በቀድሞው የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ የሚመራው ግራንት ቶሮንቶ ኢትዮጵያ የተባለው ኩባንያ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ባለሥልጣን አጠቃላይ አሠራርን ለማዘመን ከባሥልጣኑ ጋር የመግባቢያ ሰነድ ተፈራረመ፡፡
የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ባለሥልጣንና ግራንት ቶሮንቶ ረቡዕ መጋቢት 29 ቀን 2013 ዓ.ም. ስምምነቱን በተፈራመበት ወቅት እንደተገለጸው፣ ባለሥልጣኑ የአሥር ዓመት ውጥኑን በብቃት ይወጣ ዘንድ ስትራቴጅክ ዕቅድ በመቅረፅ ወደ ሥራ ገብቷል፡፡ ይህንን ለማሳካት እንዲረዳውም ከግራንት ቶሮንቶ ኢትዮጵያ ጋር ስምምነት አድርጓል፡፡
በቁጥጥር አቅም ግንባታ፣ በቴክኖሎጂ (አውቶሜሽን)፣ በአቅም ግንባታ ሥልጠና፣ መጪውን ጊዜ የሚመጥን አደረጃጀት ዝርጋታ፣ እንዲሁም የባለድርሻ አካላት ተሳትፎን በተመለከተ ባለሥልጣኑ ያሉበትን ክፍተቶች መሠረት በማድረግ ፕሮጅክት በመቅረፅና በመተግበር ውጥኑን ለማሳካት ከግራንት ቶሮንቶ ኢትዮጵያ ጋር የደረሰው ስምምነት አጋዥ ይሆናል ተብሏል፡፡
የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ባለሥልጣን ከኢትዮጵያ ምርት ገበያ መቋቋም ጋር ተያይዞ የተቋቋመ የተጣረመ ተቋም እንደሆነ ይታወቃል፡፡ በኢትዮጵያ የዘመናዊ ምርት ገበያ ሥርዓት ግንባታ ከተጀመረ 13 ዓመታት ያስቆጠረ ሲሆን፣ በዚህ ጊዜ ውስጥ ገበያው በርካታ የምርት ዓይነትና መጠን ሻጭና ገዥ የምርት ገበያ አባላት፣ ከአገናኝ አባላት ጋር የሚሠሩ በርካታ የምርት ገበያ አባል ያልሆኑ ደንበኞች ማፍራት ስለመቻሉ ባለሥልጣኑ ገልጿል፡፡
ለእነኚህ የምርት ገበያ አባላት የክፍያና የምርት ርክክብ አገልግሎት የሚሰጡ በርካታ ባንኮችና መጋዘኖች ወደ ሥራ ገብተዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ድምፅን በማስተጋባት ሲካሄድ የነበረው የግብይት አሠራር ወደ ኤሌክትሮኒክስ ግብይት በማሳደግ በአዲስ አበባ ብቻ የነበረው የግብይት ማዕከል ወደ ክልሎች ተደራሽ እንዲሆን በጎንደር፣ በሐዋሳ፣ በሑመራና በነቀምቴ የኤሌክትሮኒክ መገበያያ ማዕከላትን በመቋቋም ወደ ሥራ መግባታቸውንም በስምምነቱ ወቅት ተገልጿል፡፡
በተጨማሪም በጅማና በአዳማ ኤሌክትሮኒክ ግብይት ማዕከላት ተገንብተው የተጠናቀቁ ሲሆን፣ ዘንድሮ አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምሩ ባለሥልጣኑ አስታውቋል፡፡
የግብይት፣ የገበያተኞች ባህሪና የአገልግሎት አድማሱ እየሰፋ በመምጣቱ ተጨማሪ አቅምና አደረጃጀት ለመፍጠር በዕለቱ የተደረገው ስምምነት ጉልህ ሚና አለው ተብሏል፡፡
የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ባለሥልጣን በኢትዮጵያ ዘመናዊና ውጤታማ የሆነ የግብይት ሥርዓት መገንባቱን ለማረጋገጥ፣ እንዲሁም ግልጽና የተረጋጋ የምርት ግብይት አሠራርን ለማስፈን የቁጥጥርና የድጋፍ ሥራዎች በማከናወን የሻጮች፣ ገዥዎች፣ እንዲሁም በአጠቃላይ የኅብረተሰቡን ጥቅም ለማስጠበቅ እንዲያስችለው የክትትል፣ የድጋፍና የቁጥጥር ተግባራቱን ለመወጣት ጥረት እያደረገም ነው፡፡
ቀጣዩ ምዕራፍ የሚጠይቀውን የክትትል፣ የድጋፍና የቁጥጥር አገልግሎት ለማዘመንና አሠራሩን ከፍ ለማድረግ፣ በ2022 ዓ.ም. በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሆነ የግብይት ሥርዓትን ዕውን ለማድረግ የያዘውን ራዕይ ለማሳካት ስምምነቱ ጉልህ ድርሻ እንደሚኖረው ተገልጿል፡፡
ስምምነቱ ከተፈረመ ጊዜ ጀምሮ እስከ ሦስት ዓመት በሥራ ላይ የሚቆይ እንደሆነም ታውቋል፡፡ በስምምነቱ መሠረት ቶሮንቶ ኢትዮጵያ በባለሥልጣኑ ያለውን የአቅም ክፍተት በጥናት በመለየት ዕቅድ በማዘጋጀትና ለተፈጻሚነቱ አስፈላጊውን የሆነ ሀብት በመመደብ ትልቅ ድርሻ እንደሚኖረውም ተገልጿል፡፡
በግብር፣ በኦዲትና በቢዝነስ ማማከር ሥራዎች ላይ የተሰማራውን ግራንት ቶሮንቶ ኩባንያ የሚመሩት አቶ ኤርሚያስ አሸቱ፣ ኢትዮጵያ ምርት ገበያ ባለሥልጣንን በዋና ሥራ አስፈጻሚነት የመሩ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ከዚህም ቀደም ብሎ የዘመን ባንክ ፕሬዚዳንት እንደነበሩ ይታወሳል፡፡
ስምምነቱን የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ኡሌሮ ኡፒየውና (ኢንጂነር) የግራንት ቶሮንቶ ኢትዮጵያ ሥራ አስኪያጅ አቶ ኤርሚያስ እሸቱ ፈርመዋል፡፡