሚንቶ፣ የብረትና መሰል ግብዓቶች ዋጋም (ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መንግሥት ችግሩን ለማቃለል እየተረባረበ መሆኑ የሚበረታታ ነው) ቢሆን ፊት ለፊት የሚታይ ጫና ፈጥሯል፡፡ እነዚህን ነባራዊ ሀቆች ደግሞ ከፖለቲካው አለመረጋጋትና አሻጥር ነጥሎ ለማየት አዳጋች መሆኑ ብቻ ሳይሆን፣ በመጭው ምርጫ ሒደት ላይ ጥላ እንዳያጠሉ የሚሠጉ ጥቂት አይደሉም፡፡

መጪው አገር አቀፍ ምርጫ ሊካሄድ የወራት ዕድሜ የቀሩት አገራችን በዚህ ዓይነት ነባራዊ ሁኔታ ላይ ቆማ መሆኑን ግን ካለ ልዩነት መናገር እንችላለን፡፡ በእርግጥ ለዴሞክራሲ ምኅዳሩ መስፋትም ሆነ ለምርጫው ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊነት እነዚህ ጭብጦች ቁልፍ ጉዳዮች ይሁኑ እንጂ፣ ወሳኝ ላይሆኑ ይችላሉ፡፡ በተለይ ከዚህ ቀደም በጫካና በስደት የነበሩ ፓርቲዎች በምርጫ እንዲሳተፉ መመቻቸቱ፣ የምርጫ ቦርድም ሕግጋቱን አስተካክሎ በአዲስ መልክ መደራጀቱና መዋቅሩን በተሻለ የሰው ኃይል፣ ሀብትና ዝግጁነት ያደራጀ መሆኑ፣ መንግሥትም እስከ መጨረሻው በጥብቅ የሥነ ምግባር መመርያ ታግዞ የምርጫውን ሒደት ከሄደበት፣ እንዲሁም ፓርቲዎች  ለዴሞክራሲያዊ ምርጫ ዝግጁነታቸውን በተግባር ካረጋገጡ በችግር ውስጥም ብንሆን የሚታይ የተስፋ ብርሃን አለ፡፡

እሱ ብቻ ሳይሆን ሕዝቡ ከብዙ ፈተናዎች እንደ መማሩ በስሜት ሳይሆን በሰከነ መንገድ ምርጫን ለመሳተፍ የተሻለ ዕድል እንዳለው መታወቅ አለበት፡፡ ለዚህም ይመስላል በበርካታ አካባቢዎች ዜጎች የምርጫ ካርድ ይዘው የሚመርጡትን አካል ለመወሰን እየተመዘገቡ የሚገኙት፡፡ ሚዲያዎች፣ ምሁራን፣ የሲቪክ ማኅበራትና መሰል ተቋማትም ቢሆን በዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ረገድ የወደቀባቸውን ታሪካዊ ኃላፊነት ተገንዝበው የድርሻቸውን መወጣት ከቻሉ ከፍተኛ አስተዋጾአቸውን ሊያበረክቱ ይችላሉ፡፡

ያም ሆኖ ጉዳዩ የሥልጣን ወሳኙ ዕርምጃ ምርጫ ነውና በተለይ ሰላም፣ መረጋጋትና የሕግ የበላይነትን የማረጋገጡ ተግባር ሊታለፍ የማይችል ነው፡፡ እናም ተቃና ሲባል እየተንጋደደ፣ ተስተካከለ ሲባል መልሶ እየተበላሻ ያለው የለውጥ ማግሥት ቀውስና ግጭት አገርን ክፉኛ እየጎዳ መሆኑ ላይ ጠንካራ መግባባት ሊፈጠር ይገባዋል፡፡ በተለይ በፀጥታ ኃይሉና በፍትሕ አካላት፣ እንዲሁም አገር በሚመራው ብልፅግና ውስጥ ባሉ ሰዎች ዘንድ አፍ ከልብ ሆኖ መሥራት ከተጎደለ መፍትሔ ሊመጣ አይችልም ብሎ ማመን ያስፈልጋል፡፡

እዚህ ላይ በጥቂት ጽንፈኞችም ይባል በፖለቲካ አኩራፊዎች እየተፈጸመ ያለውን ሕገወጥ ድርጊት ሁሉ ማስቆምና መከላከል ካልተቻለ፣ ሕዝቡንም ከችግር ለማውጣት አዳጋች ነው፡፡ ከዚህ ባሻገር በምርጫ ሒደቱም ላይ ጨፍጋጋ ስሜት በማጥላት ትልቁን ተስፋችንን እንዳያጨልምብን የሚሉ አስተያየት ሰጭዎች ጥቂት አይደሉም፡፡ እናም አገር ወዳድና ሰላም ፈላጊ ዜጎችም ቢሆኑ ለሕግ የበላይነት መከበር መትጋት ይኖርባቸዋል፡፡

በተለይ አገራችን በፖለቲካ ተቸንካሪዎችና አክራሪ ብሔርተኞች ወዳልተፈለገ ግጭትና ትርምስ ገብታ መቆየቷ አንሶ፣ አሁንም ችግሩ እንዲቀጥል መፍቀድ ከቀውስ ሊያወጣን አይችልም፡፡ በዚህ ረገድ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር በቅርቡ እንዳወጣው መረጃ ከወራት በፊት በትግራይ ክልል የሕወሓት ጁንታ በዕብሪት የለኮሰው ጦርነት፣ በዚያም በዚህም ብዙዎችን ያላግባብ ሕይወታቸው ተቀጥፏል፣ አካል አጉድሏል፣ ከፍተኛ የአገር ሀብት አውድሟል፣ ከሁሉ በላይ የአገርን ገጽታና የትውልድን ታሪክ ለማዳከመ ቀውስ ፈጥሯል፡፡ እነዚህን የቀውስ ጠባሳዎች ለማረም የሚወስደው ሀብት፣ ድካምና ውጣ ውረድ ቀላል እንደማይሆንም የታወቀ ነው፡፡ አሳዛኙ ነገር አሁንም ከችግሩ ለመውጣት በሚደረገው ርብርብ ውስጥ ካለፍንበት አስቸጋሪ የፖለቲካዊ ኢኮኖሚ ውጣ ውረድ ጋር የተጋመዱ፣ ከአስተሳሰብ ትግል ይልቅ አሁንም እልህና ጦረኝነት የሚበዛባቸው የማይበጁ ሙከራዎች በዚያም በዚህም መታየታቸው ነው፡፡ በተለይ በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ በተደጋጋሚ፣ በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋና ኦሮሚያ ልዩ ዞን በቅርቡ፣ እንዲሁም በቤንሻንጉል ጉምዝ መተከል አካባቢ ባለማቋረጥ እየተፈጸሙ ያሉ ድርጊቶች እጅግ አስነዋሪ ብቻ ሳይሆኑ፣ በተቀናጀ ጥረት እንዲስተካከሉ ካልተደረገ ምርጫውን አይደለም አብሮ መኖርንም የሚፈታተኑ ናቸው፡፡

በእርግጥ እነዚህ ወቅታዊ ፈተናዎች የማይታለፉና ድቅድቅ ጨለማ እንዳልሆኑ የሚናገሩ፣ ብዙ አርቆ አሳቢዎችና በቀላሉ የማይሰበሩ ልቦች እንዳሉ ዕሙን ነው፡፡ ለዚህም ነው ያለንበትን ሁኔታ እንደ መቼዎቹም ፈታኝ ክስተቶች በመቁጠር፣ አገራችን በጀግኖች ልጆቿና በአገር ወዳድ ዜጎቿ ጥረት ከጊዜያዊ ችግሮቿ ወጥታ፣ ወደ መስመሯ ትገባለች የሚሉ የለውጥና የተስፋ ኃይሎች በዚያም በዚህም ድምፃቸውን እያሰሙ የሚገኙት፡፡ ያም ሆኖ ግን መንግሥት ለእገሌ ወይም ለእከሊት ሳይል ጠንካራ ሕግ የማስከበር ሥራውን መወጣት ግድ ይለዋል፡፡

ኢትዮጵያ አሁን በጀመረችው ልክ ብቻ ሳይሆን ጠንክሮ ከተሠራም የህዳሴ ጉዞዋን ትቀጥላለች እንጂ አትወድቅም የሚለው ተስፋም የብዙዎች ቢሆንም፣ እንደ አገር ተስፋ ለማስቆረጥ የሚሠሩ የውጭ ጠላቶችና የውስጥ ቦርቧሪዎች ሴራ መገንዘብም ጠቃሚ ይሆናል፡፡ በተለይ የዓባይን ተፈጥሯዊ ውኃ ለመጠቀም በምንረባረብበት በዚህ ወሳኝ ምዕራፍ፣ ግብፅና ሱዳን በተለያየ መንገድ በአገር ላይ ተፅዕኖ ለማድረስ እንደሚሯሯጡ ነው መንግሥትም ደጋግሞ ያረጋገጠው፡፡ ስለሆነም ሁሉንም ወቅታዊ ፈተናዎች አሸንፎ በድል ለመሻገር በዕውቀት፣ በአገር ወዳድነትና በተባበረ ክንድ መረባረብ፣ ምርጫውን በታለመለት ግብ ለመፈጸም ብቻ ሳይሆን አገራችንንም ለማስቀጠል ጠቃሚ ይሆናል፡፡

በእርግጥ አገር ከፓርቲም ሆነ ከምርጫ በላይ ነች፡፡ እናም ወዲም ተባለ ወዲህ ሁሉም ነገር አገርን በሰላምና በመረጋጋት ከማቆም የሚመነጭ ነው መሆን ያለበት፡፡ ለዚህም ሲባል የቂምና የበቀል፣ የፀብና የጥላቻን ግንብ እያፈረሱ፣ በፍቅር፣ በይቅርታና በአብሮነት መንፈስ ወደሚፈለገው ዓላማ ለመድረስ ፖለቲከኞች ብቻ ሳይሆኑ፣ ሕዝቡ የወደቀበት ታሪካዊ ኃላፊነት ከፍተኛ ነው፡፡ እናም የዘንድሮውን ምርጫ ስናስብ በለውጥ ማግሥት ፈተናዎች ሳንገደብ፣ ዘላቂውን የዴሞክራሲ አገራዊ ጉዞ በተስተካከለ ሜዳ ላይ ለማብቀል መሥራት ግድ ይላል፡፡ መትጋትም ያስፈልጋል፡፡

እውነት ለመናገር ሁከት፣ ግጭትና በጦርነት የፖለቲካ ግብን ለማሳካት የሚያስቡ ኃይሎች የት ለመድረስ ይሆን የሚፋለሙት የሚለው ጥያቄ በሁሉም በኩል መታየት ያለበት ነው፡፡ ዓለም በሠለጠነበት፣ መነጋገርና መደማመጥ እየጎላበት በመጣበት፣ ጦርነት አገርን እንደሚያወድም እነ ሶሪያና የመን ጥሩ ምሳሌ በሆኑበት፣ ወዘተ በዚህ ጊዜ ነፍጥ አንስቶ መባላት ምን ሊያስገኝ ይችላል፡፡ በጦርነት አሸናፊ መሆን ባይቻልም አሽንፎ ሥልጣን ልያዝ፣ ክልል ልገንጥል፣ ወዘተ. ቢባልስ እስከ መቼ ከጦርነት መውጣት ይቻላል ብሎ መመርመር ካልተቻለ ከጭቃው መውጣት አይቻልም፡፡

በመሠረቱ መንግሥት እንደሚለው ካለፉት ሦስት ዓመታት ወዲህ እንደ አገር በአንድ በኩል ቀደም ባሉት ሦስት አሥርት ዓመታት የተጀመረውን ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት አጠናክሮ ለማስቀጠል እንዲቻል፣ በሌላ በኩል በአገር ግንባታ ሒደቱ እንቅፋት የሆኑ ተግዳሮቶች የተለዩበት ጊዜ በመሆኑ፣ በሌላ በኩል እንደ አገር ከተመጣበት ውጣ ውረድ አኳያ የተፈጠረውን ማኅበረ ፖለቲካዊ መፈላቀቅና የተዛባ ጉዞ ለማረም የሚቻልበትን ብልኃት ለመቅረፅ ነው መንግሥትና ሕዝብ ማሰብ ያለባቸው፡፡ ይሁንና በዚህ ረገድ ሁሉም የፖለቲካና የምርጫ ተዋንያን ምን ያህል እየተንቀሳቀሱ ነው የሚለውን ጥያቄ እያንዳንዱ ወደ ራሱ እየወሰደ መጠየቅ ግድ ይለዋል፡፡

በምንገኝበት ደረጃ ትልቁ ጉዳይ ምርጫን በታሰበው ዕቅድ ልክ ማከናወን ብቻ ሳይሆን፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ የተያያዘውን የዕድገት ጉዞ ለማስቀጠልና የጠንካራ ኅብረ ብሔራዊ አገር ግንባታ የማስፋት ሥራም ሊዘነጋ አይገባም፡፡ ይሁንና ዜጎች ከላይ እስከ ታች እንዳቅማቸው ደፋ ቀና በሚሉበትና የጋራ ርዕያቸውን ዕውን ለማድረግ በሚታትሩበት ወቅት ኅብረታቸው ያስቀናቸው ኃይሎች እንዲነጣጠሉ፣ ቃል ኪዳን የተሳሰሩበትን ሕገ መንግሥት እንዳሻቸው እንዳይዘነጣጥሉትም መታገል የመንግሥትና የሕዝብ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን፣ የፖለቲካ ኃይሎችም ተግባር ሊሆን ይገባል።

ይበልጥ ሊተሳሰሩ እንጂ ፍፁም ሊለያዩ ፈቃዱም ፍላጎቱም የሌላቸውን ብሔሮችና ብሔረሰቦችን ለመነጣጠልና ኢትዮጵያን ለመበታተን ማሰብ ሊከሽፍ የሚችለው ሁሉም የድርሻውን መወጣት ሲቻል ብቻ ነው፡፡ አሁን በውጭና በአገር ውስጥ የሚገኙ ጽንፈኛ የዳያስፖራ አባላትና የጁንታው አንዳንድ ደጋፊዎች ‹‹አገሪቱ ካልተበታተነች የትግራይ ሕዝብ ጥቅም አይከበርም››፣ «እገሌ ብሔረሰብ ከዚህ ክልል ካልወጣ አንለማም»… በሚል እሳት እየቆሰቆሱ መሆናቸው የሚያስገርም ነው። ለማንም የማይበጅ አደገኛ መንገድ መሆኑንም ሊገነዘቡት ይገባል፡፡

የያዙት ኋላ ቀር አስተሳሰብ የኢትዮጵያ ብሔሮችና ብሔረሰቦችን በልዩነት ውስጥ የሚኖራቸውን አንድነት ለማጠናከር በሚያደርጉት ጉዞ ላይ እንደ አደጋ ተቆጥሮም የጋራ ትግል ሊደረግበት ይገባል፡፡ ይህን ማድረግ ደግሞ ብልፅግናን ወይም ሌላን ፓርቲ መደገፍ ሳይሆን አገርን ማዳን፣ ሕዝብን መታደግ ነው፡፡ ይህንን መላው የአገራችን ዜጎች በትኩረት እንዲገነዘቡት ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ስለምርጫ ዴሞክራሲያዊነትና ሰላማዊነት ማሰብ የሚቻለውም ከዚህ ዓይነቱ አስተሳሰብ መቃናትና መስተካከል በኋላ ቢሆን ይበጃል፡፡

በመሠረቱ የዜጎችን ደኅንነት፣ ተንቀሳቅሶ የመሥራትና በአመቻቸው ቦታ የመኖር መብት መጋፋት ኢሕገ መንግሥታዊ ነው፡፡ ክቡር የሆነውን የሰው ልጅ፣ ያውም አነሰም በዛም በአንድ አገር ለዘመናት ተሰናስሎ የኖረን ማኅበረሰብ ሽፋን እያደረጉ የሚፈጸምና የሚሠራ የፖለቲካ ድራማማ መቆም ያለበት ከወዲሁ ነው፡፡ አንዳንድ ኃይሎች ጥያቄያቸውን እንኳን ሕገ መንግሥታዊ ዕውቅና ያገኘ መሆኑን ሳያረጋግጡ፣ በፊት ለፊትም በህቡዕም የሚፈጸሙት ወንጀል በሕግ ካልተዳኘ ደግሞ፣ እንኳንስ ምርጫን በሰላም ማከናወን የአገር ህልውናንም ለአደጋ ማጋለጡ አይቀርም፡፡ ስለሆነም ከውጭ ተገዳዳሪዎች በላይ የአኩራፊ ፖለቲከኞች፣ የአቋራጭ ሥልጣን ሕልመኞችና የጽንፈኛው ዳያስፖራ አስተሳሰብ አገሪቱን የሚያጠፋ፣ ሕዝብን ወደ ዕልቂት የሚገፋ መጥፎ ሐሳብ ያዘለ፣ ለኢትዮጵያውያን የማይበጅ መሆኑን በጋራ ማጋለጥና መታገል የሁሉም ግዴታ ሊሆን ይገባል።

ብዙዎች እንደሚስማሙበት በኢትዮጵያ የሚገኙ ሁሉም ሕዝቦች ምርጫውንም ሆነ ቀድሞ ያጡትን መብትና ጥቅም ራሳቸው በጋራ ባፀደቁት ሕገ መንግሥት አማካይነት ተጎናፅፈውታል። ራሳቸውን በራሳቸው ከማስተዳደርም በተጨማሪ፣ በአገራቸው ሀብት እኩል የመጠቀምና በእኩልነት የመኖር መብታቸውና ሰላማቸው በመጠበቅ፣ ልማታቸውን በማፋጠንና ዴሞክራሲያቸውን በማጎልበት ያረጋግጡታል እንጂ በሌላ የከሰረ መንገድ ሊቀሰቅሱት አይሹም፡፡ ሕገ መንግሥቱ ያላሟላቸው፣ የጎደሉና ያዛነፋቸው አናቅፅትንም ቢሆን በሠለጠነ መነገድና በመደማመጥ ማስተካከል የሚቻለው ምንጊዜም ሰላምና ዴሞክራሲን ምርኩዝ አድርጎ መራመድ ሲቻል ብቻ ነው፡፡

ከዚህ አንፃር መላው የፖለቲካ ኃይሎች፣ የምርጫ ተዋናዮችና የዴሞክራሲ ተቋማት ከሰላምና ዴሞክራሲያዊነት የወጡና የተዛነፉ አስተሳሰቦችን እንደማይቀበሉ ማረጋገጥ አለባቸው፡፡ ለአገራቸውና ለጋራ ሕገ መንግሥታቸው ታማኝና ዘብ የሚቆሙ መሆናቸውንም ሊያረጋግጡት ይገባል የሚሉ አስተያየት ሰጪዎች የቃል ኪዳን ሰነድ እስከ መፈራረም ሊሄዱ ይገባል ነው የሚሉት። የአገራችን ሕዝቦችም ቢሆኑ እኩልነታቸውን፣ አንድነታቸውንና በጋራ ለልማትና ዕድገት መቆማቸውን በተግባራዊ ተሳትፏቸው ማጠናከር፣ ለሰላምና ዴሞክራሲ ዘብ መቆም ይኖርባቸዋል። ይህ ነው እውነተኛውን የአገር ለውጥ ዕውን የሚያደርገው፡፡

ኢትዮጵያዊያን ኅብረታቸውና አንድነታቸው እየገዘፈ የሚመጣው በእስከ ዛሬው ትግላቸው ያበበውን ዴሞክራሲያዊ መብት ጠብቀው እርስ በራሳቸው የጎደላቸውን ለማሟላት በጋራ መምከር፣ በጋራ መወሰንና መተግበር ሲችሉ መሆኑም ለአፍታም ሊዘነጋ አይገባውም። በጋራ ያፀደቁትን ሕገ መንግሥትን  በጋራ በመጠበቅ በእርሱም አማካይነት በእጃቸው ያስገቧቸውን መብቶቻቸውን በሌላ ኃይል ላለመነጠቅ መጠበቅ  ሲችሉም ነው የሚለውን የኖረ እምነት ጠብቆ መገኘትም፣ የምርጫው ሒደት ካጠላበት ጭጋግ እንዲላቀቅ ይረዳል።

እዚህ ላይ በልዩ ትኩረት መጠቀስ ያለበት ከ50 በመቶ የሕዝቡን ቁጥር የሚይዘው ወጣቱ ኃይል ነው፡፡ ይህ ትኩስና አገር ተረካቢ ኃይል ለዘንድሮው ምርጫ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊነት ብቻ ሳይሆን፣ የአገሩንም ህልውና ለመጠበቅ ታሪካዊ ድርሳን ያረፈበት ነው፡፡ ይሁንና በወጣትነት ውስጥ እጥረት የሚታይበት አንዱና ዋንኛ ነገር ቢኖር ልብ ነው፡፡ ማስተዋልና አዙሮ ማየት ከነገሮች ጀርባ ያሉትን ረቂቅ እውነታዎች ረጋ ብሎ ለመመርመር አለመትጋት፣ የነገሮችን የላይ ገጽታ (Words at their Face Value) ብቻ እያዩ ወደፊት ምን ሊያስከትሉ እንደሚችሉ ከወዲሁ አርቆ ለማየትና ለመጠንቀቅ ትኩረት አለመስጠት… ይገኙበታል፡፡ እነዚህን ቀድሞ በመረዳት በቡድንም ሆነ በጋራ ለአገርና ወገን የሚጠቅመውን ማድረግ ነው የሚያስፈልገው፡፡

ለማጠቃለል ያህል ዘንድሮ የሚካሄደው የአገራችን ብሔራዊና ክልላዊ ምርጫ ከፍተኛ ተስፋ፣ በጀትና ትኩረት የተሰጠው ነው፡፡ በፖለቲካ ኃይሎች ተሳትፎና በመረጃ ነፃነት ሥነ ምኅዳር ሲታይም ከመቼውም ጊዜ የተሻለ ዕድል ተፈጥሮለታል ቢባል ግነት የለውም፡፡ የሕጎቹ መሻሻል፣ የምርጫ ቦርድ መጠናከርና መሰል ውጥኖችም በበጎ ተወስደው፡፡ አሁን ቀሪው ተግባር የሚሆነው ሒደቱ ላይ ያጠላውን ሥጋት ፈጥኖ መግፈፍና ሕግ ማስከበር፣ ሁሉም የፖለቲካ ኃይሎችና ሕዝቡም ሕግና ሥርዓት አክብረው ለሰላማዊና የዴሞክራሲያዊ ምርጫ እንዲሠለፉ ማድረግ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ሁላችንም ኃላፊነታችንን ከወዲሁ መወጣት ይኖርብናል፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመቃወም ነፃነት ውዝግብ በኢትዮጵያ

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የሾላ አካባቢ...

የሲሚንቶን እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አጓጊ ጥረት

በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆን ከሚጠቀሱ ምርቶች...

የብሔር ፖለቲካው ጡዘት የእርስ በርስ ግጭት እንዳያባብስ ጥንቃቄ ይደረግ

በያሲን ባህሩ በሪፖርተር የኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም “እኔ...