Saturday, December 9, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹ለእሳትና ድንገተኛ አደጋዎች ምላሽ አሰጣጣችንን በቴክኖሎጂ ለማዘመን እንቅስቃሴ ጀምረናል›› አቶ ሰለሞን ፍሰሐ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የእሳትና አደጋ ሥጋት አመራር ኮሚሽነር

በአዲስ አበባ የሚከሰቱ የእሳት አደጋዎች በጣም እየጨመሩ ስለመሆናቸው መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ የአብዛኞቹ የእሳት አደጋ መንስዔዎች በውል ባይታወቁም ከጥንቃቄ ጉድለት፣ ከቤቶች መተፋፈግና ተቀጣጣይ ነገሮችን በአንድ ላይ ከማስቀመጥ የሚመጡ መሆናቸው ይነገራል፡፡ በዚህ ምክንያት በከተማው በአማካይ በቀን ስድስት ድንገተኛ የእሳት አደጋዎች ይከሰታሉ፡፡ በብዙ ሚሊዮን ብር የሚቆጠሩ ንብረቶች ይወድማሉ፣ ጥቂት የማይባሉ ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል፡፡ በዚህም የከተማው የእሳትና አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን አደጋ በተከሰተበት ቦታ ቶሎ ያለ መድረስ ችግሮች እንዳሉበት በተደጋጋሚ ኅብረተሰቡ ቅሬታ ሲያቀርብ ይሰማል፡፡ ኮሚሽኑ ሕንፃዎች ሲገነቡም ሆነ ከመገንባታቸው በፊት የእሳትና አደጋዎችን ስታንዳርድ ያማከሉ ሥራዎች እንዲሠሩ የመቆጣጠር ኃላፊነት ቢኖርበትም፣ አሠራሩ አስገዳጅ ባለመሆኑ ምክንያት የሰዎች ሕይወት፣ ንብረትና ደኅንነት ላይ ከፍተኛ ሥጋት ተደቅኗል፡፡ በሌሎች አገሮች የእሳት አደጋዎች ከመድረሳቸው በፊት ቅድመ አደጋ መከላከል ሥራ እንዳላቸው ይታወቃል፡፡ ኢትዮጵያ ከእነዚህ አገሮች ተርታ መድረስ ባትችል እንኳን፣ የእሳት አደጋዎች ከተከሰቱ በኋላ ቶሎ ማጥፋትና መቆጣጠር ላይ ክፍተቶች እንዳሉ ይታወቃል፡፡ ከእሳትና ከአደጋ ጋር በተያያዘ ከግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ ያስቆጠረ ተቋም በመዲናይቱ ይገኛል፡፡ በርከት ያሉ አደጋዎችን እያስተናገደች ስላለችው አዲስ አበባ ከተማ የአደጋ ምላሽ አሰጣጥ መዘግየትና በቴክኖሎጂ የታገዘ ያለመሆን ችግሮችን ጨምሮ መፍትሔዎች ላይ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የእሳትና አደጋ ሥጋት አመራር ኮሚሽነር ከአቶ ሰሎሞን ፍስሐ ጋር ሔለን ተስፋዬ ያደረገችው ቆይታ እንዲህ ተጠናቅሯል፡፡

ሪፖርተር፡- ለ87 ዓመታት የእሳት አደጋ መከላከል አገልግሎት በመባል፣ እንዲሁም አሁን የእሳትና አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን በሚል ስያሜ እየተንቀሳቀሰ የሚገኝ ተቋም ነው፡፡ ነገር ግን ከጊዜ ወደ ጊዜ ከተማዋ ብትስፋፋም የእሳት አደጋዎች ቁጥር ከፍ እያለ ነው፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ኮሚሽኑ ለከተማዋ የሚመጥን የአደጋ መከላከልና መቆጣጠር ሥራ እያከናወነ ነው ማለት ይቻላል?

አቶ ሰለሞን፡- ኮሚሽኑ በመዲናይቱ ካሉ ነባር ተቋማት ውስጥ አንዱ ነው፡፡ አሁን ያለው ኮሚሽን በአዋጅ 64/2011 መልሶ የተደራጀ ተቋም ነው፡፡ ከዚያ በፊት ባለሥልጣን የሚባል ሲሆን፣ ይሠራ የነበረው አደጋ ሲደርስ የማጥፋትና ቀድሞ የመከላከል ሥራ ብቻ ነበር፡፡ ከ2011 ዓ.ም. ጀምሮ ተጨማሪ ኃላፊነት ተሰጥቶታል፡፡ ይህም ሌላ ተቋም ዘንድ የነበረው በአደጋ ተጎጂ የሆኑትን ዜጎች መልሶ የማቋቋምና የማደራጀት ኃላፊነት ነው፡፡ ከቅድመ አደጋ ጀምሮ እስከ ድኅረ አደጋ ድረስ ያለውን ሥራ የሚያከናውን፣ ለአደጋ ሥጋት የሆኑ ቦታዎችን መለየትና ለሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ማሳወቅና አደጋው እንዲቀንስ የራሳቸውን ዕርምጃ እንዲወሰዱ የማሳሰብ ሥራ ይሠራል፡፡ ሰው ሠራሽም ሆነ የተፈጥሮ አደጋ ሲከሰት ተከታትሎ መጠኑን መቀነስና ሕይወት የማዳን ሥራ በኮሚሽኑ የሚከናወን ነው፡፡ በዚህ ምክንያት መፈናቅሎችና ሌሎች ጉዳቶች የደረሰባቸውን ግለሰቦች ማገዝና መደገፍ ለተቋሙ የተሰጠ ሥራ ነው፡፡ ለረዥም ዓመታት የተጓዘና ራሱን በየጊዜው እያሳደገ የመጣ ተቋም ነው፡፡ ከተማዋ እያደገች በመጣች ቁጥር ያንን የሚመጥን አደጋ የመከላከል ሥራ ለማከናወን ጥረት ይደርጋል፡፡ አሁን ባለንበት ደረጃ እንደ አገራችንም ሆነ እንደ ከተማ ብቸኛው ተቋም ይኼ ነው፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ ከመስፋፋቷ ጋር በተያያዘ ለአደጋ ተጋላጭነቷም በዚያው ልክ እያደገ መጥቷል፡፡ በተለይም አዲስ አበባ ለጎርፍና ለእሳት አደጋዎች የተጋለጠች ከተማ ነች፡፡ ምክንያቱም ቤቶች የተጠጋጉና የተፋፈጉ በመሆናቸው ለእሳት አደጋ መሰል ችግሮች የተጋለጡ ናቸው፡፡ በሌላ በኩል ተፋሰስ አካባቢ (ወንዝ ዳርቻ) የሚኖሩ የኅብረተሰብ ክፍሎች በክረምት ወቅት ያለባቸው ችግር የሚታወቅ ነው፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ግን በከተማዋ የእሳት አደጋዎች ሲከሰቱ የሚመጥን ነው ለማለት አያስደፍርም፡፡ ምክንያቱም ተቋሙ ለከተማዋ የሚመጥን አገልግሎት እንዳይሰጥ ብዙ ችግሮች አሉበት፡፡  

ሪፖርተር፡- በመዲናይቱ ረዣዥም ሕንፃዎች እየተገነቡ ናቸው፡፡ ከአረንጓዴ ልማት ጋር በተያያዘ ትልልቅ ፓርኮች፣ እንዲሁም የኢንዱስትሪ ፓርኮች ይገነባሉ፡፡ ለምሳሌ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እያስገነባ ባለው ሕንፃ 45ኛ ፎቅ ላይ እሳት አደጋ ቢከሰት፣ ይህንን የሚያጠፋ አቅም አላችሁ? በሚገነቡት ፓርኮች አደጋ ቢገጥም ዝግጁነታችሁና ተደራሽነታችሁ ምን ያህል ነው?

አቶ ሰለሞን፡- በከተማዋ ትልልቅ ሕንፃዎችና ኢንዱስትሪዎች እየተገነቡ ናቸው፡፡ እነሱን የሚመጥን አደጋ የመከላከልና የመቆጣጠር ዝግጅነት አለ ወይ ለሚለው በጣም ብዙ መሥራት እንደሚጠበቅብን እናምናለን፡፡ ለሕንፃዎች የሚሆኑ የተሰወሰኑ ግብዓቶች ለማስገባት ተሞክሯል፡፡ ለምሳሌ 72 ሜትር ርዝመት ያለው አንድ ‹‹ስካይ ሊፍት›› የሚባል የእሳት ማጥፊያ ማሽን አለን፡፡ እሱም 72 ሜትር ድረስ የተገነቡ ሕንፃዎች ላይ ብቻ ወጥቶ አደጋ ለመከላከል የሚያግዝ ነው፡፡ 72 ሜትር ድረስ ስንል በግምት እስከ 30 ፎቅ ድረስ አደጋ ሲከሰት ማጥፋትና መቆጣጠር የሚያስችል መሣሪያ ነው፡፡ በቂ ነው ወይ? በቂ አይደለም? እሱንም ተቋሙ በስስት ነው የሚጠቀመው፡፡ ምክንያቱም ከተበላሸ መጠገን የሚችሉ ባለሙያዎች እኛ አገር ባለመኖራቸው ነው፡፡ በሌሎች አገሮች በትልልቅ ሕንፃዎች ላይ እሳትና ሌሎች አደጋዎች ሲከሰቱ የሚጠቀሙት ሔሊኮፕተሮችን ነው፡፡ ኢትዮጵያ ደግሞ ለእሳት አደጋ የሚሆን ሔሊኮፕተር የላትም፡፡ ለዚህም ሲባል የሔሊኮፕተር ግዥ እንዲፈጸም ጥያቄ አቅርበን ምላሽ እየጠበቅን ነው፡፡ ሕንፃዎች ብቻ ሳይሆኑ በየዓመቱ የሚተከሉ ችግኞች ቁጥር ከፍ እያለ ነው፡፡ አብዛኞቹም እየፀደቁ በመሆናቸው በርካታ ደኖች በከተማዋና በከተማዋ ዙሪያ ይኖራሉ፡፡ ስለዚህ በበጋና በደረቅ አየር ምክንያት ድንገተኛ እሳት አደጋ የሚከሰትበት ዕድል ይኖራል፡፡ ለምሳሌ ራስ ዳሸን ተራራ በቅርቡ የደረሰው የደን ቃጠሎ ማሳያ ነው፡፡ ለዚህም ከኬንያ ሔሊኮፕተሮች መጥተው ነው እሳቱ የጠፋው፡፡ በፓርኮችና በገዳማት አካባቢ እያጋጠሙ ያሉ የእሳት አደጋዎችን እያየን ነው፡፡ እሳቱን ለመከላከል በመኪና መግባት ስለማይቻል በሔሊኮፕተር በመታገዝ ነው እሳቱን ማጥፋት የሚቻለው፡፡ ይህንን በተመለከተ 2013 ዓ.ም. በጀት ዓመት የሔሊኮፕተሮች ግዥ እንዲፈጸም የተጠየቀ ሲሆን እስካሁን ድረስ ምላሽ አላገኘንም፡፡ በ2014 ዓ.ም. በጀት ዓመት ምላሽ እናገኛለን ብለን እንጠብቃለን፡፡ በከተሞች ከሚገነቡ ሕንፃዎች ከፍታ አንፃር በሔሊኮፕተር የታገዙ እሳት ማጥፊያዎችን መጠቀም የግድ ይላል፡፡ ለምሳሌ 72 ሜትር ድረስ እሳት ማጥፋት የሚችለውን መሣሪያ ለማቆም ሰፊ ቦታ ይፈልጋል፡፡

ስለዚህ በእነዚህ ሰፊ ቦታ በሌላቸው አካባቢዎች አደጋ ቢደርስ፣ ይህንን መሣሪያ አገልግሎት ላይ ለማዋል አይቻልም፡፡ የከተማ ቱሪስት መዳረሻ በሆኑት ፓርኮች ለጊዜው ንዑስ ጣቢያዎችን ከፍተናል፡፡ በእንጦጦ ፓርክ አንድ ንዑስ ጣቢያ የተከፈተ ሲሆን፣ እዚያ ማሽነሪና የአደጋ መከላከያ ሠራተኞች ተሰማርተዋል፡፡ እነዚህ ብቻ በቂ ናቸው ወይ? በጭራሽ በቂ አይደሉም፡፡ ከከተማዋ መስፋፋት ጋር በተያያዘ ለእሳትና አደጋዎች ምላሽ ለመስጠት፣ ከዘመናዊ ቴክኖሎጂ በተጨማሪ ቅርንጫፎችን ማብዛት የግድ ይላል፡፡ አሁን ዘጠኝ ቅርንጫፎችና አንድ የማሠልጠኛ ተቋም አሉን፡፡ ማሠልጠኛው የሰው ኃይልን በማብቃት ለኮሚሽኑ የሚያቀርብ ብቸኛው ተቋም ነው፡፡ ሠራተኞችን ጀርመን ድረስ ሄደው ልምድ እንዲቀስሙና እንዲሠለጠኑ እናደርጋለን፡፡ አሁን ባለው የከተማዋ አደረጃጀት በ17 ቅርንጫፎች የእሳት አደጋ ምላሽ መስጠት የሚያስፈልግ ቢሆንም፣ በዚህ ዓመት በሦስት ተጨማሪ ቦታዎች ለመክፈት እንቅስቃሴ ጀምረናል፡፡ ቀሪዎቹ በሚቀጥለው በጀት ዓመት እንቅስቃሴ የሚደረግባቸው ናቸው፡፡ እነዚህ እንዳሉ ሆነው ንዑስን ጣቢያዎች መከፈት ስላለባቸው በሁሉም ቅርንጫፎች ለማብዛት እየሠራን እንገኛለን፡፡ ነገር ግን እነዚህን ቅርንጫፎች ለማብዛት አንደኛውና ትልቁ ማነቆ የግብዓትና (ተሽከርካሪዎች፣ አልባሳት) መሰል ነገሮች እጥረት መኖር ነው፡፡  

ሪፖርተር፡- ለእሳት አደጋ ምላሽ ለመስጠት የሚያገለግሉ ተሽከርካሪዎች ምን ያህል ናቸው? ለከተማው በቂ ስላልሆኑ እጥረቱን ለመፍታት ምን ዓይነት ዕርምጃ ወስዳችኋል? በቂ የሰው ኃይልስ አላችሁ?

አቶ ሰለሞን፡- አሁን በሥራ ላይ ያሉት 34 ተሽከርካሪዎች ናቸው፡፡ ተሽከርካሪዎቹ አዳዲሶችንም አሮጌዎችንም ጨምሮ ነው፡፡ የሚይዙት የውኃ መጠን እንደ ተሽከርካሪዎቹ ይለያያል፡፡ አሁን በኮሚሽኑ የሚገኙ ተሽከርካሪዎች ከ3,000 እስከ 6,000 ሊትር ውኃ የሚይዙ ናቸው፡፡ 3,000 የሚይዘው ሰፊ አደጋ በደረሰባቸው ቦታዎች በቂ አገልግሎት መስጠት አይችልም፡፡ በዚህም በኮሚሽኑ በኩል ደረጃቸውን የጠበቁና ከተማውን የሚመጥኑ ተሽከርካሪዎች ለመግዛት ጥናት አድርገን የጨረስን ቢሆንም፣ አሁን ካለው የውጭ ምንዛሪ ችግር ጋር ተያይዞ በበቂ ሁኔታ ገዝተን ማስገባት አልቻልንም፡፡ የውጭ ምንዛሪው በተገኘ ጊዜ ግዥ ይፈጸማል፡፡ እስከዚያው ድረስ ቦቴ መኪኖች ውኃ እንዲያቀርቡ ከአገር ውስጥ ለመግዛት ጥረት እየተደረገ ነው፡፡ በግዥ ሒደት ላይ ስላለን ያለውን ችግር በጊዜያዊነት እንፈታዋለን ብለን እናስባለን፡፡ ከተማዋን የሚመጥን ሥራ ለማከናወን በቂ የሠለጠነ የሰው ኃይል ማሟላት የመጀመርያው ነው፡፡ የሰው ኃይሉን በራሳችን እያሠለጥንን እንገኛለን፡፡ የአደጋ መከላከል ሥራ የሰው ኃይል የሚወስደው ከማሠልጠኛ ሲሆን፣ ቀሪዎቹ ከዩኒቨርሲቲዎች የሚገኙ ናቸው፡፡ በአደጋ ሥራ አመራርና መከላከል ብዙ የትምህርት ተቋማት እያስተማሩ አይደለም፡፡ አሁን ከባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ፣ ኮተቤ ሜትሮፖሊቲያን ዩኒቨርሲቲና አንዳንድ ዩኒቨርሲቲዎችም መጀመራቸውን ሰምተናል፡፡ ለተቋሙ እስከ 2,000 እና ከዚያ በላይ ሰው መቅጠር የተፈቀደ ሲሆን፣ አሁን ያለው የሰው ኃይል ከ2,000 ያነሰ ነው፡፡ ለምሳሌ በ2013 ዓ.ም. 270 ሚሊዮን ብር ለአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ምላሽ ለመስጠት ተመድቧል፡፡ ነገር ግን ግዥ ለመፈጸምና ከችግሩ ስፋት አንፃር በቂ አይደለም፡፡ ኮሚሽኑ 800 ያህል የአደጋ ሠራተኞች ሲኖሩት ገሚሱ በትምህርት የታገዙ፣ የተቀሩት ደግሞ በረዥም ጊዜ የሥራ ልምድ ያዳበሩ ናቸው፡፡ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትም በሰው ኃይል ረገድ በቅርቡ ነው ትምህርት መስጠት የጀመሩት፡፡

ሪፖርተር፡- ቅድመ አደጋ መከላከል እንዴት ነው የምትሠሩት? ለአደጋዎች መንስዔ የሆኑ ነገሮች ምንድናቸው?

አቶ ሰለሞን፡- የኮሚሽኑ ትልቁ ሥራ ብለን የምንወስደው አደጋ መከላከል ነው፡፡ አደጋ ከመድረሱ በፊት የሚከናወኑ ሥራዎች አሉ፡፡ ኢትዮጵያ ደሃ አገር በመሆኗ መጀመርያ መሠራት ያለበት አደጋ እንዳይደርስ ማድረግ ነው፡፡ አብዛኞቹ የእሳት አደጋዎች የሚደርሱት ከግዴለሽነትና ከጥንቃቄ ጉድለት የተነሳ ነው፡፡ ለምሳሌ የ2013 ዓ.ም. ሩብ ዓመት የሥራ አፈጻጸምን ስንመለከት 87 በመቶ የሚሆኑ የእሳት አደጋዎች የተነሱት በኤሌክትሪክና በሌሎች መሰል ምክንያቶች ነው፡፡ ሶኬት ባለመንቀል፣ ካውያ ባለመንቀል፣ በአንድ ሶኬት ብዙ ሆኖ መጠቀም፣ መብራት ጠፍቶ ሲመጣ ኃይል በመጨመርና ሻማ ለኩሶ በመርሳት የተከሰቱ ናቸው፡፡ ሲሊንደርና ቡታ ጋዝም እንዲሁ ምክንያቶች ሲሆኑ፣ ከሕንፃ መደርመስ ጋር ተያይዞ ደግሞ በኮንስትራክሽን ላይ ያሉ ባለሙያዎች በቂ የአደጋ ጊዜ መከላከያ ሳያደርጉ ሲቀሩና የሥራ ቦታ ግብዓቶች ትክክለኛ ባለመሆናቸው የሚደርሱ አደጋዎች ናቸው፡፡ በየመንገዱ ያሉ ቱቦዎች ባለመደፈናቸው ምክንያት በዜጎች ላይ የሚደርሰው ጉዳት ቀላል የሚባል አይደለም፡፡ በዚህም ከሚመለከታቸው የመንግሥት ዘርፎች ጋር አጥንተን በደብዳቤ አሳውቀናል፡፡ ከአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን፣ ከውኃና ፍሳሽ አገልግሎት ባለሥልጣንና ከሌሎች ጋር ተነጋግረን እንሠራለን፡፡

በሌላ በኩል በወንዝ ዳርቻ የተሠሩ በርካታ መኖሪያ ቤቶች አሉ፡፡ ክረምት ሲመጣ በጎርፍ አደጋ ይጥለቀለቃሉ፡፡ የገበያ ቦታዎችን ስንመለከት በበጀት ዓመቱ ከፍተኛ የእሳት አደጋዎች የተከሰቱባቸው ናቸው፡፡ አዋሬና ዕፎይታ የገበያ ማዕከላትን ማየት ይቻላል፡፡ ለምሳሌ ዕፎይታ የገበያ ማዕከልን ስንመለከት ብዙ ተቀጣጣይ ነገሮች ይሠራሉ፡፡ እዚያው ደግሞ የእንጨት ሥራዎች አሉ፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ ትልቁ ችግር በገበያ ሥፍራዎችና በመኖሪያ አካባቢዎች የእሳት አደጋዎችን ገብቶ ለመከላከል መንገዱ ዝግ በመሆኑ አስቸጋሪ ናቸው፡፡ በጣም በርካታ በሆኑ የገበያ ቦታዎች የትኛው ላይ ምን ዓይነት አደጋ ይከሰታል የሚለውን ጥናት በማድረግ ለንግድ ቢሮ አሳይተናል፡፡ ከዚያ ባሻገርም በጋራ ከገበያ አመራሮች ጋር ውይይት አድርገናል፡፡ እንዲሁም በከተማው አዳዲስ ሞሎች ይሠራሉ፡፡ ምን ያህሉ የአደጋ ጊዜ መውጫ አላቸው? ምቹ ናቸው ወይ? አደጋ ቢከሰት በሕንፃቸው ውስጥ የሚቀመጥ እሳት ማጥፊያ አላቸው ወይ? ይሠራል ወይ? እሱን ማንቀሳቅስ የሚችሉ ባለሙያዎች አሉ ወይ? የሚሉ ብዙ ጥያቄዎች ስናነሳ ብዙዎቹ አያሟሉም፡፡ በሚገነቡ ሕንፃዎች ላይ ጭስ፣ እሳትና ሌሎች አደጋዎች ሲኖሩ የሚጮህ መሣሪያ እንዲገጠም በአዋጅ ተቀምጧል፡፡ የግንባታ ፈቃድ ሲያወጡ መሥፈርቱን የሚያሟሉ ብዙዎች ቢሆኑም፣ በተገቢው ሁኔታ ሕንፃዎቹ ላይ ተግባራዊ ተደርጓል ለማለት ግን አያስደፍርም፡፡ በከተማዋ ያሉትን ሕንፃዎች ማየት ይቻላል፡፡ ብዙዎቹ በሚባል ደረጃ አያሟሉም፡፡

ኮሚሽኑ ይኼንን የሚከታተል ግብረ ኃይል ቢኖረውም ደንብ (መመርያ) ወጥቶለት ማስገደድ አልቻለም፡፡ ይኼን ለማድረግ ደንብ ወጥቶ የካቢኔ ውሳኔ እየተጠባበቅን እንገኛለን፡፡ ደንቡ ሲፀድቅና ማስገደድ ስንጀምር በፍርድ ቤት መጠየቅ እንጀምራለን፡፡ ከአዋጁ ተነስተን የሕንፃዎችን ግንባታዎች በተመለከተ ደንብ አውጥተናል፡፡ የከተማችን ዓቃቤ ሕግ ደግሞ ደንቡን ዓይቶ የካቢኔ ውሳኔ በመጠባበቅ ላይ እንገኛለን፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ንግድ ቢሮ ፈቃድ ሲያድስ እንደ አንድ መሥፈርት መውሰድ ያለበት፣ ከአደጋ መከላከል አንፃር ሞሎችና የገበያ ሥፍራዎች የአደጋ ጊዜ መከላከያ መጠቀም እንዳለባቸው ነው፡፡ በሌላ በኩል የገበያ ማዕከላት አንድ የእሳት አደጋ ባለሙያ ቢኖራቸው ይመረጣል፡፡ ምክንያቱም ብዙ አደጋዎች የሚከሰቱት ተቀጣጣይ ነገሮችን አንድ ላይ በማስቀመጥ በመሆኑ ነው፡፡ ባለሙያው በየሕንፃው እየሄደ እንዲያጠና፣ እንደሁም እንዲያስተምር ቢያደርጉ የተሻለ ይሆናል፡፡ የሚቀጣጠሉ ነገሮችን በአንድ ላይ የሚያስቀምጡ ብዙ ናቸው፡፡ አደጋው ቢፈጠር እንኳን ቶሎ ሳይዛመት እንዴት ማጥፋት እንዳለበት፣ ለኮሚሽኑ እንዴት ማሳወቅ እንዳለበት የሚያውቅ ባለሙያ በሞሎች ላይ ቢኖር ይመከራል፡፡ የመንግሥትም ሆነ የግል ዘርፎች የንብረትና የሒሳብ ባለሙያ እንዳላቸው ሁሉ አንድ የአደጋ ጊዜ ሠራተኛ ቢኖራቸው አደጋ እንዳይደርስና ከደረሰም በኋላ አፋጣኝ ምላሽ በመስጠት ችግሩን ለመቅረፍ ያግዛቸዋል፡፡ ብዙዎች እንደ ትርፍ ነገር ነው የሚያዩት፡፡ ነገር ግን አስገዳጅ መሆን እንዳለበት ኮሚሽኑ ያምናል፡፡ በሠራተኛ ደረጃ ኮሚሽኑ የአደጋ ጊዜ ሠራተኛ እንዲኖራቸው ማስገደድ ባይችልም፣ ሕንፃዎቹ ግን የአደጋ ጊዜ መከላከል የሚውሉ ግብዓቶችን እንዲሟሉ ማስገደድ ይችላል፡፡ በዚህ ረገድ ለማስተካከል ከንግዱ ማኅበረሰብ ውይይት አድርገናል፡፡ በቅርቡ ከኢንዱስትሪ ባለቤቶች ጋር ውይይት ለማድረግ ከኢንዱስትሪ ቢሮ ጋር እየተነጋገርን እንገኛለን፡፡ ከጎርፍ ጉዳት ጋር በተያያዘ ተመሳሰይ ሥራዎች ሠርተናል፡፡ በየዓመቱ በጎርፍ የሚጠቁ አካባቢዎች በመለየት ኅብረተሰቡን ማንሳትና ተለዋጭ ቤት መስጠት እንደሚገባ ተናግረናል፡፡ ይኼ የወረዳና የክፍለ ከተማ አመራሮች ኃላፊነት በመሆኑ ችግሮቹን አሳውቀናቸዋል፡፡ እነዚህን ቦታዎች ለይተን በደብዳቤ ለክፍለ ከተማ አመራሮች አሳውቀናል፡፡ ነገር ግን እኛ ማስገደድ አንችልም፡፡  

ሪፖርተር፡- እሳትና ድንገተኛ አደጋዎች በደረሱባቸው ቦታዎች ለመድረስ ትዘገያላችሁ፡፡ በዚህም ምክንያት ኅብረተሰቡ በተደጋጋሚ ቅሬታውን ያቀርባል፡፡ ለምንድነው የምትዘገዩት? ቶሎ በሥፍራው መድረስ የማትችሉበት ምክንያት ምንድነው?

አቶ ሰለሞን፡- ኅብረተሰቡ የሚያቀርበው ቅሬታ ለመዘግየት ብቻ አይደለም፡፡ ስልካችሁን ቶሎ አታነሱም የሚሉ ቅሬታዎች ጭምር ይቀርባሉ፡፡ ይኼን በሁለት መንገድ ከፍሎ ማየት ያስፈልጋል፡፡ አንደኛው ያለንበት ቦታና አደጋው የሚደርስበት የቦታ ርቀት ነው፡፡ በቅርቡ ጀሞ አካባቢ የደረሰውን አደጋ ብንመለከት የእኛ ቅርንጫፍ ያለው ኮልፌ ነው፡፡ ከኮልፌ ቤተል አካባቢ ተነስተን ለመሄድ መንገዱ እጅግ ተጨናንቆ እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡ አንደኛውና ዋነኛ ቶሎ የሚንደርስበት ምክንያት የትራፊክ መጨናነቅና መኪና ሲያልፍ ቅድሚያ በመስጠት መንገድ ያለ መልቀቅ ችግሮች አሉ፡፡ ተለዋጭ ወይም እንደ ሌሎች አገሮች ለአደጋ ጊዜ ተብሎ የተሠሩ መንገዶች ባለመኖራቸው ጭምር እንዘገያለን፡፡ መኪኖቻችንን እያስጮህን መንገድ የማይለቁ በርካታ አሽከርካሪዎች ናቸው ያሉት፡፡ አንዳንዴ መኪኖቻችን ይጋጫሉ፣ አንዳንዴም ሌሎች መኪኖች ይጋጫሉ፡፡ በዚህ ምክንያት እሳት ለማጥፋት እየሄዱ መንገድ ላይ የቀሩ ብዙ አሉ፡፡ እነዚህ ደግሞ በጣም መሠረታዊ ችግሮቻችን ናቸው፡፡ በሌላ በኩል ጥሪ ቶሎ ያለ መድረስ ጉዳይ ሌላኛው ችግር ነው፡፡ የእኛን የጥሪ ቁጥር ኅብረተሰቡ የማወቅ ችግር እንዳለበት ገምግመናል፡፡ አንዳንድ ጊዜ አደጋዎች ሲከሰቱ ቁጥሩን ስለማያውቁ መጥተው ይነግሩናል፡፡ በቅርቡ ተክለ ሃይማኖት ጎላ ሚካኤል አካባቢ አደጋ ሲከሰት ስልካችንን ማወቅ ስላልቻሉ በሞተረኛ መጥተው ለመንገር ተገደዋል፡፡ እንግዲህ እነሱ እዚህ እስኪደርሱና እኛ እዚያ እስክንደርስ የሚፈጠረውን ውድመት ማሰብ ከባድ ነው፡፡ እንደ አገርም እንደ ከተማም በጣም አጫጭር ስልኮች አሉ፡፡ የፖሊስ፣ የውኃ፣ የመብራት፣ የአደጋ፣ የቀይ መስቀልና የሌሎቹም የተለያዩ ሕዝባዊ አገልግሎት የሚሰጡ አጫጭር ቁጥሮች አሉ፡፡ ኅብረተሰቡ በእነዚህ ቁጥሮች ምክንያት ግራ ሊጋባ ይችላል፡፡ የሌሎች አገሮች ተሞክሮ የሚያሳየው አንድ ቁጥር ያላቸው ሲሆን፣ ቀጥታ ወደ ፈለጉት ተቋም እንዲደርስላቸው ይደረጋል፡፡

ስለዚህ ሕዝቡ በቀላሉ አንድ ቁጥር መያዝ ይችላል ማለት ነው፡፡ ነገር ግን ይኼ ሁሉ ቁጥር በቀላሉ ሊይዙ ስለማይችሉ ጥሪው ቶሎ ሳይደርስ መዘግይት ይፈጠራል፡፡ ከዚያ ውጪ እኛ ዘንድ የሥነ ምግባር ችግር ያለባቸው ሠራተኞች በወቅቱ ጥሪውን ላያደርሱ ይችላሉ፡፡ በዚህ ረገድ እኛም ችግሮቻችንን እየፈተሽን እናሻሽላለን፡፡ እሱ ብቻ ሳይሆን አደጋው ቦታ ከደረስን በኋላ ቶሎ አታጠፉም የሚሉ ቅሬታዎችም ይቀርቡልናል፡፡ እሳት የደረሰበት ቦታ ላይ ውኃ ለመርጨት መጀመርያ ኤሌክትሪክ መቋረጥ አለበት፡፡ አደጋ ደረሰ ብለን በቦታው ላይ ስንገኝ የኤሌክትሪክ አገልግሎት መቋረጥ ደግሞ አለበት፡፡ ሁለቱን ተቋማት አደጋ ሲከሰት የሚያስተሳስር ዘዴ ያስፈልጋል፡፡ ወይም እኛ ደርሰን ኤሌክትሪክ እስኪቋረጥ ድረስ መጠበቅ የግድ ይላል፡፡ እኛና የውኃና ፍሳሽ አገልግሎት ባለሥልጣን የጋራ ዕቅድ አውጥተን ከቅርንጫፎቻችን ጋር ለማስተዳደር ጥረት እያደረግን እንገኛለን፡፡   

ሪፖርተር፡- ለአደጋ ጊዜ ሠራተኞች አደጋ መከላከል የሚያስችሉ አልባሳትና ሌሎች ግብዓቶች አሏችሁ? የሠራተኞቹ ደኅንነት ጉዳይስ?

አቶ ሰለሞን፡- የሥራው ባህሪ ብዙ ዋጋ የሚያስከፍል ነው፡፡ ለሠራተኞች የሚሆኑ በቂ አልባሳት የሉንም፡፡ የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች አልባሳት ውድ ናቸው፡፡ አንድ የአደጋ መከላከያ ጃኬት በትንሹ 40,000 ብር ያስወጣል፡፡ አሁን ባለው የዶላር ምንዛሪ ጭማሪ ደግሞ ከዚህ በላይ ዋጋው ሊጨምር እንደሚችል መገመት ይቻላል፡፡ እኛ 800 ሠራተኞች አሉን፡፡ አሁን እጃችን ላይ ያሉት ከ100 የማይበልጡ አልባሳት ናቸው፡፡ አሁን ባለው የኮሮና ወረርሽኝ አንዱን ለአንዱ ማልበስ አይቻልም፡፡ በዚህ ምክንያት በርካቶች ዩኒፎርማቸው ለብሰው እሳት ለማጥፋት ይገደዳሉ፡፡ አብዛኛው ዕቃ በኢትዮጵያ ብር የሚገዛ አይደለም፡፡ እነዚህን ውድ ዕቃዎች ከውጭ የሚያስመጡ የሉም፡፡ በዚህ ምክንያት ከውጭ በጨረታ በውጭ ምንዛሪ እንዲገዙ ይደረጋል፡፡ ኮሚሽኑ ግብዓቶች ተሟልተውለት በሚፈለገው ደረጃ የተደራጀ ነው ለማለት አይቻልም፡፡ አንድ ሰው ውኃ ውስጥ ሲገባ የእኛ ዋናተኞች ናቸው ሄደው የሚያወጡት፡፡ ለዚህ ደግሞ ትልቅ መኪና ይዞ መንቀሳቀስ አስቸጋሪ ነው፡፡ የትራፊክ መጨናነቅ እንዳይኖር ትንንሽ መኪኖች ያስፈልጋሉ፡፡ ግብዓትን በተመለከተ መንግሥት ትልቅ ትኩረት ሰጥቶ ሊያሟላ የሚገባ ይመስለኛል፡፡

ሪፖርተር፡- ሠራተኞቻችሁ የግብዓት እጥረት ባለበት ሁኔታ አደጋ ቢደርስባቸው ምን ዓይነት ዋስትና አላቸው?

አቶ ሰለሞን፡- የሥራው ባህሪ ብዙ ዋጋ የሚያስከፍል ነው፡፡ አብዛኞቹ ሠራተኞቻችን ወጣቶች ናቸው፡፡ ሥራው በጣም ጉልበት የሚጠይቅ ነው፡፡ ጥሩ መመገብና ስፖርት መሥራት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ኮሚሽኑ የሚከፍላቸው ገንዘብ አነስተኛ ነው፡፡ ከከተማ ውስጥ አነስተኛ ክፍያ ከሚከፍሉ ተቋማት ኮሚሽኑ አንዱ ነው፡፡ ብዙዎች በትምህርት የዘለቁ አይደሉም፡፡ የረዥም ዓመት ልምድ ያዳበሩ ናቸው፡፡ አደጋ ሲደርስ ሠራተኞቻችን እሳቱን ለማጥፋት እንጂ ራሳቸው ላይ የሚደርሰውን ነገር አያስቡም፡፡ በቅርቡ የተከሰቱ አደጋዎችን ብናነሳ የቆርቆሮ ጣሪያ ላይ ወጥተው ለማጥፋት ሲሞክሩ ተደርምሶ ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡ እግራቸው ላይ ጉዳት የደረሰባቸው፣ የጀርባ ወገባቸው ብረት ገብቶለት የሚታከሙ አሉ፡፡ ኮሚሽኑ ማሳከም የሚችለው ድሮ ጦር ኃይሎች ሆስፒታል ነበር፡፡ አሁን ደግሞ የካቲት 12 ሆስፒታል እንዲታከሙ ያደርጋል፡፡ ምን ያህል የመንግሥት ሆስፒታሎች የሚያስፈልገውን ሕክምና ይሰጣሉ የሚለው ሌላ ጥያቄ ነው፡፡ አብዛኞቹ ምርመራዎች ከሆስፒታሎቹ ውጪ የሚከናወኑ ናቸው፡፡ የመድኃኒት፣ የላቦራቶሪ ውጤትና መሰል ነገሮች በውጭ የሚደረጉ በመሆናቸው ልንደግፍበት የሚችል አሠራር የለንም፡፡

ሪፖርተር፡- በመንግሥት ሆስፒታል ሕክምና መስጠት የማያስችል ጉዳት ከደረሰ ምንድነው የሚደረገው?

አቶ ሰለሞን፡- በመንግሥት ሆስፒታል መታከም የማይቻል ከሆነ ተጨማሪ ነገር ማድረግ የሚቻልበት አሠራር የለም፡፡ አሁን ግን መመርያ አውጥተን እየጠየቅን ነው፡፡ ከአካል ጉዳት ጋር በተያያዘ ብዙ ጊዜ ሠራተኞቻችን ችግር ይገጥማቸዋል፡፡ አደጋ ለመከላከል የሚውሉ ጫማዎች ደግሞ ጥቂቶች ነው ያሉት፡፡ በአንድ አደጋ በሁለትና በሦስት ሰዎች ላይ ጉዳት መድረሱ የተለመደ ነው፡፡ አብዛኞቹ ከእሳት አደጋዎች በተጨማሪ ውኃ ውስጥ የገባን ሰው ለማዳን ይሰማራሉ፡፡ የአዲስ አበባ ወንዞች እንደሚታወቀው በኬሚካልና በተለያዩ ፍሳሾች የተበከሉ በመሆናቸው ሠራተኞች ለተለያዩ በሽታዎች ይጋለጣሉ፡፡ አንዳንዶቹ አደጋዎች በአንድ ቅርንጫፍ ብቻ ምላሽ የሚሰጥባቸው አይደሉም፡፡ ለምሳሌ ወለቴ አካባቢ በደረሰ አደጋ ከተማ ውስጥ ያሉ ቅርንጫፎች በሙሉ እዚያ ሄዱ፡፡ እዚያ እያለን መነን ትምህርት ቤት አካበቢ የቤት ቃጠሎ ተብሎ መረጃ ደረሰን፡፡ አንዳዴም እንዲህ ዓይነት ችግሮች ይገጥሙናል፡፡ በሌላ በኩል የውኃ እጥረትም አንዱና ትልቁ ችግር ነው፡፡ አሁን ባለው የውኃ እጥረት የተነሳ አደጋ በደረሰበት ቦታ ያለው የውኃ መቅጃ ውኃ ላይኖረው ይችላል፡፡ ስለዚህ ውኃ ያለበት ቦታ ሄደን እንድናመጣ እንገደዳለን፡፡ ለውኃና ፍሳሽ ባለሥልጣን ብንደውል እንኳን ቶሎ ላይደርስ ይችላል፡፡ ምክንያቱም ውኃው በግፊት እስኪደርስ ጊዜ ስለሚወስድ ቦቴ መኪኖች የመግዛት አማራጭ ለመውሰድ ተገደናል፡፡ ትልልቅ መኪኖችን መግዛት እስኪቻል ድረስ ቦቴ መኪኖችን ለመግዛት በጨረታ ሒደት ላይ ነን፡፡ በአጠቃላይ ከጤናቸው፣ ከሥራ ሁኔታቸውና መሰል ሁኔታዎች አንፃር እስከ ውጭ  ሕክምና ድረስ አጥንተን በካቢኔ ደረጃ ይወሰናል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ በቅርቡ ለሠራተኞች የተወሰነ ጭማሪ ተደርጎላቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- አሁን ባለው ሁኔታ የእሳት አደጋ ሊከሰት ሰዎች ሲደውሉላችሁ ብቻ ነው ጥሪ የሚደርሳችሁ፡፡ ከዚያ ውጪ ሰዎች ሳይደውሉ ወደ ጥሪ ማዕከሉ የሚደርስበት ቴክኖሎጂ ለመዘርጋት አልታሰበም?

አቶ ሰለሞን፡- ለእሳትና ድንገተኛ አደጋዎች ምላሽ አሰጣጥ በዓለም ላይ ያሉ ቴክኖሎጂዎች በጣም እያደጉ መጥተዋል፡፡ ለእሳትና ድንገተኛ አደጋዎች ምላሽ አሰጣጣችንን በቴክኖሎጂ ለማዘመን ከሳይንስና ቴክኖሎጂ ኤጀንሲ ጋር እንቅስቃሴ ጀምረናል፡፡ መኪኖቻችን ጂፒኤስ ሲገጠምላቸው ለአደጋ ሲወጡ ከተማዋን ለመቃኘት ይችላሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ሙሉ የከተማዋን ሁኔታ በእስክሪን እየተከተታሉ አጠራጣሪ ነገር ሲኖር ቀድሞ ለመድረስ የሚያገለግሉ ናቸው፡፡ በከተማዋ ያሉ ካሜራዎችን በማብዛት እንቅስቃሴዎችን ከአደጋ ሥጋት መከላከል የሚቻልበትን አሠራር ለመዘርጋት በሒደት ላይ እንገኛለን፡፡ ቅድም ሳልገለጸው ያለፍኩት ትልቁ ችግር በመስመር ስልኮቻችን የሚገቡ ሐሰተኛ ጥሪዎች ጉዳይ ነው፡፡ 939 ነፃ የስልክ ቁጥራችን ነው፡፡ አደጋ ሳይፈጠር ተፈጠሯል የሚሉ አላስፈላጊ ጥሪዎች ትልቅ ችግር ናቸው፡፡ አንዳንዴም ተፈጥሯል የተባለው ቦታ ላይ ስንደርስ የማይገኘበት ሁኔታ አለ፡፡ ስለዚህ በየአካባቢው በካሜራ መታከተልና ሰዎች ከመደወላቸው በፊት ቦታው ላይ የሚደርስ ቴክኖሎጂ መጠቀም በእጅጉ አስፈላጊ ነው፡፡ በነፃ የስልክ መስመራችን ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ጥሪዎች ሐሰተኛ ናቸው፡፡ እነዚህን ነገሮች ለመቀነስ የሚቻለው በቴክኖሎጂ ማዘመን ሲሆን፣ ሁለት ዙር ጨረታ ወድቅ ሆኖብን ሦስተኛውን በአገር ውስጥ ልናሠራ እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው፡፡ እሱ በሚያልቅበት ጊዜ ደረጃውን የጠበቀ ቦታ ተዘጋጅቶለት ሙሉ ከተማዋን ለማየት የሚያስችል ሥርዓት ይዘረጋል፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹መንግሥት ለአገር ውስጥ የኅትመት ኢንዱስትሪ ገበያ ከመፍጠር ጀምሮ ሥራ የመስጠት ኃላፊነት አለበት›› አቶ ዘውዱ ጥላሁን፣ የኢትዮጵያ አሳታሚዎችና አታሚዎች ማኅበር ዋና ሥራ አስኪያጅ

የኅትመት መሣሪያ በጉተምበርግ ከተፈበረከ ከ400 ዓመታት በኋላ በኢትዮጵያ በ1863 ዓ.ም. በምፅዋ የተጀመረው የኅትመት ኢንዱስትሪ ከአፍሪካ ቀዳሚ ቢሆንም፣ ዕድገቱ ውስን መሆኑ ይነገራል፡፡ ከኢትዮጵያ በኋላ የኅትመት...

‹‹ከጨረታ በስተጀርባ ያሉ ድርድሮችን ለማስቀረት ጥረት እያደረግን ነው›› ሱሌማን ደደፎ (አምባሳደር)፣ የኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ (የቀድሞ ሜቴክ) ዋና ሥራ አስፈጻሚ

ሱሌማን ደደፎ (አምባሳደር) በተባበሩት ዓረብ ኤሜሬትስ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ሆነው ሲያገለግሉ ከቆዩ በኋላ፣ ከጥር 8 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ በኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ የቦርድ...

‹‹ባለፉት 25 ዓመታት ባለን አቅም ሁሉ የተለያዩ አጀንዳዎችን ለመዳሰስ ሞክረናል›› የራስወርቅ አድማሴ (ዶ/ር)፣ የፎረም ፎር ሶሻል ስተዲስ ዋና ሥራ አስፈጻሚ

‹‹ፎረም ፎር ሶሻል ስተዲስ›› በመባል የሚታወቀውን በኢትዮጵያ ታሪክ ከመንግሥትም ሆነ ከሌላ አካል ገለልተኛ ሆኖ የተቋቋመ ሐሳብ አመንጪ የጥናት ተቋም (ቲንክ ታንክ) ከመሠረቱት አንዱ መሆናቸውን...