Friday, December 8, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርየ“ኧረ ንካው… ንካው… በአንገትህ…” ፖለቲካ!

የ“ኧረ ንካው… ንካው… በአንገትህ…” ፖለቲካ!

ቀን:

በሁሴን አዳል መሐመድ (ዶ/ር)

ድምፃዊት ሒሩት በቀለ በጥዑመ ልሳኗ የኢትዮጵያን ሕዝብ እያዝናናች ቁምነገር ያስገበየች እጅግ በጣም ተወዳጅ አርቲስት መሆኗን አድናቂዎቿ ይናገራሉ፡፡ ላስተዋለው ሰው ያለው ቁምነገር ከአርቲስቷ አስደማሚ የዘፈኖቿ ቅላፄ ላይ ብቻ ሳይሆን፣ የዘፈኖቿ ድርሰቶች፣ ስንኞች በሚያስተላልፉት ዘመን ተሻጋሪ መልዕክት ጭምር ነው፡፡ ከአርቲስቷ አንዱ የቀድሞ የዘፈን አልበም ውስጥ “ኧረ ንካው… ንካው… በአንገትህ…” የሚለው ዘፈን የሚያስተላልፈው ጥልቅ መልዕክት የአገራችንን የብሔር ፖለቲካ ይዘትና ዓላማ ጥሩ አድርጎ ስለሚገልጽ፣ የዘፈኑ መልዕክትና የብሔር ፖለቲከኞች በጣምራ በአዕምሮዬ ድቅን ይሉብኛል፡፡ ተወዛዋዡ በአንገቱ ስለሚያስነካው የሞቀ ጭፈራ እንጂ ስለዘፈኑ መልዕክት፣ ስለግጥሙ ስንኞች ቤት መምታት አለመምታት አይጨነቅም፡፡ በዘፈኑ ውስጥ የሚደጋገሙት የሚከተሉት ስንኞች የአገራችንን ጽንፈኛ የብሔር ፖለቲከኞች ባህሪ ምንነት ይጠቁማሉ፡፡

“ኧረ ንካው… ንካው… በአንገትህ፣

ግጥሙ ባይገጥም አንተ ምን ቸገረህ…”

የሚያስገርም ግጥምጥሞሽ ነው እላለሁ፡፡ በብሔር ፖለቲከኞች አፈና ውስጥ እንደ ስኳር ሟሙቶ በጉሮሯቸው ቁልቁል በመፍሰስ ቦርጫቸው ውስጥ ገብቶ የሚንቦጫቦጨው የብሔር/ብሔረሰብ ጽንሰ ሐሳብ፣ ከአገር በቀል ፍቺው ጋር በፍፁም አይገናኝም፡፡ በሕገ መንግሥቱ ላይ የሠፈረው “ብሔር/ብሔረሰብ/ሕዝቦች” የሚለው ቃል አንድምታ፣ የሕዝብ የተከማቹ የዴሞክራሲና የፍትሕ ዕጦት ችግሮች መፍትሔ ማስገኛ መሣሪያ መሆኑ ቀርቶ በባዕድ ፍቺው ሲተገበር ተራ የፖለቲካ ጥቅም ማፍሪያ የመነሻ የፖለቲካ ወረት ሆኗል፡፡ ፖለቲከኞች ለአጉል የፖለቲካ ትርፍ ሲሉ የንፁኃን ዜጎችን አዕምሮ በተለይም የወጣቱን ትውልድ አዕምሮ በዚህ ዝባዝንኬ የፖለቲካ ወረት በመሙላት፣ ዜጎች የጤናማ ፖለቲካ አስተሳሰብ ባለቤት እንዳይሆኑ ጎጂ ተፅዕኖ አድርሰዋል፡፡ የፖለቲካ ሥነ ምኅዳሩ የተዛባ የፖለቲካ ጽንሰ ሐሳብ በንፁህ አዕምሮ ላይ ተዘርቶ የሚበቅልበት፣ አጉል የሆነ የፖለቲካ ትርፍ የሚያካብቱ በሕግ የማይጠየቁ የሚመስሉ እኩያን ፖለቲከኞች እንዳሻቸው የሚጨፍሩበት ሆኗል፡፡

አንዳንድ የጥራዝ ነጠቅ ፖለቲካ ዕውቀት ባለቤቶች ሁነኛ ፖለቲከኛ ሰው በአገር የሌለ ይመስል መርህ አልባ በሆነ አነጋገር “ፖለቲካ ቁማር ነው” በማለት ከደረጃ የወረደ አጉል የፖለቲካ ትንተና በመስጠት፣ ደቀ መዝሙሮቻቸውን በከንቱ ሲያስፈነጥዙ ይስተዋላሉ፡፡ የብሔር ፖለቲካ “ሲያስፈልግ ሕዝብን በማሳመን፣ ሲያስፈልግ በማደናገር” (Convince and Confuse) የሚጓዙበት ጎዳና እንደሆነም በመቃዠት ይጠበባሉ፡፡ የወንድም ፖለቲከኛው ወገን ደግሞ የነገሩትን ሁሉ እንደ ወረደ በመቀበል አሁንም እጁን ለአጉል የፖለቲካ ስብከት በፈቃዱ ሰጥቶ እየተመራ ለመጓዝ የመረጠ ይመስላል፡፡ ይህን የፖለቲካ ማይማን ቅዠት በግልጽ ሲያወግዝ አይሰማም፡፡ በዕውነቱ ይህ መሰሉ ጭፍን ተከታይነትም መርህ አልባነት ነው፡፡

የሁለቱም ወገን ፖለቲከኞች ከእውነታው በመራቅ “ኧረ ንካው… ንካው… በአንገትህ… ግጥሙ ባይገጥም አንተ ምን ቸገረህ…” እያሉ እንደ ችሎታቸው አንገታቸውን እንደ ዋነስ ይሰብቃሉ፡፡ የትም አገር የሌለና ለአገራችን ልዩ የሆነ የፖለቲካ ጭፈራ የሚጨፈርበት የምሽት ዳንኪራ ቤት ውስጥ ያሉ ይመስላሉ፡፡ የተዛባው የብሔር ፖለቲካ ጽንሰ ሐሳብ  ባለፉት 30 ዓመታት በወጣቱ አዕምሮ ውስጥ እንዲሰርፅ በመደረጉ፣ የዚህ መጥፎ ስርፀት ሰለባ የሆነው ወጣት  ትውልድ ቁጥር ቀላል ባለመሆኑ እኩያኑ የብሔር ፖለቲከኞች በወጣቱ ትውልድ ዝምታና ቸልተኝነት ብርድ ልብስ ተሸፋፍነው “ውሾቹም ይጮኻሉ፣ ግመሎቹም ይሄዳሉ” በሚል አጉል ፈሊጥ ስህተትን ከማረም ይልቅ የብሔር ፖለቲካ አድማስን እያሰፉ፣ ይልቁንም በሃይማኖት ፖለቲካ ምርኩዝ እየታገዙ እየተወላገዱ በመሄድ የጋራ የሆነችውን አገራችንን ገፍተው ከገደል አፋፍ ላይ አድርሰዋታል፡፡

ይህ በዚህ እንዳለ የተዛባውን የብሔር/ብሔረሰብ ፖለቲካ ጽንሰ ሐሳብ ከወጣቱ ትውልድ አዕምሮ በማፅዳት ትክክለኛው የብሔር/ብሔረሰብ ፖለቲካ አስተሳሰብ መሬት እንዲይዝ በጎ ተፅዕኖ ለመፍጠር የሐቀኛ ምሁራን ሚና አሁንም በዝቅተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡ በመሆኑም በምሁራኑ አሉታዊ ትብብር ጭምር በመታገዝ “የኧረ ንካው… ንካው… በአንገትህ…” ፖለቲከኞች አጉል የፖለቲካ ትርክት ገዥ የፖለቲካ ሐሳብ ሆኖ ለመቀጠል ሰፊ ዕድል አግኝቷል፡፡ አብዛኛው ምሁር አገሩ ያለችበትን ሁኔታ በሚገባ ተረድቶ አገር የማዳን ጥረት ከማድረግ ይልቅ፣ በገዥው የፖለቲካ ፓርቲ መንደር ውስጥ እያንጎዳጎደ “የዚህና የዚያ ብሔር ምሁራን” በሚል ተጨባጭነት በሌለው ብራንድ (መለያ) በመጠራት፣ አዕምሮውን ለመናኛ ቁሳዊ ጥቅም ከማስገዛት ባለፈ የተዛባውን የብሔር ፖለቲካ ቅኝት በቁርጠኝነት ለማስተካከልና “ሌባን ሌባ” በማለት የአገራችንን ፖለቲካ አቅጣጫ ፈር አስተካክሎ ወደ ጤናማ የፖለቲካ ሥነ ምኅዳር ለመመለስ የሚፈጀውን ጊዜ ለማሳጠር የሚያስችል ድፍረት አጣ፡፡ ይህ የተንቀራፈፈ ሒደት “ለኧረ ንካው… ንካው… በአንገትህ…” ፖለቲከኞች የፖለቲካ ትርፍ ማካበቻ የተራዘመ ዕድሜ ሲያስገኝ በአንፃሩ ምሁራኑን ለትዝብት፣ አገራችንን ለውድቀት፣ ሕዝባችንን ለእንግልት ዳርጓል፡፡

የፖለቲካ ሒደቱ የጽንፈኛ ብሔርተኝነት ፖለቲካ ቁንጮ ላይ የተቀመጡ ፖለቲከኞችን ከጊዜያዊ ጥቅም እስከ ዘላቂ ጥቅም ባለቤት ለመሆን አስችሏቸዋል፡፡ በከፍተኛ ሆቴል ቤቶች በተዘጋጁላቸው የጫጉላ ቤቶች መሽገው ንፁህ አልጋ ላይ ለመተኛት፣ ሳይሠሩ በነፃ እየተቀለቡ በሕዝብ ላብ ለመንደላቀቅና በወታደራዊ አጀብ እየተንቀሳቀሱ በመዝናናት መሰሪና ሥውር ደባቸውን ለማስቀጠል ዕድል አግኝተዋል፡፡ የጋራ መንግሥት ያቋቋሙ እስከሚመስል ድረስ በመንግሥት ሥራ ውስጥ ጣልቃ እስከ መግባት ደርሰዋል፡፡ ሕዝቡ የዕለት ከዕለት ሥራውን ተረጋግቶ እንዳይሠራ፣ እንደ አስፈላጊነቱም መስክ ላይ ባሰማሩት የታጠቀ ኃይል ሕዝቡን ከኖረበት አካባቢ እንዲፈናቀል፣ እንዲጨፈጨፍ በማድረግ ቀስ በቀስ እያደገ ለሚሄድ አገር የማፈራረስ የፖለቲካ ተፅዕኖ ራሳቸውን በተተኪነት እያዘጋጁ ይገኛሉ፡፡

ሌላው ጽንፈኛ ብሔርተኛ በበኩሉ አርቆ አሳቢነት በጎደለው ስሜት “የዜጎችን ሕይወት ማዳን” በሚል ሰበብ የተፈናቀሉ ዜጎች የአያት፣ የቅድመ አያት ቦታቸውን ለቀው ነገድ ቆጥረው ተወልደው ወዳልኖሩበት ቦታ እንዲመጡ ይገፋፋሉ፡፡ ነገር ግን የዚህ ብሔርን መሠረት ያደረገ መገፋፋትና መሳሳብ አንድምታ መዳረሻ በጣም ሩቅ ነው፡፡ በአንድ በኩል የኢትዮጵያዊነት ትስስር ገመድ ላልቶ ሊበጠስ ይችላል፡፡ ቀጥሎም፣ “የማን ቤት ጠፍቶ የማን ሊበጅ፣ የአውሬ መኖሪያ ይሆናል እንጂ” ለሚለው መሪር የቁጭት ስሜት ትግበራ ዜጎችን፣ “የተጎጂ ብሔረሰብ” አባላትን ያዘጋጃል፡፡ ለመሆኑ መንግሥት ለእነዚህ ተፈናቃይ ዜጎች በየሚኖሩበት ቀዬ መድኅን በመሆን ወይም ፀጥታው ወደ ተከበረ ቅርብ ቦታ በጊዜያዊ ማቆያ ውስጥ በማረጋጋት፣ ደኅንነታቸውና በሕይወት የመኖር መብታቸው እንዲከበር ማድረግ እንዴት ሳይቻለው ቀረ? በየጊዜው ተዳከሙ የሚባሉት ጽንፈኞችስ እንዴት እንዲህ አንሰራርተው አሥጊ ለመሆን በቁ? ጽንፈኛ የብሔር ፖለቲከኞቹ ማጣፊያ ሸማ አጠራቸው ሲባል ወዲያው የሚከናነቡት ብልኮ ያገኛሉ፡፡ በቃ አለቀላቸው ሲባል ሥልታቸውን በመቀያየርና የድጋፍ ምንጫቸውን በማባዛት ዳግም ያንሰራራሉ፡፡ የእዚህ አዲስ ጉልበት ምንጭ የአገር ውስጥ የፖለቲካ ሴራ? ወይስ የጎረቤት አገር ድጋፍ? ወይስ የሁለቱም? በዚህም ሆነ በዚያ አገራችንን ላጋጠማት ነቀርሳ ችግር በጊዜው ያለው መንግሥት ኃላፊነትና ተጠያቂነት አለበት፡፡

በአገራችን በ1960ዎቹ በዋነኛነት በተማሪዎች የተቀጣጠለው የብሔር ፖለቲካ ጽንሰ ሐሳብ እንዲዛባ ተደርጎ በዚህ ሁኔታ የጽንፈኛ ብሔርተኞች የኑሮ መተዳደሪያ የገቢ ምንጭ መሆኑ ከልብ ያሳዝናል፡፡ እንዲዛባ የተደረገው የብሔር ፖለቲካ ጽንሰ ሐሳብ የጥቂቶች ፖለቲከኞች የማይነጥፍ የፖለቲካ ኪራይ መሰብሰቢያ እንዲሆን በአገሪቱ ሕገ መንግሥት ላይ የጎላ ሥፍራ ይዟል፡፡ የአገራችን የፖለቲካ ችግር የመነጨው ሕገ መንግሥቱ ላይ ከሰፈረው የተዛባ አንቀጽ መሆኑን በመጠቆም፣ ሕገ መንግሥቱ እንዲከለስ ለሕዝባዊ ውይይት ሁዳድ ይቅረብ ተብሎ ሲጠየቅ፣ ፖለቲከኞቹ ፍፁም የማይነካ መጽሐፍ ቅዱስ/ቅዱስ ቁርዓን አድርገው ሲከላከሉ ይታያሉ፡፡ “ሲጠባ የዋለ ጥጃ ሲያስሩት ይጓጉራል” እንዲሉ ሕዝባዊ ውይይቱ ሊያስከትል የሚችለውን የግልና የቡድን ጥቅም መጓደል በርቀት ለመከላከል በማሰብ፣ በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ላይ ሕዝባዊ ውይይት የሚደረገው በእኛ መቃብር ላይ ብቻ ነው ይላሉ፡፡

በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 39 (አምስት) “ብሔር፣ ብሔረሰብ፣ ሕዝብ ሰፋ ያለ የጋራ ፀባይ የሚያንፀባርቅ ባህል ወይም ተመሳሳይ ልምዶች፣ ሊግባቡበት የሚችሉት የጋራ ቋንቋ ያሏቸው፣ የጋራ ወይም የተዛመደ ህልውና አለን ብለው የሚያምኑ፣ የሥነ ልቦና አንድነት ያላቸውና በአብዛኛው በተያያዘ መልክዓ ምድር የሚኖሩ ናቸው፤” የሚል ሰፍሮ ይገኛል፡፡ ከላይ እንደተጻፈው የሕገ መንግሥቱ አገላለጽ ከሆነ “ብሔር”፣ “ብሔረሰብ”፣ “ሕዝብ” ሦስቱም አንድ ፍቺ ተሰጥቷቸዋል፡፡ ሦስቱም የተገለጹበት መንፈስ አንድ ዓይነት ነው፡፡ የሚለያዩት በጽንፈኛ የብሔር ፖለቲከኞቹ አፍአዊ አገላለጽና ሕዝብን ከሕዝብ ለመለያየት በገሃድ በሚያደርጉት አፍራሽ የተግባር እንቅስቃሴ ውጤት ነው፡፡ አፍራሽ እንቅስቃሴ ለማድረግ እንዲችሉ ነው ቃሉን በአንድ ላይ ደርተው አደናጋሪ የሕገ መንግሥት አንቀጽ ያደረጉት፡፡ በሕገ መንግሥቱ ላይ የቀረበው “ብሔር፣ ብሔረሰብ፣ ሕዝቦች” [Nation/Nationalities/People] ድርት ቃል [Monster Terminology] ተሰነጣጥቆ በሕገ መንግሥቱ ላይ በአግባቡ ሰፍሮ ካልተተረጎመ በስተቀር አሁን ካጋጠመን መደናገር አንላቀቅም፡፡

“ብሔር” ወይም “ብሔረሰብ” በአንድ አካባቢ የሚኖሩ “ሰዎች” የሚባሉ በተስተጋብሮት የሚኖሩ ማኅበራዊ እንስሳትን ለመግለጽ የሚውል ሐሳብ ነው፡፡ በአገር በቀል ፍቺው መሠረት “ብሔር” ማለት አገር ወይም ሕዝብ፣ ብሔረሰብ ደግሞ “የዚያ አገር ሰው” ወይም “ከዚያ ሕዝብ የወጣ ሰው” ማለት ነው፡፡ የፖለቲካ ችግራችንን እንዲህ ያወሳሰበው ለአገራችን ሕዝብ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ አደረጃጀት ፍፁም ባዕድ የሆነው የማርክሲስት/ሌኒኒስት የፖለቲካ ኢኮኖሚ የብሔር/ብሔረሰብ ጽንሰ ሐሳብ ፍቺ፣ በኅብረተሰብ ዕድገት ታሪክ ወቅት ትንተና ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ በዚህም መሠረት “ብሔረሰብ” በፊውዳሊዝም ሥርዓተ ማኅበር ውስጥ የሚገኝ፣ ዝቅተኛ በሆነ የኢኮኖሚ ሕይወት የሚኖርና በዕድገት ኋላቀር የሆነ ኅብረተሰብ የሚገለጽበት ቃል ነው፡፡ “ብሔር” ደግሞ ከፊውዳሊዝም ወደ ካፒታሊዝም ሥርዓተ ማኅበር የተሸጋገረ የዳበረ የኢኮኖሚ ሕይወት ባለቤት የሆነ ኅብረተሰብን ለመግለጽ የተጠቀሙበት ቃል ነው፡፡ ካፒታሊዝም ሲዳብር ኅብረተሰቡን በሥራና በሥፍራ በማሰባሰብ፣ የኅብረተሰቡን ቋንቋ መዳበርና በሳይንስና ቴክኖሎጂ ማደግን በማስከተል በዚያው “ብሔረሰብ” ወደ “ብሔር” ዕድገት ታሪክ ወቅት ይሸጋገራል ብለው ያስባሉ፡፡ ፖለቲከኞቻችን ያለ ምንም ኃፍረት ከኢትዮጵያና ከሕዝቧ ተጨባጭ ሁኔታ ጋር የማይስማማውን ፍቺ መርጠው በማስፋፋት፣ የአገራችንን የፖለቲካ ባህል በማይሆን አቅጣጫ መሩት፡፡

በዚህ የማርክሲስት/ሌኒኒስት የፖለቲካና ኢኮኖሚ ትንተና መሠረት በ1960ዎቹም ሆነ ዛሬ በዕድገት ታሪክ ወቅት አንፃር አንዱ ከሌላው የሚለይ ሕዝብ በኢትዮጵያ የለም፡፡ የሚያርስበትን ሞፈርና ቀንበር ወይም የሚያስጎትትበትን የቤት እንስሳት ዓይነት ከሌላው ብሔረሰብ ቀድሞ የለወጠ ብሔረሰብ በኢትዮጵያ እስካሁን የለም፡፡ በአርብቶ አደሩም አኗኗር ረገድ እንዲሁ ነው፡፡ በአገራችን በአራቱም አቅጣጫ ያለው አርሶ አደርም ሆነ አርብቶ አደር የሚተዳደረው ያው ተፈጥሮ የቸረችውን ሀብት ከሞላ ጎደል ተመሳሳይ በሆነ ኋላቀር የተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀም ሥልት ለፍቶ በማምረት ነው፡፡ በኢትዮጵያ አንዱ ብሔረሰብ በፊውዳሊዝም ሥልተ ምርት ላይ ተቸንክሮ ሲቀር ወደ ካፒታሊዝም ሥልተ ምርት ተስፈንጥሮ የገባ ብሔረሰብ እስካሁን የለም፡፡

ነባር ጽንፈኛ የብሔር ፖለቲከኞች ከባዕድ የተዋሱትንና የጎነጎኑትን አሉታዊ የብሔር/ብሔረሰብ ፍቺ ትተው የአገር በቀል ፍቺውን ቢከተሉ ለአገራችን ይበጃል፡፡ አማራ፣ ትግሬ፣ ኦሮሞ፣ አፋር፣ ሶማሌ፣ ወዘተ. የሚባሉት የኢትዮጵያ ነገዶች በዘመን ብዛት በመጋመድ የጋራ የሆነች አንዲት አገር በመገንባት የብዝኃነታቸውና የአንድነታቸው መገለጫዎች የሆኑ የጋራ እሴቶችን አጎልብተው የኖሩ፣ አንድ የሚያደርጋቸው የጋራ ሥነ ልቦናና የጋራ ታሪክ ያላቸው በዓለም የሚታወቁ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሆነዋል፡፡ የኢትዮጵያን ብሔረሰቦች ከፈጠሩ ነገዶች መካከል በርካታ ነገዶች ዛሬ የሉም፡፡ ያሉትም ቢሆን ተፈጥሯዊና ማኅበራዊ የለውጥ ሒደት ባስከተለው የረዥም ጊዜ መስተጋብር ተነጣጥለው መኖር በማይቻላቸው ሁኔታ እርስ በርስ ተጋምደዋል፡፡ ጠፍተዋል የሚባሉትን ነገዶች ጨምሮ የሁሉም ነገዶች አሻራ አሁን በሚኖረው የኢትዮጵያ ሕዝብ ደም ውስጥ አለ፡፡ አገራችንን ከ5,000 እስከ 6,000 ዓመታት ወደ ኋላ በመጎተት ሕዝብን ከሕዝብ በነገድ በመለያየት አገር ለማፈራረስ የሚደረግ ሙከራ የማይቻል፣ በተገቢው ጊዜ ያልቀረበ፣ የአገራችን ታሪካዊ ጠላቶች የደገሱልን የቆየ የመከራ አጀንዳ ማስቀጠያ ጥረት መሆኑን ሁሉም ዜጋ በተለይም ወጣቱ ትውልድ ሊገነዘብ ይገባል፡፡

በጠቅላላው ኢትዮጵያን ወይም መላውን የኢትዮጵያ ሕዝብ “ብሔር”፣ በአገሪቱ ውስጥ በተወለደበትና ባደገበት ቦታ የሚኖር የተቀራረበ የባህል ገጽታና የተለየ ቋንቋ ያለውን ሕዝብ “ብሔረሰብ” በማለት ብንገልጽ ከአገር በቀሉ ትርጉም ጋር የሚቀራረብ ትርጉም ይሰጣል፡፡ ኢትዮጵያ አንድ ብሔርና የብዙ ብሔረሰቦች አገር ናት ማለት የተሻለ አመክንዮ ነው፡፡ “ሕዝብ” የአንድ ብሔር ወይም ብሔረሰብ ወይም አገር/ክፍለ አገር/አውራጃ/ወረዳ/ቀበሌ ሰዎችን የሚገልጽ ልክ እንደ አገር ተለማጭ [የሚሰፋ ወይም የሚጠብ] የወል ስም ነው፡፡ እንዲሁም “ሕዝቦች” ወይም “Peoples” የሚል የሕዝብ የብዜት ስም በአማርኛም ሆነ በእንግሊዝኛ ቋንቋ መዝገበ ቃላት ላይ ሳይኖር፣ ኢሕአዴግ ሕዝብን ከሕዝብ ለመለያየት የፈጠረው የማደናቆሪያ ቃል መሆኑን ተገንዝበን ቃሉን ከአዕምሯችን አውጥተን መጣል አለብን፡፡ “ሕዝቦች” የሚለው ይህ ክፉ የፖለቲካ ተንኮል-ለበስ የማደናቆሪያ ቃል ቀስ በቀስ “ሕዝብ” በሚለው ትክክለኛው ቃል ተተክቶ መነገሩ/መጻፉ/መነበቡ አይቀሬ ነው፡፡

መሰሪው ኢሕአዴግ ይህን አደንቋሪ ቃል ለኢትዮጵያውያን በድፍረት አስተምሮ ሞተ፡፡ የኢሕአዴግ ወራሽ የሆነው ብልፅግና ፓርቲም የተለመደውን ኧረ ንካው… ንካው… በአንገትህ…” ፖለቲካ በደቀ መዝሙሮቹ አዕምሮ እያሰረፀ መጓዝ የቀጠለ ይመስላል፡፡ የፖለቲካ ድርጅቱ ቀርቶ በግል ጥረቱ ተነሳስቶ ራሱን ለመጠየቅ የተነሳሳ የድርጅት አባል ስለመኖሩም በእርግጠኝነት መናገር አይቻልም፡፡ በነፃነት የሚያስብበትን አዕምሮ ለረዥም ጊዜ ተቀምቶ የወረደለትን ማንኛውንም ሐሳብ እንዳለ እየተቀበለ መጓዝ የለመደ ጥገኛ ሰውን የአስተሳሰብ ለውጥ በድንገት አምጣ ለማለት ይከብዳል፡፡ ምክንያቱም የአገራችን ፖለቲካ የተመራበት ዓላማ ለአብዛኞች በአስገዳጅ የዕለት ዳቦ ማብሰያነት፣ ለጥቂቶች ደግሞ ከፍ ያለ የቡድን ጥቅም በሚያከፋፍል ቋንቋ ተናጋሪነትን መሥፈርት ባደረገ የቡድን መሰባሰብ ዙሪያ እንጂ፣  በአስተሳሰብ ዕድገት ላይ በተመሠረተ በሳል አገራዊ የፖለቲካ ጽንሰ ሐሳብ ላይ አይደለም፡፡

አገራችን በዚህ ደረጃ የዳበረ የፖለቲካ ልምድ  የላትም፡፡ በአገራችን ከተቋቋሙት ፓርቲዎች መካከል አብዛኞቹ ንጥል የነገድ ፓርቲዎች ናቸው፡፡ ኅብረ ብሔራዊ አጀንዳ ይዘው የተነሱ አንዳንድ ፓርቲዎች አሉ ቢባልም ለስም ያህል እንጂ፣ በይዘትና በተግባር ሌላ ናቸው፡፡ “እየጨነቃት ዛር ትሆናለች” እንዲሉ ዛሬ ኅብረ ብሔራዊ ዓላማ አለኝ የሚል ፓርቲ፣ ነገ ከንጥል የብሔረሰብ ፓርቲ ጋር ውህደት ፈጥሬያለሁ ሲል ይደመጣል፡፡ ደግሞ በማግሥቱ ተፋታን ብሎ ያውጃል፡፡ በሌላው ወገን አንድ አገር አቀፍ ፓርቲ እንደ መሠረቱ መስለው ለመታየት የሚፈልጉ ንጥል የነገድ ፓርቲዎች እንኳን ውህድ ሊሆኑ ቀርቶ፣ የተቀላቀለ ባቄላና ጤፍ ያህል እንኳ ድብልቅ ሆነው አይታዩም፡፡ እንደ ጅብ ጎን ለጎን በመሄድ ዳፋቸው እንወክለዋለን ለሚሉት ጭቁን ብሔረሰብ ሕዝብ እየተረፈ ይገኛል፡፡ በመሆኑም መላ ቅጥ በሌለው የብሔር ፖለቲካ ቁማር አዙሪት ኢትዮጵያና ሕዝቧ ይታመሳሉ፡፡

ይህን “ግጥሙ ባይገጥም አንተ ምን ቸገረህ” የሆነ የጽንፈኛ ብሔርተኞች አውዳሚ ፖለቲካ ለመቀየር የአገራችን ምሁራን ዝምታ መሰበር አለበት፡፡ ቢያንስ ራሳቸውን ከነገድ ፖለቲካ አረንቋ በማውጣት ከጭቁኑ የኢትዮጵያ ሕዝብ ጎን መሠለፍ ይጠበቅባቸዋል፡፡ የኢትዮጵያ ምሁራን ግጥሙ በማይገጥም ፖለቲካ አንገታቸውን እየነቀነቁ ህሊናቸውን ከሚያሸጧቸውና በመሣሪያነት ከሚጠቀሙባቸው ጽንፈኛ የብሔር ፖለቲከኞች ዕቅፍ ወጥተው ለህሊናቸው ማደር የሚጀምሩት፣ ሳይማር ያስተማራቸው ጎስቋላ ሕዝብ ሐዘን ተሰምቷቸው አካፋን አካፋ ማለት የሚጀምሩበት ቀን መቼ ይሆን? ይህ ስድስተኛው አገራዊና ሕዝባዊ ምርጫ ለኢትዮጵያ ተንከባላይ የብሔር ፖለቲካ ችግሮች መቃለል አስተዋጽኦ እንዲያደርግ፣ አገር ወዳድ ዜጎች በሙሉ በንቃት ቢሳተፉ የአገራችን የሥቃይና የመከራ ጊዜ ሊያጥር ይችላል ብዬ አስባለሁ፡፡

ኢትዮጵያ በክብር ለዘለዓለም ትኑር!

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...