Tuesday, November 28, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በሚያዝያ ወር ከቡና ኤክስፖርት 111 ሚሊዮን ዶላር ለማግኘት ዕቅድ ተይዟል

ተዛማጅ ፅሁፎች

ኢትዮጵያ በመጋቢት 2013 ዓ.ም. ካገኘችው 107 ሚሊዮን ዶላር የቡና ኤክስፖርት ገቢ በበለጠ፣ በሚያዝያ ወር 111 ሚሊዮን ዶላር ለማግኘት እየተሠራ እንደሆነ ተገለጸ፡፡

የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተርና የግብይት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ሻፊ ዑመር ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት ተቀዛቅዞ የነበረው የቡና ኤክስፖርት ባለፉት ሁለት ወራት ጥሩ እንቅስቃሴ በማሳየት በመጋቢት ወር ከ27,247 ቶን ቡና 107 ሚሊዮን ዶላር ተገኝቷል፡፡

በመጋቢት ወር ኢትዮጵያ ቡና ለውጭ ገበያ አቅርባ ከፍተኛ ሽያጭ ማስመዝገቧን ያስታወቁት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ፣ በሚያዝያ ወርም ይኼንን እንቅስቃሴ በማስቀጠል 29,648 ቶን ቡና ወደ ውጪ በመላክ 111 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ለማስገኘት እየተሠራ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

የአቅራቢና የላኪ ትስስር መርዘም፣ ከክልሎች ምርቱ በወቅቱ ተሰብስቦ ወደ ግብይት ማዕከላት አለመምጣት፣ እንዲሁም በቡና አቅርቦት የተሰማሩ ተቋማት በቅንጅት አለመሥራት በቡና ኤክስፖርት እንቅስቃሴ ውጤታማነት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ሲፈጥር እንደቆየ ያስረዱት አቶ ሻፊ፣ በእነዚህ ችግሮች ላይ ሪፎርም በመካሄዱ ለተገኘው ውጤት አስተዋጽኦ አድርጓል ብለዋል፡፡

ቡና ወደ ውጪ በመላክ ሒደት ዋናው ችግር የግብይት ሰንሰለቱ መርዘም ሲሆን፣ ይኼም በመሀል ገብቶ ያልተፈለገ ዋጋ የማናር እንቅስቃሴ እንደሆነ ተገልጿል፡፡ በመሆኑም ይኼንን ሰንሰለት በማሳጠር ቡና ተመርቶ በቀጥታ ለኤክስፖርት እንዲዘጋጅ መሥራት አስፈላጊ እንደሆነ አቶ ሻፊ አስረድተዋል፡፡

የቡና ኤክስፖርት ብዙ ተቋማትን እንደሚዳሰስ፣ የቡናና ሻይ ባለሥልጣንን ጨምሮ ጉምሩክ ኮሚሽን፣ ምርት ገበያ፣ ሎጂስቲክስ አገልግሎትና ማሪታይም ድርጅቶች ተጠቃሾች ናቸው፡፡ እነዚህን ተቋማትን አቀናጅቶ ከመሥራት አኳያ መሻሻሎች እንዳሉ፣ በየጊዜው የሚደረጉት መደበኛ ስብሰባዎች ችግሮች የቱ ጋ እንዳሉ በጊዜ ለማወቅ እንደረዱ፣ ይኼም ለችግሮቹ መፍትሔ አበጅቶ የተሻለ ውጤት ለመገኘቱ ተጠቃሽነት ምክንያት እንደነበር ተገልጿል፡፡

ከኮሮና ወረርሽኝ መከሰት በፊት በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚዘጋጁ በዓመት ከአሥር የሚበልጡ የቡና ኤግዚቢሽኖች እንደነበሩ የገለጹት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ፣ ሆኖም በዚህ ወቅት እነዚህ ኤግዚቢሽኖች አለመኖራቸው ዓለም አቀፍ የቡና ግብይቱን እንደፈተነው አስታውቀው፣ ኢትዮጵያ ከገዥዎች ጋር እያደረገችው ባለው ፍሬያማ ድርድር የተሻለ ገቢ እያገኘች እንደምትገኝ አስረድተዋል፡፡

በተያዘው በጀት ዓመት 150 ሺሕ ቶን የሚጠጋ ቡና ለውጭ ገበያ እንደቀረበ፣ ያለፉትን ሁለት ወራት ሳይጨምር በመጀመርያዎቹ ሰባት ወራት 346 ሚሊዮን ዶላር ገቢ መገኙቱ ተገልጿል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች