ሰላም! ሰላም! ጎበዝ እንዴት ሰነበታችሁ እንዳልል አሰነባበታችንን አውቀዋለሁ፡፡ እንዲያው በደምሳሳው እንደ አራዳ ልጆች ‹ፒስ ናችሁ አይደል…› ካልኩኝ በቂ ነው፡፡ በቀደም አንዱ ረዥሙን ጃንጥላውን ዘርግቶ አንገቱን አቀርቅሮ ሲሄድ አግኝቼው፣ ‹‹ወንድሜ እንዴት ውለሃል… ምነው በጠራራው አንገትህን አቀርቅረህ ትሄዳለህ…›› ብዬ በማስተዛዘን ስጠይቀው፣ ‹‹ተወኝ እባክህ አንበርብር አሁንስ ያስፈራል…›› ብሎኝ መንገዱን ሊቀጥል ሲል፣ ‹‹እንዴ ምንድነው ነገሩ… የሚያስፈራውስ ምን ይሆን…›› በማለት ወጥሬ ያዝኩት፡፡ አንገቱን ካቀረቀረበት ቀና አድርጎ፣ ‹‹በዚህ ሳምንት አምስተኛውን ሰው ቀብሬ መምጣቴ ነው…›› ሲለኝ፣ ‹‹ምን ሆነው ሞቱ እባክህ…›› እያልኩ ስጣደፍ፣ ‹‹ሕዝቡን እኮ ኮሮና እየረፈረፈው ነው… ይልቅስ 65 ከሞላህ በዕድሜህ፣ ከ55 በላይ ሆነህ ተጓዳኝ ሕመም ካለብህ ጤና ጣቢያ ሄደህ ተከተብ… የሚያዋጣው መከተብ ነው እንጂ ዘንድሮ እንጃ…›› ብሎኝ በቆምኩበት ጥሎኝ ሄደ፡፡ እኔ ነኝ ሰውዬው ብዬ ግራና ቀኝ ሳላይ በፍጥነት ዕርምጃ አካባቢዬ ያለ ጤና ጣቢያ ስደርስ በአረጋውያን ተሞልቶ አገኘሁት፡፡ ወረፋዬን ይዤ በትዕግሥት እየጠበቅኩ ሳለ አረጋውያኑ በየመንደራቸው የደረሰውን የሞት ቁጥር ያወጋሉ፡፡ ድንገት ጥልቅ ብዬ፣ ‹‹በየዕለቱ በጤና ሚኒስቴር የሚወጣው መረጃ እኮ እናንተ እንደምትሉት ከሆነ በአሥር እጥፍ ሞት ያረዳን ነበር…›› ስል ከት ብለው በትብብር ሳቁብኝ፡፡ አንዱ አዛውንት፣ ‹‹ወንድሜ እየተነገረን ያለው እኮ ፅኑ መታከሚያ ውስጥ ሕይወታቸው ስላለፉ ወገኖቻችን ነው… የአስከሬን ምርመራ ቢደረግ ኖሮ አንተ ያልከው ቁጥር ይነገረን ነበር…›› ሲሉኝ አሁን ገና ገባኝ፡፡ እኔ ደላላው አንበርብር ምንተስኖት ተራዬ ደርሶ የደም ግፊቴ ተጋላጭ እንደሚያደርገኝ አስደርጌ 60 ፈሪ ተመዝግቤ ተከተብኩ እላችኋለሁ፡፡ ነገሩ ‹ሀ ራስህን አድን› እንዲሉ ማለት ነው፡፡ ተግባባን አይደል!
እነሆ በሎጂክ ማሰብ አቁመን በቡድን ዓርማ መባዘናችንን መቀጠላችንን ስነግራችሁ ኃፍረት ይሰማኛል። ቡድን የምንወደው ለምን ይሆን? ኳስ እንጂ ሐሳብ የቡድን ሥራ ይፈልጋል እንዴ? እኔ እኮ ግራ ገባኝ እናንተ? ‹‹ቢረታ ሚስቱን ገብቶ መታ…›› አሉኝ ባሻዬ፡፡ ‹‹ማነው እሱ?›› ስላቸው፣ ‹‹ማንነቱ ምን ይሠራልሃል? ዝም ብለህ ከምሳሌው ተማር፣ ምነው አንተም በማንነት ስም የሚቀነቀን እኔነት አለብህ?›› ብለው ቆጣ አሉ። እኔነት የሰው ልጆች ሁሉ ደካማ ጎን እንደሆነ እያወቁ ባሻዬ ራሳቸው አንዱ የሎጂክ ፀር ሲሆኑ ሳይ ተስፋ ቆረጥኩ። መቼም ዘንድሮ ተስፋ ቆርጦ ተስፋ የሚያስቆርጠን በዝቷል። ቆይ ለምን ብቻቸውን አይቆርጡም? ለምን ሌላውን ጭምር ከእንጀራ ገመዱና ከመኖር ስስቱ ጋር ያቆራርጡታል? እንጃ ዘንድሮስ። ‹ኮሜንት› በቡድን፣ ‹ላይክ› በቡድን፣ ‹ብሎክና ኢግኖርም› በቡድን ሆኗል። ከሁሉ ከሁሉ ግን የሚገርመኝ እያንዳንዷ ጥቃቅን ነገር ሳትቀር እንደ ‹ሳውንድ› ትራክ ፖለቲካዊ አጀንዳ መያዟ ነው። ያውም በመንጋ ፖለቲካ ተቀፍድዳ፡፡ ከኮሮና ወረርሽኝ ራሳችሁን ለመከላከል ርቀታችሁን ጠብቁ፣ ማስክ አድርጉ፣ እጃችሁን በሳሙና ታጠቡ፣ ክትባት ሲገኝ ደግሞ ተከተቡ ሲባል ደግሞ መንጋው ዓይን ለዓይን እየተጠባበቀ ይተያያል፡፡ አሰማሪው ካልፈቀደለት ለራሱ አያስብም፡፡ በቡድን ጭንቅላት ይነዳል፡፡ በቃ ይህ ነው የገጠመን ችግር!
ምን ልበላችሁ አንዲት እርግብ ከትናንት ወዲያ ከተመረቀው የእገሌ ሕንፃ መስታወት ጋር ተጋጭታ ሕይወቷ አለፈ ሲባል አንዱ ጀርጃራ፣ ‹‹የሰው አልበቃ ብሏችሁ ደግሞ ምንም የማያውቁትን እንስሳት መግደል ጀመራችሁ?›› ብሎ ኮሜንት ይሰጣል። ያዝ እንግዲህ ይባልልኛል። አንዱ በቀደደው መንቆርቆር ነው። ግር ብለን እንነዳዳለን። የእገሌ ትርፍ አንጀት ፈንድቶ ወደ ሕክምና ጣቢያ ሳይደርስ ሕይወቱ አለፈ ሲባል፣ ‹‹ከዚህ ግድያ በስተጀርባ ያለውን ሴራ እናውቃለን…›› ብሎ አንዱ ጣቱን የሆነ ቡድን ላይ መጠንቆል መጀመር ብቻ ነው የሚጠበቅበት። ከዚያ ሌሎቻችን መግተልተል ነው። ደላላው አንበርብር ምንተስኖት ሎጂክ ትተን በደቦ ማሰብ ጀምረናል አለ ቢባል፣ ‹ስንት ምሁር ባለባት አገር በመኃይም ደላላ እንመከር እንዴ…› ማለት ብቻ ነው የሚጠበቅባችሁ። የምትጣበቁበት ይኑራችሁ እንጂ ተከታዩ ሺሕ ነው፡፡ ያውም ማገናዘብ የማይችል ከአውሬ የባሰ መንጋ፡፡ ጨካኝ ሁሉ!
እናላችሁ ከመብራት መጥፋት በተጨማሪ የውኃ መጥፋት ሲታከልበትና በተነዱበት መነዳትና ያለ ምክንያት ማሰብ በየአቅጣጫው ሲወረኝ፣ እውነቴን ነው የምላችሁ ነገር ሁሉ ይሰለቸኝ ጀምሯል። ለምን የሚሉት ጥያቄ ጠፍቷል፣ ተሰዶብናል። የት? እንዴት? መቼ? ቀብረናቸዋል። አስቡት እስኪ እንደ ‹በደንባራ በቅሎ ቃጭል ተጨምሮ› ስንሆን። እናማ ከእኔ በላይ የተማረና አዋቂ ላሳር የሚለው ደግሞ ባሰ። በዚህ ላይ ደግሞ ጥራዝ ነጠቁ እንደ አሸን ፈልቷል፡፡ በቀደም ከምሁሩ የባሻዬ ልጅ ጋር አንድ ካፌ ውስጥ ቡና እየጠጣን አንዱ ድንገት ደርሶ፣ ‹‹ሰው አለው?›› አለን። ወንበሩን መሆኑ ነው። ‹‹የለውም ውሰደው…›› አለው የባሻዬ ልጅ፡፡ ከዚያ ገና ሳይቀመጥ፣ ‹‹ለነገሩ ዘንድሮ እንኳን ወንበሩ መንበሩስ ምን ሰው አለው ብላችሁ ነው?›› ብሎ ጀመረላችኋ። እንኳን ይህችን የዝንብ ጠንጋራ ቀርቶ የዝንብ ወፈፌም እናውቃለን አልኩና በልቤ፣ ‹‹ቢል ታመጣልን?›› አልኩት አስተናጋጁን። ‹‹ቆይ ሰውየው የጀመረውን ወግ ይጨርስ እንጂ…›› ሲለኝ የባሻዬ ልጅ ያ ነገረኛ አሁንም፣ ‹‹አዬ እንጃ ይኼ ኮሮና የሚሉት ነገር ክትባቱም የሚያቆመው አይመስለኝም…›› ብሎ ብቻውን ሳቀ። አሳሳቁ ታዲያ ቲፎዞ ፍለጋ ስለሚመስል ነገረ ሥራው አላማረኝም፡፡ ‹ሰው ብርቱ ነው በጎርፍ ውስጥ አረማመድ ያሳምራል› ያለው ገጣሚ ትዝ ብሎኝ ፈገግ ስል ለእሱ የሳቅኩለት መስሎት፣ ‹‹ለማንኛውም ዛሬ እኔ ልጋብዛችሁ…›› አለን። እንዲህ ነው እንጂ ማመቻቸት!
በአጋጣሚምም በስህተትም ብርጭቋችን ተጋጨ ተብሎ እዚህ ደረጃ ደርሰናል። ፆታዊ ጥቃት ያደረሰ ብቻ ይመስላችኋል አይደል ደፋሪ? የክብርና የሐሳብ ነፃነት ተጋፊ፣ የልዩነት ፀሮችም እኮ ከዚያ በላይ ናቸው። የሰውዬውን ሁኔታ መልሼ መላልሼ ሳስበው ወሬ ምን ያህል እንደተጠማ ታሰበኝ፡፡ ሁለታችን የግላችንን ጉዳይ ይዘን እያወጋን ነው እንግዲህ ሞገዱን አሳብሮ ነው ወሬ የለቀቀብን፡፡ እኛ ላለማስቀየም ብለን ትንሽ ፍንጭ ስናሳየው በሁለት ፊንጃል ቡና ሰተት ብሎ ገብቶ ሲያጋብስ የዋለውን ወሬ ላያችን ላይ ሊያራግፍ ተንጠራራ፡፡ ‹‹ለማንኛውም በዚህ ዘመን ኢሉሙናቲዎች በጣም እየበዙ ስለሆነ ተጠንቀቁ… ኮሮናን ላቦራቶሪ ውስጥ የፈጠሩት የዓለምን ሕዝብ በግማሽ ለመቀነስ አስበው ነው… አሁን ክትባት ውሰዱ የሚሉን ሰውነታችን ውስጥ በፈሳሽ መልክ ቺፕስ አስገብተው እንደ ሮቦት ተቆጣጥረውን የሰይጣን ዓላማ ሊያስፈጽሙን ስለሚፈልጉ መሆኑን ብዙ ሊቃውንት ደርሰውበታል…›› እያለ ሲቀደድ ምሁሩ የባሻዬ ልጅ አስቆመው፡፡ ‹‹ወዳጄ የትምህርት ዝግጅትህ በዚህ በነገርከን ዘርፍ ነው… ወይስ…›› ሲለው፣ ‹‹እኔ ወንድሞቼ ከውጭ በሚልኩልኝ ዶላርና ከወላጆቼ በወረስኩዋቸው ቤቶች ኪራይ ነው የምተዳደረው… ብዙ ጊዜ ግን በዚህ ጉዳይ የተጻፉ የትርጉም መጻሕፍትን አነባለሁ…›› ሲለን በተቀመጠበት ትተነው ሄድን፡፡ ወገኖቼ በሳይንስና በጥንቆላ መሀል ያለው ልዩነት ከተውቃቃበት ሰው ጋር መቆየት በጊዜ ላይ ኃጢያት መሥራት ነው፡፡ ይኸው ነው!
መቼስ አንዳንዴ ስሜታዊ እየሆንኩ ጨዋታዬ እንደ ዘመኑ ተቃዋሚዎችና ደጋፊዎች ድርቅ ይላል አይደል። ምንላድርግ ቀልድ ጠፋ። ማለቴ ቀልዱ ሁሉ ያው እንደምታዩት የምር የምኖረው ኑሮ ሆኗል። ቀልድ አሯሯጫችን መሆኑ ቀርቷል። እንደ ሳይንስ ፊክሽን ማለቴ ነው። የዛሬን አያድርገውና በቀደሙት ዘመናት አሁን በእጃችን የጨበጥናቸው ኪሳችን የከተትናቸው፣ ቆፍረን የቀበርናቸው ቴክኖሎጂዎች ትናንት ተረት ነበሩ። ቀልድና ሳይንስ ፊክሽን የሚያመሳስላቸው ይኼው ነው። ትናንት ቀልድና ስላቅ እንደ ዛሬው እያንዳንዳችን የሚያጋጥመን የምኖረው ሀቅ አልነበረም፣ በአብዛኛው ነው የምላችሁ። ዘመኑ የመረጃና የማስረጃ ነውና ማስረጃዬን ላቅርብ። በቀደም አንድ ቪላ ቤት እያሻሻጥኩ ነበር። የማሻሽጠው ቤት የነበረበት አካባቢ አንድ ቡቲክ ሞቅ አድርጎ በሁለት ሞንታርቦ ሙዚቃ ከፍቷል። ይኼኔ ነው ድንገት ጆሮዬ የገባው። ይኼ ጆሮዬ ደግሞ ከየቦታው እየሳበ መስማት ለምዶ ነው መሰል ምንም አያሳልፍም፡፡ ምን ይደረግ!
የጥንት የጠዋቱን የዝነኛውን የጥላሁን ገሠሠ ‹‹ያሳለፍነው ጊዜ›› የሚለው ዘፈን ይሰማኛል፡፡ ያለፈውን ዘመን በጣም ርቄ አሰብኩት፡፡ በዚያን ዘመን ከነበሩ ታዋቂዎች እስከ እኛ ዓይነቶቹ ተርታዎች ድረስ አስታወስኩ፡፡ ዓመታት ነጉደው እዚህ ዘመን ላደረሰኝ አምላክ ምሥጋና አቀረብኩ፡፡ እኔ 60 ፈሪ ሆኜ ቀሪውን ዘመኔን እያሰብኩ የተባረከ ያደርገልኝ ዘንድም ልመና አሰማሁ፡፡ ከሚወራውና ከሚፈራው ሰውሮ የሚያኖር አምላክ አለኝ ብዬም በደስታ ተዋጥኩ፡፡ ያለፉ ዘመናት ትዝ ሲሉ የፈጣሪ ችሮታ መታወስ አለበት እላለሁ፡፡ ምሁሩ የባሻዬ ልጅም ዘወትር የሚመክረኝ ይህንን ነው፡፡ እኔም ሥራዬን ጨርሼ ኮሚሽኔን ተቀባብዬ ለውዲቱ ባለቤቴ ለመስጠት ወደ ቤቴ ስጣደፍ ብሄድ፣ ውድ ማንጠግቦሽ ቤቱ እንደ ተዝረከረከ ለጥ ብላ ተኝታለች። ሰዓቴን ሳይ ከቀኑ ስምንት ሰዓት ይላል። እንግዲህ ተመልከቱ ይኼን እያየ እየሰማ ራሱ የኢትዮጵያን ዕድገት የሚጠራጠር አለ? ለነገሩ የእኛ እንቅልፍ በዕድገት የሚረዝም በረሃብ የሚያጥር አይደለም፡፡ እሱ በኪነ ጥበቡ እያኖረን በመሆኑ ነው እንጂ፣ እንደምንታወቅበት ዘገምተኝነትና ዳተኝነት የለንም ነበት። ባሻዬ ይኼን አስተሳሰቤን ስለሚጋሩኝ፣ ‹‹የእኛ ጠላታችን ከድህነት በባሰ የተጫነን ድንቁርና ነው…›› ይሉኛል፡፡ ዘንድሮ ደግሞ አጉል ቀስቃሽ በአየቅጣጫው የዘመተበት ሁኔታ ነው ያለው ብል፣ በአንድ ወቅት በዜና አንድ ሮቦት አይቼ እንደነበር አስታውሳለሁ። ሮቦቷ ሴት ናት። ይገርማል እኮ እናንተ። እንደ ምዕራባውያን ኑሮ ግራ ያጋባን የለ? ተፈጥሮ ፆታ መዳድባ ቦታና ሥፍራ እያቀያየረች ስታዞርብን ከርማ ደግሞ፣ በጎን ሰው ሠራሹን ነገር ሴት ወንድ እያለች ፆታ ታድላለች። ግሩም ነው!
ቆይ ግን ታዳዩና አዳዩ የሚገናኙበት ዘመን ሳይመጣ እንሞት ይሆን? ብቻ ወደ ጀመርኩት ልመለስና ያቺ እንስት ሮቦት ሥራዋ አዛውንቶችን ማጫወት ነው። አንድ ጋዜጠኛ ቃለ መጠይቅ ሲያደርግላት፣ ‹‹እንዲያውም ሥራዬ ማውራት ነው። በወሬ ዕጦት የተጎዱ ሰዎችን እያነጋገርኩ ማጫወት የሕይወቴ ግብ ነው…›› ስትለው ያለ አስተርጓሚ ገባኝ። ደግሞ ለዚህ አስተርጓሚ ልጥራና ጉድ ልሁን? በቀደም ይኼው እንዲሁ ዓይነት ስለሕይወት ግብ የሚጫወትን ጎልማሳ ቃለ መጠይቅ እያዳመጥኩ አልገባህ ብሎኝ አንድ የሠፈር ልጅ ጠራሁና ምን እንደሚል ንገረኝ እለዋለሁ፣ ‹‹የሕይወቴ ለውጥ የጀመረው የእነ ኦሾን መጽሐፍ ማንበብ ስጀምር ነው ይላል…›› አይለኝ መሰላችሁ? ሰው እንዴት ከዚህም ከዚያም በተቃረመ አጉል ፍልስፍና ሕይወቴ ተለወጠ ይላል እያልኩ ስገረም፣ ‹‹የእዚህ ዘመን ሰው ጥልቀት ያለው ዕውቀት እየሸሸ ጥቅስ ሲያነበንብ ነው እኮ የሚውለው…›› ብሎ ወጣቱ ሲነግረኝ እንዲህም የሚያስብ አለ እንዴ ብዬ ተፅናናሁ፡፡ ሰው አደባባይ ወጥቶ ሲደሰኩር ትንሽ ማሰላሰል ለምን እንደሚያቅተው ግራ ይገባኛል፡፡ ከታሪኩ ባይማር፣ ሲነገረው ባይገባው፣ ሲጨቀጭቁት ቢደክመው፣ ሲያመላክቱት ቢሰለቸው እንዴት አጠገቡ ካለው አቻው መማር ያቅተዋል? ‹‹አንዳንዴ እኮ ለሰው ሳይሆን ለግድግዳው የምናወራ ነው የሚመስለው…›› ያለኝን አስተማሪ አልረሳውም፡፡ ተስፋ ቆርጦ ነዋ!
በሉ ልንሰነባበት ነው። ብቻ የዚህችን ‹የሕይወቴ ለውጥ› የምትባል አባባል እንዲህ በትንሽ በትልቁ አፍ መግነን ግርም እያለኝ፣ ‹‹ሰው ከሰውነት ሮቦትነት ተቀይሯል እንዴ? ሕይወቱን በተሻለ መንገድ መቅረፅ አቅቶት በካርቦን ኮፒ ያበደው?›› ብዬ ሳልጨርስ ማንጠግቦሽ ትዝ አለችኝ። አስተኛኘቷ ደስ አላለኝም። ከመጮኼ በፊት አንዴ ልሞክራት ብዬ ነካ አደርጋታለሁ፣ ‹‹የቀሰቀሷቸውን ደንበኛ አሁን መነሳት አይችሉም። እባክዎ ከሰዓታት በኋላ እንደገና ይሞክሩ…›› ብላኝ ተገላብጣ ተኛች። ደህና ከሆንሽስ ብዬ ከባሻዬ ልጅ ጋር ተያይዘን ወደ ግሮሰሪያችን አመራን። ምሁሩ የባሻዬ ልጅ የማንጠግቦሽን ኩመካ ሰምቶ ሲያበቃ፣ ‹‹አንዳንዱ እንቅልፍ እኮ ለበጎ ነው አንበርብር። ባንነቃ ባንቀሰቀስ የሚሻለን ጊዜ አለ፣ ሰሚ የለም እንጂ…›› ሲለኝ፣ ‹‹አንዳንዴ ሳምንቱ ቅጣቱ ሲከብድ፣ ምንም አይሳካም ከእሑድ እስከ እሑድ…›› ብሎ አንዱ በአንድ ወቅት ያጨደው መከራ ትዝ አለኝ። ምነው የዘንድሮ ባሰ አልኩ። መነካት በማይገባን ጎናችን እየተነካን፣ መቀስቀስ በሌለብን ሰዓት እየቀሰቀሱን እኛም አቤት እያልን ከእሑድ እስከ እሑድ፣ ከትውልድ እስከ ትውልድ፣ ከዓመት እስከ ዓመት፣ ከሚሊኒየም እስከ ሚሊኒየም፣ እንዲሁም እስከ ዛሬ ድረስ የተባላነው አይበቃም ጎበዝ? እስከ መቼ በእንቅልፍ ላይ እንቅልፍ? ምሁሩ የባሻዬ ልጅ፣ ‹‹ክትባቱ እንዴት ነው…›› ሲለኝ፣ ‹‹አሁንም ከጭንቀት ተገላግዬ ውስጤ በተስፋና በሐሴት እየተሞላ ነው…›› አልኩት፡፡ ‹‹ክትባቱ እንዳለ ሆኖ ጥንቃቄዎቹ ግን መረሳት የለባቸውም…›› ብሎኝ፣ ‹‹እኔማ ክትባቱ ለእኔና ቢጤዎቹ የሚዳረስበት ጊዜ እየናፈቀኝ ነው… እስከዚያው ድረስ ግን ብቸኝነት እንደ ከበበው ሰው ከጥላዬ በስተቀር የሚከተለኝ ያለ አይመስለኝም…›› ብሎ ፈገግ ሲል የብዙዎቻችንን የልብ ትርታ የነካ መሰለኝ፡፡ ጥላችን ብቻ ነው መሰል የሚከተለን… መልካም ሰንበት!