- የምግብ ዘይት ጉዳይ በምን ደረጃ ላይ ይገኛል?
- ክቡር ሚኒስትር የፋብሪካዎች ምርት በከፍተኛ ደረጃ ተሻሽሏል።
- አቅርቦቱስ?
- አቅርቦቱ ላይ መቆራረጥ አለ፣ ግን መቀረፉ አይቀርም፡፡
- የሲሚንቶ ጉዳይስ?
- ቀድሞውንም ቢሆን ሲሚንቶ በበቂ ሁኔታ ይመረታል፣ የምርት ችግር የለም።
- አቅርቦቱስ?
- አቅርቦቱ ተቋርጧል፡፡
- እና ምን እያደረጋችሁ ነው?
- አምራቾቹ የሚያነሱት የዋጋ ጥያቄ አለ፣ ቢሆንም መፈታቱ አይቀርም።
- ነዳጅስ?
- መንግሥት ያለውን የውጭ ምንዛሪ ቅድሚያ የሚሰጠው ለነዳጅ ግዥ እንደሆነ ይታወቃል።
- ስለመታወቁ አልጠየቅኩም፣ ምርቱ በበቂ ሁኔታ እየቀረበ ስለመሆኑ ነው፡፡
- ወደ እሱ ልገባ ነው፡፡
- እሺ ግባ…
- በቂ ነዳጅ ተገዝቷል
- የት ነው የሚገኘው?
- ወደ እሱ ልመጣ ነው፡፡
- እሺ፡፡
- ምርቱ ተገዝቶ ጂቡቲ ይገኛል፡፡
- ስለዚህ የአቅርቦት ችግር የተፈጠረው ለዚህ ነው?
- አይደለም ምርቱን ከጂቡቲ በሚጓጓዝበት ኮሪደር ግጭት በመከሰቱ በጊዜ መድረስ አልቻለም ፡፡
- ታዲያ የአቅርቦት ችግሩን ለመፍታት ምን አደረጋችሁ?
- ችግሩ ጊዜያዊ ስለሆነ ነዳጁ ገብቶ ይሠራጫል ፡፡
- ጊዜያዊ ችግሩን ለመቅረፍ ምን እንዳደረጋችሁ ነው የጠየቅኩት፡፡
- ወደ እሱ ልመጣ ነው ክቡር ሚንስትር?
- አንተ እስክትመጣ ይቀረፋል፡፡
- ምኑ?
- የነዳጅ ችግሩ መቀረፉ ስለማይቀር ሌላውን እንመልከት፡፡
- የስንዴና የዳቦ አቅርቦት ማቅረብ እችላለን፡፡
- ቀጥል፡፡
- መንግሥት ለስንዴ በሰጠው ትኩረት እርስዎም እንደተመለከቱት የበጋ ስንዴ ምርት ማጨድ ጀምረናል፡፡
- አቅርቦቱ ላይ አተኩር፡፡
- የስንዴ አቅርቦት ችግር በመኖሩ በዳቦ ፍላጎት ላይ ክፍተት ፈጥሯል።
- ምን እያደረጋችሁ እንደሆነ ነው ማወቅ የምፈልገው፡፡
- የአቅርቦት ችግሩ መፈታቱ አይቀርም እየሠራንበት ነው።
- የሁላችሁም መልስ ችግሩ መፈታቱ አይቀርም የሚል ነው… ማነው የሚቀርፈው? መቼ ነው የሚቀረፈው?
- እሱንም ለመቅረፍ እየተመካከርን ነው።
- ምኑን?
- መቼና ማን ይቅረፈው የሚለውን!
[ክቡር ሚኒስትሩ እንደ አዲስ ለሚቋቋመው የመንግሥት መሥሪያ ቤት የቀረበላቸውን የተቋማዊ አደረጃጀት ረቂቅ ሰነድ እየተመለከቱ ሳለ ረቂቁን ያዘጋጀው ቡድን አባል ወደ ቢሯቸው ገባ]
- እንደምን አሉ ክቡር ሚኒስትር?
- ኦ… አንተ ነህ እንኳን መጣህ።
- የተቋሙ አደረጃጅትን በተመለከተ ያዘጋጀነው ረቂቅ ሰነድ እንደደረሰዎት ተስፋ አደርጋለሁ።
- እሱን እየተመለከትኩት ነው የመጣኸው።
- የተለያዩ አገሮችን ተሞክሮዎች አጥንተን ለኢትዮጵያ ተስማሚ ይሆናሉ ያልናቸውን አደረጃጀቶች አካተናል።
- ተስማሚ ተሞክሮ ነው ያልከው?
- አዎ፣ የተጀመረውን ለውጥ ሊገልጹ የሚችሉትን ተስማሚ ተሞክሮዎችን ነው የወሰድነው፡፡
- እርግጠኛ ነህ?
- አይጠራጠሩ ክቡር ሚኒስትር፣ ሙሉውን ሰነድ አላዩትም እንዴ?
- ሙሉውን አይቼዋለሁ፣ ግን ተስማሚ ያልከውን ሳይሆን ሌሎች ነገሮችን ነው ያገኘሁት፡፡
- ሌላ ምን አገኙ?
- አስቀያሚ፡፡
- ተስማሚ ያልሆነ አስቀያሚ?
- ለምሳሌ ኢንዶክትሪኔሽን፣ ዳይሬክቶሬት የሚል አደረጃጀት ምን ማለት ነው?
- በጥናታችን የተለያዩ አገሮች ውጤታማ የሕዝብ ግንኙነት ሥራ የተወጡበት አደረጃጀት መሆኑን ለይተናል።
- ጥናት ነው ያልከው?
- አዎ! እንደ ካናዳ፣ እንግሊዝና የመሳሰሉ አገሮች የተገበሩትና ውጤት ያገኙበት አደረጃጀት ነው።
- ጥናቱን ተወውና የቃሉን ጥሬ ትርጉም ልትነግረኝ ትችላለህ?
- ጥሬ ቃሉን አላጠናንም፣ ነገር ግን የሕዝብ ግንኙነት ሥራ ማለት አይደል እንዴ?
- ኢንዶክትሪኔሽን?
- እንደዚያ መሰለኝ፡፡
- እሱን ነገር መቼ ነው የምትተወው ግን?
- ምኑን?
- መሰለኝ ደሳለኙን?
- እየሞከርኩ ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ከምትሞክር ለምን አትፈልግም?
- ምን?
- የሌላ አገር ተሞክሮ፡፡
- ኮሚክ እኮ ነዎት ክቡር ሚንስትር
- ለማንኛውም ኢንዶክትሪኔሽን ማለት ሐሳብን ማጥመቅ ወይም ጭንቅላት ማጠብ ማለት ነው።
- ለዚያ እኮ ነው ይህንን ተሞክሮ ለእኛ ተስማሚ ይሆናል ብለን ያመጣነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ተሞክሮ ነው ያልከው?
- አዎ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- የአገር ውስጥ ተሞክሮ ነው?
- በአገር ውስጥም አንዳንድ ተቋማት ይጠቀሙበታል፣ እኛ ግን የካናዳን…
- እንዳትጨርሰው፡፡
- አልቋል…ግን ትቼዋለሁ፡፡
- ቢገባህ ይህንን አደረጃጀት ልትደግመው ይቅርና ከሌሎች ተቋማት ጭምር ታስቀር ነበር፡፡
- ኃላፊነቱን ከሰጡኝ እችላለሁ፡፡
- የማን ኃላፊነት ነው እሱን አደረጃጀት የማስቀረት፡፡
- መጀመርያ ከራስህ ጀምር፡፡
- ከየት?
- ከዚህ ሰነድ ላይ፡፡
- ጥሩ እንዳሉት አደርጋለሁ፡፡
- ተወው እንዲያውም፡፡
- ለምን ክቡር ሚኒስትር?
- በድጋሚ ይሠሩታል፡፡
- ማን ይሠራዋል?
- ባለሙያ፡፡
- እይሆንም ክቡር ሚኒስትር፣ ለባለሙያ ኃላፊነት ሊሰጡ?
- ሌላ ቦታ እስክታገኝ ውጣ!