Friday, March 31, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

መንግሥት ትኩረቱን አንገብጋቢ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ያድርግ!

በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ከምትገኝበት ነባራዊ ሁኔታ አኳያ፣ መንግሥት በሕግ የተሰጠውን ሥልጣን ተጠቅሞ ሊያከናውናቸው የሚገቡ አንገብጋቢ ጉዳዮች አሉ፡፡ የአገርን ብሔራዊ ጥቅምና ደኅንነት ማስከበርና ሉዓላዊነቷን ከማናቸውም ጥቃቶች መከላከል የመንግሥት አንደኛውና ተቀዳሚው ኃላፊነት ሲሆን፣ የሕዝቡን ሰላምና ደኅንነት መጠበቅም በዚሁ ሥር የሚወድቅ ነው፡፡ በተጨማሪም የአገሪቱ ሕጎች ተከብረው ዜጎች በሕግ ፊት እኩል መሆናቸውን ማረጋገጥ፣ በማንኛውም መንገድ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እንዳይፈጸሙ ነቅቶ መጠበቅ፣ የመሰብሰብ፣ የመደራጀት፣ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽና ሌሎች ዴሞክራሲያዊ መብቶች እንዲከበሩ ማድረግ፣ ለሕዝብ ጤና አደገኛ የሆኑ ድርጊቶችን ማስወገድ፣ ዜጎች በመረጡት ሥፍራ የመኖር፣ የመዘዋወር፣ የመሥራትና ሀብት የማፍራት መብትን በተግባር ማረጋገጥ፣ ለሕገወጥነትና ለሥርዓተ አልበኝነት ምቹ መደላድል የሚፈጥሩ ብልሹ አሠራሮችን ማምከን፣ ለተለያዩ ችግሮች በቀላሉ ተጋላጭ የሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ማገዝ፣ ማናቸውም ተግባራቱ ግልጽነትና ተጠያቂነት እንዲኖርባቸው ማድረግ የመንግሥት ኃላፊነትም ግዴታም ነው፡፡ የሥልጣን ሉዓላዊ ባለቤት እንደሆነ የሚታመነው ሕዝብ የማወቅ መብት ስላለው ለብሔራዊ ደኅንነት ሥጋት ከሚሆኑት ውጪ፣ በመንግሥት እጅ ያሉ መረጃዎች ወቅታዊነታቸውን ጠብቀው ለሕዝብ መድረስ አለባቸው፡፡ የኮሮና ወረርሽኝ እንደ ሰደድ እሳት ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ ስለሆነ፣ መንግሥት ያወጣቸው የጥንቃቄ መመርያዎች በሁሉም ወገኖች ዘንድ ተፈጻሚ እንዲሆኑ ከፍተኛ ቁጥጥር ያድርግ፡፡ ይህንን ከባድ ጊዜ ለመሻገር ደግሞ ኢትዮጵያዊያን ይተባበሩ፡፡ በዚህ መነሻ አንዳንድ አሳሳቢ ጉዳዮችን ማንሳት ተገቢ ነው፡፡

በአራቱም የአገሪቱ ማዕዘናት የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን በሰላም ወጥቶ የመግባት ጉዳይ ከመቼውም ጊዜ በላይ እያሳሰባቸው ነው፡፡ በተለያዩ አካባቢዎች ማንነትን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶች በተደጋጋሚ እየተፈጸሙ በብዙ ሺሕ የሚቆጠሩ ንፁኃን ተገድለዋል፣ አካላቸው ጎድሏል፣ ንብረታቸው ወድሟል፣ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ተፈናቅለዋል፡፡ በንፁኃን ወገኖች ላይ የሚፈጸሙ ጭካኔ የተሞላባቸው ግድያዎችና ማፈናቀሎች በጣም ከመበርከታቸው የተነሳ የቱ ዳር፣ የቱ መሀል እንደሆነ ብዙዎችን ግራ እያጋባ ነው፡፡ በተለያዩ መንገዶች ጉዳት ከደረሰባቸው ወገኖች በተገኙ መረጃዎች መሠረት በስም ከሚጠቀሱ ነውጠኛ ቡድኖች በተጨማሪ፣ በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ባሉ ግለሰቦችና የፀጥታ አስከባሪዎች ጭምር ከፍተኛ ጉዳት ደርሷል፣ ወይም ተባባሪዎች ሆነው ለጥቃት ፈጻሚዎች ከለላ ሰጥተዋል፡፡ እንዲህ ዓይነት አሰቃቂ ድርጊቶች በመፈጸማቸውና መቆም ባለመቻላቸው ምክንያት፣ ብዙዎች ፅኑ የሆነ የደኅንነት ሥጋት አለባቸው፡፡ ይህ ሥጋትም ለመንግሥት አመራሮች በተለያዩ መንገዶች እንዲደርሳቸው ተደርጓል፡፡ በመሆኑም መንግሥት የሕዝቡን ሥጋት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለማስወገድ፣ ቆፍጠን ያለ ሕጋዊ ዕርምጃ የመውሰድ ግዴታ እንዳለበት መገንዘብ ይኖርበታል፡፡ የመከላከያ፣ የፖሊስና የፀጥታ ኃይሉን በማቀናጀት በተለይ ጥቃት እንደሚፈጸምባቸው የሚታወቁ ሥፍራዎች ላይ በማተኮር ተገቢውን ዕርምጃ መውሰድ አለበት፡፡ ጉዳት ከደረሰ በኋላ ከመተረማመስ አስቀድሞ መከላከል የመንግሥት ኃላፊነት በመሆኑ፣ ይህ ጉዳይ ይዋል ይደር ሳይባል ትኩረት ይሰጠው፡፡ ትኩረት ከተሰጠውና ሕዝብን ማስተባበር ከተቻለ ከአቅም በላይ አይሆንም፡፡ ካልሆነ ግን አገር ሊያፈርስ የሚችል ቀውስ እያንዣበበ ነው፡፡

አዲስ አበባ ከተማን ጨምሮ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ወንጀሎች እየተበራከቱ ነው፡፡ ከኪስ አውላቂ ጀምሮ እስከ በመሣሪያ ተደራጅቶ የመዝረፍ እንቅስቃሴ አድማሱን አስፍቶ፣ በአሁኑ ጊዜ የቆመ መኪና እንዳለ ተሰርቆ የት እንደሚደርስ አይታወቅም፡፡ አነስተኛ ተሽከርካሪዎችን በመከራየት በከተማው የተለያዩ ክፍሎች በመሰማራት ዜጎች ከቤታቸው፣ ከመሥሪያ ቤታቸው፣ ከባንክና ከመሳሰሉት ሥፍራዎች ሲወጡ ተከታትሎ መዝረፍ የየዕለት ትዕይንት ከሆነ ቆየ፡፡ ለትራንስፖርት አገልግሎት የሚውሉ ተሸከርካሪዎችን በማሰማራት፣ ዜጎችን አፍኖ መዝረፍና በአካላቸውና በሕይወታቸው ላይ አደጋ ማድረስ የተለመደ ድርጊት ከሆነ ሰነባብቷል፡፡ በከፍተኛ የኃላፊነት ስሜት የተሰጣቸውን ሥራ በአግባቡ የሚያከናውኑ በርካታ ምሥጉን የፖሊስ አባላት እንዳሉ ሁሉ፣ ከዝርፊያ በሚገኝ ሀብት ኑሮአቸውን ለማደላደል የሚፈልጉ ደግሞ ለሕገወጦች ሽፋን እየሰጡ ችግሩ እንዲስፋፋ ምክንያት መሆናቸው በኅብረተሰቡ ውስጥ በስፋት የሚነገር ሀቅ ነው፡፡ ኅብረተሰቡ ጥቆማ ሲያቀርብ አጣርቶ ዕርምጃ መውሰድ ላይ ዘገምተኝነት ይታያል፡፡ የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላትና የፖሊስ መዋቅሮች በዚህ ጉዳይ ላይ ማጣራት በማድረግ ተገቢውን ዕርምጃ መውሰድ ካልቻሉ፣ በአደገኛ ወንጀለኞች ምክንያት ከፍተኛ ቀውስ እንደሚደርስ ለማንም ግልጽ ነው፡፡ አገር የሚያስተዳድረው መንግሥትም ይህንን ችግር ተገንዝቦ ለተግባራዊ ምላሹ ፈጣን ውሳኔ ላይ መድረስ ይጠበቅበታል፡፡ ውንብድና ከሚታሰበው በላይ እየሆነ ነው፡፡ ቸልተኝነቱ በዚህ የሚቀጥል ከሆነ አገር የወንጀለኞች መጫወቻ ትሆናለች፡፡

ሌላው ትኩረት የሚያሻው ጉዳይ የኑሮ ውድነት ነው፡፡ የመሠረታዊ የፍጆታ ዕቃዎች ዋጋ በየዕለቱ እያሻቀበ ኑሮ ለዜጎች ከአቅማቸው በላይ እየሆነባቸው ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የግብይት ሥርዓቱ በደላላ የተጠለፈ ስለሆነና ለማስተካከል የሚደረግ ጥረት ስለማይታይ፣ በሰው ሠራሽ የዋጋ ጭማሪ ሳቢያ የዜጎች ሕይወት እየተመሰቃቀለ ነው፡፡ መሠረታዊ የፍጆታ ዕቃዎች በተለይ መንግሥት ድጎማ የሚያደርግባቸው ጭምር ከገበያው እንዲሰወሩ እየተደረገ፣ በተለያዩ መጋዘኖች ውስጥ ተከማችተው ምክንያታዊ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ ተደርጎባቸው እንደ ኮንትሮባንድ ዕቃ ውስጥ ለውስጥ ግብይት ይፈጸምባቸዋል፡፡ ከአምራቾች/አስመጪዎች እስከ ጅምላ አከፋፋዮችና ቸርቻሪዎች ድረስ ያለው የግብይት ሰንሰለት ለደላሎች ተመቻችቶ በመለቀቁ፣ የምርቶችን ሥርጭት በሕግ በተሰጣቸው ሥልጣን የመከታተል ኃላፊነት ያለባቸው አካላት ጭምር ግራ ሲጋቡ ማየት፣ ምን ያህል የግብይት ሥርዓቱ እንደ ዘቀጠ አንዱ ማሳያ ነው፡፡ ዱቄት፣ ስኳር፣ ዘይት፣ ሲሚንቶና ሌሎች ምርቶች መጠናቸው ከሥርጭታቸው ጋር ታውቆ የፍላጎትና የአቅርቦት ሚዛኑ በቀላሉ መለካት ሲገባው፣ በዘቀጠው የግብይት ሥርዓት ምክንያት ዜጎች ያለ ኃጢያታቸው ምክንያታዊ ባልሆነ ሰው ሠራሽ የዋጋ ግሽበት እየተመቱ ኑሮአቸው ሲኦል እየሆነ ነው፡፡ መንግሥት በገበያ ሕግ የሚመራ ኢኮኖሚ ውስጥ ገብቶ ዋጋ ተማኝ ይሁን ሳይሆን፣ የተበላሸው የግብይት ሥርዓት ጤናማ ሆኖ ሥርዓት ያለው ግብይት እንዲፈጠር ዘመናዊ አሠራሮችን ይከተል፡፡ ኃላፊነት በጎደላቸው የተደራጁ ሕገወጦችና ሥራቸውን በአግባቡ በማይወጡ መንግሥታዊ አካላት ምክንያት ሕዝብ ያለ ጥፋቱ አይቀጣ፡፡ የኑሮ ውድነቱ በዚህ ከቀጠለ ለአገር ቀውስ እንደሚያስከትል ግንዛቤ ይያዝ፡፡

ኢትዮጵያ በርካታ ውጥንቅጦች ውስጥ ሁና ምርጫ ለማካሄድ ሽርጉድ እየተባለ ነው፡፡ በምርጫ አማካይነት በሕዝብ ይሁንታ ቅቡልነት ያገኘ መንግሥት መሰየም ይሁን የሚባል ተግባር ነው፡፡ ነገር ግን ለመጪው ምርጫ ከሚደረገው ዝግጅት በተጨማሪ፣ ለውዝግብ መነሻ ሊሆኑ የሚችሉ ችግሮችን ከወዲሁ ማስወገድ ተገቢ ነው፡፡ የቅድመ ምርጫ ወቅት ሒደቱ ያማረ እንዲሆን ገዥውን ፓርቲ ጨምሮ ሁሉም ተፎካካሪ ፓርቲዎች፣ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ኃላፊነቱን በነፃነትና በገለልተኝነት እንዲወጣ ከማናቸውም ጣልቃ ገብነቶች መታቀብ አለባቸው፡፡ ምርጫ ቦርድ ድጋፍ ሲፈልግ ሕጉ በሚያዘው መሠረት ብቻ ተግባራቸውን መወጣት፣ ምርጫውን ከወዲሁ ተዓማኒነቱን ለማሳጣት የሚደረጉ አሉባልታዎችን ተባብሮ ማስቆም፣ ሲሳሳትና ተገቢ የማይመስሉ ድርጊቶች ሲከሰቱ በፍጥነት ቅሬታ ወይም አቤቱታ በማቅረብ እርምት መጠየቅ፣ ሰላማዊና ሕጋዊ መንገዶችን በመከተል ተቃውሞ ማሰማትና ሒደቱ የበለጠ እንዲሰምር ዕገዛ ማድረግ ለምርጫው ስኬት ጠቃሚ ነው፡፡ ቅድመ ምርጫው በተለያዩ መንገዶች ሲሰነካከልና ተገቢ ያልሆኑ ድርጊቶች ሲፈጸሙ፣ ስለምርጫው ፍትሐዊ መሆን በፍፁም ማሰብ አይቻልም፡፡ በተለይ መንግሥትም ሆነ ገዥው ፓርቲ ከማንም በበለጠ ከፍተኛ ኃላፊነት አለባቸው፡፡ ሰላም በሌለበት ምርጫ እንደማይኖር፣ ዜጎች ደኅንነታቸው እያሳሰባቸው ለምርጫ እንደማይዘጋጁ፣ ተፎካካሪ ፓርቲዎች መድረስ ያለባቸው ቦታ በፀጥታ ችግር ምክንያት ካልደረሱ መፎካከር እንደማይችሉ፣ በአጠቃላይ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ያለው ነፃና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ማድረግ እንደሚያዳግት መገንዘብ ይገባል፡፡ መንግሥት ከዚህ ቀደም የነበሩ አሳዛኝ የምርጫ ታሪኮች በኢትዮጵያ እንዳይደገሙ ቃል በገባው መሠረት ኃላፊነቱን ይወጣ፡፡ ይህንን ማድረግ አቅቶት ትኩረቱን ‹‹የትም ፍጪው ዱቄቱን አምጪው›› የሚለው አስተዛዛቢ ዕሳቤ ላይ ካደረገ ታሪክ ይፋረደዋል፡፡ በአጠቃላይ በበርካታ ችግሮች የተከበበችው ኢትዮጵያ የመፍትሔ ያለህ እያለች ነው፡፡  በመሆኑም መንግሥት ትኩረቱን አንገብጋቢ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ያድርግ!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

በደቡብ አፍሪካ የተጀመረውን የሰላም ንግግር አሜሪካንን ጨምሮ ተመድና ኢጋድ እየታዘቡ ነው

ለሰሜን ኢትዮጵያ ግጭት ሰላማዊ መፍትሔ ለማምጣት በአፍሪካ ኅብረት አማካይነት...

አገር የሚገቡ የግል ዕቃዎችን በሚገድበው መመርያ ምክንያት በርካታ ንብረቶች በጉምሩክ መያዛቸው ተገለጸ

በአየር መንገድ ተጓዦች ወደ አገር የሚገቡትን የግል መገልገያ ዕቃዎች...

መንበሩ ካለመወረሱ በስተቀር መፈንቅለ ሲኖዶስ መደረጉን ቤተ ክህነት አስታወቀ

ቅዱስ ሲኖዶስ ከነገ ጀምሮ ውይይት እንደሚጀምር ተነገረ ‹‹እኛ ወታደርም ሆነ...

ከአማራ ክልል ወደ አዲስ አበባ የሚጓዙ በርካታ ሰዎች ወደ ከተማዋ እንዳይገቡ በፖሊስ መከልከላቸውን ገለጹ

‹‹የኦሮሚያ ክልል መፍትሔ እንዲሰጥበት አሳውቀናል›› የአማራ ክልል ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ‹‹ጉዳዩ...
- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

ተወግዘው የነበሩ ሦስቱ ሊቀጳጳሳትና 20 ተሿሚ ኤጲስ ቆጶሳት ውግዘት ተነሳ

_ቀሪዎቹ ሦስት ህገወጥ ተሿሚዎች የመጨረሻ እድል ተሰጥቷቸዋል ​ ጥር 14...

በሕወሓት አመራሮች ላይ ተመስርቶና በሂደት ላይ የነበረው የወንጀል ክስ ተቋረጠ

በቀድሞ የትግራይ ክልል ፕሬዚደንት ደብረጽዮን ገብረሚካኤ,(ዶ/ር)ና ባለፈው ሳምንት በተሾሙት...

[የምክር ቤቱ አባል ላቀረቡት ጥያቄ በተሰጣቸው ምላሽ አቤቱታቸውን ለክቡር ሚኒስትሩ እያቀረቡ ነው]

ክቡር ሚኒስትር እየሆነ ያለው ነገር ትክክል ነው? ምነው? ምክር ቤቱም ሆነ...

የጉራጌ የክልልነት ጥያቄ ትኩሳት

ቅዳሜ መጋቢት 16 ቀን 2015 ዓ.ም. በጉራጌ ዞን ወልቂጤ...

አይ የእኛ ነገር!

የዛሬው ጉዞ ከጀሞ ወደ ፒያሳ ነው፡፡ መንገዱ ለሥራ በሚጣደፉ፣...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የሰላም ዕጦትና የኑሮ ውድነት አሁንም የአገር ፈተና ናቸው!

ማክሰኞ መጋቢት 19 ቀን 2015 ዓ.ም. የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ በርካታ ጥያቄዎች አቅርበዋል፡፡ ጥያቄዎቹ በአመዛኙ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ ያጠነጠኑ...

ግልጽነትና ተጠያቂነት የጎደለው አሠራር ለአገር አይበጅም!

ሰሞኑን የአሜሪካና የኢትዮጵያ መንግሥታት በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ተፈጽመዋል በተባሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችና የጦር ወንጀሎች መግለጫ ላይ አልተግባቡም፡፡ አለመግባባታቸው የሚጠበቅ በመሆኑ ሊደንቅ አይገባም፡፡ ነገር ግን...

የምግብ ችግር ድህነቱን ይበልጥ እያባባሰው ነው!

በአገር ውስጥና በውጭ የተለያዩ ተቋማት የሚወጡ መረጃዎች እንደሚያሳዩት፣ በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ከ22 ሚሊዮን በላይ ዜጎች አስቸኳይ የምግብ ዕርዳታ ያስፈልጋቸዋል፡፡ እነዚህ ወገኖች በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት፣...