Monday, September 25, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

የጥሬ ገንዘብ ዝውውርን ለማስቀረት መሠረተ ልማቱ ይጠናከር!

የባንክ ኢንዱስትሪውን ለማዘመን ባንኮች የየራሳቸውን ጥረት እያደረጉ ነው፡፡ የዘመናዊ የባንክ አገልግሎት መገለጫዎች ናቸው የተባሉ አዳዲስ አሠራሮች እየተገበሩም ነው፡፡ ኢንዱስትሪውን ማዘመንም በጥሬ ገንዘብ ላይ መሠረት ያደረገውን የአገሪቱን የግብይት ሥርዓት በመለወጥ ረገድ ዓይነተኛ ሚና ይኖረዋል፡፡

በባንክ የአገልግሎት አሰጣጥ ረገድ ዓለም የደረሰበትን ደረጃ ለመቋደስም እነዚህ በቅርብ ዓመታት ውስጥ የተጀመሩ ዲጂታል የባንክ አገልግሎቶች ትልቅ ዕገዛ ይኖራቸዋል፡፡

ዘመናዊ የባንክ አገልግሎቶች እንዲጎሉና የጥሬ ገንዘብ አልባ እንቅስቃሴዎችን ለመተግበር የሚያስችሉ አሠራሮችን ለማስረፅም ብሔራዊ ባንክ እያወጣቸው ያሉ መመርያዎችም አጋዥ ይሆናሉ ተብሎ ይታመናል፡፡

ማንኛውም የገንዘብ እንቅስቃሴ ከጥሬ ገንዘብ ይልቅ በሌሎች አማራጭ ቴክኖሎጂዎች ማለትም ሞባይልና በኢንተርኔት የባንክ አገልግሎቶች እንዲሁም ከአንዱ ባንክ ወደ ሌላው ባንክ ገንዘብ ማዘዋወር እንዲቻል ጭምር ሁኔታዎች ተመቻችተው እየተተገበሩ ነው፡፡

በዕለት ከባንክ በጥሬ ገንዘብ ማውጣት የሚቻለው መጠን ገደብ እንዲበጅለትና ከ50 ሺሕ ብር በላይ ለማንቀሳቀስ ከተፈለገ ደንበኞች ሌሎች የገንዘብ ማንቀሳቀሻ ዘዴዎችን እንዲጠቀሙ የሚል መመርያ እንዲተገበር ከተደረገበት ምክንያቶች አንዱ ይኸው ዘመናዊ የባንክ አገልግሎትን ለማስፋትና በጥሬ ገንዘብ ግብይት ከማካሄድ ለመውጣት ነው፡፡

በጥሬ ገንዘብ የሚደረግ ግብይትን ቀስ በቀስ ማክሰምና ዲጂታል የባንክ አገልግሎቶችን ማስፋት የግድ ነው ተብሎ የተጀመረው ወቅታዊው ተነሳሽነት  ሌላም መገለጫ አለው፡፡ ይኽም ማንኛውም የገንዘብ ዝውውርና ጠቀሜታ የግብይት ሥርዓቱ ባንክን ማዕከል አድርጎ እንዲሠራ ማስቻሉ ነው፡፡

በየሜዳው ይታዩ የነበሩ በሚሊዮንና በቢሊዮን ብሮች የሚገመቱ ግዥና ሽያጮች ሕጋዊ መሠረት እንዲኖራቸው ከተፈለገ፣ ገዥ ክፍያ ሲፈጽም ሆነ ሻጭ ሲቀበል በባንክ የገንዘብ ዝውውሩ እንዲያካሂድ መደረጉ ለግብይት ሥርዓቱ ዘመናዊነት ትልቅ ጠቀሜታ አለው፡፡

ዲጂታል የባንክ አገልግሎቶችን በማጎልበት ከጥሬ ገንዘብ ለመውጣት የተጀመሩት ቴክኖሎጂ ቀመስ አገልግሎቶች ደንበኞች ባሉበት ቦታ ሆነው የተሻለ አገልግሎት የሚያገኙበት በመሆኑ ባንኮች እንደ አንድ መወዳደሪያ እያደረጉት ነው፡

ከጊዜው ጋር የተናበበ የክፍያ ሥርዓትን መጠቀም ጊዜና ጉልበትን በመቆጠብ ሕይወትን ቀለል ያደርጋል፡፡ በመሆኑም በኤቲኤም የተጀመረው አገልግሎት ዛሬ ላይ የሞባይል፣ የኢንተርኔትና የካርድ ባንክ አገልግሎቶችን ጨምሮ እያሰፋ በመምጣት አሁን ወደ ተለያዩ የካርድ አገልግሎት እየተገባና ያለው ተገልጋይ ቁጥርም  እየጨመረ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መመርያን መሠረት ያደረገው ከአንዱ ባንክ ወደ ሌላው ባንክ ገንዘብ ማዘዋወርና ተያያዥ አማራጭ የገንዘብ ማንቀሳቀሻዎችን የሚያሳልጡ አገልግሎቶች በሙሉ ግን የኢትዮ ቴሌኮምን መሠረተ ልማት የሚፈልጉ መሆናቸውን ልብ ማለት ይገባል፡፡

መሠረተ ልማቶች በአግባቡ አገልግሎት የማይሰጡ ከሆነ አሁን እየገባንበት ያለው ዲጂታል የባንክ አገልግሎት ግቡን አይመታም፡፡ በአሁኑ ወቅት ከባንክ ሥራው ጋር በተያያዘ አልፎ አልፎ ሳይሆን ብዙ ጊዜ ኔትወርክና ሲስተም የለም በሚል የሚፈጠር የአገልግሎት መስተጓጎል ደንበኞችን ምን ያህል እያማረረ እንደሆነ ይታወቃልና እንዲህ ያሉ መቆራረጦች ባሉበት ሁኔታ ዲጂታል የባንክ አገልግሎትን እንዴት ማስፋት ይችላል? የሚል ጥያቄ ማንሳቱ ተገቢ ነው፡፡

አሁን ላይ በዋናነት መታሰብ ያለበት ይህ ነው፡፡ ተወደደም ተጠላ እነዚህን ዲጂታል የባንክ አገልግሎቶችን ሁሉም መጠቀሙ ግድ መሆኑ ስለማይቀር እንዲሁም ገንዘብ ተሸክሞ ገበያ መውጣት ታሪክ የሚሆንበት ጊዜ እሩቅ አይደለምና አሁን መሞገት ያለብን ይህ ዓይነቱን አገልግሎት ለማግኘት የሚያስፈልጉ መሠረተ ልማቶች ጉድለት እንቅፋት መሆን የለበትም ብለን ነው፡፡

ገንዘብን በጥሬ ገንዘብ አታንቀሳቅሱ ሌሎች አማራጮችን ተጠቀሙ እየተባለ በሲስተም የለም ወይም ኔትወርክ የለም የሚል ሰበብ እንዳይሰማ ለማድረግ ከወዲሁ የሚታየውን ችግር በርትቶ በመሥራት መቅረፍ ይገባል፡፡ 

ከዚሁ ጋር ተያይዞ ከአንዱ ባንክ ኤቲኤም ማሽን የሌላ ባንክ ደንበኛ ለመገልገል ቢፈልግ እንደተባለው አገልግሎቱን ለማግኘት እንዴት አስቸጋሪ እንደሆነ ማየት ነው፡፡

ስለዚህ እንዲህ ያሉ እንቅፋቶች ባልጠፉበት ሁኔታ ከጥሬ ገንዘብ ግብይት እንውጣ የካርድ ባንክ አገልግሎትን እናስፋ ብሎ መነሳት ሊያመጣ የሚችለውን ችግር ከወዲሁ በማሰብ መሠረተ ልማቱ ላይ መሠራት አለበት፡፡

ዲጂታል ባንኪንግ ጠቀሜታው ከፍተኛ ነውና ሕዝብን ማስተማር የሁሉም የፋይናንስ ተቋማት ኃላፊነት ነው፡፡

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት