የአዲስ አበባ ከተማ የእሳትና አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ካሉት ዘጠኝ ቅርንጫፎች በተጨማሪ፣ ሦስት ቅርንጫፎች ሊከፍት መሆኑን አስታወቀ፡፡
የቅርንጮፎቹን ቁጥር ወደ አሥራ ሁለት ከፍ ለማድረግ እንቅስቃሴ የተጀመረ ቢሆንም፣ አዲስ አበባ የሚያስፈልጓት 17 የእሳትና አደጋ ሥጋት ቅርንጫፎች እንደሆኑ፣ የአዲስ አበባ ከተማ የእሳትና አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽነር አቶ ሰሎሞን ፍስሐ ለሪፖርተር ገለጹ፡፡
በቅርቡ ወደ ሥራ የገቡት ሦስት ቅርንጫፎች ኮዬ ፈ˜፣ የካ አባዶና ጀሞ መሆናቸውን የጠቆሙት አቶ ሰሎሞን፣ በ2014 ዓ.ም. የሚጠናቀቁ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡
እንደ አቶ ሰሎሞን ገለጻ፣ አሁን ካሉት ዘጠኝ ቅርንጫፎች በተጨማሪ ሦስት ንዑስ ጣቢያዎች አገልግሎት እየሰጡ ነው፡፡
በዘጠኙም የእሳትና አደጋ ሥጋት ቅርንጫፎች ንዑስ ጣቢያዎችን ለመክፈት እንቅስቃሴ መጀመሩን፣ በአሁኑ ጊዜም በለሚ ኢንዱስትሪ መንደር፣ በእንጦጦና በሸገር ፓርኮች አገልግሎት የሚሰጡ ንዑስ ጣቢያዎች እንዳሉ አስረድተዋል፡፡
በተቀሩት ስድስት ቅርንጫፎች ንዑስ ጣቢያዎች በመክፈት ቁጥራቸውን ከፍ ለማድረግ እየተሠራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ከጊዜ በኋላ ደግሞ ንዑስ ጣቢያዎችን አቅማቸውን ከፍ በማድረግ ዋና ቅርንጫፍ ለማድረግ መታቀዱን አቶ ሰሎሞን ተናግረዋል፡፡
አሁን ካለው የከተማዋ ቆዳ ስፋት አንፃር 17 ቅርንጫፎች ቢያስፈልጉም፣ የአቅም ውስንነት በመኖሩ ለጊዜው ቁጥሩን ወደ አሥራ ሁለት ከፍ ለማድረግ እየተሠራ ነው፡፡
በአሁኑ ጊዜ ንዑስ ጣቢያዎች ሆነው የሚያገለግሉት ደግሞ ራሳቸውን ችለው ቅርንጫፎች ይሆናሉ ብለዋል፡፡ ቅርንጫፎችና ንዑስ ጣቢያዎች የሚገነቡት ለኮሚሽኑ ማስፋፊያ ከተያዘው መደበኛ በጀት መሆኑን ተገልጿል፡፡
በአሁኑ ጊዜ በአዲስ አበባ ከተማ የእሳት አደጋ በተደጋጋሚ እያጋጠመ ሲሆን፣ በወር ውስጥ በአማካይ 53 የእሳት አደጋዎች ተከስቷል፡፡