መረጃ ለሰው ልጅ ኃይል ነው፣ ሀብት ነው፣ ጊዜ ነው፡፡ በተለይም የዜጎችን የመወሰን አቅምን ለማጎልበትና ለማብቃት እጅግ አስፈላጊ ከሆኑ ሀብቶች አንዱና ዋነኛው መረጃ ነው፡፡ መረጃ ያላቸው ሰዎች፣ እንዳሉበት ሁኔታና በአቅማቸው ልክ በመንግሥት አስተዳደር ውስጥ ብልሹ አሠራሮች እንዳይገነግኑ መረጃን መሠረት በማድረግ ያጋልጣሉ፡፡ የመረጃ ነፃነት ሲከበር ዜጎች በመንግሥት አስተዳደር አካላት ላይ ጠንካራ እምነት ይኖራቸዋል፡፡ ስለሆነም የሰዎች መረጃ የማግኘት መብት መሠረታዊ የሰብዓዊ መብት ከመሆኑም በተጨማሪ፣ ለሌሎች መብቶች መከበር መሠረት ስለመሆኑ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብት መግለጫ (UDHR)፣ እንዲሁም ኢትዮጵያ በፊርማዋ በተቀበለቻቸው ዓለም አቀፍ የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ቃል ኪዳን (ICCPR) እና በአፍሪካ ኅብረት የሰብዓዊና የሰዎች መብት ቻርተር (ACHPR) ሰፊ ዕውቅና አግኝቷል፡፡ በዚህም የመረጃ ነፃነት ዓለም አቀፍ ሕግ መሆን ከጀመረ ሰነባብቷል፡፡
የኢትዮጵያ ሕዝቦች ሉዓላዊ የሥልጣን ባለቤት መሆናቸው፣ የሕዝቦች ሉዓላዊ የሥልጣን ባለቤትነት የሚገለጸው ደግሞ ወቅቱን ጠብቆ በሚከናወን ነፃ፣ ፍትሐዊና ተዓማኒ ምርጫና ሕዝቦች በቀጥታ በሚያደርጉት ዴሞክራሲያዊ ተሳትፎ አማካይነት እንደሆነ በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት ተረጋግጧል፡፡ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ዜጋ በማንኛውም የመንግሥት ደረጃ በየጊዜው በሚካሄድ ምርጫ የመምረጥና የመመረጥ መብት እንዳለውና ምርጫው ሁሉ አቀፍ፣ በሁሉም እኩልነት ላይ የተመሠረተና በሚስጥር ድምፅ አሰጣጥ መራጩ ሕዝብ ፈቃዱን በነፃነት የሚገልጽበት ዋስትና የሚሰጥ መሆን እንዳለበት በሕገ መንግሥቱ በግልጽ ተደንግጓል፡፡
ከላይ እንደተጠቀሰው መረጃ የመጠየቅ፣ የማግኘትና የማሠራጨት መብት መሠረታዊ መብት መሆኑ በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥትና በመገናኛ ብዙኃንን መረጃ ነፃነት አዋጅ ቁጥር 590/2000 የተረጋገጠ ከመሆኑም በተጨማሪ፣ ለሕዝቦች ሉዓላዊ የሥልጣን ባለቤትነትና ዴሞክራሲያዊ ተሳትፎ፣ እንዲሁም ለግልጽ የመንግሥት አሠራርና ተጠያቂነት መረጋጥ መሠረት መሆኑ ተደንግጓል፡፡ በተጨማሪም ከምርጫ ጋር በተያያዘ የሰዎች መረጃ የማግኘት መብት መከበር ለነፃ፣ ፍትሐዊ፣ ተዓማኒ ዴሞክራሲያዊና ሰላማዊ ምርጫ ዕውን መሆን መሠረታዊ ቅድመ ሁኔታ ስለመሆኑ በኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ ምግባር አዋጅ ቁጥር 1162/2011 በማያሻማ መልኩ በግልጽ ተመልክቷል፡፡
የኢትዮጵያ መንግሥትም የሕዝብን የሥልጣን ባለቤትነት ተሳትፎ ባረጋገጠና ዓለም አቀፍ የምርጫ መርሆዎችን በተከተለ መንገድ በየደረጃው በሚደረጉ ሁሉን አቀፍ ነፃ፣ ፍትሐዊና ሰላማዊ ምርጫዎች ዜጎች በትክክለኛና በበቂ መረጃ ላይ በመሥራት በምርጫ ላይ እንዲሳተፉና ፈቃዳቸውን በእኩልነትና በነፃነት እንዲገልጹ ለማድረግና የፖለቲካ ፓርቲዎች የተለያየ ዓላማና አመለካከታቸውን በሰላማዊና ሕጋዊ መንገድ ለመራጩ ሕዝብ በመግለጽ በምርጫ የሚሳተፉት የምርጫ ሥርዓት ለመዘርጋት በቁርጠኝነት እንደሚሠራ በዚሁ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ ምግባር ሕግ ላይ ሠፍሯል፡፡
ከምርጫ ጋር በተያያዘ ለሕዝብ የሚገለጹ የመረጃ ዓይነቶችና ፈጻሚ አካላትም በዚሁ አዋጅ በአብዛኛው ተለይተዋል፡፡ በእርግጥም በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ራሱን በራሱ የሚያስተዳደር ኅብረተሰብ የሚፈጠረው በመረጃ ላይ የተመሠረተ ዕውቀት ሲኖር መሆኑ ልብ ሊባል ይገባል፡፡
በመንግሥታዊ አካላት ዘንድ የሰዎች መረጃ የማግኘት መብት ተግባራዊ የሚደረገው አንድም መረጃ ጠያቂ ሲመጣ የተጠየቀውን መረጃ በመስጠትና መረጃ ጠያቂ ባይመጣም የሕዝቡን ጥቅም የሚመለከቱ መረጃዎችን በተለያየ የማሠራጫ ዘዴ አስቀድሞ ለሕዝብ በመግለጽ (Proactive Disclosure of Information) ነው፡፡
በኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ ምግባር አዋጅ ቁጥር 1162/2011 መሠረት ከምርጫ ጋር በተያያዘ በኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድና ባለድርሻ አካላት (Electoral Stakeholders) እጅ የሚገኙ መረጃዎች የሕዝብን ጥቅም የሚመለከቱ በመሆናቸው አስቀድሞ ለሕዝብ ይፋ ከሚደረጉት የመረጃ ዓይነቶች ጎራ የሚመደቡ ናቸው፡፡ ምርጫ ቦርድም እንደማንኛውም መንግሥታዊ አካል በሕገ መንግሥቱና በመረጃ ነፃነት አዋጁ መሠረት ለመረጃ ጠያቂ መረጃ የመስጠት ወይም የመከልከል፣ እንዲሁም መረጃው የሕዝብን ጥቅም የሚመለከት በሆነ ጊዜ ደግሞ በተለያየ የማሠራጫ ዘዴ አስቀድሞ ለሕዝብ ይፋ የማድረግ ኃላፊነት አለበት፡፡
በዚህም ምርጫ ቦርድ የመገናኛ ብዙኃንና መረጃ ነፃነት አዋጅ ቁጥር 590/2000 አንቀጽ 13 እና በተለይም የምርጫ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ ምግባር አዋጁ በሚያዘው አግባብ የምርጫ ሒደቱ ከተጀመረበት ዕለት ጀምሮ በርካታ መሠረታዊ መረጃዎችን ለሕዝብ ይፋ እያደረገ እንደሆነ ተቋሙ ይገነዘባል፡፡ ይሁን እንጂ ከምርጫ ጋር የተያያዘ መረጃን አስቀድሞ ለሕዝብ ይፋ የማድረጉ ጉዳይ በሁሉም ባለድርሻ አካላት ዘንድ በቂ ግንዛቤና ትኩረት አግኝቷል ማለት አይቻልም፡፡ ሉዓላዊ የሥልጣን ባለቤት የሆነው ሕዝብ በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ዘንድ ትክክለኛ መረጃ ማግኘት ባለመቻሉ ለአሉባልታ ወሬና ለሐሰተኛ መረጃ መጋለጡ ልብ ይሏል፡፡
የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም በመገናኛ ብዙኃንና መረጃ ነፃነት አዋጅ ቁጥር 590/2000 አንቀጽ 13 መሠረት በመንግሥታዊ አካላት ለሕዝብ ይፋ እንዲደረጉ ስለታዘዙ መረጃዎች ዝርዝር ማብራሪያ የማዘጋጀት፣ እንዲሁም የመረጃ ነፃነትን አፈጻጸም አስመልክቶ አሠራሮችን ለማዳበርና ለመሻሻል የሚረዱ አጠቃላይና ወይም ዝርዝር የውሳኔ ሐሳቦችን ለመንግሥታዊ አካላት የማቅረብ ኃላፊነት ተሰጥቶታል፡፡
ስለሆነም ተቋማችን ከምርጫ ጋር በተያያዘ በሰዎች መረጃ የማግኘት መብት ትግበራ ላይ የሚታዩትን ዋና ዋና ክፍተቶች እንዲሻሻሉ የውሳኔ ሐሳብ ለማቅረብ ይረዳው ዘንድ የክትትልና ድጋፍ ጋይድ ላይን አዘጋጅቶ ወደ ሥራ ገብቷል፡፡ በክትትልና ድጋፍ ወቅት በሚታዩት የአፈጻጸም ክፍተቶች ላይ እንደ አስፈላጊነቱ ጉዳዩ ለሚመለከተው አካል የውሳኔ ሐሳብ የምናቀርብ ወይም በጋዜጣዊ መግለጫ ለሕዝብ ይፋ የምናደርግ ሲሆን፣ ምርጫ ቦርድና ባለድርሻ አካላት ለተቋማችን የክትትልና ድጋፍ ባለሙያዎች ተገቢውን ትብብር እንድታደርጉ እንጠይቃለን፡፡
የምርጫ ተዋናዮችና የምርጫ መረጃ የማድረስ ኃላፊነት ያለባችሁ አካላትም በሙሉ የምርጫ መረጃዎችን የአካል ጉዳት ያለባቸውንና ልዩ ትኩረት የሚሹ የኅብረተሰብ ክፍሎችን፣ የቋንቋ ብዝኃነት፣ የአገሪቱን የቆዳ ስፋትና የሕዝብ ቁጥር ታሳቢ በማድረግ በተለያዩ የመገናኛ አማራጮች በመጠቀም የቅድመ ምርጫ፣ የምርጫ ዕለትና የድኅረ ምርጫ መረጃዎችን ለሁሉም ዜጎች ተደራሽ ታደርጉ ዘንድ ከወዲሁ እናሳስባለን፡፡
የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም