Sunday, March 26, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየልኳንዳ ነጋዴዎች እሮሮ

የልኳንዳ ነጋዴዎች እሮሮ

ቀን:

በክርስቲያኖች ዘንድ በትልቅነቱ የሚታወቀው ዓብይ ፆም ሊያልቅ/ሊፈታ የቀናት ጊዜ ብቻ ነው የቀረው፡፡ ለሁለት ወራት ያህል ተዘግተው የቆዩ ልኳንዳ ቤቶችም በእነዚህ ቀሪ ቀናት በርና መስኮቶቻቸው ተከፍተው እንዲናፈሱ ይደረጋል፡፡ ይፀዳሉ፣ አንዳንዶችም ይታደሳሉ፡፡ በነጭ ቀለም አሸብርቀውም ለአገልግሎት ዝግጁ ይሆናሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት ግን ይህ ዓይነቱ ሁኔታ እምብዛም አይታይም፡፡ እንዲያውም አንዳንድ ልኳንዳ ነጋዴዎች የንግድ አገልግሎታቸውን ለማቆምና በሥራቸው የሚተዳደሩ ሠራተኞችን ለማሰናበት መገደዳቸውን ይናገራሉ፡፡

የአዲስ አበባ ልኳንዳ ነጋዴዎች ማኅበር ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ አየለ ሳህሌ እንደነገሩን፣ ነጋዴዎቹ ሥራቸውን ለማቆም የገፋፋቸው የግምት ታክስ ስሌት አፈጻጸም መመርያ መውጣቱ ነው፡፡ በመመርያው ቁጥር 138/2010 መሠረት ገቢና ወጪያቸውን ከግምት ውስጥ ያላስገባና አግባብነት የሌለው ታክስ ከተጣለባቸው መካከል ዝቅተኛው አንድ ሚሊዮን ሁለት ሺሕ ብር ሲሆን፣ ከፍተኛ ደግሞ አሥራ አንድ ሚሊዮን ብር ነው፡፡

በመሠረቱ ይህ ዓይነቱ መመርያ የወጣው በ2010 ዓ.ም. ጳጉሜ ሲሆን  ጉዳዩ የሚመለከተው ግብር ሰብሳቢ መሥሪያ ቤት ወዲያውኑ ሊያሳውቃቸው ሲገባ ነጋዴዎቹ እንዲያውቁትና እንዲተገብሩት የተደረገው ከሐምሌ 1 ቀን ጀምሮ ባለው የግብር ማሳወቂያ ጊዜ መሆኑን ነው የተናገሩት፡፡

ነጋዴዎቹ የቫት ተመዝጋቢ እንደመሆናቸው መጠን ማሽንና የሒሳብ መዝገብ እንዳላቸው፣ የሰበሰቡትንም የተጨማሪ እሴት ታክስ በማሽንና በሒሳብ መዝገባቸው አማካይነት ለግብር አስገቢ ተቋማት በየወሩ፣ ከዚህ ዓመት ጀምሮ ደግሞ በየሦስት ወራት እንደሚያሳውቁ ነው፡፡ ግብር በግምት የሚወሰነው የሒሳብ መዝገብ ለሌላቸው ነጋዴዎች እንጂ ለቫት ተመዝጋቢዎች አለመሆኑ እየታወቀ እንዲህ ዓይነት ሥራ መሠራቱ የአፈጻጸም መመርያው ችግር እንዳልበት የሚያሳይ መሆኑን ሥራ አስኪያጁ  ገልጸዋል፡፡

እንደ አቶ አየለ ገለጻ፣ ነጋዴዎች ግብርና ተጨማሪ እሴት ታክስን ገቢ የሚያደርጉት የፌዴራል ገቢዎች ባለሥልጣን በ2009 ዓ.ም. ባወጣው መመርያ መሠረት ነው፡፡ ይህንንም አካሄድ በመከተል ነጋዴዎቹ ገቢ ሲያደርጉ ተቋማቱም ገቢውን ሲቀበሉ ከቆዩ በኋላ በመካከሉ የ2011 በጀት ዓመት አልቆ በቀጣዩ የበጀት ዓመት ግብር ማሳወቂያ ጊዜ የሰበሰቡትን የግብር ገንዘብ ገቢ ለማድረግ ወደ የተቋማቱ ሲሄዱ በአዲሱ የታክስ ስሌት አፈጻጸም መመርያ መሠረት ካልተሠራ በስተቀር የቀድሞውንና ሲያያዝ የመጣውን መመርያ በተከተለ አኳኋን የተሠራውን ሒሳብ ተቋማቱ ተቀብለው ለማስተናገድ ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል፡፡

ነጋዴዎቹም አዲሱን መመርያ እንደማያውቁት፣ መመርያው መውጣቱን የነገራቸው አካልም ሆነ ግለሰብ እንደሌለ፣ ክስተቱ ዱብ ዕዳ እንደሆነባቸው፣ በዚህም የተነሳ ግዴታቸውን ለመወጣትና የንግድ ፈቃዳቸውንም ለማደስ እንደተሳናቸው ነው ዋናው ሥራ አስኪያጅ የተናገሩት፡፡

‹‹አንድ አዲስ ሕግ ሲወጣ ወደፊት እንጂ ወደኋላ ተመልሶ እንደማይሠራ፣ ከዚህ አኳያ አዲሱ የግምት ታክስ ስሌት የአፈጻጸም መመርያን በግብር ማሳወቂያ ጊዜ ተግባራዊ ለማድረግ መንቀሳቀስ አግባብነት የጎደለው አካሄድ ነው፤›› ሲሉም አክለዋል፡፡

ይህንኑም ችግር ማኅበሩ ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት፣ ለአዲስ አበባ አስተዳደር ምክትል ከንቲባና ጉዳዩ በይበልጥ ለሚመለከታቸው መንግሥታዊ አካላት በጽሑፍ እንዳሳወቀና መፍትሔም እንዲበጅለት መጠየቁን ዋና ሥራ አስኪያጁ ገልጸው፣ ባቀረበውም ጥያቄ መሠረት ጽሕፈት ቤቱ፣ ለቀድሞ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ለአቶ ታከለ ኡማ ጉዳዩ እንዲታይላቸው የሚያሳስብ ደብዳቤ መጻፉን አስረድተዋል፡፡

አቶ ታከለም ጉዳዩን ከዳር እንዲያደርሱት ለገቢዎችና ንግድ ቢሮዎች እንዳሳወቋቸውና ቢሮዎቹም ታኅሣሥ 23 ቀን 2012 ዓ.ም. አጠቃላይ ስብሰባ ጠርተው በጉዳዩ ላይ ውይይት እንዳደረጉበት ነው አቶ አየለ የገለጹት፡፡

በገቢዎች ቢሮ የስብሰባ አዳራሽ በተከናወነው፣ ከ800 በላይ ልኳንዳ ነጋዴዎች በተሳተፉበትና የየቢሮዎቹ ኃላፊዎች በመሩት በዚሁ ስብሰባ ላይ በችግሮቹ ላይ ውይይት ከተደረገበት በኋላ ኃላፊዎቹ ለችግሩ ዘላቂ መፍትሔ በቅርቡ እንደሚያበጁ ቃል ከገቡና ነጋዴዎቹም ወደ ቀድሞው ሥራቸው ተመልሰው ለኅብረተሰቡ አገልግሎት እንዲሰጡ በማሳሰብ ስብሰባው እንዳበቃ ነጋዴዎቹም የንግድ ፈቃዳቸውን እያሳደሱ ወደ ሥራ እንደተመለሱ ገልጸዋል፡፡

ይህም ሆኖ ግን የተገባው ቃል ፍጻሜ ማግኘት ሲገባው፣ በተቃራኒው የግምት ታክስ ስሌት አፈጻጸም መመርያ ቁጥር 138/2010 መሠረት የተሰላው ግብር ተፈጻሚ እንዲሆን የሚገልጽ የግብር ውሳኔ ማስታወቂያ፣ ለሁሉም ነጋዴዎች እንዲደርሳቸው መደረጉን ከዋናው ሥራ አስኪያጅ ማብራሪያ ለመረዳት ተችሏል፡፡

ይህ ዓይነቱም ውሳኔ የማኅበሩን አባላት/ነጋዴዎች፣ ቤተሰቦቻቸውና በሥራቸው የሚተዳደሩ ሠራተኞች ወደ ጎዳና ወጥተው ነገ እንደገና የመንግሥት ዕዳ እንዲሆኑ ከማድረጉ በፊት አስተዳደራዊ መፍትሔ እንዲበጅለት ዋና ሥራ አስኪያጅ አሳስበዋል፡፡

ውሳኔው ከደረሳቸውም ነጋዴዎች መካከል በልደታ ክፍለ ከተማ የሚገኙና ስማቸው እንዲገለጽባቸው ያልፈለጉ ልኳንዳ ነጋዴ ይገኙበታል፡፡ እኚሁ ነጋዴ ‹‹በየዓመቱ ወቅቱንና ጊዜውን  ሳላዛንፍ የሚፈለግብኝን ታክስ ለግብር አስገቢው ተቋም ስከፍል፣ ለከፈልኩትም ሒሳብ ተገቢውን ደረሰኝ ስቀበል ቆየሁ፡፡ አሁን  መጨረሻ  ላይ ድጋሚ  ገቢ ለማድረግ ስሄድ በየዓመቱ የከፈልከው እንደተጠበቀ በአዲስ መመርያ መሠረት ቀደም ሲል በከፈልከው ላይ ተጨማሪ የመክፈል ግዴታ አለብህ ተባልኩ፤›› ብለዋል፡፡

የብዙ ቤተሰብ ኃላፊና በሥራቸውም በርካታ ሠራተኞችን እንዳቀፉ ገልጸው፣ የተጠየቁትን 1.7 ሚሊዮን ብር ለመክፈል አቅም እንደሌላቸው፣ በዘርፉም በድጋሚ ለመሰማራት እንደሚቸገሩ በዚህም የተነሳ ሠራተኞቻቸውን በማሰናበት እሳቸውና ቤተሰቦቻቸው የአገር ሸክም ሆነው እንደሚቀሩ ነው የገለጹት፡፡

በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ ስድስት የሚገኙ ሌላው አስተያየት ሰጪ የልኳንዳ ነጋዴም የ2011 በጀት ዓመት እሴት ታክስ በሒሳብ መዝገብ ገቢ ካደረጉና የንግድ ፈቃዳቸውን አድሰው ወደ ሥራ ከገቡ በኋላ፣ እንደገና ተጠርተው 9.9 ሚሊዮን  ብር በድጋሚ እንዲከፍሉ የሚጠይቅ የግብር ውሳኔ ማስተካከያ እንደተሰጣቸው ተናግረዋል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የገቢዎች ቢሮ የግብር አወሳሰንና አሰባሰብ  ዳይሬክተር አቶ ወንድምአገኝ ካሳዬ ስለዚሁ ጉዳይ በስልክ ተጠይቀው ሲመልሱ፣ ‹‹ከአሁን በፊትም የዚሁ ዓይነት ጥያቄ አቅርበው ነበር፡፡ በዚህም የተነሳ ጉዳዩ በጋራ ታይቶ ውሳኔ ላይ ተርሶበታል፡፡  በጋራ የተደረሰበትንም  ውሳኔ  ያገባኛል የሚል ማንኛውም አካል ቢሮአችን ድረስ መጥቶ ማየት ይችላል፤›› ብለዋል፡፡

ከአቅም በላይ የሆነ ከፍተኛ ታክስ ተጥሎብናል ለተባለው አቤቱታም የግብር ውሳኔ ማስታወቂያ የደረሰው፣ አሉኝ የሚላቸውን ማስረጃዎች ይዞ ታክሱን ከወሰነውና እንዲከፍልም ማስታወቂያ ካወጣው የግብር አስገቢ ተቋም ጋር በመወያየት መግባባት ላይ መድረስ እንደሚያስፈልግ፣ በዚህም ቅሬታ የተሰማው ሰው አግባብ ባለው መንገድ ጉዳዩ ለሚመለከተው አካል ማቅረብ እንደሚችል ነው ዳይሬክተሩ የተናገሩት፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለፋይናንስ ዘርፉ ብቃት ያለው የሰው ኃይል የማፍራት የቤት ሥራን የማቃለል ጅማሮ

የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ እያደገ ለመሆኑ ከሚቀርቡ ማስረጃዎች ውስጥ  የግል...

የምድር ባቡርን የሚያነቃቃው የመንግሥት ውሳኔ

በኢትዮጵያ ወደብ አልባነት ላይ የተደመረውን የሎጀስቲክስ ችግር ለመፍታት ግዙፍ...

የፓርላማ አባላት ስለሰላም ስምምነቱ አፈጻጸም ግልጽ መረጃ የለንም አሉ

‹‹ሕወሓትን ለፍረጃ አብቅተውት የነበሩ ጉዳዮች በአብዛኛው መልክ ይዘዋል›› ሬድዋን...