አሁን ላይ እየታየ ያለው የዋጋ ንረት ሸማቹንም ሆነ መንግሥትን በእጅጉ እየፈተነ ነው፡፡ ከመቀነስ ይልቅ ከፍ እያለ የመጣው የዋጋ ንረት አሳሳቢነትን በመገንዘብ፣ በመንግሥት ደረጃ የተለያዩ ዕርምጃዎች እየተወሰዱ ቢሆንም፣ ገበያው ሊረጋጋ አልቻለም፡፡፡ በሁሉም ምርቶች ላይ የሚታየው የዋጋ ንረትን ለመቀንስ አሁንም ተጨማሪ ዕርምጃዎች ሊወሰዱ እንደሚገባም እየተገለጸ ነው፡፡
ሰሞኑን ይፋ የሆነው የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ መረጃ የመጋቢት 2013 ዓ.ም. የዋጋ ንረት ከ20.6 በመቶ በላይ መድረሱን አመላክቷል፡፡ በተለይ ምግብ ነክ ምርቶች ላይ ንረቱ ጎልቶ የታየ ስለመሆኑም ተጠቁሟል፡፡
በኢትዮጵያ የዋጋ ንረት በዚህን ያህል ደረጃ ደረሰበት ጊዜ እንደሌለ እየተገለጸ ከሞኑም በላይ እየታየ ያለው የዋጋ ንረት ከሌሎች አገሮች አንፃርም ሲታይ፣ የኢትዮጵያ በከፍተኛነቱ የሚጠቀስ እስከመሆን ደርሷል፡፡
በዋጋ ንረትና በመፍትሔው ዙሪያ ያነጋገርናቸው የምጣኔ ሀብት ባለሙያው ዓለማየሁ ገዳ (ፕሮፌሰር) እንደሚገልጹትም፣ አሁን ላይ በኢትዮጵያ ያለው የዋጋ ንረት ከአካባቢው አገሮች አንፃር ሲታይ ፈጽሞ የማይገናኝና ከፍተኛ የሚባል ስለመሆኑ ያመለክታሉ፡፡
የምሥራቅ አፍሪካ አገሮችን ወቅታዊ የዋጋ ንረት ምጣኔን ለመዳሰስ የሞከሩት ፕሮፌሰር ዓለማየሁ፣ በወፍ በረር ቅኝታቸው እንደ ኬንያ፣ ሩዋንዳ፣ ማላዊና ታንዛኒያ ያሉ የአካባቢው አገሮች የዋጋ ንረት ምጣኔያቸው ከሦስት በመቶ የማይበልጥ መሆኑን ነው የሚገልጹት፡፡ እንዲያውም የአንዳንዶቹ አገሮች ሁለት በመቶ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ግን 20.6 በመቶ ደርሷል፡፡
እነዚህ አገሮች ምን አድርገው ነው የዋጋ ንረቱን ምጣኔ እዚህ ያደረሱት? እዚህስ ለምንድነው በዚህን ያህል ደረጃ የዋጋ ንረቱ የወጣው? ብሎ ማሰብ ያስፈልጋል ያሉት ፕሮፌሰር ዓለማየሁ፣ መንስዔው አራት መሠረታዊ ጉዳዮች ላይ የሚወድቅ ሆኖ እንደሚያገኙት ጠቅሰዋል፡፡
የዋጋ ንረቱም ከዚህ ቀደም ከነበረው አሠራር ጋር የተያያዘና እየተንከባለለ የመጣ ሲሆን፣ በእሳቸው እምነት አሁን ላለው ሁኔታ አድርሰውናል ብለው ካስቀመጧቸው አራት ዋና ዋና ጉዳዮች አንዱ ከዚህ ቀደም ለተለያዩ መሠረተ ልማቶች እየተባለ ብር በማተም ኢኮኖሚ ውስጥ እንዲሠራጭ መደረጉ ነው፡፡
ይሠራል ተብሎ ለተያዘ መሠረተ ልማት የሚፈልገው ገንዘብ የሚሸፈነው በብድር ወይም ብር በማሳተም በመሆኑ የዋጋ ግሽበት እንዲጨምር ምክንያት ሆኗል ብለው ያምናሉ፡፡ ምክንያቱም ብድርም ሆነ ገንዘብ ኅትመት ሁለቱም ለዋጋ ንረት መንስዔዎች ስለሆኑ ነው፡፡
በውጭ ምንዛሪ የምትበደረው በብር ተቀይሮ ኢኮኖሚ ውስጥ የሚገባ በመሆኑ ለንረቱ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ ከብሔራዊ ባንክም በከፍተኛ መጠን መበደርም ብር ማሳተም እንደማለት ነውና ከዚህ ቀደም የተሄደባቸው መንገዶች ለዋጋ ንረት የራሳቸው አስተዋጽኦ ነበራቸው ብለዋል፡፡
አሁን ለደረስንበት የዋጋ ንረት ምክንያት ናቸው ብለው የጠቀሱት ሁለተኛ ጉዳይ ደግሞ፣ የወጪና የገቢ ምርቶች ያለመጣጣም ነው፡፡ አገሪቱ በገፍ ዕቃዎችን ከውጭ የምታስገባና ኑሮው በገቢ ዕቃ ላይ የተመሠረተ ከመሆኑ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት ሦስት ቢሊዮን ብር የሚያወጣ ምርት ሸጠን ከውጭ የምናስገባው ምርት ደግሞ 17 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ስለዚህ በገቢ ንግድ ላይ የተንጠለጠለች አገር ሳይቋረጥ የብር ምንዛሪ ለውጥ (ዲቫሉዌሽን) ማድረግ ለዋጋ ንረቱ ሌላው መንስዔ ነው ባይ ናቸው፡፡ ምክንያቱም ቀደም ብሎ በነበረ የምንዛሪ ዋጋና ዲቫሉዌሽን ከተደረገ በኋላ ያለው የምንዛሪ መጠን ልዩነት ያለው ስለሚሆን የዋጋ ንረት ያስከትላል፡፡ በ29 ብር ይገዛ የነበረ ዕቃ በ41 ብር እየተባዛ ከሆነ ንረት ታየ ማለት ነው፡፡ በሌላ በኩልም ዲቫሉዌሽን ሲደረግ የምንዛሪ ዋጋ 29 ብር በነበረ ጊዜ የተያዘ በጀት አሁን 41 ብር ሲገባ ከውጭ የሚመጣው ዕቃ ካለ ዋጋው ከፍ ይላል በማለትም ዲቫሉዌሽን በዋጋ ንረት ላይ ያለውን ተፅዕኖ አስረድተዋል፡፡
እንዲህ ያለው የውጭ ምንዛሪ ለውጥ ደግሞ ድጋሚ በጀት እንዲጠየቅ ስለሚያደርግም፣ ያልተቋረጠ ዲቫሉዌሽን ለዋጋ ንረት ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው አስረድተዋል፡፡ ይህ ማለት እንደገና ብር እንደማተም የሚቆጠር ስለሆነ የዋጋ ንረቱን ከፍ ያደርገዋልም የሚል ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
አሁን ለተደረሰበት የዋጋ ንረት ምክንያት ነው ብለው ያስቀመጡት ሦስተኛውና እንዲያውም ዋና ያሉት የአገሪቱ የእርሻ ምርት መጠን ከሕዝብ ብዛት ዕድገት ጋር የተመጣጠነ ሆኖ ያለመገኘት ነው፡፡
ይህንንም ሲያብራሩ የኢትዮጵያ አማካይ የሕዝብ ብዛት ዕድገት 2.7 በመቶ መሆኑን ያስታወሱት ፕሮፌሰሩ፣ ከፍተኛ የዋጋ ንረት የሚታይበት የምግብ ሰብል ምርት የሚያድገው በአማካይ በ2.5 በመቶ ነው፡፡ ይህ አኃዝ የሚያመለክተው በነፍስ ወከፍ የሚደርሰው ምርት መጠን እየቀነሰ መምጣቱን በመሆኑ የአቅርቦት እጥረትን የሚፈጥር ነው፡፡
ፕሮፌሰር ዓለማየሁ ለዋጋ ንረቱ መንስዔ ነው ብለው ያስቀመጡት አራተኛ ነጥብ ደግሞ፣ የነጋዴዎች ያልተገባ ትርፍ ህዳግ ነው፡፡ ተገቢ ያልሆነ የትርፍ ምጣኔ ለዋጋ ንረት የራሱ አስተዋጽኦ እንዳለው በመጥቀስም ኢትዮጵያ ውስጥ መቶ በመቶ ማትረፍ እንደ ቀላል የሚታይና ቁጥጥር የማይደረግበት መሆኑ የዋጋ ንረትን እያስከተለ ነው፡፡ ይህ መሆን የማይገባው፣ ግን እየሆነ ያለው ልክ የሌለው የትርፍ ሕዳግ ያለመወሰን ችግሩ እንዲጎላ አድርጓል፡፡
በአሜሪካ አማካይ የትርፍ ህዳግ መጠን አሥር በመቶ ነው፡፡ 20 በመቶ ከተገኘ ጉድ ሊባል የሚችል ነው፡፡ በኢትዮጵያ ግን 10 ብር የነበረ ዕቃ 20 ብርና 30 ብር እየተሸጠና ትርፍ ህዳጉ ከመቶ በመቶ በላይ ሆኖ እንኳን መቆጣጠር ያለመቻሉ ሌላው ዋጋ ንረት ምክንያት ስለመሆኑም አስረድተዋል፡፡ እነዚህ አራት ዋና ዋና ለዋጋ ግሽበት መንስዔ ናቸው የተባሉ ጉዳዮች መፍትሔያቸው በእነዚሁ ላይ መሥራት ስለመሆኑም ጠቅሰዋል፡፡
እንደ እሳቸው እምነት፣ ከአራቱ ችግሮች በቶሎ ሊሠራበት የሚገባውና መቅደም አለበት የሚሉት የእርሻ ምርታማነትን ማሳደግ የሚለውን ነው፡፡
የእርሻ ምርታማነት ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባበት በርካታ ምክንያቶች አሉ፡፡ በተለይ ምግብ ነክ የሆኑ ምርቶች እንደ ስንዴና ዘይትን ጨምሮ በቢሊዮን ዶላር በሚቆጠር ወጪ ተደርጎባቸው የሚገቡ በመሆናቸው ትኩረት ሊያገኙ ይገባል፡፡ ከገቢ ምርቶች ወደ 20 በመቶ የሚሆነው ምግብ ነክ ምርት መሆኑን በማመልከትም፣ ምግብ ነክ ምርቶችን ከውጭ ከማስገባት እዚህ እንዲመረት ማድረግ ቀዳሚው መፍትሔ ስለሚሆን በዚህ ላይ መሥራት የዋጋ ንረቱን ለማረጋጋት ጠቃሚ ይሆናል፡፡
ከአጭር ጊዜ አንፃርም ሲታይ፣ ከውጭ የሚገቡትን ምግብ ነክ ምርቶች እዚሁ እያመረቱ ለመተካትና ገበያን ለማረጋጋት ያለው አማራጭ አሁን ባለው የማምረት አቅም በዓመት ሁለት ጊዜ በማምረት ቀስ በቀስ ፍላጎትን ማሟላት የሚቻልበት ደረጃ ላይ ሊደረስ ይችላል፡፡ ይህ ንረቱን ለመቀነስ ከሚያስችሉ ዕርምጃዎች አንዱ ነው፡፡
ምርታማነትን ለማሳደግና በዓመት ሁለቴ ለማምረት ደግሞ በመስኖ ልማትን ማስፋት ይጠይቃል ያሉት ፕሮፌሰር፣ አሁን መንግሥት ይህንን እየሞከረ ስለመሆኑም አስታውሰዋል፡፡
የመንግሥት ጥረት ተገቢና የሚደነቅ ዕርምጃ ቢሆንም፣ በትክክል ፕላን የተደረገበት ነው የሚለው ላይ ግን እርግጠኛ መሆን እንደማይችሉ ጠቅሰዋል፡፡ ነገር ግን ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በመስኖ እየለሙ ያሉትን አካባቢዎች በሚጎበኙበት ወቅት የምናየው የመስኖ ሥራ እየሰፋ መምጣቱን መገንዘብ ችለዋል፡፡
የመስኖ ሥራ ኢንቨስትመንት የሚጠይቅና በዕቅድ መሠራት ያለበት ሲሆን፣ በትክክል እየተተገበረ ከሄደ የዋጋ ንረትን ይቀንሳል የሚል እምነት አላቸው፡፡ እዚህ ላይ ገበሬውም እንዳይጎዳ ማሰብ የሚጠይቅ መሆኑንም አስታውሰዋል፡፡
አሁን ያለውን የዋጋ ንረት በአንድ ጀንበር ማውረድ ባይቻልም፣ የምግብ ሰብል ምርቶችን ማሳደግ በዓመት ሁለቴ እንዲመረት ማድረግ ለዘለቄታውም ቢሆን ወሳኝ ስለመሆኑ ከፕሮፌሰሩ ማብራሪያ ለመረዳት ተችሏል፡፡
በኢትዮጵያ ውስጥ ለታየው የዋጋ ንረት የምንዛሪ ለውጥ ወይም ዲቫሉዌሽን አንዱ ምክንያት መሆኑን የሚጠቁመው የፕሮፌሰር ማብራሪያ፣ ዲቫሉዌሽን መቆም አለበት ብለው ያምናሉ፡፡ ፈጣን የሆነውን ዲቫሉዌሽን ማቆም የዋጋ ንረቱን ለማውረድ የራሱ የሆነ አስተዋጽኦ እንዳለው፣ ዲቫሉዌሽን ሲደረግ እንደ አንድ ምክንያት የሚቀርበው የወጪ ንግድን ያበረታታል ኢምፖርትን አያበረታታም በሚል የውጭ ሰዎች ትንታኔን መሠረት ያደረገ ነው፡፡
ዕርምጃው ወደ ነፃ ገበያ ለመሄድ የሚመች ስለመሆኑ ቢገለጽም፣ በእሳቸው ዕይታ ግን የተለየ ነው፡፡ ይህንንም ለማለት የሚደፍሩ ኤክስፖርትን ለማበረታታትና ከውጭ የሚገባ ምርትን ለመቀነስ ዲቫሉዌሽን ያግዛል የሚለው አመለካከትና የተወሰደው ዕርምጃ ለውጥ ባለማምጣቱ ነው፡፡
ባለፉት ሦስትና አራት ዓመታት የታየውም ኤክስፖርቱን ማበረታታቱን አይደለም ይላሉ፡፡ ሺሕ ጊዜ ዲቫሉዌሽን ቢደረግም የወጪ ንግዱን አልቀየረውም፡፡ ኤክስፖርቱን ያበረታታል ተብሎ የተደረገው ዲቫሉዌሽን ውጤቱ ሲታይ አሁንም የኤክስፖርቱ ገቢ ሦስት ቢሊዮን ዶላር ላይ በመቆሙ ነው፡፡
ሌላው ማሳያቸው ደግሞ ኢምፖርትን እንዲቀንስ ያደርጋል የሚለው ጉዳይም ያለመሥራቱ ነው፡፡ ምክንያቱም 80 በመቶ የሚሆነው የገቢ ምርት ስትራቴጂክ የሚባልና የሚፈልግ ምርት በመሆኑ በምንም ዋጋ ቢሆን መግዛቱ ግድ ስለሆነ ነው፡፡
እንደ ነዳጅና ሌሎች መሠረታዊ የሚባሉ ምርቶች እንዲሁም ከምግብ ነክ ምርቶችም የሚገባው እንደ ስንዴ፣ የልጆች ምግብና የመሳሰሉት በመሆኑ እኒህን መሠረታዊ ምርቶች ማስገባት አይቀርም፡፡ ስለዚህ የብር ምንዛሪ ለውጥ ማድረግ ገቢ ዕቃዎች እንዳይበረታቱ ያደርጋል የሚለውን አመለካከት እንዳይቀበሉ አድርጓቸዋል፡፡ ምክንያቱም እዚህ ምርቶች አስፈላጊ በመሆናቸው ዋጋ ቢጨምሩም የሚገዙ በመሆኑ ነው፡፡ ፈረንጆቹ ዲቫሉዌሽን ማድረግ ጥቅም ያስገኛል ብለው የሚያስቀምጡትን ግብ አይቀበሉትም፡፡ በአንፃሩ ግን ዲቫሉዌሽን ያመጣው የዋጋ ንረት ነው ብለው ያምናሉ፡፡ ስለዚህ ዲቫሊዌሽንን ማቆም የዋጋ ንረቱ እንዳይጨምር ያግዛል የሚል እምነት አላቸው፡፡
ፕሮፌሰር የዋጋ ንረቱን አንድ መንስዔ ነው ብለው የሚያምኑ የስግብግብ ነጋዴዎች ያልተመጠነ የትርፍ ህዳግ ነው፡፡ ያልተመጠነ የትርፍ ህዳጉ ጉዳት ማምጣቱ ቢታወቅም፣ ይህንን ለመቆጣጠር ግን ከባድ ነው፡፡ መንግሥት ይህንን ለመቆጣጠር ሞክሮ እንደነበር ፣ ዕርምጃው ግን ረዥም ሠልፎች እንዲፈጠሩና በድብቅ መሸጥ እንዲጀመር ማድረጉን ፕሮፌሰር ዓለማየሁ ያስታውሳሉ፡፡
ከዚህ አንፃር የሚታየውን ክፍተት ለማጥበብ የምርት መጠኑን መጨመር ነው፡፡ በተለይ መሠረታዊ የሚባሉ ምርቶች ላይ ምርትን መጨመር ነው፡፡ አሁን ካለው ችግር አንፃር የአጭር ጊዜ መፍትሔው ለምሳሌ አዲስ አበባ ውስጥ 200 ሺሕ ነጋዴዎች ቢኖሩ፣ ይህንን ሁሉ ተቆጣጥሮ ስለማይቻል መሠረታዊ ዕቃዎችን እንደ ኢትፍሩት ዓይነት አደረጃጀት ፈጥሮ በወረዳ/ቀበሌ ማከፋፈል መፍትሔ ሊሆን እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡ ኢትፍሩትን እንደ ምሳሌ ያነሱት ለ30 እና ለ40 ዓመታት በተመጣጣኝ ዋጋ ምርቶችን እየሸጠ በመሆኑ ከእርሱን ልምድ መውሰድ ውጤታማ ያደርጋል ብለው ስለሚያስቡ ነው፡፡
እንደ ጤፍ፣ የሽሮ እህል፣ ዘይትና የመሳሰሉትን መርጦ በቀበሌዎች ማከፋፈል ለአጭር ጊዜ መፍትሔ ስለሚሆን እንዲህ ያሉ ምርቶችን ከማሠራጨት አንፃር አሁን ላይ ሥራ ላይ ባሉ የሸማቾች ማኅበራት በኩል ማከፋፈሉ ውጤት ላያመጣ ይችላል የሚል አመለካከትም አላቸው፡፡ በባለሙያዎች የሚመራና በየቀበሌው በአዲስ አደረጃጀት የሚተገበር የሽያጭ ማዕከል መፍጠርም ያስፈልጋል፡፡ መሠረታዊ የሚባሉ ምርቶችን ዋጋ ወስኖ መሸጥ መፍትሔ ይሆናል፡፡
ሌላው መፍትሔ እንደ ኦልማት ዓይነት ሱፐር ማርኬቶችን በመንግሥትና በግል ዘርፍ ጥምረት (PPP) እንዲቋቋሙ በማድረግ የትርፍ ህዳጋቸው ተወስኖ እንዲሸጡ ማድረግም ከአጭር ጊዜ መፍትሔ አኳያ ውጤት ይኖረዋል ብለው እንደሚያምኑም ገልጸዋል፡፡