Wednesday, March 22, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የነዳጅ እጥረት ሲፈጠር መንግሥት አፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጥ ተጠየቀ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

መሰንበቻውን በአዲስ አባበ ከተማ የነዳጅ እጥረት ሲፈጠር መንግሥት ከዴፖዎች አውጥቶ በፍጥነት ችግሩን ለመቅረፍ ያሳየው ዘገምተኛ ምላሽ አግባብ አለመሆኑን፣ የኢትዮጵያ ነዳጅ አዳዮች ማኅበር አስታወቀ፡፡ ይህ ዓይነቱ ዘገምተኝነት ሊሻሻል እንደሚገባም አሳስቧል፡፡

ከሳምንት በፊት ከጂቡቲ ወደ መሀል አገር ይመጡ የነበሩ የነዳጅ ጫኝ ተሽከርካሪዎች፣ በአፋር ክልልና በሶማሌ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች በተከሰት ግጭት ምክንያት መንገድ በመዘጋቱ በመቆማቸው፣ በአዲስ አባባ ከተማ የነዳጅ አቅርቦት ለሳምንት ያህል ተስተጓጉሎ አንደነበር ይታወሳል፡፡

በዚህም በከተማዋ የሚገኙ ተሽከርካሪዎች በማደያዎች አካባቢ ለረዥም ሰዓታት ነዳጅ ለመቅዳት ተሠልፈው ሲጉላሉ ተስተውለዋል፡፡ በተፈጠረው መንገድ መዘጋጋት ምክንያት እጥረት ሲያጋጥም፣ በማደያዎች አካባቢ ነዳጅ በሕገወጥ መንገድ በበርሜልና በጄሪካን በመቅዳት፣ ከታሪፍ በላይ ይሸጥ እንደነበር፣ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ እሸቴ አስፋው ተናግረዋል፡፡

በሚኒስቴሩ ፍተሻና በነዋሪዎች ጥቆማ ሰሚት አካባቢ የሚገኘው ናይል ፔትሮሊየም የተባለ ማደያ በጄሪካንና በበርሜል ነዳጅ እየቀዳ ሲያከማች በቁጥጥር ሥር በመዋሉ፣ የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ እንደተሰጠው ሚኒስትር ዴኤታው ገልጸዋል፡፡

መንግሥት በየቀኑ ከአሥር ሚሊዮን ሊትር በላይ ናፍጣና ሦስት ሚሊዮን ሊትር ያህል ቤንዚን እያቀረበ ቢሆንም፣ አንዳንድ የነዳጅ ማደያዎች በበርሜል፣ በጄሪካንና በሌሎች ዕቃዎች ነዳጅ በመቅዳትና በማስቀመጥ የአቅርቦት ችግር እንዳለ በማስመሰል ደንበኞችን ሲያጉላሉ እንደነበረ አቶ አሽቴ አክለው ተናግረዋል፡፡

ይሁን እንጂ የኢትዮጵያ ነዳጅ አዳዮች ማኅበር የቦርድ አባል አቶ ኤፍሬም ተስፋዬ፣ ምንም እንኳ የሚባለው ዓይነት ብልሹ አሠራር በየትኛውም ዓይነት የንግድ ሥርዓት የተለመደ ቢሆንም፣ ከሰሞኑ የተከሰተው መጉላላት በመንግሥት በኩል ፈጣን ምላሽ አለመስጠትና ዘገምተኝነት ትልቁ ችግር እንደነበር ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

መንግሥት መሰል ክስተቶች ሲፈጠሩ ሱሉልታ ካለው የነዳጅ ቋት አንድ ቀን ባልፈጀ ጊዜ ውስጥ ለአዲስ አበባ ከተማ ማቅረብ ሲችል፣ ብዙ ጊዜ ዝምታ መርጦ እዳልሰማ መሆኑ የተለመደ እንደሆነ አቶ ኤፍሬም አስረድተዋል፡፡

በሌላ በኩል የኢትዮጵያ የነዳጅ ኩባንያዎች ማኅበር ፕሬዚዳንት አቶ ታደሰ ጥላሁን ሰሞኑን የተፈጠረው የቤንዚን እጥረት፣ በአፋርና በሶማሌ ክልሎች መሀል በተፈጠረው ችግር መንገድ በመዘጋቱ እንጂ፣ በበርሜልም ሆነ በጄሪካን ነዳጅ በመቀዳቱ ምክንያት እንዳልሆነ ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ታደሰ ኃይለ ማርያም በበኩላቸው የተከሰተው የመንገድ መዘጋት ችግር እንዳለ ሆኖ፣ ተሽከርካሪዎች ለረዥም ሰዓት የሚቆሙበት ዋነኛው ምክንያት በከተማዋ የሚገኙ ነዳጅ ማደያዎች ቁጥር አነስተኛ በመሆኑና ብዙዎችም በማርጀታቸው እንደሆነ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

ለአዲስ አበባ ከተማ በትንሹ 300 ያህል ነዳጅ ማደያዎች የሚያስፈልጓት ቢሆንም፣ አሁን ያሏት 120 ያህል ማደያዎች መሆናቸውንና ያረጁ ከመሆናቸውም በላይ አንዳንዶቹ አገልግሎት የማይሰጡ፣ እንዲሁም ከሚጠበቅባቸው አገልግሎት ደረጃ በታች እንዳሉ ጠቁመዋል፡፡

በመሆኑም የቤንዚን ወይም የናፍጣ አቅርቦቱ ከፍተኛ ቢሆንም፣ የአገልግሎት አሰጣጡ ዘመናዊ እስካልሆነ ድረስ የተሽከርካሪዎችን ሠልፍ ማየት የማይቀር መሆኑን አቶ ታደሰ አስታውቀዋል፡፡

ዋና ሥራ አስፈጻሚው ችግሩ አሁን ላይ መቃለሉንና ቀጣይነት ያለው ሥራ ለማከናወን ግን በተለይ ነዳጅ መደበቅና ማሸሽ ድርጊት ላይ የተሰማሩ አካላትን ለሕግ ማቅረብና ማስተማር ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ በዓመት በ100 ቢሊዮን ብር ገደማ ነዳጅ ገዝታ ወደ አገር እንደምታስገባ የተናገሩት አቶ ታደሰ፣ አሁን በአገሪቱ ምንም ዓይነት የአቅርቦት ችግር እንደሌለና ከሚጠበቀው በላይ እየገባ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ወደፊት በአቅርቦት ረገድ ችግሮችን ይፈታሉ ያላቸውን በቅርቡ በዱከም፣ በቀጣይ አምስት ዓመታት ደግሞ በድሬዳዋ፣ እንዲሁም በወልዲያ እያንዳንዳቸው ቢያንስ ለ35 ቀናት ፍጆታ መያዝ የሚችሉ ዴፖዎችን ለመገንባት ሥራ መጀመሩን ዋና ሥራ አስፈጻሚው ገልጸዋል፡፡

በአሁኑ ጊዜ ከጂቡቲ ወደ አዲስ አበባ ነዳጅ የሚያመላልሱ ተሽከርካሪዎችን ቁጥር ለመጨመር ግዥ እየተፈጸመ መሆኑን፣ በሌላ በኩል ከጂቡቲ እስከ አዋሽ ድረስ ባቡር በመጠቀም ነዳጅ ለማጓጓዝ ሥራ መጀመሩን፣ በተጨማሪም በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙትን የማደያዎች ቁጥር ለመጨመር ከከተማ አስተዳደሩ ጋር ውይይት እየተደረገበት እንደሆነ፣ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታው አቶ እሸቴ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች