የበጎ አድራጎትና ማኅበራት አዋጅ የተሻረበት 2011 ዓ.ም. ለሲቪል ማኅበራት ድርጅቶች አዲስ ጅማሮ እንደሆነ ሲነገር ቆይቷል፡፡ ለዚህም ምክንያቱ አሳሪ ከሚባሉ የአገሪቱ ሕጎች አንዱ ነው የሚባለው የበጎ አድራጎትና ማኅበራት አዋጅ ተሽሮ፣ ማኅበራትን ሊያሠራ የሚችል ሕግ በምትኩ ፀድቋል፡፡ የአገራዊ ሪፎርሙ አካል የሆነው ይኼ የሕግ ማሻሻያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ወደ ሥልጣን መምጣታቸውን ተከትሎ የተደረገ ሲሆን፣ የመገናኛ ብዙኃንና የሲቪል ማኅበረሰቦች የሕግ ማዕቀፍ ማሻሻያዎች ከኢትዮ ኤርትራ ዕርቅ ጋር ተዳምሮ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚያው ዓመት የተሰጠውን የኖቤል የሰላም ሽልማት ሊያሸንፉ ችለዋል፡፡ ከሕጉ ከሚመነጩ የሲቪል ማኅበረሰቦች ገደቦች መካከል እነዚህ ድርጅቶች በልማት እንቅስቃሴዎች እንጂ፣ በሰብዓዊ መብቶች ላይ እንዳይሳተፉ መደረጋቸውና ከውጭ አገር የሚያገኙት የገንዘብ ምንጭ ላይ የተቀመጠው ገደብ ይገኙበታል፡፡ የሕጉ መቀየርን ተከትሎ በ2013 በጀት ዓመት የመጀመርያ ግማሽ ዓመት 1,805 የሲቪል ማኅበራት በድጋሚ እንደተመዘገቡና የ1,300 አዲስ ማኅበራት ምዝገባ መከናወኑን የሲቪል ማኅበራት ኤጀንሲ አስታውቋል፡፡ አሁን በአገሪቱ የሚንቀሳቀሱ የሲቪል ማኅበራት ቁጥር ወደ 3,200 ደርሷል፡፡ የእነዚህ ሲቪል ማኅበራት ድርጅቶች መንሰራፋት ኅብረተሰቡ እንዲነቃ፣ የዴሞክራሲ ባህል እንዲሰፋና ለድምፅ አልባው ድምፅ ለመሆን ያስችላቸዋል የሚል ተስፋ ተጥሎባቸው ነበር፡፡ የሕግና የአሠራር ማነቆዎች የተወገዱላቸውም ቢሆንም ቅሉ፣ ሲቪል ማኅበራት ከራሳቸው በሚመነጩ ተግዳሮቶች ውስጥ ይገኛሉ፡፡ በዚህ ላይ በቀጣዩ ጠቅላላ ምርጫ ከፍተኛ ሚና እንዲጫወቱ ይጠበቅባቸዋል፡፡ እነዚህንና መሰል የሲቪል ማኅበራት ድርጅቶችን የተመለከቱ ጉዳዮች ብሩክ አብዱ ከክርስቲያን የረድኤትና ልማት ማኅበራት ጥምረት፣ (ሲሲአርዲኤ) ዋና ሥራ አስፈጻሚ ንጉሡ ለገሰ (ዶ/ር) ጋር የሚከተለውን ቆይታ አድርጓል፡፡ ንጉሡ (ዶ/ር) ከሲሲአርዲኤ የሥራ አስፈጻሚ አባልነታቸው በተጨማሪ፣ ሲቪል ማኅበራት ለምርጫ የፈጠሩት ቅንጅት ቦርድ አባል፣ የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንትና የኢትዮጵያ የሲቪል ማኅበራት ኤጀንሲ የቦርድ አባል ናቸው፡፡
ሪፖርተር፡- ለበርካታ ዓመታት በተግባር ላይ የነበረው የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማኅበራት አዋጅ በ2011 ዓ.ም. በሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች አዋጅ መተካቱን ተከትሎ፣ ለሲቪል ማኅበረሰቦች መስፋፋትና ለእንቅስቃሴያቸውም መጠናከር በር ከፋች ይሆናል ተብሎ ተስፋ ተጥሎበት ነበር፡፡ በእርግጥ በዚህ ሳቢያ 1,805 ድርጅቶች በአዋጁ መሠረት ዳግም ምዝገባ እንዳደረጉና 1,300 አዳዲስ ተቋማት እንደተመዘገቡ የሲቪል ማኅበራት ኤጀንሲ በ2013 የግማሽ ዓመት ሪፖርቱ ላይ ገልጿል፡፡ ዕውን እነዚህ ድርጅቶች አዋጁ የሰጣቸውን ዕድል ተጠቅመው የበዙትን ያህል ጉልህ ሚና እየተጫወቱ ነው ማለት ይቻላል?
ንጉሡ ለገሰ (ዶ/ር)፡- እንደምናውቀው የቀድሞው የበጎ አድራጎትና ማኅበራት አዋጅ ሲቪል ማኅበረሰቡን ልምሻ ያስያዘ ሲሆን፣ ሁሉንም እንቅስቃሴያቸውን ገድቦ ነበር፡፡ በርካታ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች በተለይም በሰብዓዊ መብቶች ላይ የሚሠሩት፣ በአዋጁ ምክንያት ቢሯቸውን ዘግተውና አገር ጥለው እንደ ሄዱ የቅርብ ጊዜ ታሪክ ነው፡፡ አሁን አዲሱ አዋጅ ከወጣ ሁለት ዓመት ከግማሽ ቢሆነው ነው፡፡ አዲሱ አዋጅ ጥሩ ጥሩ ለውጦችን ያመጣ ሲሆን፣ ሲቪል ማኅበረሰቡም በንቃት መሳተፍ እንዲችል ዕድል የከፈተ ነው፡፡ ይሁንና ለአሥር ዓመታት ታግቶ የነበረው የሲቪል ማኅበረሰብ፣ ሕጉ ስለወጣ ብቻ ወዲያውኑ ንቁ ሆኖ መንቀሳቀስ ስለማይችል ጊዜ መውሰዱ አይቀርም፡፡ ሠራተኞቻቸው የለቀቁባቸው በመሆኑና ያሉትንም ሆነ የአዳዲሶቹን ሠራተኞች አቅም በሥልጠናና በተለያዩ ድጋፎች ማጎልበት ይኖርባቸዋል፡፡ ይህም አዲስ በተፈቀዱላቸው የሰብዓዊ መብት ጥበቃና የማኅበረሰብ ማጎልበት ተግባራት ላይ ለመሰማራት ይረዳቸዋል፡፡ እነዚህን ማድረግ ነው በዋናነት ከእኛ የሚጠበቀው፡፡ አሁን በወጣው አዋጅ መሠረት በሰብዓዊ መብቶች ጥበቃ ላይና ማኅበረሰቡ ንቁ ሆኖ ጥያቄ የሚጠይቅ፣ መብትና ግዴታውን የሚያውቅ እንዲሆን ማንቃት እንችላለን፡፡ ስለዚህ ይኼን ለማድረግ በርካቶች ራሳቸውን እያዘጋጁ፣ የሰው ኃይል እያደራጁና ሥልጠና እየሰጡ ነው፡፡ ምክንያቱም ይኼ ዘርፍ ለኢትዮጵያ የሲቪል ማኅበረሰቦች አዲስ ነው፡፡
አሁን ባለው አስተሳሰብ የአገልግሎት አቅርቦቶችም ቢሆኑ ከሰብዓዊ መብቶች ጋር መተሳሰር እንዳለባቸው ነው፡፡ ባለፉት አሥር ዓመታት በነበሩባቸው ገደቦች ምክንያት ግን ከአዲሱ ሁኔታ ጋር በፍጥነት ራሳቸውን ማጣጣም አልቻሉም፡፡ አሁን ወደ መስመር እየገባን ስለምንገኝ ለወደፊት ከሲቪል ማኅበረሰቡ ንቁ ተሳትፎ የሚኖርበት እንደሚሆን ተስፋ አለኝ፡፡ እስካሁን ድረስ የዳግም ምዝገባና የዝግጅት ወቅት ነበር፡፡ ለምሳሌ እስካሁን ድረስ በሲቪል ማኅበረሰቦች ኤጀንሲ ተመዝግበዋል ተብለው የሚታሰቡ ድርጅቶች 3,000 ገደማ ይሆናሉ ተብሎ ነበር፡፡ ይሁንና ዳግም ምዝገባ ሲባል የተመዘገቡት 1,800 ብቻ ናቸው፡፡ የተቀሩቱ የት ገቡ? ማንም አያውቅም፡፡ ከስረውም ከሆነ ለኤጀንሲው ማሳወቅ ነበረባቸው፡፡ ሌሎቹ ደግሞ ሳያሳውቁ አገር ጥለው ተሰደዋል፡፡ እኛ እንደ ሲሲአርዲኤ 248ኛ ጠቅላላ ጉባዔያችንን ስናደርግ ለአባላቶቻችን ዳግም ምዝገባ እንዲያደርጉ ነገርናቸው፡፡ ምክንያቱም ኤጀንሲው ሳያውቃቸው የእኛ አባል ሆነው መቀጠል አይችሉምና፡፡ አሁን በርካቶቹ ቢሮ እያደራጁ ሲሆን፣ የሰው ሀብት እያደራጁ የዝግጅት ምዕራፍ ውስጥ ይገኛሉ፡፡ ነገር ግን አዋጁ ሁሉንም ነገር ክፍት ያደረገ ሲሆን፣ አንቀጽ 85 የሲቪል ማኅበረሰቦች ምክር ቤት እንዲመሠረት የፈቀደ ነው፡፡ በዚህም መሠረት ታኅሳስ 22 ቀን 2013 ዓ.ም. ይኼንን ምክር ቤት አቋቁመን 21 የአስፈጻሚ ኮሚቴ አባላትን መርጠናል፡፡
ሪፖርተር፡- ስለዚህ አዋጁ ይህን ያህል ምኅዳሩን የከፈተላችሁ ቢሆንም፣ እነዚህ ማኅበራት በሙሉ አቅማቸው ወደ ሥራ መግባት ላይ ገደብ አለባቸው ማለት ይቻላል?
ንጉሡ ለገሰ (ዶ/ር)፡- በእርግጥ ላለፉት አሥር ዓመታት አብረውን የነበሩ ችግሮቻችን በአንዴ ሊቀረፉ አይችሉም፡፡ የፋይናንስና የሰው ኃይል ውሱንነቶችን ማለፍ ይኖርብናል፡፡ ይኼንን በአጭር ጊዜ መወጣት ለጥቂቶቹ ካልሆነ በስተቀር ለበርካቶች ከባድ ነው፡፡ ለምሳሌ ሲሲአርዲኤ 436 አባላት የሆኑ የሲቪል ማኅበረሰቦች ያሉት ሲሆን፣ ለአባላቶቻችን ገንዘብና ሌሎች ሀብቶችን እናሰባስብላቸዋለን፡፡ ምክንያቱም እኛ እንደ እነሱ በፕሮጀክት ትግበራና በሌሎች መስኮች አንፎካከርም፡፡ የእኛ ሥራ ሠራተኞቻቸውን በማሠልጠን ፍላጎት ባለበት ቦታ አቅም መገንባት ነው፡፡ በርካቶች ደግሞ ለዘርፉ አዲስ ገቢዎች ናቸው፡፡ ነገር ግን አሁን መነቃቃት ጀምረዋል፡፡
ሪፖርተር፡- ሲቪከስ (CIVICUS) የተባለ ዓለም አቀፍ የሲቪል ማኅበረሰቦች ጥምረት በመጋቢት ወር ይፋ ባደረገው ሪፖርቱ፣ የኢትዮጵያ የሲቪል ማኅበረሰቦች ምኅዳር የተጨቆነ (ሪፕረስድ) ነው ይለዋል፡፡ አዋጁ ምኅዳሩ ክፍት እንዲሆን ቢፈቅድም እንዲህ ያለ የግምገማ ውጤት ሊታይ የቻለው፣ የቀድሞ ተግዳሮቶች መልካቸውን ቀይረው አሁንም ድረስ የሚታዩ ስለሆነ ነው ወይስ ሌላ ምክንያት አለው ይላሉ?
ንጉሡ ለገሰ (ዶ/ር)፡- እውነት ለመናገር ላለፉት አሥር ዓመታት የነበሩ ችግሮቻችን አሁን የሉም፡፡ ምንም ገደብ የለብንም፡፡ ያሉብን ገደቦች ከሲቪል ማኅበረሰቡ ወገን ያሉ ናቸው፡፡ በሲቪል ማኅበረሰቦች ኤጀንሲ ላይም ሆነ በሌሎች የመንግሥት ተቋማት ላይ ቅሬታ የለንም፡፡ አሁን ያሉብን ችግሮች ከሰው ኃይልና ከገንዘብ አቅም ጋር የተገናኙ ናቸው፡፡ ከዚህ ውጪ ደግሞ እነዚህ ድርጅቶች ራሳቸውን ከአዲሱ ሁኔታ ጋር ማጣጣም ይኖርባቸዋል፡፡ ይኼንን ማድረግ ለበርካታ ሲቪል ማኅበረሰቦች ጊዜ ወሰደባቸው፡፡ አሁን ምንም ገደብ የለብንም ማለት እችላለሁ፡፡ የሲቪል ማኅበረሰቡም ይኼንን ዕድል ተጠቅሞ መንቀሳቀስ ይጀምራል ብዬ አምናለሁ፡፡
ሪፖርተር፡- ስለዚህ ሲቪከስ (CIVICUS) ያወጣው ሪፖርት ውስጥ የተጠቀሰው ግምገማ፣ ከሕግና ከመንግሥታዊ አሠራር ገደቦች የመነጨ ሳይሆን ከሲቪል ማኅበረሰቦች ከራሳቸው የመጣ ነው እያሉኝ ነው?
ንጉሡ ለገሰ (ዶ/ር)፡- አዎን! አሁን እኛን የሚገድበን ምንም ዓይነት የሕግ ማዕቀፍም ሆነ የመንግሥት አሠራር የለም፡፡ እንዳልኩት በሰው ኃይልና በፋይናንስ ራሳችንን በማጎልበትና ከአዲሱ የሕግ ማዕቀፍ ጋር ራሳችንን ማጣጣም ላይ የራሳችን ውሱንነቶች አሉን፡፡ ይኼንን ማድረግ ደግሞ ጊዜ ይጠይቃል፡፡ በእነዚህ ምክንያቶች እንቅስቃሴያችን መዘግየት ቢታይበትም፣ አሁን በርካቶች መስመር እየያዙ ነው፡፡ እኛም የሲሲአርዲኤ አባላትን እንዴት ከማኅበረሰቡ ጋር እንደሚነጋገሩና ምን መሥራት እንዳለባቸው ባለሙያ ቀጥረን ሥልጠና እየሰጠናቸው ነው፡፡
ሪፖርተር፡- እርስዎ እንደጠቀሱልኝ ሲቪል ማኅበረሰቦች በአዋጁ በተፈቀደላቸው መሠረት ምክር ቤት አቋቁመዋል፡፡ ከዚያ አስቀድሞ ደግሞ ሲቪል ማኅበረሰቦች መድረክ ፈጥራችሁ ትንቀሳቀሱ ነበር፡፡ ምክር ቤቱና ፎረሙ ከላይ የጠቀሱልኝን የሲቪል ማኅበረሰቦችን ችግሮች ለመቅረፍ ምን ሚና አላቸው?
ንጉሡ ለገሰ (ዶ/ር)፡- ፎረሙን የመሠረትነው 52 ማኅበራት ነን፡፡ ይኼም አባላቶቹ በጋራ ጉዳዮቻቸው ላይ ተሰባስበው እንዲሠሩ የሚያስችል ነው፡፡ ፎረሙ 13 አባላት ያሉት የዲሬክተሮች ቦርድ አለው፡፡ ቦርዱ የሚመራው ፎረም ምክር ቤቱ እስከሚመሠረት ድረስ እንደ መሸጋገሪያ ነው ያገለገለው፡፡ ፎረሙ በቆየባቸው ጊዜያት አገራዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ የተለያዩ መግለጫዎችን በመስጠት ከፍ ባለ የፖሊሲ ተፅዕኖ ላይ ትኩረት አድርገን ሲሠራ ነበር፡፡ አዲሱ የሲቪል ማኅበራት አዋጅ በ2011 ዓ.ም. መፅደቁን ተከትሎ ወደ ምክር ቤት እንዲያድግ ሆነ፡፡ በዚህም መሠረት የመመሥረቻ ጽሑፍ፣ የመተዳደሪያ ደንብና የስትራቴጂ ዕቅድ ማዘጋጀት ስለነበረብን የዝግጅት ጊዜው ረዥም ነበር፡፡ እያዳንዱን ሰነድ ያዘጋጁትም የፎረሙ አባላት በሦስት ግብረ ኃይል ተከፍለው ነበር፡፡ እነዚህ ሰነዶች ከተገመገሙ በኋላ ከሲቪል ማኅበራት ኤጀንሲ ጋር በመሆን የጋራ ኮሚቴ ተቋቋመ፡፡ ምክንያቱም መሥራች ጉባዔ ለማድረግ የመጀመርያውን ጥሪ የሚያስተላልፉት እነሱ ናቸውና፡፡ ነገር ግን የተለያዩ ፍላጎቶች በመኖራቸው አንዳንዴም ወደ ውዝግብ ስላመሩ ምክር ቤቱን ማቋቋም ከተጠበቀው በላይ ወስዷል፡፡ ሆኖም ለምሥረታው የሚያስፈልጉ 300 አባላት ስለነበሩ መሥራች ጉባዔውን የሚያሟሉት፣ ከጠቅላላ 3,000 ሲቪል ማኅበረሰቦች መመረጥ ነበረባቸው፡፡ ጥምረት የመሠረቱትን መወከል ቀላል ቢሆንም፣ ጥምረት ውስጥ ያልገቡና በግላቸው የሚንቀሳቀሱ 1,750 አባላትን መወከል ያስፈልግ ነበር፡፡ ነገር ግን ቢያንስ 1,000 አባላት ቢገኙ ተብሎ ጥሪ ተደርጎ 250 ብቻ ተገኝተው ምክር ቤቱ ተመሠረተ፡፡ በዚህም ፎረሙ ወደ ምክር ቤት ሽግግር አደረገ፡፡
ሪፖርተር፡- ፎረሙን ወደ ምክር ቤት ማሸጋገርና ምክር ቤቱን መመሥረት ላይ የታዩ ልዩነቶች ምን ነበሩ?
ንጉሡ ለገሰ (ዶ/ር)፡- መልካም፡፡ ፎረሙ የተመሠረተው ሲቪል ማኅበረሰቡ በጋራ ተሰባስቦ ለጋራ ፍላጎቶቻቸው የሚኖሩበትና ለጋራ ጥቅማቸው የሚቆሙበት እንዲሆን ታስቦ ነው፡፡ ከፎረሙ መመሥረት አስቀድሞ የማስተባበር ሥራውን ያከናውን የነበረው ሲሲአርዲኤ ነበር፡፡ ፎረሙ ሲመሠርት እኛም የዚያ ፎረም አባል ሆንን፡፡ ሆኖም በዚህ ፎረም የሚሳተፉ ሲቪል ማኅበራት በተናጠል ሳይሆን በኮንሶርቲየም ስለሆነ፣ በውሳኔዎች ላይ የሚኖራቸው ተሳትፎ አናሳ ነበር፡፡ ምክር ቤቱ ግን በተለየ ሲቪል ማኅበረሰቦች በተናጠልም መወከል የሚችሉበትን አሠራር ነው ያመጣው፡፡ በዚህ ከፎረሙ ወደ ምክር ቤት የተደረገ ሽግግር መሀል የፎረሙ ዕጣ ፈንታ ምን ይሆናል የሚል ጥያቄ መነሳት ጀመረ፡፡ ምክንያቱም ወደ ምክር ቤቱ ተሸጋግሯልና ምን ያደርጋል ካልን በኋላ የሚሉ ነበሩና፡፡ ዕቅዱ የነበረው ፎረሙን በአንድ ዓመት ውስጥ ሥራዎቹን እያገባደደ በሒደት እንዲከስም ነበር፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ፎረሙ ከተለያዩ ለጋሾች ገንዘብ ወስዶ ሲሠራቸው የቆዩ ፕሮጀክቶች በመኖራቸውና እነሱ መጠናቀቅ ስለሚጠበቅባቸው ነው፡፡ ወደ ምክር ቤቱ ሊሄዱ አይችሉም፡፡ እስከዚያ ድረስ የፎረሙ ዳይሬክተርና የፋይናንስ ኃላፊ ምክር ቤቱን እንዲያግዙ ምክረ ሐሳብ ቀርቦ ነበር፡፡ ነገር ግን አሁኑኑ መክሰም አለበት ብለው የሚጠይቁ ስላሉ ይኼንን ተሰብስበን መወሰን ይኖርብናል፡፡
ይኼ ምክር ቤት በአዋጁ መንፈስ የተመሠረተ ነው፡፡ ሆኖም ከላይ ሆኖ የሚቆጣጠረው አካል እንዲኖረው የሚያደርግ አካል ስለማይኖርና በቦርድ የሚተዳደር ስለሆነ፣ ከሲቪል ማኅበረሰቦች ኤጀንሲ ተቃውሞ አስነስቶ ነበር፡፡ በዚህም ምክንያት ምሥረታው ከተጠበቀው ረዘም ያለ ጊዜ ወሰደ፡፡ በተጨማሪም ኤጀንሲው ከምክር ቤቱ ጋር የሚኖረው ግንኙነት የጎንዮሽ ነው ወይስ ከላይ ወደ ታች የሚለው አሳስቦት ነበር፡፡ እኛ አዋጁን ያወጣው ፓርላማው ስለሆነ የበላይ ተቆጣጣሪ መኖሩ የግድ ከሆነ ፓርላማው ይሁን ብለን ተከራከርን፡፡ በሒደቱ አንዱ የልዩነት ምንጭ የነበረው ይኼ ነው፡፡ የምክር ቤቱ አባላት ጥፋት ካጠፉ የሚኖርባቸውን ተጠያቂነት በተመለከተም ሥጋት ገብቷቸው የነበረ ሲሆን፣ ለዚህ ደግሞ ያዘጋጀነው የመተዳደሪያ ደንብ አለን ብለን እሱን አቀረብን፡፡ አሁን ምክር ቤቱ አገራዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ይሳተፋል፡፡ በተጨማሪም ለአባላቱ ጥበቃ የሚሰጥ ሲሆን፣ ውዝግብ ሲነሳም ከመንግሥት ጋር ይነጋገራል፡፡ በየትኛውም ደረጃ ካለ የመንግሥት አካል ጋር የመነጋገር ሥልጣን ተሰጥቶታል፡፡ ይኼም ሥልጣን በአባላቶቻችንም ሆነ በሕዝቡ ውስጥ የማቀንቀን ሥራ (አድቮኬሲ) እንዲንሠራ ያስችለናል፡፡ ስለዚህ ምክር ቤቱ በተለይ የአቅም ግንባታ ላይ ለሲቪል ማኅበረሰቡ ከፍተኛ ድጋፍ ይሰጣል፡፡
ሪፖርተር፡– የሲቪል ማኅበረሰቦች ሚናዎች በሁለት ሊመደቡ ይችላሉ፡፡ ማኅበረሰቡን ማንቃትና ለድምፅ አልባዎች ድምፅ መሆን፡፡ ሆኖም በሲቪል ማኅበረሰቡ ዘንድ እነዚህን በማድረግ ረገድ ውሱንነቶች የሚታዩ ሲሆን፣ በተለይም በተለያዩ ጊዜያት ንፁኃን ሲገደሉና ከቀዬአቸው ሲፈናቀሉ ደፍረው ድምፅ ሊሆኑላቸው የቻሉት ኢምንት ናቸው፡፡ እንዲያው ሲቪል ማኅበረሰቡ ይኼንን ማድረግ እንዳይችል አድርጎ የሸበበው ምክንያት ምን ይሆን?
ንጉሡ ለገሰ (ዶ/ር)፡- ለድምፅ አልባው ድምፅ ለመሆን ወደ እነዚህ ግጭት የተከሰተባቸው አካባቢዎች በመጓዝ ዳሰሳ መሥራት ይጠበቅብናል፡፡ እኔ በጥናት አምናለሁ፣ ሕይወቴም ሥራዬም ከጥናት ጋር የተቆራኘ ነው፡፡ በአንድ ወገን ላይ የሚደረግ፣ እገሌ ገደለ፣ ወዘተ. የሚለው ለማንም አይጠቅምም፡፡ በጥናት መደገፍ አለበት፡፡ ስለዚህ ሲቪል ማኅበረሰቡ ያለ መረጃ ዘሎ ወደ እዚህ ከገባ የባሰ ችግር ነው የሚፈጥረው፡፡ በመሬት ላይ ያለውን ጉዳይ እንዲያጣሩ ሰዎች ልኬ እነሱ የሚያመጡትን መረጃ ተመልክቼ ካልሆነ ወጥቼ መግለጫ ልሰጥ አልችልም፡፡ ያለበለዚያ አስቸጋሪ ነው የሚሆነው፡፡ ቀድሞ የነበርኩበት መሥሪያ ቤት ደግሞ በዚህ ረገድ ጥሩ ትምህርት ያገኘሁበት ነበር፡፡ ወደ እዚህ ከመምጣቴ አስቀድሞ የዓለም የቤተ ክርስቲያናት ምክር ቤት የአፍሪካ ዲሬክተር ነበርኩና አንዱ የአፍሪካ ችግራችን የነበረው ቦኮ ሐራም ነበር፡፡ በተጋጋሚ የጅምላ መቃብሮች ሄደን ፀሎት አድርሰን እናውቃለን፡፡ ነገር ግን የምናየውን ከሕዝቡ መረጃ ሰብስበንና ተወያይተን እነሱ የሚያምኑትን ሪፖርት ነው የምናቀርበው፡፡ ድርጅቱም ይኼንን ወስዶ ዓለም አቀፋዊ ውትወታ ያከናውናል፡፡ ለዚህ ደግሞ በጥናት ላይ በእጅጉ እንመረኮዛለን፡፡ እንዲህ ባሉ ሁኔታዎች ሲቪል ማኅበረሰቦች ገለልተኛ ሆነው በቅርበት በማየት ሪፖርት ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው እናምናለን፡፡ ነገር ግን እነዚህ ችግሮች የሚፈጠሩባቸው ቦታዎች መድረስ አንችልም፡፡ እነዚህና መሰል ተግዳሮቶች ሲቪል ማኅበረሰቡ ለድምፅ አልባው ድምፅ እንዳይሆኑ ያደርጓቸዋል፡፡ በጠቅላላው ወጥቶ እንዲህ ያለው ጥፋት መልካም አይደለም ማለት ይቻላል፡፡ ግን ዝርዝር ማቅረብ አንችልም፡፡ ዝርዝር በመሬት ላይ ያለውን ነገር መመርመር ይጠይቃል፡፡ ነገር ግን ይኼንን ማድረግ የሚችሉ አቅም ያላቸው ሲቪል ማኅበረሰቦች የሉም፡፡
እውነት ለመናገር በአገሪቱ እየሆነ ያለው ያሳዝናል፡፡ የክልል ፖሊሶች ለወጣቶች ከለላ እየሰጣቸው ስንት ነገር ሲደረግ ተመልክተናል፡፡ ይኼንንም እኔ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ አጠገባቸው ተቀምጬ ነግሬያቸዋለሁ፡፡ የኦሮሚያ ክልል ፖሊስ ለኦሮሞ ወጣት ከለላ ሰጥቶ ዜጎች የሚሞቱ ከሆነ አገር እየመራን ነው ለማለች ያስቸግራል ነው ያልኳቸው፡፡ በእነዚህ አካባቢዎች ሄጄ መረጃ ልሰብስብ ብትልስ ማን ነው ትክክለኛ መረጃ የሚሰጥህ? ይኼ በሁሉም ሥፍራ የምናየው ችግር ነው፡፡ መረጃ በሌለበት ሁኔታ ተነስተን አንድ ነገር ለማለት ብንሞክር ሌላ ችግር ልንፈጥር እንችላለን፡፡ ይኼ ብቻ ሳይሆን የሰሜኑ ችግር እንደተከሰተ የሰብዓዊ ድጋፍ ለማድረስ ሞክረን ነበር፡፡ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያንና ከካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ጋር ትብብር ፈጥረንም ነበር፡፡ ይኼንን ያደረግነው በከፊል እነዚህ ተቋማት በየቦታው ቤተ ክርስቲያን ስላላቸው መረጃ ለማግኘትም ያግዛል በሚል ነበር፡፡ ነገር ግን እነሱ ሰፊ ሥራ ስለነበረባቸውና ከመንግሥትም ጋር ይሠሩ ስለነበር ይኼ ሊሆን አልቻለም፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የሲቪል ማኅበረሰቦች ሰብዓዊ ድጋፍ ለማቅረብ ተከልክለው ስለቆዩ እጅግ ተዳክመዋልና ወዲያውኑ ምላሽ መስጠት አይችሉም፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ ድጋፍ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት (ኦቻ) ድጋፍ የሚያደርስ ቢሆንም፣ የአገር ውስጥ ሲቪል ማኅበረሰቦች ግን ከእነሱ ጋር በጥምረት መሥራት አይፈቀድላቸውም ነበር፡፡ ለዚህ እንደ ምክንያት የሚያቀርቡትም አገር በቀል ተቋማት አቅም የላቸውም በማለት ነበር፡፡ እዚህ ምን ልትሠሩ መጣችሁ ታዲያ ብዬ ጠየቅኳቸው? አቅም ልትሆኑን አይደለም እንዴ? ይኼ እጅግ ከባድ የነበረ ሲሆን፣ እነሱን አሳምኖ በጋራ ለመሥራት ስድስት ወራት ፈጀብን፡፡ አሁን የዚህ ተልዕኮ አካል ነን፡፡ የነጮች ብቻ ክበብ ነበር፡፡ በኢትዮጵያ የቅኝ ግዛት እርሻ የለንም እስከ ማለት ድረስ ተገድጄ ነበር፡፡
ሪፖርተር፡- በእርግጥ ሰብዓዊ ዕርዳታ ለማድረስም ሆነ ለጋዜጠኞችና ለሌሎች አካላት ለመድረስ አስቸጋሪ የሆኑ አካባቢዎች እንዳሉ ዕሙን ነው፡፡ ነገር ግን ቀስ በቀስ እየተከፈቱ የመጡ እንደ ትግራይ ያሉ አካባቢዎች አሉ፡፡ በዚህም ምክንያት የንፁኃን ግድያዎች፣ አስገድዶ መደፈርና የመሳሰሉ ሪፖርቶች እየተሰሙ ነው፡፡ እነዚህን መሰል ተግባራት ላይ የሲቪል ማኅበረሰቡ እየተሳተፈ ያልሆነው ከአቅም ማነስ ነው? ወይስ በፍላጎት ማጣት?
ንጉሡ ለገሰ (ዶ/ር)፡- በፍፁም በፍላጎት ማጣት አይደለም፡፡ ሲቪል ማኅበረሰቡ ይኼንን ተግባር መፈጸም በሚችልበት ደረጃ ላይ አይደለም ያለው፣ እንደ ሲሲአርዲኤ እነግርሃለሁ፡፡ እኛ በኮሚቴ የሚመሩ የክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች አሉን፡፡ መረጃ ለማግኘት ከእነዚህ ኮሚቴዎች ሰብሳቢዎች ጋር እንገናኛለን፡፡ በትግራይም ጠንካራ ጽሕፈት ቤት አለን፡፡ የክልሉን ጽሕፈት ቤት አስተባባሪ የተወሰነ ዳሰሳ እንዲሠራና በዚያ መሠረት ሰነድ አዘጋጅተን ከለጋሾች ድጋፍ እንድናስገኝላቸው በተደጋጋሚ ጠይቄው ነበር፡፡ ሆኖም መንቀሳቀስ እንደማይቻል ነበር የነገረን፡፡ እንደ ኦክስፋም፣ አክት አላያንስና አክሽን ባይ ቸርችስ የተባሉ የረድኤት ድርጅቶች ከኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ጋር ተባብረው ድጋፍ እያደረሱ ይገኛሉ፡፡ እንደ ሲሲአርዲኤ ማድረግ የነበረብን በሥፍራው ከሚገኙ አባላቶቻችን መረጃ መሰብሰብ ነበር፡፡ ነገር ግን እነሱ የደኅንነት ሥጋት አለባቸው፡፡
ሪፖርተር፡- ስለሰብዓዊ ድጋፍ ካነሳን ከወራት በፊት ከድምፃዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ በኋላ በተከሰቱ ግጭቶችና ጥቃቶች ሳቢያ ለተጎዱ ወገኖች ድጋፍ ለማድረግ ስትንቀሳቀሱ ነበር፡፡ ከውጭ አገር ሳይቀር ድጋፍ አግኝታችሁ ነበርና ይህ ገንዘብ የት ደረሰ? ምን ያህል ሰዎች ተጠቃሚ ሆኑ?
ንጉሡ ለገሰ (ዶ/ር) የዚህ ድጋፍ እንቅስቃሴ የተጀመረው ቀደም ብሎ በጥቅምት ወር 2012 ዓ.ም. የአቶ ጃዋር መሐመድ ጥበቃዎች ሊነሱ ነው ሲባል የነበረውን አመፅ ተመልክቶ 86 ሰዎች ሲሞቱ ነበር፡፡ ከተለያዩ ሰዎች ጋር በመነጋገር 20 አባላት ያሉት ኮሚቴ መሠረትን፡፡ ከዚያም ከያኔው የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጄኔራል እንደሻው ጣሰው ጋር ተገናኝተን ከተወያየን በኋላ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድንም አግኝተን እንዴት ግጭቶቹ ሊረግቡ እንደሚችሉ ውይይት አደረግን፡፡ ይኼ ኮሚቴ ነው እንግዲህ ድምፃዊ ሃጫሉ ሲገደል ድጋፍ ሊያደርግ የተነሳው፡፡ ነገር ግን የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ይኼ ኮሚቴ ንዑስ ኮሚቴ ሆኖ ከእነሱ ጋር እንዲሠራ ሲፈልጉ፣ እኛ ሁኔታውን ተዘዋውረን ስንጎበኝ እናንተ ግን ሄዳችሁ ተጎጂዎቹን ለማየት እንኳን አልፈለጋችሁም ብለን በመከራከር አይሆንም አልን፡፡ በወቅቱ እኛ በሦስት አቅጣጫዎች በባሌ፣ በሻሸመኔና በሐረር ቡድኖችን አሰማርተን ነበር፡፡ እኔ በራሴ 50 ሰዎች ያሉትን ልዑክ ይዤ ወደ ባሌ ሄጄ ነበር፡፡ በመጨረሻም ተስማማንና ከሁለቱ ወገኖች ሰባት ሰባት ሰዎችን መድበን 14 አባላት ያሉት ኮሚቴ እንዲዋቀር ተደረገ፡፡ በዚህ ኮሚቴ አማካይነት 40 ሚሊዮን ብር ተሰበሰበ፡፡ በመሀል ማኅበረ ካህናት ዘ ሰሜን አሜሪካ በኦሮሚያ ጉዳት ለደረሰባቸው ድጋፍ የሚሆን ገንዘብ ሲያሰባስብ ነበርና እነሱ ያሰባሰቡት ሁለት ሚሊዮን ዶላር በሲሲአርዲኤ አማካይነት ለድጋፍ ፈላጊዎች እንዲዳረስ ተደረገ፡፡ ቀድሞ የተሰበሰበው 40 ሚሊዮን ብር በጥሬ ገንዘብ ለተጎጂዎች እንዲከፋፈል ተወስኖ በባንክ ለእያንዳንዳቸው ገቢ የተደረገ ቢሆንም፣ የባንክ ደብተር ስላልተሰጣቸው ግን ገንዘቡን ሊጠቀሙት አልቻሉም ነበር፡፡ ሆኖም በእኛ በኩል የመጣው 78 ሚሊዮን ብር ገደማ የሚሆን ገንዘብ ደርሶ መተንፈሻ ሆናቸው፡፡ በመቀጠልም በተለያዩ ሁኔታዎች በዚያውዓመት ጉዳት የደረሰባቸው ድጋፍ እንዲያገኙ አደረግን፡፡ ይኼ አጋጣሚ የሰብዓዊ ድጋፍ ሥራን በተመለከተ ጥሩ ትምህርት ያገኘንበት ነበር፡፡
ሪፖርተር፡- ከሰጡኝ ማብራሪያ እንደምረዳው የተሰጠው ድጋፍ ለክርስቲያኖች የተደረገ ነው፡፡ ይኼ አድሎዓዊ አይሆንም?
ንጉሡ ለገሰ (ዶ/ር)፡- አይደለም፡፡ ችግሩ የተከሰተው በኦሮሚያ ሲሆን፣ የሃጫሉ ግድያን ተከትሎ ጉዳት የደረሰባቸውን ሰዎች ስንመለከት ክርስቲያኖች ናቸው፡፡ በተለይም የኦርቶዶክስ ክርስቲያኖች፡፡ ይኼ ማለት ግን ኦሮሞዎች ጉዳት አልድረሰባቸውም ማለት አይደለም፡፡ ለምሳሌ በወቅቱ የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ያወጣው ሪፖርት በአርሲ ከተገደሉ 35 ሰዎች መካከል 22 ሰዎች ክርስቲያን ኦሮሞዎች ናቸው፡፡ ስለዚህ ተጠቂዎቹ ክርስቲያኖች መሆናቸው አያጠያይቅም፡፡ የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን በበኩሏ 67 ሰዎች ተገድለውብኛል ብላለች፡፡ በጠቅላላው 167 ሰዎች መገደላቸው ሪፖርት የተደረገ ሲሆን፣ የተቀሩት 100 ሟቾች ጉዳይ የሕግ ማስከበር ዕርምጃው ተከትሎ የተከሰተ ሊሆን ይችላል፡፡
ሪፖርተር፡- እንዲህ ያሉ ሰብዓዊ ዕርዳታዎች ጊዜ የማይገድባቸው ተግባራት ናቸው፡፡ በተወሰነ ጊዜ የሚመጡ እንደ ምርጫ ያሉ ሁነቶችም በተመሳሳይ የሲቪል ማኅበረሰቡን ንቁ ተሳትፎ ይሻሉ፡፡ በዚህ ዓመት ይደረጋል ተብሎ ለታቀደው ምርጫ የሲቪል ማኅበረሰቦች የመራጮች ትምህርት ለመስጠትና ለመታዘብ የሚያስችላቸውን ቅንጅትም ፈጥረዋል፡፡ ሆኖም እስካሁን በታየው ሒደት ሲቪል ማኅበረሰቡ በምርጫው በቂ ሚና እየተጫወተ ነው ማለት ያስችላል?
ንጉሡ ለገሰ (ዶ/ር)፡- ወደ ምርጫ ስንመጣ ከሲቪል ማኅበረሰቡ ብዙ ነገር ነው የሚጠበቀው፡፡ በሚያሳዝን ሁኔታ ምርጫ በአገራችን የችግር ምንጭ ሲሆን፣ ከአሁን ቀደም አባላቶቻችን ሁሉ እንዲታሠሩ ያደረገ ነበር፡፡ የአሁኑ የሰብዓዊ መብቶች ዋና ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር) ምርጫ 97ን ተከትሎ ነበር ለእስር የተዳረጉት፡፡ እኛም ብንሆን ሌት ተቀን እየተጠራን እንመረመር ነበር፡፡ ሥልጣን ላይ ለመቆየት ሲባል የሲቪል ማኅበረሰቡ ተገፍቶ ነበር፡፡ አሁን ሕጉ የተሻሻለ ቢሆንም ሲቪል ማኅበረሰቦች ምርጫው በሚፈልገው ደረጃ ራሳቸውን መልሰው ለማደራጀት ቀላል አይሆንላቸውም፡፡ ካሁን ቀደም በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት የተራዘመው የምርጫ ሰሌዳ ይፋ ሲደረግ የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበረሰቦች ለምርጫ የሚባል ቅንጅት ፈጥረን ነበር፡፡ ጽሕፈት ቤቱም የአውሮፓ ኅብረት ለምርጫ ድጋፍ በተከራየው ሆቴል ውስጥ ነበር፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የአሜሪካዎቹ ብሔራዊ የምርጫ ኢንስቲትዩትና የኢንተርናሽናል ሪፐብሊካን ኢንስቲትዩት ከእኛ ጋር በትብብር ይሠሩ ነበር፡፡ የእነሱ መኖር ለሲቪል ማኅበረሰቡ አቅም መገንባት መልካም ዕድል ፈጥሯል፡፡ ምርጫው ሲራዘምም ለምርጫ ተብለው የተቀጠሩ ሰዎች እስከ ማስተርስ ዲግሪ የደረሰ ሥልጠና ወስደዋል፡፡
ቅንጅቱን በሕግ አስመዝግበን ሰው ቀጥረናል፡፡ ዳይሬክተር ስላለው በእሱ አማካይነት የሴሬታሪያት፣ የስትራቴጂ ጉዳዮችንና ከለጋሾች ጋር የሚደረጉ ግንኙነቶችን ይመራል፡፡ ቅንጅቱ ሰባት የቦርድ አባላት ያሉት ሲሆን፣ ከሰባቱ አንዱ እኔ ነኝ፡፡ ምርጫን በተመለከተ እኔ የዚምባቡዌን ምርጫ ከአንዴም ሁለቴ፣ የናይጄሪያን ምርጫ፣ የኮንጎን ምርጫ፣ የቡሩንዲን ምርጫ፣ የደቡብ ሱዳንን እ.ኤ.አ. የ2009 ሕዝበ ውሳኔ ተከታትያለሁ፡፡ ከዚያ አኳያ ሐሳብ እየተለዋወጥን ይኼንን ለመገንባት ችለናል፡፡ አዲስ ድርጅት ስታቋቁም ገንዘብ ማግኘት አስቸጋሪ ነው፡፡ አሁን ነው ትንሽ እያወቁን የመጡት፡፡ በሲዳማ ሕዝበ ውሳኔ ምርጫ ቦርድ ጋብዞን በምን ልታግዙን ትችላላችሁ ሲለን በምን እናግዝ አልነው፡፡ ታዘቡልን አለንና 220 ሰዎች አሰማራን፡፡ ያ ዱብ ዕዳ ነበር፡፡ ድንገት በአምስት ወራት ውስጥ ሕዝበ ውሳኔው ይከናወናል ነበር የተባለው፡፡ ግን ለእኛ ብዙ ጠቅሞናል፡፡ ብዙ ልምድ አገኘንበት፣ ለዚህኛው የሚጠቅም፡፡ አሁንም ለዚህ ምርጫ ለታዛቢነት ብቻ ወደ 3,000 ሰዎችን፣ ክትትል የሚያደርጉና በፍጥነት ሪፖርት የሚያደርጉ እናሰማራለን፡፡ ከዚያ በፊት ያለው ትልቁ ሥራ ለመራጮች ትምህርት መስጠት ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ መጀመሪያ ምርጫ ቦርድ ፈቃድ ይሰጣል፡፡ መሟላት የሚኖርባቸውን መሥፈርቶች ዓይቶ ስለሚፈቅድ ከሲሲአርዲኤ ከ400 አባላት መካከል 33 ናቸው ፈቃድ ያገኙት፡፡ እነዚህ 33 ሲቪል ማኅበራት ገንዘብ ስለሌላቸው ገንዘብ ፈልጉልን ብለውን፣ ለዚህ ብለን ያሰባሰብነውን ገንዘብ ባላቸው ተሳትፎ አማካይነት መመርያ ሰጥተን አከፋፍለናል፡፡
ሪፖርተር፡- ይኼ ማለት መጋቢት 24 ቀን 2013 ዓ.ም. የምርጫ ፕሮጀክቶቻችሁን ይፋ ያደረጋችሁበት ቀን ማለት ነው፡፡ የራሳችሁ ዝግጅትን ጨምሮ ሲቪል ማኅበረሰቦች በምርጫው የሚያደርጉት እንቅስቃሴ አልዘገየም? አሁን የመራጮች ምዝገባም ሁለት ሳምንታት ብቻ ነውና የቀረው ድባቡ የተቀዛቀዘ መሆኑ አያሳስብም?
ንጉሡ ለገሰ (ዶ/ር)፡- የዘገየበትን ምክንያት እንደነገርኩህ ነው፡፡ ቢያንስ ከአንድና ከሁለት ሳምንት ቀደም ብሎ መጀመር ነበረበት፡፡ በምርጫ ቦርድ በኩል ይኼ የመታወቂያ ዝግጅት ሳይሟላ ማካሄድ አይቻልም፡፡ ከአቅማችን በላይ ነው ጥያቄው፡፡ ሥጋቱ አለ፡፡ ዕውን ሁሉም እንደልቡ መረጃ ይደርሰዋል ወይ? በሚዲያ ከሚነገረውና መንግሥት ከሚለውና ሰው ከሚሰማው ካልሆነ በስተቀረ እውነት ለመናገር በእኛ ደረጃ የሚደረግና ማድረግ የነበረብን ነገር ከሚገባን ያነሰ ነው፡፡ መቀዛቀዙ ትክክል ነው፡፡ ሲቪል ማኅበረሰቡ ወጣ ብሎ ለዚህ ለዚህ ይጠቅማችኋላ ማለት ነበረበት፡፡
ሪፖርተር፡- ከዚህ ባለፈ የፀጥታ ጉዳይ የበርካቶች ሥጋት ሆኖ ይገኛል፡፡ በየጊዜው ንፁኃን ይገደላሉ፣ ከቤት ንብረታቸው ይፈናቀላሉ፡፡ አንዳንዶች እንዲያውም ምርጫ ከማድረግ አስቀድሞ አገሪቱን በሁለት እግር ማቆም ላይ ይተኮር ይላሉ፡፡ ዕውን አገሪቱ ምርጫ ማድረግ የሚያስችላት ድባብ አላት ይላሉ?
ንጉሡ ለገሰ (ዶ/ር)፡- ምርጫው ካልተካሄደ በራሱ ከባድ ችግር ነው፡፡ ካሁን ቀደም በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት ምርጫው ይተላለፍ ተባለ፡፡ ያን ጊዜ የገጠመንን ችግር ዓይታችኋል፣ በአገር ደረጃ ይባል የነበረውን ማለት ነው፡፡ ምናልባትም ያኔ ብናካሂደው ኖሮ ደህና ልንሆን እንችል ይሆናል፡፡ ግን ስለማይታወቅ ነው፡፡ ኮሮና ከቻይና አልፎ ፈረንሣይ ገብቶ፣ በስፔንና በጣልያን የፈጀውን ፈጅቶ አትላንቲክን ተሻግሮ ደግሞ አሜሪካ ውስጥ ፈጀ፡፡ ያንን ነበር የምናየው፡፡ እኛ ዘንድ አሁን እንደ ደረሰው እንኳን ችግር አላየንም ያኔ፡፡ ያን ያየ ዓይን እዚህ እንደዚያ አይሆንም ተብሎ የሚታሰብበት ሁኔታ አይኖርም፡፡ አሁን እዚህ ደረጃ ተደርሶ ሰላም የለም፣ ምርጫ አላካሂድም ለማለት ያስቸግራል፡፡ አሁን እንዲያው አጠቃላይ ሁኔታውን ስታየው እንደ ልብ ለመንቀሳቀስ አስቸጋሪ ነው፡፡
ሪፖርተር፡– ሲሲአርዲኤ በምርጫ 97 ጠንካራና ፊት ለፊት መንግሥትን የተጋፈጠ ነበር፡፡ አሁንም ይኼ ጥንካሬ ይኖረዋል?
ንጉሡ ለገሰ (ዶ/ር)፡- በደንብ ነው የሚኖረው፡፡ ያን ጊዜ የነበረውን ጥንካሬ ይገርምሃል 35 ሆነን ነበር የጀመርነው፣ ምርጫውን ለመከታተል፡፡ ቀስ በቀስ 13 ብቻ ቀርተው ሰዎች አሰማሩ ምርጫውን ለመታዘብ፡፡ ችግር እስከሚገጥማቸውና እስከሚታሰሩ ድረስ ሲሠሩ ነበር፡፡ ለ20 ወራት ነው ከተቃውሞ ጋር የታሰሩት፡፡ ከእነ ብርሃኑ ነጋና ብርቱካን ሚደቅሳ ጋር ነው የተፈቱት፡፡ ዛሬ ግን ጥንካሬው ሁሉም ነገር የተፈቀደበት ስለሆነ ምንም ወደ ኋላ የምንልበት ምክንያት የለም፡፡ ሰዎች አሰማርተናል፣ ክትትል ማድረግ ነው፡፡ እኛ ገብተን የምንሠራው ነገር የለም፡፡ መከታተልና መቆጣጠር ነው ሥራችን፡፡ በተቻለ መጠን ጥረት እያደረግን ነው፡፡