Tuesday, February 27, 2024

ግብፅና ሱዳንን አጣብቂኝ ውስጥ የከተተው የኢትዮጵያ ጥሪ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

‹‹በግብፅና ሱዳን ላይ ጉዳት እንዲደርስ አንፈልግምጉዳት የሚያደርስ ተግባርም አንፈጽምም ሲሉ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር በተደጋጋሚ ተደምጠዋል፡፡ ለምን አታምኗቸውም?›› 

ከላይ የተመለከተው ጥያቄታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ድርድሮች ላይ ለሚሳተፉት የሱዳን ዋና ተደራደሪና የአገሪቱ የውኃ ሀብትና መስኖ ሚኒስትር ለሆኑት ያሲር አባስ (ፕሮፌሰር)፣ ለአልጄዚራ ቴሌቪዥን ሰሞኑን በሰጡት ቃለ ምልልስ ላይ የቀረበ ነበር። 

ሚኒስትሩ በሰጡት ምላሽ፣ ‹‹አሁን ኢትዮጵያ ይህንን ቃሏን ወደ ተግባር መለወጥ የሚጠበቅባት ወቅት ነው። ምክንያቱም ባለፈው ዓመትም እንደዚያ ብለው ነበር፡፡ ነገር ግን ምን ዓይነት ቅድመ መረጃ ሳይሰጡን 4.9 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ  አነስተኛ የውኃ መጠን በግድቡ ሞልተዋል፡፡ ይህም በሱዳን ዋና መዲና ካርቱም የመጠጥ ውኃ አቅርቦትን አስተጓጉሏል። ዘንድሮም በተመሳሳይ መንገድ ምንም ዓይነት ቅድመ መረጃ ሳይሰጡን ካለፈው ዓመት ሦስት ዕጥፍ ውኃ ለመያዝ አቅደዋል። ታዲያ እንዴት ልናምናቸው እንችላለን?›› የሚል ምላሽ ሰጥተው ነበር። 

የቴሌቪዥን ጣቢያው ጋዜጠኛም መለስ ብሎ፣ ‹‹በግድቡ ምን ያህል የውኃ መጠን ቢያዝ ነው ሱዳንና ግብፅ ከሥጋት ነፃ የሚሆኑት?›› በማለት ይጠይቃቸዋል።

በግድቡ የሚያዘው የውኃ መጠን የልዩነት ምንጭ አይደለም በማለት ምላሽ መስጠት የጀመሩት የሱዳኑ ሚኒስትር፣ ‹‹በግድቡ የሚያዘው የውኃ መጠን የልዩነት ምንጭ አይደለም። የሚያዘውን የውኃ መጠን በተመለከተ የቴክኒክ ጉዳዮች ላይ ተስማምተናልበረቂቅ የስምምነት ሰነዱ ላይም የሰፈረ ጉዳይ ነው። ነገር ግን ኢትዮጵያ ባለፈው ዓመት በግድቡ የያዘችው የውኃ መጠን በጣም ትንሽ ቢሆንም፣ የውኃ ሙሌቱን ያከናወነችው ግን በአጭር ጊዜ በአንድ ሳምንት ውስጥ ነው። በሁለት ወይም በሦስትናአራት ሳምንታት ውስጥ ውኃው ተይዞ ቢሆን ችግር የለውም። ወይም ደግሞ ኢትዮጵያ ውኃ እንደምትይዝ ቀድማ ብታሳውቀን ኖሮ እኛም የጥንቃቄ ቅድመ ዝግጅቶችን ማድረግ እንችል ነበር፤›› ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል። 

የሱዳን የውኃ ሀብት ሚኒስትር ይህንን ቢሉም ኢትዮጵያ በተጠቀሰው ዓመት የመጀመርያ ዙር የውኃ ሙሌት እንደምታካሂድ ለሁለቱም የታችኞቹ ተፋሰስ አገሮች አሳውቃ የነበረ ሲሆንበወቅቱ በድርድሩ ውስጥ ሚና የነበረው የአሜሪካ መንግሥት የገንዘብ ተቋም (ትሬዠሪ) የጋራ ስምምነት ሳይደረስ ኢትዮጵያ የውኃ ሙሌት ማካሄድ የለባትም የሚል መግለጫ አውጥቶ እንደነበር ይታወሳል።

የመጀመርያው ዓመት የውኃ ሙሌቱ በአንድ ሳምንት ውስጥ እንዳልተከናወነ በኢትዮጵያ መንግሥት በኩል ተደጋግሞ የተገለጸ ሲሆን፣ ይህንኑ ጉዳይም የተለያዩ ተቋማት የውጭ የሳተላይት መረጃዎችን መሠረት አድርገው በወቅቱ ማስረዳታቸው አይዘነጋም። 

በተጨማሪም 2012 ዓ.ም. ክረምት ወቅት በኢትዮጵያ ይጥል የነበረው ከመደበኛው ከፍ ያለ የዝናብ መጠን በሱዳን የተለያዩ አካባቢዎች የጎርፍ መጥለቅለቅና የመፈናቀል ጉዳቶችን ጭምር አስከትሎ እንደነበር ይታወሳል። በመሆኑም የሱዳን ሚኒስትር ሰሞነኛ ክስ በድርድሩና በመጪው የውኃ ሙሌት ላይ ጫና ለመፍጠር ሆነ ተብሎ የተሰነዘረ እንደሆነ የኢትዮጵያ ወገን ተደራዳሪዎች ይገልጻሉ። 

የውኃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ስለሺ በቀለ (/) ባለፈው ሳምንት በሰጡት መግለጫ የሱዳን መንግሥትን ክስ ያጣጣሉ ሲሆንየመጀመርያው ዙር የውኃ ሙሌት በሱዳን ላይ የውኃ እጥረት ሊያስከትል ፈጽሞ እንደማይችልና በወቅቱም ሱዳን ከፍተኛ የጎርፍ መጥለቅለቅ አደጋ አጋጥሟት እንደነበር አስታውሰዋል። 

ችግሩ ተከስቶ ከሆነም ሊከሰት የሚችለው ኢትዮጵያ የውኃ ሙሌት በማካሄዷ ሳይሆንበሱዳን ያለው የመጠጥ ውኃ መሠረተ ልማት ላይ የቴክኒክ ችግር አጋጥሞ ሊሆን ስለሚችል በዚህ አካባቢ ፍተሻ ቢያደርጉ የተሻለ ነው የሚል ምክረ ሐሳብ ለግሰው ነበር። 

የሱዳን ሚኒስትር ያሲር አባስ (ፕሮፌሰር) ለአልጄዚራ ቴሌቪዥን ቃለ ምልልስ በሰጡት በአምስተኛው ቀን፣ የሦስቱ አገሮች ድርድር የዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ዋና ከተማ ኪንሻሳ ተካሂዷል። 

በኪንሻሳው ስብሰባ ውይይት የተደረገበት አንኳር ጉዳይ ሦስቱን አገሮች እያደራደረ የሚገኘው የአፍሪካ ኅብረትን ሚና ለማጠናከር በሚል፣ በሱዳንና በግብፅ በኩል የቀረበ አዲስ አማራጭ ነበር። አዲሱ አማራጭ የአፍሪካ ኅብረትን ሚና ለማጎልበት ይባል እንጂየቀረበው አማራጭ ሦስቱ አገሮች ልዩነታቸውን በፍጥነት መፍታት እንዲችሉ የአፍሪካ ኅብረት የአደራዳሪነት ሚና ሌሎች አካላት ተጨምረውበት ወደ ሽምግልና እንዲቀየር የሚጠይቅ ነበር። ከአፍሪካ ኅብረት በተጨማሪም የአውሮፓ ኅብረት፣ አሜሪካና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አሸማጋይ ሆነው እንዲሳተፉ የሚጠይቅ ነበር። 

ይህንን የሱዳንና የግብፅ ሴራ የተገነዘቡት የኢትዮጵያ ተደራዳሪዎች ድርድሩ ወደ አፍሪካ ኅብረት እንዲገባ በማድረግ ከሞላ ጎደል ላለፈው አንድ ዓመት የአደራዳሪነት ሚና የነበራት ደቡብ አፍሪካ በተጨማሪነት እንድትሳተፍ ሐሳብ ያቀረቡ ሲሆንከሦስቱ አገሮች ውጪ ያሉት የሁሉም ባለድርሻዎች ሚና አሸማጋይነት ሳይሆን ሦስቱ አገሮች መግባባት ባልቻሉባቸው ነጥቦች ላይ በአገሮቹ ጥያቄ ሲቀርብላቸው የማማከር ሚና ብቻ እንዲኖራቸው የሚጠይቅ ነበር። 

የግብፅ መንግሥት የኢትዮጵያን ሐሳብ ውድቅ እንዳደረገ የሚገልጹት የኢትዮጵያው ሚኒስትር ስለሺ በቀለ (/)፣ ሱዳን ተመሳሳይ አቋም ቢኖራትም በይፋ እንዳልተናገረች፣ ነገር ግን በዚህ ጉዳይ ላይ ስምምነት ሳይደረስ የኪንሻሳው ስብሰባ መቋጨቱን አስረድተዋል። 

ያለ ስምምነት ከተጠናቀቀው የኪንሻሳው ስብሰባ መልስ የሱዳኑ ሚኒስትር ያሲር አባስ (ፕሮፌሰር)ኢትዮጵያ ስምምነት ሳይደረስ በመጪው ክረምት ሁለተኛውን ዙር የውኃ ሙሌት ለማካሄድ ዝግጅት እያደረገች እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ለታችኞቹ የዓባይ ተፋሰስ አገሮች በቅድሚያ ሳታሳውቅና ድርደሩን በማካሄድ ስምምነት ላይ ሳይደረስ ኢትዮጵያ የውኃ ሙሌት ማካሄድ እንደማትችል፣ ኢትዮጵያ ይህንን ካደረገች የሱዳን መንግሥት የሚደርስበትን ጉዳት ለመቀልበስ ዓለም አቀፍ ሕግን መሠረት በማድረግ ሁሉንም አማራጮች ተግባራዊ እንደሚያደርግ ተናግረው ነበር።

በግብፅ መንግሥት በኩልም ተመሳሳይ መግለጫዎችን በማውጣት፣ ኢትዮጵያ ስምምነት ሳይደረስ በመጪው ሐምሌ ወር ሁለተኛውን ዙር ማካሄድ አትችልም ብሏል። 

‹‹ከግብፅ የውኃ ድርሻ አንድ ጠብታ መውሰድ አይቻልምይህ የግብፅ ብሔራዊ ደኅንነትን የተመለከተ ቀይ መስመር ነው። የግብፅ የውኃ ድርሻ ከተነካ የአካባቢውን ሰላም ሊደፈርስ ይችላል፤›› የሚል ዛቻና ማስፈራሪያም በግብፅ ፕሬዚዳን አብዱልፈታህ አልሲሲ በይፋ መነገሩ ይታወሳል።

ሁለቱን አገሮች አጣብቂኝ ውስጥ የከተተው የኢትዮጵያ ጥሪ

ኢትዮጵያ ሁለተኛውን የውኃ ሙሌት በዘንድሮ የክረምት ወቅት እንዳታካሂድ በግብፅናሱዳን በኩል የተለያዩ ዲፕሎማሲያዊ ጫናዎችና ማስፈራሪያ ያዘሉ መግለጫዎች ቢወጡምየኢትዮጵያ መንግሥት ከኪንሻሳው ስብሰባ መልስ ለሁለቱ አገሮች በላከው ደብዳቤ በመጪው ክረምት የውኃ ሙሌት እንደሚካሄድ በማሳወቅ ሁለቱም አገሮች የሙሌቱ አካሄድን ምንም ዓይነት ጉዳት እንደማይደርስባቸው መተማመኛ ያገኙ ዘንድ፣ የውኃ ኃይል ማመንጫ ግድብ አስተዳደርን የሚረዱ ባለሙያዎችን መርጠው እንዲወክሉና ሙሌቱን በተመለከተ የመረጃ ልውውጥ እንዲደረግ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ላይ ጥሪዋን አቅርባለች። 

ግብፅና ሱዳን ዘንድሮ የሚካሄደውን የውኃ ሙሌት የተመለከተ መረጃ ለመለዋወጥ እንዲረዳ አንድ አንድ ባለሙያዎችን እንዲመርጡ የጠየቀች ሲሆንበሁለቱ አገሮች ከሚወከሉት ባለሙያዎች ጋርም በአካል ወይም በበይነ መረብ አማካይነት ካሉበት አገር ሆነው የመረጃ ልውውጥ ለማድረግ ኢትዮጵያ ፅኑ ፍላጎት እንዳላት ይገልጻል።

ኢትዮጵያ ይህንን ጥያቄ ያቀረበችው ከዚህ ቀደም በሦስቱ አገሮች የተወከሉ ገለልተኛ የባለሙያዎች ቡድን ባቀረቡትና ስምምነት በተደረሰበት ምክረ ሐሳብ መሠረት እንደሆነ በላከችው ደብዳቤ አስታውቃለች።

ቀጣዩን የውኃ ሙሌት የተመለከተ የመረጃ ልውውጥ ለማድረግ ሁለቱ አገሮች ባለሙያዎችን መርጠው ቢያሳውቁ ትክክለኛ የመረጃ ልውውጥ ሥነ ሥርዓት ለመዘርጋት እንደሚጠቅም፣ አጠቃላይ ስምምነት እስኪደረስም በሦስቱ አገሮች መካከል መተማመንን ለመገንባት እንደሚረዳ ኢትዮጵያ ለሁለቱ አገሮች የውኃ ጉዳይ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች በላከችው ደብዳቤ አስታውቃለች።

ኢትዮጵያ ለሁለቱ አገሮች የላከችውን ደብዳቤ አስመልክቶ ሪፖርተር ያነጋገርናቸው ለጉዳዩ ቅርብ የሆኑ አንድ የኢትዮጵያ ባለሥልጣንይህ ደብዳቤ ግብፅና ሱዳን ሁለተኛውን ዙር የውኃ ሙሌት ለማስቆም አቅደው የሚያደርጉትን ዘመቻ የመቀልበስ ውጤት እንደሚያስከትል ታስቦ የተላከ መሆኑን ገልጸዋል።

ሁለቱም አገሮች ደብዳቤው ሲደርሳቸው ምን ሊመልሱ እንደሚችሉ በኢትዮጵያ በኩል አስቀድሞ እንደተገመተ የሚገልጹት እኚሁ ባለሥልጣንምናልባት በሱዳን በኩል ጥሪውን የመቀበል ፍላጎት ሊኖር እንደሚችል ግንዛቤ እንደነበርም አስረድተዋል። 

በሱዳን መንግሥት በኩል ካለፈው አንድ ዓመት ተኩል ወዲህ በገሀድ የአቋም ለውጥ እንደታየው፣ በሱዳን ላይ ይደርሳል የተባለውን ጉዳት በግልጽ ለይቶ የማያስረዳና ተለዋዋጭ እንደሆነ የሚጠቅሱት ባለሙያው፣ ‹‹የሱዳን ባለሥልጣናት በቋሚነት የሚገልጹት አንድ ነገር አለ ከተባለ ቅድመ ማስታወቂያ ሳይሰጥ የሚደረግ የውኃ ሙሌት፣ በሱዳን ላይ ጉዳት ያደርሳል የሚልና ይህም በአብዛኛው ሱዳናዊያን ዘንድ ጆሮ ያገኘ ነው፤›› ብለዋል። 

ከሳምንት በፊት ለአልጄዚራ ቃለ ምልልስ የሰጡት የሱዳን ሚኒስትር ያሲር አባስ (ፕሮፌሰር) ኢትዮጵያ አስቀድማ ሳታሳውቅ ሙሌት በማካሄዷ በሱዳን ላይ መጠነኛ ጉዳት ደርሷል የሚል ክስ አቅርበው የነበረ ሲሆንአስቀድማ አሳውቃ ቢሆን ለሱዳን የመዘጋጀት ዕድል ስለሚሰጥ ጉዳቱን ለመቋቋም የሚያስችሉ ተግባራትን ትፈጽም እንደነበር መግለጻቸውን ባለሙያው አስታውሰዋል።

በመሆኑም ሱዳን ለኢትዮጵያ ጥሪ በጎ ምላሽ ትሰጣለች የሚል ግምት በኢትዮጵያ በኩል እንዳለ የተናገሩት ባለሙያውሱዳን ለጊዜው የሰጠችው ምላሽ ተቃራኒውን ቢሆንም በዚህ ጉዳይ ላይ አቋሟን በጥቂት ጊዚያት ውስጥ ልትቀይር ትችላለች ተብሎ በኢትዮጵያ በኩል እንደሚታመን ተናግረዋል። 

ኢትዮጵያ ያቀረበችውን ጥሪ የሱዳንና የግብፅ መንግሥታት ውድቅ ያደረጉት ሲሆንአጠቃላይ ስምምነት ሳይደረስ የውኃ ሙሌቱ መካሄድ የለበትም የሚል መግለጫ ማውጣታቸው ተዘግቧል። 

የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሱዳንና ግብፅ የሰጡትን ምላሽ በተመለከተ በሰጠው አጭር አስተያየትሱዳን የህዳሴ ግድቡን የውኃ ሙሌት በመቃወሟ የሱዳን ሕዝብ ጥቅም እንደማይከበር ገልጿል።

‹‹የሱዳን ባለሥልጣናት ላለፉት ዓመታት ሲገልጹ የነበሩት የህዳሴ ግድቡ የጎርፍ አደጋን በማስቀረት፣ ዓመቱን ሙሉ የተመጠነ ውኃ በማቅረብ፣ ወደ ሱዳን ግድቦች የሚገባውን ከፍተኛ ደለል በማስቀረትና ርካሽ የኤሌክትሪክ ኃይል ከኢትዮጵያ እንድታገኝ ዕድል የሚፈጥር ሰፊ ጠቀሜታ ያለው ግድብ እንደሆነ ለዓመታት ሲገልጹ ነበር። ታዲያ አሁን የሱዳን አመራሮች የህዳሴ ግድቡን የውኃ ሙሌት መቃወማቸው ማንን ይጠቅማል? የውኃ ሙሌቱን በመቃወም የሱዳን ሕዝብን ጥቅም እንዴት ማስከበር ይቻላል?›› የሚል ጥያቄ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አንስቷል። 

ግብፅን አስመልክቶ በሰጠው አጠቃላይ አስተያየትምበሉዓላዊ ግዛቱ የሚያካሄድን የውኃ ኃይል ማመንጫ ግንባታን በተመለከተ ከውኃው ተጋሪ ከሆነ አገር የታችኛው ተፋሰስ አገሮችን ለድርድር የጋበዘ ተሞክሮ በዓለም እንደሌለነገር ግን ግብፅ ይህንን የኢትዮጵያ ቅን አስተሳሰብ ልትቀበል አልቻለችም ሲል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ተችቷል።

በጉዳዩ ላይ ሪፖርተር ያነጋገራቸው አንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባልደረባኢትዮጵያ ያቀረበችው ጥሪን ሱዳኖች ለራሳቸው ብሔራዊ ጥቅም ሲሉ መቀበላቸው እንደማይቀር ይገልጻሉ። 

ይህም በሱዳንና በግብፅ መካከል መከፋፈል የማምጣት ዕድል ሊፈጥር እንደሚችል ከወዲሁ መገመቱንና በግብፅ በኩልም የአቋም ለውጥ ከወዲሁ መታየት መጀመሩን ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያ ያቀረበችውን ጥሪ ሁለቱም አገሮች በይፋ ውድቅ ቢያደርጉትም በግብፅ በኩል የአቋም ለውጥ ማስከተሉን የጠቀሱት ዲፕሎማቱከኢትዮጵያ ደብዳቤ በኋላ በግብፅ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት የውኃ ሙሌቱ በግብፅ ላይ ጉዳት እስካላደረሰ ትኩረት እንደማያደርጉበት በይፋ መናገራቸውን ጠቁመዋል።

የግብፅ የውኃ ሚኒስትር ሞሐመድ ናስር ኤልዲን ባለፈው እሑድ ለግብፅ ቴሌቪዥን በሰጡት አስተያየት፣ ‹‹ኢትዮጵያ የውኃ ሙሌት ብታካሄድ የሚያስጨንቅ አይደለም፡፡ ምክንያቱም ሊመጣ የሚችለውን የአጭር ጊዜ ጉዳት ለመቋቋም የሚያስችል በቂ የውኃ ክምችት በአስዋን ግድብ ይገኛል፤›› በማለት መግለጻቸውን በዋቢነት ጠቅሰዋል። 

በመሆኑም ኢትዮጵያ የላከችው ደብዳቤ ጨዋታውን የቀየረና ሁለቱንም አገሮች አጣብቂኝ ውስጥ እንደከተተ የሚናገሩት ዲፕሎማቱበመጪው ክረምት የሚሞላው የውኃ መጠን ግዙፍ መሆኑንና በቀጣዮቹ የወደፊት የውኃ ሙሌቶች ዘንድሮ የሚያዘውን ያህል የውኃ መጠን በአንድ ዓመት ውስጥ እንደማይያዝ ገልጸዋል።  በመሆኑም የዘንድሮ ሙሌት ቀጣይ የጭቅጭቅ ምክንያቶችን የማድረቅ አቅም እንደሚኖረውም አስረድተዋል።

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -