Tuesday, May 28, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

የውጭ ምንዛሪ እጥረቱ የፈጠራቸው ያልተገቡ አሠራሮች ይታዩልን

በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ውስጥ እንደ ከፍተኛ ችግር ተደርገው ከሚጠቀሱት አንዱ የውጭ ምንዛሪ እጥረት ነው፡፡ የውጭ ምንዛሪ እጥረት የአገሪቱ የከረመ ችግር ሲሆን አሁንም ቀጥሏል፡፡ በእጥረቱ ሳቢያ የፋብሪካዎች የምርት ሒደት ሲስተጓጎል ማየትም አዲስ ነገር አይደለም፡፡ የውጭ ምንዛሪን በወረፋ እስከ መስጠትም ተደርሷል፣ ይህም ቢሆን ከተሳካ ማለት ነው፡፡

በኢትዮጵያ ከሚላከው ምርት ከሚገኘው ውጭ ምንዛሪ በላይ ወጥቶም ከውጭ ዕቃዎች ይገባሉ፡፡ ይህም የአገሪቱን የንግድ ሚዛን ጉድለት በእጅጉ እንዲሰፋ አድርጎታል፡፡ በየዓመቱ የሚገባው ዕቃ መጨመርና የወጪ ንግዱ ገቢ ያለበት ቦታ መቆም የውጭ ምንዛሪ ፍላጎቱን አሳድጎታል፡፡

በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ በዓመት 17 ቢሊዮን ዶላር ወጪ የሚጠይቁ ምርቶችን ከውጭ የምታስገባ ሲሆን፣ በአንፃሩ ከወጪ ንግድ በዓመት የምታገኘው የውጭ ምንዛሪ ከሦስት ቢሊዮን ዶላር በልጦ አያውቅም፡፡ ይህም ከ14 ቢሊዮን ዶላር ያላነሰ ጉድለት መኖሩን ያሳያል፡፡ ስለዚህ የገቢ ዕቃዎችን ወደ አገር ለማስገባት የሚያስፈልገው ከ14 ቢሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሪ ከተለያዩ ምንጮች ከሚገኙ የውጭ ምንዛሪ ገቢዎች የሚሸፈን መሆኑ እንጂ ሸጠን በሚገኝ የውጭ ምንዛሪ የምንገዛው አይደለም፡፡  

ስለዚህ ሁሌም ለገቢ ንግድ የሚፈለገውን የውጭ ምንዛሪ ለመሸፈን ያለው ፍዳ እንዲህ በቀላሉ የሚታይ አይሆንም፡፡ የአገር ፈተናም ነው፡፡ በመንግሥት ደረጃ ያለውን የውጭ ምንዛሪ በአግባቡ ለማድረስ ሲባል ከወረፋ ባሻገር ቅድሚያ የሚሰጣቸው ምርቶችን በመለየት የውጭ ምንዛሪው እንዲከፋፈል ሲያደርግ ቆይቷል፡፡

 የውጭ ምንዛሪ አጠቃቀምን ፍትሐዊ ለማድረግ ይረዳሉ የተባሉ የተለያዩ መመርያዎችንም ሥራ ላይ አውሏል፡፡ ይህም ምናልባት የተወሰነ ለውጥ አሠራር ላይ እንዲታይ ከማድረግ የዘለለ መሠረታዊውን የውጭ ምንዛሪ ችግር አይቀርፍም፣ አልቀረፈም፡፡ ለዚህም ነው በሕጋዊ የምንዛሪ ዋጋና በጥቁር ገበያ መካከል ያለው ልዩነት እየጠበበ ከመሄድ ይልቅ እየሰፋ የመጣው፡፡ በውጭ ምንዛሪ ፍላጎትና በአቅርቦቱ መካከል ያለው ልዩነት እጀግ ሰፊ መሆኑ፣ እንዲሁም ውጭ ምንዛሪ የማግኘት ዕድሉ የጠበበ ሆኖ ለዓመታት በመዝለቁም ከውጭ ምንዛሪ አጠቃቀምና አፈቃቀድ ዙሪያ በርካታ ችግሮች እንዲታዩ አድርጓል፡፡

ባንኮች ያላቸውን የውጭ ምንዛሪ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ባስቀመጠው ደንብና ሕግ መሠረት ያስተናግዳሉ ቢባልም፣ አጠቃላይ የውጭ ምንዛሪ እጥረቱ ለብልሹ አሠራር ተጋላጭ አድርጎታል፡፡

የጥቁር ገበያ እንዳይጠፋ ምክንያት ሆኗል፡፡ ውጭ ምንዛሪ ለማግኘት ሲባል የሚፈጸሙ ያልተገቡ ተግባራት ደግሞ የተረጋጋ ገበያ እንዳይኖር በማድረግ የራሳቸው አሉታዊ ተፅዕኖ ስለሚኖራቸው በአገር ኢኮኖሚ ላይ የሚያደርሱት ችግርም በተጨባጭ ይታያል፡፡

ከውጭ ምንዛሪ አጠቃቀም ጋር ተያይዞ ለበጎ የታሰቡ መመርያዎች ችግር ሆነው የሚገኙበት አጋጣሚም ተደጋግሞ መታየቱ ሊነሳ ይችላል፡፡

ጥሩ ማሳያ የሚሆነን፣ በቅርቡ እንዲሻሻል የተደረገው የዳያስፖራ አካውንት ነው፡፡ ዳያስፖራዎችን ለመጥቀም እግረ መንገዱንም አገርን ለማገዝ ተብሎ በዳያስፖራ አካውንት የውጭ ምንዛሪ ማስቀመጥና ዕቃዎችን ለማስገባት በዚህ አካውንት መጠቀም እንደሚቻል የወጣው ሕግ ሥራ ላይ በዋለ በአጭር ጊዜ ውስጥ ላልተገባ ዓላማ መዋሉ ነው፡፡ ይህም በተጨባጭ ተደርሶበት መመርያው እንዲሻሻል ተደርጓል፡፡

ለግል መገልገያ የታሰበው የዳያስፖራ አካውንት የጥቁር ገበያ መፈንጫ በመሆን ሕገወጥ ነጋዴዎች በዚህ ቀዳዳ ገብተው ሕገወጥ ተግባራት ሲፈጸምበት ቆይቷል፡፡ ሕገወጥ ሥራ እየተሠራበት መሆኑ እስከተደረሰበት ጊዜ ድረስ በእነዚህ አካውንቶች ብዙ ያልተገቡ ተግባራት ተፈጽመዋል፡፡ አሁንም መመርያው ተሻሽሎ ሥራ ላ እንዲውል ቢደረግም፣ የተሻሻለው መመርያ በቀጣይ ምን ለውጥ እንደሚያመጣ በጋራ የምናየው ይሆናል፡፡

አሁንም ክፍተቶችን ተጠቅሞ ሊሠሩ የሚችሉ ሥራዎችን እግር በእግር መከታተልና ፈጣን ዕርምት ለመውሰድ መዘጋጀት ግን ተገቢ ነው፡፡ በውጭ ምንዛሪ አጠቃቀም አፈቃቀድና ተያያዥ ጉዳዮች የሚታዩ ያልተገቡ ተግባራት የአገሪቱን የዋጋ ግሽበት ከፍ ስለማድረጋቸው ልብ ሊባልም ይገባል፡፡

አሁንም ቢሆን ከውጭ ምንዛሪ እጥረት ጋር ተያይዞ ያለውን ችግር ለመቅረፍ ወጪ ንግዱን ማሳደግ ቀዳሚው ዕርምጃ ቢሆንም፣ አገሪቱ የምታገኘውን የውጭ ምንዛሪ በአግባቡ መጠቀም ግድ ይላል፡፡

የውጭ ምንዛሪን አስመልክቶ አንዳንድ አካላት በግልጽም ሆነ በሥውር የሚጫወቱት ጨዋታ ሄዶ ሄዶ የበለጠ ተጎጂ የሚያደርገው ሸማቹን ነው፡፡ በምንም መንገድ ይሁን በሚያገኙት የውጭ ምንዛሪ የሚያስመጡትን ዕቃ እጥረቱን እያሳበቡ ዋጋ በመቆለል የሚሸጡ በመሆኑ፣ የዋጋ ግሽበትን እያባባሰው ነው፡፡ ስለዚህ አሁንም ያልታዩ ጉዳዮች ስላሉ በውጭ ምንዛሪ አጠቃቀም ዙሪያ ብሔራዊ ባንክ ተጨማሪ ሥራ በመሥራትና የተሻለ አሠራር መዘርጋት ግድ ይለዋል፡፡   

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት