የሐረሪ ክልል መስተዳድር ምክር ቤት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሚያዚያ 1 ቀን 2013 ዓ.ም. የሐረሪ ክልል ብሔራዊ ጉባዔን አስመልክቶ ያስተላለፈው ውሳኔ፣ የክልሉን ሕገ መንግሥት ያላማከለና ሕገ መንግሥትዊ አመክንዮ የሌለው ነው አለ፡፡
ከክልሉ ውጪ የሚኖረው የሐረሪ ክልል ከሕዝብ ባለፉት አምስት ምርጫዎች የመምረጥ መብት ተሰጥቶት የመረጠ ቢሆንም፣ ግንቦት 28 ቀን 2013 ዓ.ም. በሚካሄደው ምርጫ ላይ መሳተፍ የሚችለው በክልሉ በመገኘት እንጂ ከክልሉ ውጭ መምረጥ እንደማይችል፣ ምክንያቱ ደግሞ ከክልሉ ውጪ የሚኖረው ሕዝብ መምረጥ የሚያስችለው የሕግ መሠረት ስለሌለ መሆኑን መግለጹ ይታወሳል፡፡
የሐረሪ ክልል መስተዳድር ምክር ቤት (ካቢኔ) ሚያዚያ 3 ቀን 2013 ዓ.ም. ባካሄደው አስቸካይ ስብሰባ፣ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የሐረሪ ብሔራዊ ጉባዔን አስመልክቶ ያስተላለፈውን ውሳኔ በሚመለከት ባደረገው ውይይት፣ የሐረሪ ክልል ምርጫ አፈጻጸም ሒደት በክልሉ የሐረሪ ጉባዔና የፌዴራል ሕዝብ ተወካይ ልዩ ውክልና ምርጫ፣ የመራጮች ምዝገባ እየተካሄደ እንዳልሆነና ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሚያዚያ 1 ቀን 2013 ዓ.ም. የሐረሪ ጉባዔን አስመልክቶ ያስተላለፈው ውሳኔ፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መጋቢት 6 ቀን 1987 ዓ.ም. ባካሄደው 102ኛ መደበኛ ስብሰባ ያሳለፈው ውሳኔ፣ የክልሉ ሕገ መንግሥትና የምርጫ ሕጉን በሚፃረር መንገድ የተሰጠ መሆኑን፣ ሕገ መንግሥታዊ ይዘት እንደሌለውና ከሕግ አንፃርም ተቀባይነት እንደሌለው ድምዳሜ ላይ መድረሱን ገልጿል።
ምርጫ ቦርድ ሚያዚያ 1 ቀን 2013 ዓ.ም. የሐረሪ ብሔራዊ ጉባዔ ምርጫን አስመልክቶ ያስተላለፈው ውሳኔ፣ ሕገ መንግሥትዊ፣ ሕጋዊ፣ ፍትሐዊና አመክንዮአዊ እንዳልሆነ፣ እንዲሁም የሐረሪ ክልል ሕገ መንግሥትን ያላማከለ ስለሆነ ከሕግ አንፃር ተቀባይነት እንደሌለው አስታውቋል።
የክልሉ ካቢኔ በውሳኔው የክልሉ ሕገ መንግሥትና የሕግ የበላይነት እንዲከበር፣ እንዲሁም የፌዴራል ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያስተላለፈው ውሳኔ ሊከበር እንደሚገባና እነዚህን ችግሮች ለማረም አግባብነት ያለው አካል ተቋቁሞ ተገቢው የዕርምት ዕርምጃ እንዲደረግ መወሰኑን፣ የክልሉ መንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት በማኅበራዊ ተስስር ገጹ አስታውቋል።