Saturday, May 25, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዓለምየሱዳንና የደቡብ ሱዳን መንግሥታት ከስምምነት ያልደረሱበት የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ከአብዬ ግዛት ይውጣ...

የሱዳንና የደቡብ ሱዳን መንግሥታት ከስምምነት ያልደረሱበት የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ከአብዬ ግዛት ይውጣ ጥያቄ

ቀን:

ደቡብ ሱዳንና ሱዳን በአብዬ ግዛት ይገባኛል ውዝግብ ወደ ጦርነት የገቡት እ.ኤ.አ. በጥር 2011 ነበር፡፡ በነዳጅ ሀብት የበለፀጉት አብዬና ደቡብ ኮርዶፋን ለሁለቱ ሱዳኖች የጦርነት መነሻ ሆነው የዘለቁት ለአራት ወራት ያህልም ነበር፡፡ በሱዳን ሕዝቦች የነፃነት እንቅስቃሴ (ኤስፒኤልኤም) እና በሱዳን መንግሥት ወታደሮች መካከል ከባድ ጦርነትን ያስተናገደችው አብዬ ግዛት፣ በሰሜንና በደቡብ ሱዳናውያን መካከልም የመቃቃር ምክንያት ሆናለች፡፡

በግዛቲቱ የተፈጠረውን ግጭት ለማርገብ ሥፍራውን ከሁለቱም ወገኖች ነፃ የማድረግ ሥራ በቅድሚያ የተመቻቸው በቀድሞው የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ታቦ እምቤኪ ሲሆን፣ ‹‹ዘ አዲስ አበባ አግሪመንት ኦን አብዬ››ም በሁለቱ ሱዳኖች መካከል እ.ኤ.አ በሰኔ 2011 ነበር የተፈረመው፡፡

በአፍሪካ ግጭቶችና አፈታቶች ዙሪያ በርካታ ምርምሮችና ጥናቶች ያደረጉት መሐሪ ታደለ ማሩ (ዶ/ር)፣ በአብዬ ሰላም ማሥፈን፣ የኢትዮጵያ ሚናና አስተዋጽኦ በሚል ባሠፈሩት ጽሑፍ፣ በአብዬ ግዛት ስምምነቱን የማድረግ ዋና ዓላማ በሥፍራው የወሰን ማስከበር ሥራ እስከሚከናወን አካባቢውን ከወታደር ነፃ ማድረግ ነበር፡፡ በዚሁ ስምምነት መሠረትም፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰላም አስከባሪ ኃይል ከኢትዮጵያ ወታደሮች ተዋቅሮ በሥፍራው እንዲሠፍር የሚለው ይገኝበታል፡፡   

- Advertisement -

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ፀጥታው ምክር ቤት፣ ለተባበሩት መንግሥታት ኢንትሪም ሴኪዩሪቲ ፎርስ ፎር አብዬ (ዩኒሳፍ) በሰጠው ኃላፊነት መሠረትም ሲቪል ፖሊሶችን ጨምሮ 4,250 የኢትዮጵያ ወታደሮች ኃላፊነት ተሰጥቷቸው በዚያው ዓመት በአብዬ ግዛት ሰላም የማስከበር ሥራን ጀምረዋል፡፡

የሱዳንና የደቡብ

 

በወቅቱም የካርቱምም ሆነ የጁባ ባለሥልጣናት በኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ወታደሮች ላይ እምነት መጣላቸውን በመግለጽ የኢትዮጵያ ኃይል በሥፍራው ሰላም እንዲያሠፍን ባቀረቡት ጥያቄ መሠረት ዩኒሳፍ ወደ ሥፍራው ተሰማርቷል፡፡ ላለፉት ወደ አሥር ዓመታት ያህል በሥፍራው ሰላም እያስከበረ የሚገኘው የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ኃይል፣ ሱዳንና ደቡብ ሱዳን ዳግም ባቀረቡት ጥያቄ መሠረት ከሁለት ዓመታት ቆይታ በኋላ ወደ 5,326 አድጓል፡፡

በሥፍራው የዩኒሳፍ ሰላም አስከባሪ ከገባ በኋላ ሁለቱ ሱዳኖች በግዛቲቱ ምክንያት ወደ ጦርነት አልገቡም፡፡ በሥፍራው የሠፈነውን ሰላም ለማስቀጠልም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የዩኒሳፍ ሰላም አስከባሪ ኃይል የቆይታ ጊዜን እያራዘመ 2021 ላይ ተደርሷል፡፡

ባፈለው ሳምንት ግን ከሱዳን ካርቱም፣ የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ኃይል ከአብዬ ይውጣ የሚል ጥያቄ ቀርቧል፡፡ ሱዳን፣ የተባበሩት መንግሥታት በሥፍራው እንደሠፍር ዕውቅና የሰጠውን የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ኃይል በሌላ እንዲተካ ጥያቄ ማቅረቧንም የተለያዩ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል፡፡

የአብዬ የይገባኛል ጥያቄ ባልተፈታበትና ድንበር ባልተካለለበት ሁኔታ በደቡብ ሱዳንና ሱዳን ድንበር ላይ የሠፈረው የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ በሌላ እንዲተካ ከሱዳን ካርቱም ጥያቄ የቀረበው የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ኃይል በሥፍራው መኖር ምክንያታዊ አይደለም ከሚል ሐሳብ እንደሚነሳ የተለያዩ ዘገባዎች ያሳያሉ፡፡

የሱዳን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሜሪያም ኤል ሰዲቅ ኤል ማህዲ በካርቱም በሰጡት መግለጫ፣ የኢትዮጵያ ኃይል በሱዳን ምሥራቅ ድንበር አካባቢ እየተጠጋ ባለበት ሁኔታ ስትራቴጂክ በሆነው ሥፍራ የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ መኖሩ አያስፈልግም ማለታቸውን ደባንጋ ሱዳን ዘግቧል፡፡  

ኢትዮጵያ፣ ግብፅና ሱዳን እ.ኤ.አ. በ2015 በኢትዮጵያ ታላቁ የህዳሴ ግድብ ዙሪያ ስምምነት ከደረሱ በኋላ፣ ግድቡ ዕውን እንዳይሆን በሱዳንና በግብፅ በተደጋጋሚ የሚታየው አሉታዊ ዘመቻ ሥር ሰዶ አንዴ አሜሪካ፣ በኋላ የተባበሩት መንግሥታትና የአውሮፓ ኅብረት ባሉበት ዳግም ስምምነት ይደረግ የሚል ሐሳብ ማራመድ ከጀመሩ ዓመት ተቆጥሯል፡፡

ኢትዮጵያ በዚህ ሁሉ አልፋ ዓምና የመጀመርያውን የውኃ ሙሌት ያከናወነች ሲሆን፣ ሁለተኛውን ሙሌት ዘንድሮ ከሰኔ በኋላ መሙላት ትጀምራለች፡፡ ሁለተኛው የውኃ ሙሌት ከመከናወኑ በፊት ‹‹አሞላሉ ላይ መደራደር አለብን፤›› በሚል ግብፅንና ሱዳን የጀመሩት የእንደራደር ዘመቻ እስካሁን አልተሳካም፡፡

ሱዳን ካርቱምም የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ኃይል በግጭት ምክንያት ከሁለቱም ሱዳኖች ወታደሮች ነፃ ከተደረገው አብዬ ግዛት ይውጣልን፣ በሌላ ይተካ ያለችው ባለፈው ሳምንት በኪንሻሳ የነበረው የሦስቱ አገሮች ውይይት ያለስምምነት በተጠናቀቀ ማግሥት ነው፡፡

አል ማህዲ እንደሚሉት፣ ኢትዮጵያ የህዳሴ ግድቡን በተመለከተ ግብፅና ሱዳን እንደሚፈልጉት አልሆነችላቸውም፡፡ በዚህም ምክንያት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በሁለቱ አገሮች ጥያቄ መሠረት ከኢትዮጵያውያን ብቻ ያዋቀረውንና ዕውቅና የሰጠውን ሰላም አስከባሪ ዩኒሳፍ በሌላ እንዲተካ ጠይቀዋል ሲል ዓረብ ኒውስ ዘግቧል፡፡

አብዬ እንጎክ ዲንካ የተባሉትና ከደቡብ ሱዳን ዲንካ ጎሳ ጋር የጠበቀ ግንኙነት ያላቸው ሕዝቦች የሚኖሩባት ግዛት ናት፡፡ በአብዬ ፕሮቶኮል መሠረትና በውስጥ እንደሚታወቀውም የደቡብ ሱዳንና የሱዳን ካርቱም ናት፡፡

እስካሁን መቋጫ ካላገኘው ከዚህ ሥፍራ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሰላም አስከባሪ በፍጥነት እንዲገባ ያደረገው፣ ከዛሬ 10 ዓመት በፊት በሁለቱ ሱዳኖች መካከል በግዛቲቱ ይገባኛል ጥያቄ ከባድ ጦርነት መካሄዱን ተከትሎ ነው፡፡

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ምላሽ

በ2011 በደቡብ ሱዳንና በሱዳን ካርቱም መካከል በአብዬ ግዛት ይገባኛል ጥያቄ የተነሳውን ጦርነት ለማርገብ፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሥፍራውን ከሁለቱም ወገን ወታደሮች ነፃ በማድግ ሰላም አስከባሪ ኃይል አሰማርቷል፡፡ ዩኒሳፍ የተባለው ሰላም አስከባሪ ኃይል ሙሉ ለሙሉ የተዋቀረው በኢትዮጵያ ወታደሮች ሲሆን፣ ያለፉት አሥር ዓመታትንም በአካባቢው ሰላም ሲያስከብር ቆይቷል፣ አሁንም በሥፍራው ይገኛል፡፡

ይህ ሰላም አስከባሪ ከአካባቢው ይውጣልኝ ስትል ሱዳን ካርቱም ባለፈው ሳምንት ጥያቄ ማቅረቧን ተከሎት፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መልስ፣ መጀመርያ አገሮቹ ችግራቸውን በሰላም ከሚፈቱበት ደረጃ አልደረሱምና አሁን ላይ ጥያቄውን መቀበል አማራጭ እንዳልሆነ ነው፡፡

የተባበሩት መንግሥታት ደብዳቤን ጠቅሶ አሶሲየትድ ፕሬስ እንደዘገበው፣ የተመድ ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬስ፣ በአብዬ ግዛት ያሉትን ወደ 3,700 የሚጠጉ የሰላም አስከባሪ ወታደሮች ለመቀነስም ሆነ ሥራቸውን ለማቋረጥ አማራጭ መስጠት እንደማይችሉ አሳውቀዋል፡፡ 3,700 ያህል ጠንካራ ሰላም አስከባሪዎችን የግጭት ቀጣና ከሆነችው አብዬ ግዛት ለማስወጣት በደቡብ በሱዳንና በሱዳን ካርቱም መካከል ልዩነቶች መፍትሔ አላገኙም፣ በዚህ ሁኔታ አማራጭ ውሳኔ ለመስጠት እንደማይችሉም አክለዋል፡፡

በደቡብ ሱዳንና በሱዳን ድንበር በሚገኘው አብዬ ግዛት በሠፈረው ሰላም አስከባሪ ዕጣ ፈንታ ላይ ለመወሰን በሁለቱ ሱዳኖች በኩል ልዩነት መኖሩን ያመለከቱት ዋና ጸሐፊው ጉተሬስ፣ ‹‹ሁለቱ አካላት [ሱዳንና ደቡብ ሱዳን] ከገለጹት በመነሳት ልንቀበለው የምንችለው አማራጭ የለም፤›› ብለዋል፡፡

እ.ኤ.አ. በ2005 ደቡብ ሱዳን ነፃ አገር እንድትሆን ስምምነት ከተደረሰ በኋላ፣ በ2011 ራሷን የቻለች አገር በሆነችው ደቡብ ሱዳንና ሱዳን ካርቱም በአብዬ ላይ ያላቸውን አቋም በሰላም እንዲፈቱ ጥረት ቢደረግም፣ ችግሩ አሁንም ድረስ አልተፈታም፡፡

በአብዬ ከ2011 ጀምሮ ሰላም ለማስከበር የተሰማራው የዩኒሳፍ የአገልግሎት ጊዜ በኅዳር 2020 ሲራዘምም፣ የፀጥታው ምክር ቤት ጉተሬስ ከሱዳን፣ ደቡብ ሱዳንና ኢትዮጵያ ጋር ውይይት እንዲያደርጉ አሳሰቦ ነበር፡፡ ሌሎች የሚመለከታቸው አካላትም የሰላም አስከባሪው በሚወጣበት ስትራቴጂና ቁጥር የመቀነስ አማራጮች ላይ እንዲመክሩበት ብሎ ነበር፡፡ ነገር ግን ጉተሬስ ከሦስቱ አገሮች አመራሮች ጋር የነበራቸውን የጋራ ውይይት በኮቪድ-19 ምክንያት አላደረጉም፡፡ በተናጠል መነጋገራቸውን ግን ዘገባው ያሳያል፡፡

እሳቸው እንደሚሉት፣ የሱዳን መንግሥት በአብዬ የፀጥታ ሁኔታ አስቸጋሪ ቢሆንም፣ ዩኒሳፍ ፀጥታውን በማረጋጋት ወሳኝ ሚና ተጫውቷል፣ ሆኖም የዩኒሳፍ ቁጥር መቀነስ ከግምት እንዲገባ፣ ‹‹ይህም በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ቀስ በቀስ እንዲሆን፤›› ፍላጎት አሳይቷል፡፡ ይህም ሁለቱ ሱዳኖች ጊዜያዊ አስተዳደርና የፀጥታ ሁኔታን በተመለከተ በ2011 የገቡትን ስምምነት ለመተግበር ይረዳቸዋል፡፡ ሁለቱም ወገኖች ከአፍሪካ ኅብረትና ከኢጋድ ጋር ተተኪን ስለማቀናጀት ለመምከርም የአንድ ዓመት ጊዜ ያገኛሉ፡፡

በደቡብ ሱዳን በኩል ግን በአብዬና በምዕራብ ኮርዶፋን አካባቢ ያለው የደኅንነት ሁኔታ የዩኒሳፍን መኖርና መቀጠል ግድ ያደርገዋል የሚል ሐሳብ መሰጠቱን ጉተሬስ አመልክተዋል፡፡

የደቡብ ሱዳን ባለሥልጣናት የንጎክ ዲንካ ጎሳ ከፍተኛ ኃላፊ በ2013 መገደላቸውን፣ በጥር 2020 ከሱዳን ካርቱም ጋር ግንኙነት ባላቸው አርብቶ አደሮች ንፁኃን ላይ የተፈጸመውን ግድያ ለአብነት በማንሳት ዩኒሳፍ በሥፍራው መቀጠል አለበት ብለዋል፡፡

ደቡብ ሱዳን፣ ከሱዳን ካርቱም ጋር የጋራ ተቋም መገንባት የሚለውን ሐሳብም አልተቀበለችም፡፡ ምክንያቱም ከዚህ ቀደም የተደረሱ ስምምነቶች በ2007 እና በ2011 ለተደረጉት ጦርነቶች ምክንያት መሆናቸውን የደቡብ ሱዳን ባለሥልጣናት ማንሳታቸውን ጉተሬስ አስታውሰዋል፡፡ በሁለቱ ወገኖች መካከል መተማመን እንደሌለም አክለዋል፡፡

በኢትዮጵያ በኩል የሁለቱ ወገኖች ፍላጎት ባልተቋጨበት የዩኒሳፍ ከአብዬ ግዛት መውጣት በአካባቢው የደኅንነት አለመኖርን ያባብሰዋል የሚል ሐሳብ ቀርቧል፡፡ ይህ በአፍሪካ ኅብረት በኩል የተስተጋባ አመለካከት ነው ሲሉም ዋና ጸሐፊው ገልጸዋል፡፡

ጉተሬስ በኢትዮጵያና በሱዳን ካርቱም መካከል ያለው ውጥረት እንደሚረግብ ተስፋ አድርገዋል፡፡ ይህ ዩኒሳፍ በሥፍራው አሁን ባለው ጥንካሬ እንዲቆይ፣ የአብዬን ደኅንነትና መረጋጋት እንዲያስጠብቅና ከዚሁ ጎን ለጎን የድንበር ቅኝት እንዲያደርግ ያስችለዋል፡፡

ዩኒሳፍ የተሰጠውን ኃላፊነት መወጣት የማይችልበት ደረጃ ከደረሰ ግን በአብዬ ያለውን መረጋጋት በጉልህ በአሉታዊ መንገድ ይጎዳዋል፡፡  ከዚህ ባለፈም በደቡብ ሱዳንና በሱዳን ካርቱም ግንኙነት መካከል የሚያሳድረው አሉታዊ ተፅዕኖ ከባድ ይሆናል ብለዋል፡፡

ዋና ጸሐፊው እንደሚሉት፣ ዩኒሳፍ የተሰጠውን ኃላፊነት አጠናቆ ሊወጣ የሚችለው፣ በደቡብ ሱዳንና በሱዳን ካርቱም መካከል መልካም ጉርብትና ሲሠፍን ነው፡፡ ለዚህም ሁለቱ አገሮች በአብዬ ግዛት ላይ ያላቸውን ልዩነት በቀጣናው፣ በአፍሪካ ኅብረትና በተመድ ድጋፍ መፍታት አለባቸው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የማዳበሪያ አቅርቦትና ውጣ ውረዱ

በቅፅል ስሙ “The Father of Chemical Warfare” እየተባለ የሚጠራው...

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የትርፍ ምጣኔውን ከ70 በመቶ በላይ አሳደገ

ከሁለቱ መንግሥታዊ ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ...