Friday, June 9, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርከኢኮኖሚው ጋር ያልተግባባ ትውልድና ፖለቲካ

ከኢኮኖሚው ጋር ያልተግባባ ትውልድና ፖለቲካ

ቀን:

በአንድነት ኃይሉ

እኔ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ማንንም ተወቃሽ ማድረግ አልፈልግም፡፡ ሁሉም ለራሱ ትክክል ነው፣ ሁሉም ኢትዮጵያን ሊሠራት የሚፈልገው ካያትና ከተረዳት ቦታ በመነሳት ነው፡፡ ሌላውም እንደዚያው፡፡ ስለዚህ ሁሉም ከቆመበት ቦታ ራሱን ትክክል፣ ሌላውን ደግሞ የተሳሳተ ያደርጋል፡፡ አንዱ ለሌላው የተሳሳተ የሚመስለው በዕይታው ሳቢያ ነው፡፡ አፍሪካ ውስጥ የሚኖሩ ፖለቲከኞችና ሕዝቡ የልዩነታቸው መጀመርያ ይኸው ነው፡፡ ከቆሙበት ብቻ ራስንም ሌላውንም ማየት በየዘመኑ አዲስ አስተሳሰብ ቢመጣም፣ ያለውን ሳያጣጥሙ አዲስ ሐሳብና ፍላጎት ናፋቂ የምንሆነው ለዚህ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት  አብዛኛው አፍሪካዊ መሪ በአንድ እጅ ለሕዝቡ፣ በሌላው እጁ ደግሞ ከሕዝቡ ጋር እየታገለ ይኖራል፡፡ ለዚህ ዋናው ምክንያት ግራ የሚያጋቡ ዕውቀቶችን እንድንኖራቸው መደረጉ ነው፡፡

እነዚህን ዕውቀቶች ፈትሸን ካላስተካከልናቸው ችግራቸው በኑሮ ውድነት ላይ ብቻ የሚያቆም አይደለም፡፡ ስለገንዘብ፣ ስለውጭ ምንዛሪ፣ ስለትርፍና ስለገቢ ወዘተ. ያለን ዕውቀት ካልታረመ ነገ ስህተትን ከማረም ይልቅ፣ ስህተትን በተለየ መንገድ መድገም ይከተላል፡፡ ዛሬ የሰው ገንዘብ ወደ ኢኮኖሚህ ብታስገባ ነገ ጥገኛ ነህ፣ ዛሬ በገዛ ገንዘብህ ኢኮኖሚውን ብትሠራው ነገ ነፃ ሰው ነህ፣ ዛሬ የሰው ገንዘብ ወደ ኢኮኖሚህ ብታስገባ ድህነት መልኩን ይቀይር ይሆናል እንጂ አሁንም ደሃ ነህ፡፡ ዛሬ ባቡር ገዝተህ ብታስገባ ነገ መለዋወጫ ይቸግርሃል፡፡ ነገር ግን ዛሬ ባቡር ባይኖርህም ለመሥራት ብትነሳ ነገ ይኖርሃል፡፡ ባቡርህን ስትሠራው ሥራ ትፈጥራለህ፣ ተፈጥሮህን ትጠቀማለህ፣ ለሕዝብህ በቀላሉ ታዳርሳለህ፡፡ ስትገዛና ስትሠራ መንገዱም፣ ግብዓቱም ውጤቱም የተለያየ ነው፡፡ ስትገዛ ሥራ አትፈጥርም፣ ተፈጥሮህን አትጠቀምም፣ የድህነት መልኩን መቀየርህ ብቻ ነው ትርፍህ፡፡ ሕዝብህ ግን ተምሮ እንዳያስብ፣ እንዳይሞክር፣ ስደተኛ እንዲሆን ማድረግ ብቻ ሳይሆን አገር ለመባል ክብርና ሞገስ ያሳጣታል፡፡ የሰው ገንዘብን ላለመፈለግ ዛሬ ብንቆርጥ ነገ የራሳችን ነገር ይኖረናል እንጂ፣ ለመበደርም ለማበደርም የማትመች አገር እስከመባል አያደርሰንም፡፡

ትናንት የውጭ ምንዛሪን የምናይበት መንገድ ወይም የሰው ገንዘብ የምንፈልግበት ምክንያት ዛሬም ያው ከሆነ፣ ትናንት የሰው ገንዘብ የሚያስፈልገን መጠን ዛሬ ላይ ያው ከሆነና ቆም ብለን ካላስተካከልነው፣ እንደ አንዳንድ አገሮች በሰው ገንዘብ ሲያመርቱና ሲገዙ ቆይተው ገንዘባቸውን አጫዋች ብቻ አድርገውት ኖረው በድንገት የሰው ገንዘብ ሲከለከሉ በአንዴ የውድቀት ቁልቁለትን ከተያያዙት መማር ካልቻልን፣ ነገ የኛም ዕጣ እሱ ነው፡፡ ምንጊዜም በሰው ገንዘብ የተገነባ ኢኮኖሚ መጨረሳው የውርደት ተገዥ ነው የሚያደርገው፡፡ ዛሬ በርካታ አገሮች ገንዘባቸው ረክሶ  ገንዘብ አላቸው ወይ እስከመባል የደረሱትና የገዛ ገንዘባቸውን እንደ ሸቀጥ ያዋረዱት፣ በኢኮኖሚያቸው  ውስጥ የሰው ገንዘብን ያስገቡበት መጠን የተሳሳተ ስለነበር ነው፡፡

አንድ አገር በሰው ገንዘብ አምርታ በራሷ ገንዘብ የምትሸጥበት ፐርሰንት፣ በሰው ገንዘብ ገዝታ በራሳ ገንዘብ የምትገበያይበት ሥርዓት በገዛ ገንዘቧ ከምታመርተውና ከምታገበያየው ምርት ጋር የማይተሳሰርና የማይነፃፀር ከሆነ ተራ ስህተት ብቻ አይደለም፡፡ በስመ ልማት ብቻ ፋብሪካ እየተከሉና በሰው ገንዘብ ግብዓት እያሟሉ ምርትን በአገር ውስጥ ማገበያየት የአገርን ገንዘብ በአፍጢሙ ነው የሚደፋው፡፡ የአገር ህልውናም የዚያኑ ያህል ጥገኛ ይሆናል፡፡ በሰው ገንዘብ ጥገኛ የሆነች አገርን  የሚመራ መሪ  በሁለት እጁ ለሕዝቡ መሥራት ወይም ከሕዝቡ ጋር መሥራት አይችልም፡፡

አንዳንድ ምሁራን ኢትዮጵያ በሚቀጥሉት ዓመታት የውጪ ምንዛሪ ግኝቷ በዚህን ያህል ከፍ ካላለ፣ ወይም የውጪ ምንዛሪ ለማግኘት ይህንን ካላደረገች ጉዷ ፈላ ይላሉ፡፡ እኔን ግን እነሱ የገባቸውና ያልገባቸው ነገር ምን እንደሆነ ይምታታብኛል፡፡ ምክንያቱም የእኛ ትልቁ ችግራችንና ለዚህ ያበቃን የሰው ገንዘብ ነው፡፡ አገራችን ከተገቢው በላይ  የሰው ገንዘብ ጥገኛ መሆኗና በአገር ውስጥ ኢኮኖሚ ከሚያስፈልገው በላይ የሰው ገንዘብ መግባቱ ነው ሥራ አጥ፣ ደሃና ተረጂ ወዘተ. ያደረገን፡፡  እኛ የራሳችን ገንዘብ ያለን ኢትዮጵያውያን ነን፡፡ የአገራችንን ኢኮኖሚ በገዛ ገንዘባችን የምንገነባውና የምንመራው እንጂ፣ የሰው ገንዘብ የሚያስፈልገን ከሆነ መሆን ያለበት ከአገሮቹ ጋር በምንፈጥረው የጋራ ፍላጎት ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ በጋራ የምንወስነው እንጂ ለእኛ መኖር መሠረታዊ ስለሆነ ከሆነ ችግር አለ፡፡ አባቶቻችን ተሳስተው የገቡበት መንገድ ይኖራል፡፡ እኛ ቆም ብለን ከዚህ ስህተት ለመታረም ካልሠራን መዘዙ የከፋ ነው  የሚሆነው፡፡ በሰው ገንዘብ ላይ ጥገኛ  የሆነ ሕዝብ ብቻ ሳይሆን፣ የገዛ ገንዘቡ ለመኖር ምንም የማይጠቅመው ሕዝብ እንሆናለን፡፡ ለመኖርና ለመልማት ዋስትናችን የገዛ ገንዘባችን ነው መሆን ያለበት፡፡ እስከ ዛሬ የሰውን ገንዘብ ለማግኘት መቶ በመቶ ለፍተን ከሆነ ከአሁን በኋላ የሰው ገንዘብ ላለመፈለግ  ከ200 ፐርሰንት በላይ የምንለፋበት ሰዓት ላይ ነን፡፡  

እኛ ኢኮኖሚውን ለመምራት የሰው ገንዘብ ቸገረን የሚል ምክንያት ብድር ታጣ የሚል ሰበብ የሚያከትምበትን መፍትሔ ካልፈለግን ነገሩ ኑሮ ውድነት ላይ ብቻ አይቆምም፡፡ ለዘመናት የተሳሳተ ችግርን መቅረፍ ከባድ ቢሆንም ዛሬ ግን መጀመር  አለብን፡፡ ቢያንስ አሁን ከሚያስፈልገን የሰው ገንዘብ በላይ አለመፈለግ፣ በሰው ገንዘብ ልማትን ማቆም የሚገጥሙንን ችግሮች ለመጋፈጥ መወሰን፣ የሰው ገንዘብ በአዲስ መልክ ወደ ኢኮኖሚው እንዳይገባ ማድረግ የሥራው መጀመርያ ነው፡፡ እኛ ከሰው ገንዘብ ተላቀን ወደ ራሳችን ገንዘብ ለመግባት የግብይት ሥርዓቱ በገዛ ገንዘባችን ላይ መሥራት አለበት፡፡ በገዛ ገንዘባችን ምግብ ላይ፣ ቤት ላይ፣ ልብስ ላይ፣ ትምህርት ላይ፣ የአገር ውስጥ ቱሪዝም  ላይ፣  ሥነ ጥበብ ላይ፣ ዜጎች እንዲያመርቱና በገዛ ገንዘባቸው እንዲገበያዩ ብናስችል የሰው ገንዘብ ፍላጎታችንን ምን ያህል ይቀንሳል? በዚህ ዘመን የእኛ የቤት ግንባታ በከፍተኛ ደረጃ የሰው ገንዘብ ላይ ጥገኛ እንደሆነ የሚታወቅ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት የሚባክነው ገንዘባችን ሥራ ፈጥሮ ስንት ችግር ይቀርፍልን ነበር ፡፡

 አንድ አገር ገንዘቧን በሥራ ላይ ለማዋል በመሠረታዊነት የሚያስፈልጋት የልማት ፍላጎት ነው፡፡ የልማት ፍላጎት ካለ ሥራ አለ፣ ሥራ ካለ ግለሰብ ገቢ ይኖረዋል፡፡ ግለሰብ ገቢ ካለው ፍላጎት ይኖረዋል፡፡ ፍላጎት ካለ ግብይት አለ ማለት ነው፡፡ እነዚህ ሁሉ ባሉበት አገር ውስጥ ተግባብቶ መኖር ከባድ የሚሆንበት ምክንያት ነው የማይገባኝ፡፡ አንድ አገር ለመልማት ከባድ የሚሆንባት ለሕዝቡ ሥራ ለመፍጠር ምክንያት የሚሆን ፍላጎት ሲጠፋ ነው፡፡ እኛ ዘንድ ደግሞ ያለው የልማት ፍላጎት ተነግሮ አያልቅም፡፡ ይህ ሁሉ ሀብት ባለበት አገር ውስጥ ፍላጎታችንን እርስ በርሱ አስተሳስረን ልማትን ላለመፍጠር ትልቁ ምክንያት የሆነብን፣ በፍላጎቶቻችን መሀል የሰው ገንዘብ ጣልቃ ማስገባታችን ነው፡፡ ይህ ገንዘብ ያደረገልንን ነገር ብንገመግም ደሃና ባለዕዳ አደረገን፣ ያለንን እንዳናይና እንዳንጠቀም፣ ሠራተኞች ሳይሆን ገዥዎች እንድንሆን አደረገን እንጂ ምንም የጠቀመን የለም፡፡ በዓለም ላይ በሰው ገንዘብ የለማ አገር የለም፡፡ አገር የምትለማው በዕውቀት ነው፡፡ ገንዘብ የሚያስፈልገው ተራ በሆነ አነጋገር ግብይትን ለመፍጠር ነው፡፡ ገንዘብ አያለማም፣ ገንዘብ ለድህነት ምክንያት መሆን አይችልም፡፡

በእኔ እምነት አንድ መሪ አገሩን በገዛ ገንዘቡ ብቻ የመምራት መብት ነው ያለው፡፡ አንድ ሕዝብ ከገዛ ገንዘቡ ውጪ የመጠየቅ መብት የለውም፡፡ አገሩ እንዴት እንደምትኖር የማያውቅ ሕዝብና አገሩን ለብቻው የሚመራ መሪ ካልሆንን በስተቀር፣ ከእያንዳንዱ የሰው ገንዘብ ጀርባ ብዙ ኪሳራ አለ፡፡ በዚያ ላይ መቼም ሕዝብ መግባባት አይችልም፡፡ ምክንያቱም ሕዝብ የሚይጠይቀውን አያውቅም፡፡ መሪም ሥራው ‹‹የትም ፍጪው ዱቄቱን አምጪው›› ይሆናል፡፡

 ድሮ አገርን መሪ ነበር የሚመራት፣ ምክንያቱም ዓለም እንደዚህ አልነበረችም፡፡ ብሩህ አዕምሮ ካለውና ሐሳቡ ሁሉ የሚቀድም ከሆነ፣ የሚያስፈልገውን ግብዓት ከገዛ ዕውቀቱና አገሩ የራቀ አይደለም፡፡ ዓለም መንደር በሆነችበት በዚህ ዘመን በዓለም ላይ ደሃ ሕዝብን መምራት ከባድ ነው፡፡ አገሩን ሳይሆን ዓለምን ነው የሚያውቃት፡፡ ሕዝብ አገሩን በሚገባ ካላወቃት መግባባት ከባድ ይሆናል፡፡ ዛሬ ያለን ኢትዮጵያውያን ከመሠረታዊ ፍላጎቶቻችን አንስቶ ቅንጦት ናቸው የምንላቸው ነገሮች እንዴት የእኛ ልናደርጋቸው እንደምንችል ካልገባን፣ ፍላጎታችን ሁሉ ትክክልና ቀላል ከመሰለን ይህ ዕውቀት ለመሪም ለተመሪም አስቸጋሪ ነው፡፡ በዚያ ላይ በመሪውና በተመሪው መካከል ያለው ፍላጎት ልዩነት ምክንያት የሰው ገንዘብ ከሆነ ማን ተጠያቂ፣ ማን ጠያቂ፣ የማን ስህተት ሊሆን ነው፣ ስህተቱንስ በስህትት ልናርመው ነው?

አንድ መሪ የሰው ገንዘብ በምንም ምክንያት ከየትም አምጥቶ ኢኮኖሚ ውስጥ  ከሚያስገባ ችግራችንን ዋጥ አድርገን ነፃ የሚያወጣንን መፍትሔ እንጠብቃለን፣ እንፈጥራን የሚል ሕዝብ ነው ወደ ትክክለኛው ጎዳና መግባት የሚችለው፡፡ የራስ ሀብት አገርን ያሳድጋል፣ ሥራ ይፈጥራል፣ ሥራ ይሰጣል፣ አምራች ያደርጋል፣ ነጋዴ ያደርጋል፣ የኑሮ ውድነት ያመጣል፣ አያመጣም የሚለውን ፈትሹት፡፡ እኔ ግን ለድህነታችን ምክንያቱ የሰው ገንዘብ መልመዳችን ሳንሠራ የምንኖር፣ ሳናመርት የምንሸጥ መሆናችን ነው፡፡ ዛሬም እንደ ድሮው  ሕዝብ ልማትን የሚጠይቀው ሳይሠራ እየተገዛለት እንዲቀርብለት ከሆነ፣ የሰው ገንዘብ ፍላጎታችን ማቆሚያ አይኖረውም፡፡ እንደ ሕዝብ  እዚህ ጋ ቆም ካላደረግነው እንደ አገር መቀጠላችን ከባድ ይሆናል፡፡ ምክንያቱም ፍላጎትና አቅርቦት ማቆሚያ አይኖረውም፣ የኑሮ ውድነቱ በሕዝብ መሀል የሚፈጥረው የሐሳብ ልዩነት ብቻ ያጠፋናል፡፡ ይህ ሁሉ ሕዝብና ፍላጎት ባለበት አገር ውስጥ በማንኪያ የምናገኘውን የሰው ገንዘብ ምን ላይ፣ ለማንስ ልናውለው ነው? የቱን ሠርተን የቱን ልንተወው ነው? ውጤቱና ልማቱ ዘላቂ ይሆናል ወይስ አይሆንም? ዛሬ አሁኑኑ እንደሚያስፈልገን ልናገኘው ለምንችለው ወደ ገዛ ገንዘባችን፣ ፍላጎታችንንና ልማታችንን ካላዞርን ጉዟችን አጥፍቶ ከመጥፋት አይተናነስም፡፡

ዛሬ የገጠመን የኑሮ  ውድነትና የገንዘባችን የመግዛት አቅም መዳከም ምክንያቱ፣ ለዘመናት ገንዘባችንን የማምረት አቅም ስላላለበስነው ነው፡፡ ገንዘባችን የማምረት አቅም ሳይኖረው ምን ዓይነት ሕይወት ሊኖረን ይችላል? የገንዘባችን መርከስና ሌላው ትንሽ ጉዳይ ቢሆንም፣ ውጤቱ ግን ከዚያ በላይ ይሆናል፡፡ አገርን በካሬ ሜትር ለክተው ሊያስረክቡ የደረሱ አገሮች ምሳሌዎቻችን ናቸው፡፡ ቬኑኒዙዌላ ከእኛ በተሻለ ለገበያ ታውለው የነበረ ከፍተኛ የነዳጅ ሀብት እያላት ዛሬ የት ናት፣ ትናንት ገንዘቧን ረስታውና የማምረት አቅም ሳትሰጠው አሁን ለሕዝቧ መሆን አልቻለችም፡፡ ለመገበያየት ገንዘባቸውን በጋሪ ይዘው የሚንቀሳቀሱ አገሮች ምሳሌዎቻችን ይሁኑ፡፡ እኛም ቶሎ ነቅተን አሁኑኑ  በገዛ ገንዘባችን ማምረትና መገበያየት መጀምር አለብን፡፡

ይህ  ሁሉ ሕዝብ  ባለበት አገር ውስጥ በልብስ ማምረት ላይ የተሰማራው ሠራተኛ ቁጥር ዝቅተኛ መሆኑ፣ ልብስ ለማምረት የሚያገለግሉ ግብዓቶች አቅርቦት ዝቅተኛ መሆኑ፣ ቢመረት እንኳ ገበያ አጣሁ የሚል አምራች ማየት ያስገርማል፡፡ ለቤት ግንባታ የሚውል በርካታ ጥሬ ዕቃ ባለበት አገር፣ ለግንባታ የሚሰማራ በርካታ ሠራተኛ እያለ፣ የቤት ፈላጊው ቁጥር ከመቼውም ጊዜ በላይ ከፍተኛ ሆኖ፣ ሥራ መፍጠርና መጠቀም እየቻልን እንቅፋት የሆነብን የሰው ገንዘብ ላይ ካልነቃን፣ ይህ ሁሉ ሕዝብና ባለበት ሥራ ፈላጊ ባለበት አገር ውስጥ ሳያመርቱ መሸጥና አገር ነጋዴ ሆነች፣ ድህነት ሥራ አጥነት፣ ስደትና የመሳሰሉት ቀላል ችግሮች ናቸው፡፡ ዛሬ መንገዳችንን ካላስተካከልን ሌሎች አገሮች ከገጠማቸው ችግር የባሰ ብዙ ነገር ይገጥመናል፡፡ በየመንገዱ እንደ ቀልድ ከቻይና፣ ከቱርክና ከእንግሊዝ… እየተባሉ የሚሸጡ ልብሶች ለአንተ ሥራ ፈጥሮልህ ይሆናል፣ ልጅህን ግን ስደተኛ ያደርገዋል፡፡ ዛሬ ስትለብሰው አምሮውብህ ይሆናል፣ ነገ ልጅህን ሥራ ያሳጣዋል፡፡ እንኳን ጫማ፣ ልብስ፣ ሶፋ እያልን የምናባክነው ሥራ ተፈጥሮ ግብይት የሚባለው ቀርቶ፣ እንደ ቀልድ በየሜዳው የምንተክላቸው ማምረቻዎች ገንዘባችንን ነፃ የማያወጡልን ካልሆነ ቢቀርብን ይሻላል፡፡ ነገ  የአገር ውድመትን ሊያመጡ ይችላሉ፡፡  እንኳን ለጫማና ለልብሱ ይቅርና ልማቱን ገታ ልናደርገው ይገባል፡፡ ምክንያቱም ገንዘባችንን በትክለኛው መንገድ እየተጠቀምንበት ነው ብሎ ማለት አይቻልም፡፡ ገንዘባችንን ለማምረቻነት ሳይሆን ለመግዣነት ነው ያዋልነው፡፡ 

በዚህ ላይ ይህ ሁሉ ሕዝብ ገንዘብን የሚያገኝበት መንገድና ምክንያትም ትክክል አይደለም፡፡ መንግሥት ከሚመሠረትባቸው በርካታ ምክንያቶች አንዱ አገር ያላትን ሀብት በአግባቡ እንድትጠቀምና መፈጠር ያለበትን ሀብት በሙሉ አቅሟ መፍጠር እንድትችል ነው፡፡ አገር በምታዘጋጀው ገንዘብ ሁሉም እኩል መብት ነው ያለው፡፡ አንዱ ከአንዱ የሚለያይበት ምክንያት ቢኖር ገንዘብን ለመጠቀም ያለው አቅምና ምክንያት ነው፡፡ ገንዘብ የጋራ ሀብት ነው፡፡ ሁሉም በፍትሐዊነት መገልገል አለበት፡፡ ስለዚህ ገንዘብ ሕዝቡ ዘንድ የሚደርስበት መንገድና ምክንያት ግልጽ መሆን አለበት፡፡ ድሮ ኢትዮጵያ ገንዘቧን ወደ ሥራ ስታስገባ ለሕዝቡ በምን አግባብ እንዳዳረሰችው አላውቅም፡፡ ዛሬ ላይ የትኛውም ግለሰብ ገንዘብ የሚያገኝበት ብቸኛው መንገድ ገበያ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ትልቅ ስህተት ነው፡፡ ሕዝብ ገንዘብን ከገበያ ውስጥ ብቻ ያግኘው ማለት በአንድ እጅ እንደ ማጨብጨብ ነው፡፡ ስህተቱ እንደሚታየው የዋጋ ንረት ወይም ገንዘብን ለማግኘት ሲባል ወንጀል መብዛቱ ብቻ ሳይሆን፣ ይህንን ሁሉ ሕዝብ እንዳይሠራ፣ እንዳያስብ፣ እንዳይፈጥር፣ በአጠቃላይ  ገበያ ውስጥ የመግባት  ዕድል ያገኘ ግብሰብ ብቻ እየከበረ ሌላው ተመልካች እንዲሆን ማድረግ ነው፡፡ ወይም ይህ ሁሉ ሕዝብ ባለበት አገር ውስጥ ገበያ ውስጥ መግባት የቻለው ብቻ እንዲሠራ፣ እንዲያስብ፣ ሥራ እንዲፈጥር መጠበቅ  ካለው ፍላጎት እኩል ሊጣጣም አይችልም፡፡ በገቢ አለማደግ ሳቢያ የሚፈጠረው ድህነት በማን ህልም ሊካካስ ነው? ለዚህም ነው ድህነቱ አዙሪት የሆነብን፡፡ አንዱን ስንደፍን ሌላው ይቀደዳል፡፡ እዚህ ጋ ስንገነባ እዚያ ጋ የሚፈርስብን፣ አገር ከሕዝብ ቁጥርና ፍላጎት ጋር የተመጣጠነ የግብይት ሥርዓት መፍጠር ባለመቻሏ ስለሆነ ምንም ነገር ትክክል ሊሆን አይችልም፡፡

 የሕዝብ ቁጥር ከፍተኛ በሆነበት አገር ውስጥ ግብይት ውስጥ የገቡ ሰዎች ጥቂት በሆነበት ሁኔታ፣ መንግሥት ትልልቅ ልማቶችን ባከናወነ ቁጥር ጥቂቶች ባለገንዘብ ይሆናሉ፡፡ ግብይት ውስጥ መግባት ያልቻሉና በታማኝነት አገራቸውን  የሚያገለግሉ ተቀጣሪዎች አንገታቸውን እንዲደፉ ነው የሚያደርገው፡፡ ሰፊውን ሕዝብ ባላካተተና በውስን ሰዎች በተዋጠ ግብይትም ይሁን ልማት ጤናማ የሆነ የሀብት ክፍፍል ስለማይኖር፣ ለፍቶ ብቻ መለወጥ ተስፋ ያስቆርጣል፡፡  ስለዚህ ግለሰብ ትኩረቱ ገንዘብ ላይ ብቻ ሆኖ ገንዘብ አድራጊ ፈጣሪ ይሆናል፡፡ ዛሬ በኑሮ ውድነት ስትማረሩ ነገ ከዚያ የባሰ ሕይወት ርካሽ የሆነበት ትውልድ እንዳይመጣ ዛሬውኑ ገንዘብን አድራጊ ፈጣሪ እንዳይሆን አድርጎ መሥራት ያስፈልጋል፡፡

ገንዘብን አድራጊና ፈጣሪ እንዳይሆን ማድረግ የሚቻለው ባለ ዕዳ የሆነ ሕዝብ መፍጠር ሲቻል ብቻ ነው፡፡  አገር ለዜጎች ሁሉ እኩል ነች ማለት የሚቻለው ባዶ የሆነ ሕዝብ ሳይሆን፣ ባለዕዳ የሆነ ሕዝብ ሲኖር ነው፡፡ እኛ እኮ ባለ ዕዳ የሆነ ሕዝብ  እንዲኖር ለማድረግ በርካታ ዕድሎች ያሉን ነን፡፡ ልዩነቱ የተፈጥሮ ሀብት፣ የሕዝብ ቁጥርና ድህነቱ ትልቅ ሀብት ነው፡፡ ላወቀበት ድህነት ትልቅ ሀብት ነው፡፡ ድህነት የሚያሳየው ያልተሠራ ነገር መኖሩን ነው፡፡ የሚሠራ ነገር ካለ ሥራና ግብይት ይኖራል ማለት ነው፡፡ በአገር ውስጥ ያሉ የገንዘብ ተቋማት የተቋቋሙበትን ዓላማ ትንሽ ቀየር ቢያደርጉት ነገን ዛሬ ላይ እየኖረ፣ ዛሬን በሥራ ውስጥ የሚያሳልፍ ማኅበረሰብ መፍጠር ቢቻል ኖሮ  ምን ዓይነት አገር ይኖረን ነበር? እንደ አገር የገንዘብ ኪሳራ የሚባል ወይም ገንበዝ ከየት ይመጣል የሚባል ነገር የለም፡፡ ሁሌም እለዋለሁ ገንዘብ የፋብሪካ ውጤት ነው፡፡ ገንዘብ ትርጉም የሚያጣው በሥራ ላይ የሚውልበት ምክንያት ሲያጣ ነው፡፡ እኛ ደግሞ ይህ ሁሉ ፍላጎት፣ ይህ ሁሉ ተፈጥሮ፣ ሥራ ፍለጋ የሚሰደድ ራሱን አሳልፎ የሚሰጥ ትውልድ ባለበት አገር ውስጥ ተራ የሆነውን ገንዘብ በመጠቀምና በማምረት በሕዝቦች መካከል ግብይት መፍጠር ይከብዳል ማለት አሳማኝ ያልሆነ ባዶ ምክንያት ነው የሚሆንብኝ፡፡

 ሕዝብም እንደ ከዚህ ቀደሙ ዛሬም ሳያመርት ይገዛልኝ፣ ሳይሠራ ይሟላልኝ ማለት አይችልም፡፡ በሰው ገንዘብ የመጠቀም ልማዱን ቆም አድርጎ በገንዘቡና በዕውቀቱ መኖር ካልወሰነ፣ ሰው ሆኖ ከሰው በታች ለመኖር ካላማረው በስተቀር ሳይሠራ የሚሟላለት፣ ሳያመርት የሚሸጠው ሳይኖረው የሚፈልገው ምንም ነገር የለም ሊኖርም አይችልም፡፡ እኛ ግን ከመለማመዳችን የተነሳ ስህተቱ ትክክል ካልመሰለን፣ እንዲህ ውጥንቅጡ ከጠፋበት ሕይወት መላቅጡ ከማይታወቅ የግብይት ሥርዓት መላቀቅ የምንችለው ስንወስን ነው፡፡ የፖለቲካችን አለመረጋጋትና ሁሌም አዲስ የሚሆነው ፖለቲካውም፣ ሕዝቡም ከኢኮኖሚው ጋር አለመግባባታቸው ነው ሕዝብና ሕዝቡ የማይግባባው ተመጋጋቢ ስላልሆነ ነው፡፡ የአንዱ መኖር ለሌላው ያለው ዋጋ በሰው ገንዘብ፣ ዕውቀት፣ ሥራ፣ ወዘተ. ተተክቷል፡፡ በአንድ አገር ውስጥ ያሉ ሕዝቦች የሚያግባባቸው የግል ፍላጎትና የጋራ ግብይት የሚስተናገድበት የጋራ ገበያ ሲኖራቸው ነው፡፡ ይህ ሲሟላ የበለጠ ተጠቃሚ እዲሆኑ የጋራ ግብዓት የሆነች ትልቅ አገር እንደምታስፈልጋቸው ያምናሉ፡፡ ያኔ የጋራ የሆነችውን አገር ለመሥራት በአንድነት ይቆማሉ፣ ይታገላሉ፡፡ ይህንን ባላደረግንበት አገር ውስጥ የጋራ ራዕይ ያለው ትውልድ ከየት ይመጣል? የሥራን ጣዕም ሳያውቀው የአገርን ጣዕም እንዴት ሊያውቀው ይችላል? ከሥራ በፊት ሁሉም ነገር ገንዘብ አገርም በገንዘብ ብቻ የምትሠራ ትመስለዋለች፡፡

ሁሉም ነገር ገንዘብ ብቻ ከሚመስለው ትውልድ ጋር መግባባትም ሆነ ፖለቲካዊ አስተሳሰብ ለማራመድ ከባድ ይሆናል፡፡ ያውም የሰው ገንዘብ በዘመናችን አንዳንድ ፖለቲከኞች ሰውና አገር ጠል የሆኑበት ምክንያት፣ ሁሉንም ነገር በገንዘብ ዓይን ስለሚያዩት ነው፡፡ ፖለቲከኛ ሆኖ ዓላማውንና ዓለምን  ያለ ሰው እንዴት እንደሚያየው  አይገባኝም፡፡ ዓላማ ማለት ሰው ነው፣ ዓለም ማለት ሰው ነው፡፡ ዓላማውና ዓለም ሰው የሆነበት ፖለቲከኛ ጠላት የለውም፡፡ ምክንያቱም ለዓላማው ግብዓት ሊሆነው የሚችለውን ሀብት እንዴት ጠላት ሊያደርገው ይችላል? ዓላማው ሥልጣን ብቻ የሆነበት ካልሆነ በስተቀር፣ ዓላማውን ለማሳካት ግብዓት የሚሆነው ምን እንደሆነ የማያውቅ ካልሆነ በስተቀር፣ ግብዓት ሳይኖረው እንዴት ከግቡ ሊደርስ ይችላል? በአገራችን በርካታ በጠላትነት የታለፉ የፖለቲካ ታሪኮች አሉን፡፡ ከጥንት ጀምሮ በጠላትነት ስትፈላለጉ፣ ስትጋደሉና ስትሞቱ እዚህ ደርሰናል፡፡ ከሞታችሁ ምን አተረፍን? ዛሬስ ከማን ሞት ምን ልናተርፍ ነው?

ሌላውን ትተን ሁሉም ፖለቲከኞች የልማት ዕቅዳቸው ውስጥ ሰው የሚባል ነገር እንደሌለ ለማወቅ ብዙ መመራመር አያስፈልግም፡፡ ምክንያቱም ሞተዋል፣ ገድለዋል፣ ተጣልተዋል፣ ወዘተ፡፡ ዕቅዳቸውን እንዴት እንደሚያዘጋጀት ለማወቅ ባልችልም፣ ለአንድ አገር ልማት መሠረታዊው ነገር  ሰው ነው፡፡ ለአንድ አገር ልማት ሰው ከፋብሪካ በላይ ነው፣ ሰው ገበያ ነው፣ የተፈጥሮ ሀብት ወደ ሥራና ገንዘብ ተለውጦ ወደ ሀብት ለመድረስ ምክንያት የሚሆነው አሁንም ሰው ነው፡፡ ከዚህ ውጪ የሰው ልጅ በምድር ለመኖር ምንም የሚያጓጓ ነገር የለም፡፡

ዓለም ለሰው ነው የተፈጠረችው፡፡  ያለ ሰው ሕይወት የላትም፣ ሰውም ያለ ሰው ሕይወት የለውም፡፡ ዛሬ ዓለም ወደ አንድ መንደርነት ካልመጣሁ ያለችው ሰው ማለት ምን ማለት እንደሆነ የገባቸው፣ ከሰው ምን ማትረፍ እንደሚችሉ የተረዱ፣ መኖራቸው ብቻ ሳይሆን ያላቸው ነገር ዋጋ የሚኖረው ከሰው ጋር ሲኖሩ እንደሆነ የገባቸውና የሰውን ዋጋ የሚያውቁ ስለኖሩ ነው፡፡ እኛ ግን በተቃራኒው እርስ በርስ በጠላትነት እንኖራለን፡፡ ምክንያቱ ደግሞ በውስጣችን አገር እንዴት እንደምትሠራ ያልገባቸው ፖለቲከኞች በመፈጠራቸ ነው፡፡ አገርን ሠርተዋት ሳይሆን በሰው ገንዘብ የሚፈልጉትን እየገዙ አገርን መምራት የሚችሉ መስሏቸው አገር ቀላ ስትታያቸው ፖለቲከኛ ሆኑ፡፡ እኛ ከተጠቀምንበት ያለፈው ታሪካችን በቂ ማሳያ ነው፡፡ ሌሎች አገሮችም ለምንድነው ያልተሳካላቸው ብለን ብንጠይቅ፣  በአንድም በሌላም ምክንያት የብድር ድጋፍና የውጭ ምንዛሪ የሚባል ስህተት ውስጥ ራሳቸውን ስለከተቱት ነው፡፡ 

መቼም እንደ ኢትዮጵያዊ አገሩን ለመለወጥ ዋጋ የከፋለ የለም፡፡ ያ ሁሉ ትውልድ ዋጋ የከፈለው ለምን ይሆን ስንል ዛሬስ መጣላት አቆምን? ከድህነት ወጣን? ተግባባን? ትናንት የተከፈለው መስዋዕትነት ትክክል ቢሆን ኖሮ የተሻገርነውን ታሪካችንን በሚያሳዝን ሁኔታ ባልደገምነው ነበር፡፡ ንግግራችን ሁሉ ስለሌላ በሆነ ነበር፡፡  ጊዜያችን በአንድ ዓይነት ታሪክ ውስጥ መዳከሩን የሚያቆመው በገዛ ገንዘባችን፣ ዕውቀታችን፣ የተፈጥር ፀጋችንንና አገራችንን በገዛ ገቢያችን ላይ ስንሠራ ብቻ ነው፡፡ በሰው ገንዘብ እንኳን አገርን ጊዜን ማሻገር አይቻልም፣ እዚያው ነው የምንዳክረው፡፡  ሕዝባችን  ሀ ብሎ እንደገና ወደ ራሱ መመለስ አለበት፣ ያኔ ነው አገርም ትክክል የምትሆነው፡፡

በትክክል ችግሩ የገባው ፖለቲከኛ አገሪቱን ለመቀየር በርካታ ዓመታት ቢወስዱበትም፣ የአገሪቱ ችግር ምን እንደሆነ የገባው ሕዝብ ለመፍጠር ግን ተጨማሪ ብዙ ዓመታት አያስፈልጉትም፡፡ የአገሪቱ ችግር ምን እንደሆነ የገባው ሕዝብ ደግሞ ለመመራት ምቹ ነው፡፡ አሁኑኑ የሰው ገንዘብ አጠቃቀማችንና የምንፈልግበትን ምክንያት ካላስተካከልን፣ የራሳችንንና የሰው ገንዘብ የምንጠቀምበትን መንገድ ካላስተካከልን፣ የሰው ልጅ ረክሶ ግላዊነት ብቻ ነግሦ ሰው ሰብዕናውን አውልቆ ለገንዘብ ብሎ ምንም ነገር የሚያደርግ ማኅበረሰብ ከመምጣቱ በፊት፣ አገራችንን የምንገነባበትን መንገድ በመፈተሽ የራሳችን ገንዘብ መገልገያ ርካሽ፣ ሁሉም በቀላሉ የሚያገኘውና በእኩልነት የሚጠቀምበት የገንዘብ ሥርዓት ማዘጋጀት ይጠበቅብናል፡፡ ዋናው ማንም ግለሰብ መኖርና የገንዘብ ባለቤት መሆን ከፈለግ ብቸኛው መንገድ ወደ ሥራ መግባት፣ የሐሳብ ባለቤት መሆን ነው ያለበት፡፡ የሐሳብ ባለቤት ለመሆን መማር የግድ ይሆናል፡፡ በዚህ መንገድ የሐሳብ ባለቤት ከሆንክ ማምረት፣ ሥራ መፍጠር፣ ግብይት እንዲፈጠር ምክንያት መሆን ትችላለህ፡፡ የተፈጥሮ ሀብታችንን እድንጠቀም ያስችለናል፡፡

ሕዝቡን ወደ ሥራ ማስገባት የሚችሉ ሰዎች ካሉን ችግራችን ምንድነው? የሰው ገንዘብ ለምንድነው የምንፈልገው? ከልማታችን ተቃራኒ ለመቆም ካልሆነ በስተቀር ማንም ሰው ለሌላው መኖር ምክንያት መሆን ብቻ ነው የሚጠበቅበት፡፡ ሰውን በምክንያት ተጠቅሞ ሰውን ለማኖር የሚጠቅም ዕውቀት የሚሰበሰበው በሕዝብ ቆጠራ ወቅት ነው፡፡ ትክክለኛውን የሕዝባችንን መጠን አውቀን ይህንን ለማድረግ እግዚአብሔር ይርዳን፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ