Saturday, June 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የቀን ሠራተኞች ለአመራርነት ክህሎት የማብቃት ሒደት

በኢትዮጵያ በአበባ እርሻ ላይ በቀንና በማታ ሠራተኝነት የሚሠሩ ከ16 ሺሕ በላይ ሠራተኞች እንዳሉና ከእነዚህም ውስጥ 85 በመቶ የሚሆኑት ሴቶች መሆናቸው ይነገራል፡፡ ዘርፉ ከሚያስገባው የውጭ ምንዛሪ በተጓዳኝ ከፍተኛ የሥራ ዕድል መፍጠር ችሏል፡፡ አበባው ለገበያ እስኪቀርብ ደረስ በእርሻ ላይ እያለ ከፍተኛ ጥንቃቄና ልፋትን ይጠይቃል፡፡ በሌላ በኩል በተለይ የሴት ሠራተኞች ቁጥር ከመብዛቱ አንጻር፣ ለፆታዊ ትንኮሳ የበለጠ ተጋላጭ እንደሚሆኑ ይነገራል፡፡ በሥራ ላይ በሚያጋጥማቸው ያለጊዜ ወሊድ ምክንያት እስከመጨረሻው ከሥራ ገበታቸው እስከመሰናበት ደረጃም ይደርሳሉ፡፡ ሠራተኞቹ ራሳቸውን ከፆታዊ ትንኮሳ መጠበቅ እንዲችሉ፣ መብትና ግዴታቸውን እንዲያውቁና የመሪነት ክህሎታቸውን ማሳደግ እንዲችሉ የሚያግዝ ሥልጠናን ፌርትሬድ አፍሪካ በተባለ በጎ አድራጎት ድርጅት እያገኙ ይገኛል፡፡ ድርጅቱ በስድስት የአበባ እርሻዎች ውስጥ ለሚገኙ ሠራተኞች የሥልጠና ድጋፍ ይሰጣል፡፡ ቅድስት ከበደ በፌርትሬድ አፍሪካ የዲግኒቲ ፎር ኦል ፕሮጄክት የፆታና የአካል ጉዳተኞች ኃላፊ ሲሆኑ፣ ለሠራተኞች ስለተደረገላቸው ድጋፍና ቀጣይ ሥራዎች ጋር በተያያዘ ዳዊት ቶሎሳ አነጋግሯቸዋል፡፡  

ሪፖርተር: – ፌርትሬድ አፍሪካ በአበባ እርሻ ላይ ለተሰማሩ ሠራተኞች ምን ዓይነት ድጋፍ እየሰጠ ይገኛል?

ቅድስት:- ፌርትሬድ በአበባ እርሻ ላይ ለተሰማሩ ሠራተኞች በአምስት የተለያዩ ዘርፎች ላይ ሠራተኞችን መሠረት ያደረገ ድጋፍ ይሰጣል። ይኼምሠራተኛ ማኅበራትን ማደራጀት፣ የሠራተኞችን ጤና እና ደኅንነት መጠበቅ፣ የሠራተኞች ፆታዊ ጉዳዮችን መከታተል እንዲሁም አካል ጉዳተኛ ሠራተኞችን ማካተት ላይ ትኩረቱን አድርጎ ይሠራል። በዋናነትም በስድስት የአበባ እርሻዎች ላይ የሴቶች እኩልነትን መሠረት አድርገን እየሠራን እንገኛለን። ፕሮጀክቱ የሚደገፈው መቀመጫውን እንግሊዝ አገር ካደረገ አልዲ ከሚባል ድርጅትሱፐር ማርኬቶች ላይ ከሚያገኝ የገንዘብ ፈንድ የሚከናወን ነው። ከሱፐር ማርኬቶቹ በሚገኘው የገንዘብ ድጋፍም ለሴቶች የአመራርነት ሥልጠና ይሰጥበታል፡፡

ሪፖርተር:- በአገር ውስጥ በአበባ ምርት ላይ የተሰማሩ ካምፓኒዎች በርካታ የሰውይል እንደሚጠቀሙ ይታወቃል። ተቀጥረው ከሚሠሩት ሠራተኞች አብዛኞቹ የሚሆኑት ሴቶች ናቸው። የእነዚህን ሠራተኞች መሠረታዊ ፍላጎት ከሟሟላት አንፃር እንዲሁም የሚደርስባቸው ፆታዊ ትንኮሳ ከመከላከል አንፃር ምን ተሠርቷል?

ቅድስት:- በአበባ እርሻ ላይ በተሰማሩት ስድስት ድርጅቶች ውስጥ 16 ሺሕ በላይ ሠራተኞች ይገኛሉ። ባቱ የሚገኘው ሼር ኢትዮጵያ 12 ሺሕ በላይ ሠራተኞች አሉት። በስድስቱም የአበባ እርሻዎች ላይ ከሚሠሩት ሠራተኞች ውስጥ 85 በመቶ የሚሆኑት ሴቶች ናቸው። ስለዚህ ሴቶች መበረታትና ማንቃት ዋንኛ ሥራችን ነው፡፡ ድጋፍ ሰጪዎችም ምርቱን ከመግዛት በተጨማሪ ሴት ሠራተኞችን መበረታትና በራሳቸው መተማመን እንዲኖራቸው ድጋፍ ያደርጋል፡፡ ቀዳሚው ሴቶችን ለማነቃቃትና ለማበረታታት የተጠቀሙበት መንገድ ደግሞ ሴቶችን ወደ አመራርነት ለማምጣት ክህሎታቸውን የሚያሳድጉበት ሥልጠና እንዲያገኙ ማድረግ ተጠቃሾች ናቸው፡፡ ይኼም እ.ኤ.አ 2019 ጀምሮ በስድስቱም የአበባ እርሻዎች ላይ የሚገኙት ሴቶችና አካል ጉዳተኞች ኮሚቴ አዋቅረው ሠራተኞቹን ከመረጡ የመሪነት ክህሎትን ሥልጠና እንዲያገኙ ተደርጓል፡፡

ሪፖርተር፡- በስድስቱም አበባ እርሻ ውስጥ ከሚሠሩት ሠራተኞች ምን ያህሉ ዕድሉን አግኝተዋል?

ቅድስት፡- የገንዘብ ድጋፍ የሚያደርገው ድርጅት አበባ ከሚገዛቸው ካምፓኒዎች ውስጥ ለሚሠሩ ሠራተኞች ብቻ ድጋፍ ይሰጣል፡፡ እኛ ግን እንደ ፕሮጀክት ሥልጠናውን  በሁሉም የአበባ እርሻዎች ውስጥ ለሚገኙ ሠራተኞች እየሰጠን እንገኛለን፡፡ በዚህም በመጀመሪያው ዙር 40 ተሳታፊዎችን መርጠን አሥር የሚነበቡ ሞጁሎችን ተሰጥቷቸው፣ 26ቱ አጠናቀዋል፡፡ እነዚህ ሞጁሎች ትኩረታቸው ሰብዓዊ መብትን በተመለከተ፣ በራስ መተማመን፣ ሴቶች በገንዘብ ራሳቸውን እንዴት መቻልና መብታቸውን ማስከበር እንዳለባቸው፣ እንዴት የመሪነትን ክህሎት ማሳደግ እንዳለባቸው ግንዛቤ የሚሰጥ ነው፡፡ ቀድሞ በተለያዩ ጊዜያት ሥልጠና የሚሰጣቸው የነበረ ሲሆን ባለፉት አንድ ዓመት ግን በኮቪድ-19 ምክንያት በተለያዩ የጽሑፍ ቁሳቁሶች ሥልጠናውን ሲያገኙ ቆይተዋል፡፡ በአጠቃላይ በሁለት ዙር ከ66 በላይ ሠራተኞች ሥልጠናውን መውሰድ ችለዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ሥልጠናው በተጨባጭ ሠራተኞቹ ላይ ያመጣው ለውጥ ምንድን ነው?

ቅድስት፡- በአበባ እርሻዎቹ በሺሕዎች የሚቆጠሩ ሠራተኞች እንዳሉ ይታወቃል፡፡ እነዚህም ሠራተኞች በቀንና በማታ በፈረቃ ይሠራሉ፡፡ የአበባ ሥራ በርካታ ችግሮች ያሉበት የሥራ ዘርፍ ነው፡፡ በተለይ ከፆታዊ ትንኮሳ ጋር ተያይዞ በርካታ ችግሮች ያጋጥማሉ፡፡ ለሁሉም ሥልጠናውን መስጠት ባይቻልም የተመረጡ ሠራተኞች ሥልጠና እንዲያገኙ ካደረግን በኋላ፣ በየእርሻዎቹ ላይ ለሚሳተፉ ቀሪ ሠራተኞች ትምህርት እንዲያካፍሉ ይደረጋል፡፡ ይኼም መብትና ግዴታቸውን ከማወቅና ከመጠየቅ ባሻገር ከቀን ሠራተኘነት ወደ አመራርነቱ እንዲመጡ ያስችላቸዋል፡፡ በርካቶችም አበባ ከመልቀም፣ ከማሸግ ወደ መቆጣጠር እንዲሁም ወደ አመራርነት ማደግ የቻሉ ሠራተኞች አሉ፡፡ የአመራርነት ክህሎታቸውን ማሳደግ ችለዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ሠራተኞቹ በሥራ ቦታቸው ላይ ለሚደርስባቸው ትንኮሳ የሚሞግት አለ?

ቅድስት፡- በእያንዳንዱ የአበባ እርሻ ውስጥ ከፆታዊ ትንኮሳዎች ጋር በተያያዘ ችግሮች ሲከሰቱ የሚከታተል ኮሚቴ አለ፡፡ ይኼ ኮሚቴ ቀድሞም የነበረ ነው፡፡ በአንጻሩ ግን እዚህ ኮሚቴ ውስጥ የነበሩ ተሳታፊዎች እኛ በምንሰጠው የክህሎት ሥልጠና ላይ የሚካፈሉ ናቸው፡፡ ይኼ ፆታ ላይ ትኩረቱን አድርጎ የሚሠራው ኮሚቴ፣ ከተለያዩ ተቋማትም ተጨማሪ ሥልጠና ማግኘት ችሏል፡፡ ስለዚህ ሴቶች ላይ የሚደርስ ማንኛውም ፆታዊ ትንኮሳ ላይ ትኩረቱን አድርጎ ይሠራል፡፡ ማንኛውም ችግር ሲፈጠር ቀድሞ ደርሶ ቸግሩን ለመፍታት በአካባቢው ከሚገኙ የፍትሕ አካላትና ፖሊሶች ጋር በጋራ ይሠራል፡፡

ሪፖርተር፡- የመሪነት ክህሎት ማሳደግ ሥልጠና ከመስጠት ባሻገር የዕለት ገቢያቸውን ከማሳደግ አንጻር ምን ተሠርቷል?

ቅድስትከዚህ ሥልጠናዎች በተጓዳኝ ሠራተኞቹ ተጨማሪ የገንዘብ ምንጭ የሚፈጥሩበትን መንገድ፣ የሚረዱበትን ሥልጠና አግኝተዋል፡፡ አዲስ የቢዝነስ ሐሳብ አመንጭተው እንዲያመጡ ካደረግን በኋላ መነሻ ገንዘብ እንዲያገኙ በማድረግ በአበባ እርሻው ላይ ከሚሠሩት ሥራ፣ የራሳቸውን የገቢ ምንጭ እንዲፈጥሩ አድርገናል፡፡ በዚህም የተለያዩ ሥራዎችን በመፍጠር ከአበባ እርሻው ላይ ከሚያገኙት በተጓዳኝ ተጨማሪ የገቢ ምንጭ መፍጠር ችለዋል፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

ለቀድሞ የኢትዮጵያ ጦር ሠራዊት የቆመው የብርጋዲየር ጄኔራል ለገሠ ፋውንዴሽን

የቀድሞ የኢትዮጵያ የጦር ሠራዊት አባላት ለአገራቸው የሕይወት መስዋዕትን ለመክፈል የወደዱ፣ ለአገራቸው ክብር ዘብ የቆሙና ውለታን የዋሉ ናቸው፡፡ እነኚህ የአገር ጌጦች በአገሪቱ በተከሰተው የሥርዓት ለውጥ...

ገደብና አፈጻጸም የሚሹ የአየር ሙቀት መጠንና የካርቦን ልቀት

የአየር ንብረት ቀውሱን ለመቋቋም የዓለም ከተሞች ከንቲባዎችን የሚያስተሳስረው ቡድን (ግሩፕ) ሲ-40 (C-40) ተብሎ ይታወቃል፡፡ ከተቋሙ ድረ ገጽ መገንዘብ እንደሚቻለው፣ አዲስ አበባን ጨምሮ የ40ዎቹ ከተሞች...

ሕፃናትን ከመስማት ችግር የሚታደገው የቅድመ ምርመራ ጅማሮ

‹‹መስማት ለኢትዮጵያ›› በጎ አድራጎት ማኅበር በጨቅላ ሕፃናት ደረጃ የመስማት ችግር እንዳይከሰትና በሕክምናውም ዙሪያ በዘመኑ ሕክምና መሣሪያዎች በመታገዝ ሕክምና ለመስጠት ሚያዝያ 2014 ዓ.ም. የተመሠረተ ነው፡፡...