Monday, September 25, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትከፍተኛ ፉክክር የታየበትና ክብረ ወሰኖች የተሻሻሉበት የአትሌቲክስ ሻምፒዮና

ከፍተኛ ፉክክር የታየበትና ክብረ ወሰኖች የተሻሻሉበት የአትሌቲክስ ሻምፒዮና

ቀን:

ለዓመት በውድድር ድርቀት ተመተው እንዲሁም በመደበኛ ልምምድ ተሰላችተው የነበሩት አትሌቶች የዓመት ልፋታቸውን በጥቂቱም ቢሆን በዘንድሮው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ራሳቸውን መገምገም ችለዋል፡፡ ብሔራዊ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን የ50ኛ ዓመት ወርቅ ኢዮቤልዩ ሻምፒዮና ከመጋቢት 28 እስከ ሚያዚያ 3 ቀን 2013 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ስታዲየም አከናውኗል፡፡

በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት በርካታ ስፖርታዊ ውድድሮችን ማከናወን ቀላል ባለመሆኑ በርካታ ውድደሮች ሲሰረዙ ሰንብተዋል፡፡ ቀድሞ በዓመት ውስጥ በርካታ የቅድመ ማጣሪያ ውድድሮች ያስተናግድ የነበረው የአትሌቲክስ ፌዴሬሽንም ውድድሮችን ለመሰረዝ ተገዷል፡፡

በዚህም ምክንያት በተለይ በዓለም አቀፍ ውድድሮች ላይ የመሳተፍ ዕድል የሌላቸውን ተተኪ እንዲሁም ታዳጊ አትሌቶችን ህልም ያጨለመ ወቅት ነበር፡፡ እሑድ ሚያዝያ 3 ቀን የተጠናቀቀው የዘንድሮ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ለበርካታ አትሌቶች የውድድር ዕድል ከመፍጠርም ባሻገር አዳዲስ አትሌቶችን የማየት አጋጣሚንም ፈጥሮ ነበር፡፡

ሻምፒዮናው በአጭር፣ በመካክለኛና ረዥም ርቀት እንዲሁም በሜዳ ተግባራት ላይ ክለቦችን፣ ከተማ አስተዳደሮችን፣ የግል ተወዳዳሪዎችን፣ የማሠልጠኛ አካዴሚዎችና ተቋማትን አሳትፏል፡፡

በውድድሩ ከ1200 በላይ አትሌቶች የተሳተፉበት ሲሆን ከሜዳ ተግባር ጀምሮ እስከ ረዥም ርቀት ላይ በርካታ ክብረ ወሰኖች ተሻሽለውበታል፡፡ ክብረ ወሰኖቹ የተሻሻሉት በሁለቱም ፆታ ተወዳዳሪዎች ነው፡፡

ከእነዚህም መካከል የኋላዬ በለጠው ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የ10 ሺሕ ሜትር ዕርምጃ 44፡48.96 በማጠናቀቅ፣ ጉዳፍ ጸጋይ ከኦሊምፒክ ቡድን በ5000 ሜትር 14፡49.6 በመግባት፣ እንዲሁም ለምለም ኃይሉ ከኦሊምፒክ ቡድን በ1500 ሜትር 4፡05.09 በመጨረስ ቀድሞ የነበረውን ክብረ ወሰን ማሻሻል ችለዋል፡፡

በወንዶች ያሬድ ተስፋዬ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 400 ሜትር መሰናክል 50.95 ሰከንድ ሲያጠናቅቅ፣ ምንተስኖት አበበ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በመዶሻ ውርውራ 50.72ሜ እንዲሁም ኡታጌ ኡባንግ ከመከላከያ በጦር ውርወራ 72.40ሜ በመወርወር አዲስ ክብረ ወሰን በስማቸው ማስፈር ችለዋል፡፡

ከዚህ ቀደም ከተከናወኑት ሻምፒዮናዎች የተሻለ ዝግጅት ማድረጉን የገለጸው ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ግቡን ማሳካቱን ገልጿል፡፡ በፌዴሬሽኑ የተሳትፎና የውድድር ዳይሬክተር አቶ አስፋው ዳኜ አስተያየት ከሆነ፣ ሻምፒዮናው በሁሉም ርቀቶች አዳዲስና ተተኪ አትሌቶች ተስተውሎበታል፡፡

‹‹ሻምፒዮናው ከምንጊዜም በላይ በስኬት የተጠናቀቀ ነው፡፡ የሁሉም ክለቦች አትሌቶች በቂ ዝግጅት ማድረጋቸውን ተከትሎ በፉክክር የታጀበ ውድድር ነበር፤›› በማለት አቶ አስፋው ለሪፖርተር አስታየታቸውን ሰንዝረዋል፡፡

 በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ከውድድር ርቀው የቆዩት አትሌቶች በሻምፒዮናው ያሳዩት ፉክክር፣ የረዥም ጊዜ ዝግጅት ማድረጋቸውን የሚያሳብቅ እንደሆነም ዳይሬክተሩ ያስረዳሉ፡፡

ሻምፒዮናው ለአትሌቶቹ የውድድር ዕድል ከመፍጠሩም ባሻገር፣ ግንቦት 6 ቀን 2013 ዓ.ም. በሄንግሎ በሚሰናዳው የአኅጉራት ውድድር፣ እንዲሁም ግንቦት 28 በአልጄሪያ የሚከናወነው የአፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ አገራቸውን የሚወክሉ አትሌቶችን ለመምረጥ ያስቻለ መሆኑ ተገልጿል፡፡

በተለይ በአልጄሪያ የሚከናወነው ሻምፒዮና ላይ የሚሳተፉ አትሌቶች፣ ለቶኪዮ ኦሊምፒክ ጨዋታ ለሚኖራቸው ቅድመ ዝግጅት ትልቅ ፋይዳ እንዳለው አቶ አስፋው ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡

በኮቪድ-19 ምክንያት በርካታ ውድድሮች እየተሰረዙ ባሉበት በዚህ ወቅት፣ የአፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮና መደረግ ለኦሊምፒክ ዝግጅት ወሳኝ መሆኑ ሐቅ ቢሆንም፣ የቫይረሱ ዳግም ማንሰራራት የሻምፒዮናው መደረግ አለመደረጉን ጥያቄ ውስጥ እንደሚከተው እየተነገረ ይገኛል፡፡

ሆኖም የዘንድሮ ሻምፒዮና ለኦሊምፒክ ቡድኑ ቅድመ ዝግጅት አንጻር ያለው ፋይዳ ቀላል የሚባል እንዳልሆነ ተገልጿል፡፡ በአዲስ አበባ ስታዲየም በተከናወነው ሻምፒዮና ላይ ከ3.6 ሚሊዮን ብር በላይ ለሽልማት አዘጋጅቶ ኮኮብ አትሌት፣ ኮኮብ አሠልጣኝ እንዲሁም ኮኮብ ዳኞች የሚል የሽልማት ዘርፍ አካቶ ነበር፡፡ በዚህም በወድድሩ ላይ ክብረ ወሰን ማሻሻል የቻሉና ጥሩ ነጥብ መሰብሰብ የቻሉ ሽልማት ተበርክቶላችዋል፡፡

በ50ኛው ዓመት የወርቅ ኢዮቤልዩ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ በሁለቱም ፆታ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 299 ነጥብ አንደኛ፣ መከላከያ 297 ነጥብ ሁለተኛ፣ ኦሮምያ ክልል በ243 ነጥብ ሦስተኛ ደረጃን በመያዝ አጠናቀዋል፡፡

ውድድሩ የኮቪድ-19 ፕሮቶኮል ባሟላ መልኩ የተከናወነ ሲሆን ተሳታፊ ክለቦቹ በግል ሆስፒታሎች ምርመራ ሲያደረጉ እንደነበረና ቫይረሱ የተገኘባቸውም ከውድድሩ ውጪ ሆነዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የቤት ባለንብረቶች የሚከፍሉትን ዓመታዊ የንብረት ታክስ የሚተምን ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ

በአዋጁ መሥፈርት መሠረት የክልልና የከተማ አስተዳደሮች የንብረት ታክስ መጠን...

እንደ ንብረት ታክስ ያሉ ወጪን የሚያስከትሉ አዋጆች ከማኅበረሰብ ጋር ምክክርን ይሻሉ!

የመንግሥትን ገቢ በማሳደግ ረገድ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የሚታመኑት የተጨማሪ እሴት...

ለዓለምም ለኢትዮጵያም ሰላም እንታገል

በበቀለ ሹሜ ያለፉት ሁለት የዓለም ጦርነቶች በአያሌው የኃያል ነን ባይ...