Thursday, June 13, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ለስምንት ዓመታት በኪራይ መጋዘን የተቀመጡ 485 ሺሕ ኩንታል የማዳበሪያ ግብዓቶች ለጨረታ ቀረቡ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ከስምንት ዓመታት በፊት በግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽንና በክልል ማኅበራት በ657 ሚሊዮን ብር የተገዛው 485 ሺሕ የማዳበሪያ ግብዓት፣ ለበርካታ ዓመታት በኪራይ መጋዘን ያለ ምንም ጥቅም ከተቀመጡበት ወጥተው ለጨረታ መቅረባቸው ተነገረ፡፡

በግብርና ሚኒስቴር ትዕዛዝ በ2006 ዓ.ም. የተገዛው ፖታሽ፣ ዚንክና ቦሮን የተሰኙ የማዳበሪያ ግብዓቶች ወደ አገር ውስጥ ገብተው በቀላሉ ተቀይጠው ለአርሶ አደሩ በቅናሽ ዋጋ ለማቅረብ ታስቦ የተገዙ ቢሆንም፣ የታሰበው ዓላማ ሳይሳካ ለብዙ ዓመታት በዓመት ከ2.6 ሚሊዮን ብር በላይ ለመጋዘን ኪራይ እየከፈለባቸው መቆየታቸው ታውቋል፡፡

በወቅቱ የማዳበሪያ ግብዓቶቹ ጥናት ተደርጎባቸው ወደ አገር የገቡ ቢሆንም፣ አገር ቤት ያሉ ፋብሪካዎች ማቀነባበር ባለመቻላቸው በተለያዩ አካባቢዎች በመጋዘን ታሽገው መቆየታቸውን የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ክፍሌ ወልደ ማርያም ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

የማዳበሪያ ግብዓቶቹ የመጠቀሚያ ጊዜያቸው ያለፈባቸው ስላልሆነ፣ ወደፊት መጠቀም ለሚፈልጉ ድርጅቶች እንዴት ማስተላለፍ እንደሚቻል የግብርና ሚኒስቴር ጥናት ማድረጉን አስረድተዋል፡፡

ጥናቱን ተከትሎ በመጀመርያ የጨረታ ማስታወቂያ የቀረበው አንድ ድርጅት ብቻ በመሆኑና የተሻለ ዋጋ ለማግኘት ሲባል ጨረታው ታጥፎ ለሁለተኛ ጊዜ ከወጣ በኋላ ስምንት ተጫራቾች ተሳትፈውበት፣ የመጨረሻዎቹ ሦስት ድርጅቶች ተለይተው ማጣራት እየተደረገ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

ይሁን እንጂ የሚቀርበው የመሸጫ የጨረታ ዋጋ የማዳበሪያ ግብዓቶቹ የተገዙበትን ዋጋ ሊተካ እንደማይችል ዋና ሥራ አስፈጻሚው ጠቁመዋል፡፡

ሦስት ድርጅቶች ያቀረቡት ዋጋ ተከፍቶና ተተንቶኖ ለግብርና ሚኒስቴር የቀረበ መሆኑን፣ ሚኒስቴሩ የቀረበውን ዋጋ ዓይቶ ውሳኔውን በቅርቡ ያሳውቃል ተብሎ እንደሚጠበቅ አቶ ክፍሌ ተናግረዋል፡፡

በተለያዩ መጋዘኖች በኪራይ የተቀመጡ የማዳበሪያ ግብዓቶችን አስመልክቶ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የገቢ፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ  ከኮርፖሬሽኑ የሥራ ኃላፊዎች ጋር ሰኞ ሚያዝያ 4 ቀን 2013 ዓ.ም. ውይይት ያደረገ ሲሆን፣ የማዳበሪያ ግብዓቶች በአስቸኳይ እንዲወገዱ ማሳሰቢያ መስጠቱን ፓርላማው በድረ ገጹ አስነብቧል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች