Saturday, November 26, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ዜናበአጣዬ ከተማና ነዋሪዎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱን ሸሽተው የተደበቁ ነዋሪዎች ተናገሩ

  በአጣዬ ከተማና ነዋሪዎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱን ሸሽተው የተደበቁ ነዋሪዎች ተናገሩ

  ቀን:

  ‹‹ችግሩን እያደረሱ ያሉት የኦነግ ሸኔ ታጣቂዎችና ተባባሪዎቻቸው ናቸው›› የአማራ ክልል መንግሥት

  በሰሜን ሸዋ ዞን አጣዬ ከተማ ላይ ቁጥራቸው ያልታወቁ ነዋሪዎችና የፀጥታ አስከባሪዎች ላይ ከባድ ጉዳት መድረሱን፣ ዝርፊያና ቃጠሎ መፈጸሙን ሸሽተው በተለያዩ ቦታዎች የተደበቁ ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡

  ከወር በፊት ከአንድ ግለሰብ ግድያ ጋር በተያያዘ በአካባቢው በሚኖሩ የኦሮሞ ማኅበረሰብና የአጣዬ ከተማ ነዋሪዎች መካከል ግጭት የተፈጠረ ለማስመሰል የኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች በተለይ በአጣዬ ከተማ ነዋሪዎች ላይ ባደረሱት ጥቃት ቁጥራቸው በዛ ያሉ ነዋሪዎች መገደላቸው ይታወሳል፡፡

  የኢፌዲሪ መከላከያ ሠራዊትና የአማራ ክልል ልዩ ኃይል በመተባበር በወሰዱት ዕርምጃ ችግሩ የተወገደና ማኅበረሰቡም ወደ ሰላማዊ እንቅስቃሴው ተመልሶ የነበረ ቢሆንም፣ እጅግ በተጠናከረና በተጠና ሁኔታ ሚያዝያ 6 ቀን 2013 ዓ.ም. ምሽት ላይ የተጀመረው ጥቃት ተባብሶ በመቀጠሉ፣ ታጣቂ ኃይሉ ሚያዝያ 8 ቀን 2013 ዓ.ም. አጣዬ ከተማን መቆጣጠሩን ነዋሪዎቹ ተናግረዋል፡፡ አጣዬ ከተማንና ኤፍራታ ግድም ወረዳን ከመቆጣጠር ባለፈ በተለይ የከተማ አመራሮችን ቤተሰብና ንብረቶቻቸው ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንዳደረሱ ጠቁመዋል፡፡ ቤቶችን የሚያቃጥሉት በተሰጣቸው ጥቆማ መሠረት ሲሆን፣ ዝርፊያውን ግን በሁሉም ላይ መፈጸማቸውን ነዋሪዎቹ ተናግረዋል፡፡ በከተማው የነበሩ የክልሉ ልዩ ኃይልና መከላከያ ሠራዊት ከአቅማቸው በላይ እንደሆነባቸውም ነዋሪዎቹ አክለዋል፡፡

  መንግሥት ደርሶ ካላዳናቻው በስተቀር በተደበቁበት ቦታ ደርሰው ‹‹ይገድሉናል›› የሚል ሥጋት ውስጥ መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡ ጉዳዩ ከመንግሥት ቁጥጥር ውጪ ሊሆን ስለማይችል እንዲደርስላቸውም ጠይቀዋል፡፡

  ስለተፈጸመው ግድያ፣ ዝርፊያና ቃጠሎ በሚመለት ሪፖርተር ያነጋገራቸው የአማራ ክልል መንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ግዛቸው ሙሉነህ እንደገለጹት፣ በአማራ ክልል በተመሳሳይ ሁኔታ ሦስት ቦታዎች ላይ ማለትም ሰሜን ሸዋ ዞን አጣዬ ከተማ ላይ በኦነግ ሸኔ፣ በማዕከላዊ ጎንደር አይከል አካባቢ በሕወሓት ተላላኪና ታጣቂ የቅማንት ቡድን እንዲሁም በምዕራብ ጎጃም ፍኖተ ሰላም ከተማ ላይ ሕገወጥ የሕወሓት ተላላኪዎች ጥቃቶች ተፈጽመዋል፡፡ በአጣዬ ከተማ ነዋሪዎችና የኦሮሞ ማኅበረሰብ መካከል ከወር በፊት ኦነግ ሸኔ የፈጠረውን ግጭት በክልሉ ልዩ ኃይልና መከላከያ ሠራዊት እንዲሁም በኅብረተሰቡ ትብብር ሲከሽፍበት፣ ወር ጠብቆና ተጠናክሮ በመምጣት አጣዬን ቆርጦ መያዙን አቶ ግዛቸው አረጋግጠዋል፡፡

  አጣዬ ከተማ፣ ኤፍራታ ግድም ወረዳና አካባቢው ላይ ለጊዜው የጉዳቱ መጠን ያልታወቀ ጥቃት መፈጸማቸውንና የፀጥታ አስከባሪዎችም መጎዳታቸውን፣ ንብረት መቃጠሉንና ዘረፋ መካሄዱንም ተናግረዋል፡፡

  በማዕከላዊ ጎንደር አይከል አካባቢ ከሕወሓት ተላላኪ ኃይሎችና የቅማንት ጽንፈኛ ቡድን ሚያዝያ 6 ቀን 2013 ዓ.ም. ባደረሱት ጥቃት ንፁኃን መጎዳታቸውን አቶ ግዛቸው ገልጸዋል፡፡

  ሚያዝያ 8 ቀን 2013 ዓ.ም. ደግሞ በምዕራብ ጎጃም ፍኖተ ሰላም ከተማ ነዋሪዎች ስለሚደርሰው ጥቃት ማብራሪያ እንዲሰጣቸው የሰላማዊ ሠልፍ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ እያሉ ተጣቂ የጽንፈኞችና ተላላኪዎች ባደረሱት ጥቃት የፀጥታ አስከባሪዎች መጎዳታቸውን አስረድተዋል፡፡

  ይኼ እየተደረገ ያለው ሆን ተብሎ ክልሉን ለማተራመስና በምርጫ ላይ እየተሠራ ያለውን ሥራ ለማደናቀፍ፣ ክልሉን የቀውስ ማዕከል ለማድረግ መሆኑን ጠቁመው፣ ‹‹ይኼ ግን አይሳካላቸውም›› ብለዋል፡፡

  የክልሉ መንግሥት ከፌዴራል መንግሥት ጋር በጋራ በመሆን ችግሩን ባጭሩ ለማስቀረት እየተንቀሳቀሱ መሆኑንና ችግሩን አስወግደው ሕዝቡን ወደሰላማዊ እንቅስቃሴ ለመመለስ እየሠሩ መሆኑን አክለዋል፡፡

  የጎንደሩና የፍኖተ ሰላሙ የሕገወጥ ታጣቂ ቡድን እንቅስቃሴ በቁጥጥር ሥር ውሎ ሰላም መፈጠሩን ገልጸው፣ በአጣዬ፣ ኤፍራታ ግድም ወረዳ፣ አንፆኪያና ሌሎች አካባቢዎች ላይ ያለውን ችግር ለመቅረፍ በጋራ እየተሠራ መሆኑን አቶ ግዛቸው አስረድተዋል፡፡

  የክልሉ ልዩ ኃይል በተለያዩ አካባቢዎች በተፈጠሩት ችግሮች ምክንያት በመስማራቱ እንጂ፣ ኦነግ ሸኔና ተባባሪዎቹ የፈጸሙት ጥቃት ከቁጥጥር ውጪ አለመሆኑን ገልጸዋል፡፡ በሁሉም አካባቢዎች ስለደረሰው ጥቃትና ጉዳት መረጃዎችን በማሰባሰብ ለሕዝብ ይፋ እንደሚደረግም አቶ ግዛቸው ተናግረዋል፡፡

  spot_img
  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  የትርፍ መጠኑን በ127 በመቶ ያሳደገው አቢሲኒያ ባንክ ካፒታሉን በ2.5 ቢሊዮን ብር እንዲያድግ ወሰነ

  የአቢሲኒያ ባንክ ዳይሬክተሮች ቦርድ የባንኩ  ካፒታል በ2.5 ቢሊዮን ብር...

  አዋሽ ባንክ ካፒታሉን 55 ቢሊዮን ብር ለማድረስ ወሰነ

  የአዋሽ ባንክ ዳይሬክተሮች ቦርድ ዛሬ ህዳር 17 ቀን 2015...

  ከብሔራዊ ባንክ እውቅና ያገኘው ፔይሊንክ አክሲዮን ማህበር ምሥረታውን አካሄደ

  ከገንዘብ ንክኪ ነፃ የሆነ የዲጂታል ክፍያ ሥርዓት ለመተግበር ያቀደው...