ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ሳቢያ በአንድ ዓመት ተራዝሞ ግንቦት 28 ቀን 2013 ዓ.ም. እንደሚከናወን ይፋ ከተደረገበት ጊዜ አንስቶ፣ በበርካቶች ዘንድ ሲነሳ የነበረው ጥያቄ ዕውን አገሪቱ ምርጫ ማድረግ የሚያስችል ሁኔታ ላይ ትገኛለች የሚል ነበር፡፡ ይኼንን ሥጋት ከዕለት ዕለት የሚያጎሉ ክስተቶች የምርጫው የጊዜ ሰሌዳ ዳግም ይፋ ከመደረጉ አስቀድሞ መታየት ጀምረው ነበር፡፡
በትግራይ ክልል በሚካሄደው ጦርነት ሳቢያ በክልሉ ምርጫ እንደማይደረግ ታውጆ በሌሎቹ የአገሪቱ አካባቢዎች ምርጫ ለማድረግ ምርጫ ቦርድ ሽር ጉድ ከተጀመረ እነሆ ወራት ሲቆጠሩ፣ የድምፅ መስጫ ቀኑም በሳምንታት የሚቆጠር ዕድሜ ቀርቶት ሳለም ቀድሞ ሲነሱ የነበሩ ጥያቄዎች እንዲሰሙ ያደረጉ ክስተቶችን ደጋግሞ መስማት አዲስ አልሆነም፡፡
በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል መተከልና ቡለን አካባቢዎች፣ በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ አራት ዞን የጉጂ ዞኖች፣ በደቡብ ክልል ከቤንች ሸኮ ዞን ጉራፈርዳ ወረዳ እስከ ደቡብ ኦሞና አማሮ ልዩ ወረዳ፣ በአማራ ክልል ከትግራይ ድንበር አካባቢዎች እስከ አጣዬና የኦሮሞ ብሔረሰብ ዞን የተለያዩ ሥፍራዎች፣ በአፋርና በሶማሌ ክልሎች ወሰን አካባቢዎች፣ በጋምቤላ ክልል በተለያዩ ሥፍራዎች የሚታዩ ግጭቶች ለጥያቄዎቹ ማጠናከሪያነት ይነሳሉ፡፡
የምርጫውን ዝግጅቶች ተከትለው የመጡት እንደ ሐረሪ ክልል ከክልል ውጪ ያሉ የብሔሩ አባላት ድምፅ ይስጡ የሚል ጥያቄና የቦርዱ አይሆንም ባይነት፣ የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር የከተማውና የገጠሩ ነዋሪ የምርጫ ክልል ቁጥር መዘበራረቅ ያስከተለው ውዝግብ፣ የአፋርና የሶማሌ ክልሎች ወሰን አካባቢ የሚገኙ 30 የምርጫ ጣቢያዎች የታቀዱባቸው ወረዳዎች ውዝግብና ምርጫ ቦርድ በእነዚህ ሥፍራዎች የምርጫ ጣቢያዎችን እንደማያቋቁም ማስታወቁ፣ የሶማሌ ክልል የምርጫ ቦርድ ውሳኔ ካልተስተካከለ በምርጫው ለመሳተፍ ያስቸግረኛል የሚል ዛቻ ማሰማቱ፣ ወዘተ ምርጫው አገሪቱ ያሉባትን ንቃቃት በማስፋት፣ ለመጠገን የሚያስቸግር ክፍተት ሊፈጥሩ ይችላሉ የሚል ሥጋትም እንዲደመጥ ያደርጋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም በምርጫ ቦርድ የምርጫ ዝግጅቶች ላይ ከፍተኛ ጫና እያደረሱ በመሆናቸው፣ ምርጫውን በታቀደለት የጊዜ ሰሌዳ ማከናወን ይቻላል ወይ? የሚል ጥያቄም እንዲነሳ ግድ ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ የምርጫ ዝግጅት ዕቅዱንና የምርጫ የጊዜ ሰሌዳውን ይፋ ካደረገና ወደ ትግበራ ምዕራፍ ከገባ ጀምሮ፣ በዕጩዎች ምዝገባና በመራጮች ምዝገባዎች ላይ የእነዚህ አገራዊ ችግሮች ጥላ እንዲያጠላ ሆኗል፡፡ በ673 የምርጫ ክልሎች በተከናወነው የዕጩዎች ምዝገባ ወቅት የክልሎች ትብብር አነስተኛ ስለነበረ የምዝገባ ጊዜው በሁለት የጊዜ ሰሌዳ እንዲመራ የተደረገ ሲሆን፣ በዚህ የዕጩዎች ምዝገባ ወቅት የታዩ ክፍተቶች 50,000 በሚሆኑ የምርጫ ጣቢያዎች የሚከናወነውን የዕጩዎች ምዝገባ ብሎም የድምፅ መስጫ ሒደቱን ሊጎዱ እንደሚችሉ ቦርዱ ቀድሞውንም አልካደም ነበር፡፡
ይኼ ሥጋት ግዘፍ ነስቶ በአገሪቱ በአጠቃላይ ሊቋቋሙ ከታቀዱ የምርጫ ጣቢያዎች 50 በመቶ ብቻ እንዲቋቋሙ ያደረገ ሲሆን፣ የቅስቀሳ እንቅስቃሴንም ያስተጓጎለ ሆኗል፡፡ የምርጫ ቁሳቁስ ወደ ምርጫ ጣቢያዎች ለማሠራጨት በተደረገው እንቅስቃሴ፣ ከቦሌ ዓለም አቀፍ ኤርፖርትና በአዲስ አበባ የገበያ ልማትና ኤግዚቢሽን ማዕከል ተከማችተው የነበሩ ቁሳቁሶችን በማጓጓዝ ሒደት መከላከያ ካደረገው የአሥር ተሽከርካሪዎችና የአውሮፕላን ድጋፍ በተጨማሪ በሥምሪት የሚሠሩ ተሸከርካሪዎችን ለመጠቀም ጥረት ተደርጓል፡፡ ይሁንና አስቸጋሪ የመንገድ ሁኔታ፣ ከፍተኛ የማጓጓዣ የጨረታ ዋጋ አቅርቦት፣ እንዲሁም በቂና የተደራጁ የተሽከርካሪ ማኅበራትን ማግኘት አዳጋች እንደሆነ ተነግሯል፡፡ ለአብነት ያክልም በሰሜን ሸዋ ዞን በሚገኙ የምርጫ ጣቢያዎች የምርጫ ቁሳቁሶችን ለማሠራጨት በተደረገው ጨረታ ሦስት ማኅበራት 17 ሚሊዮን ብር ጠይቀዋል ተብሏል፡፡
ቦርዱ ይኼንን የዕጩዎች ምዝገባና የምርጫ ዝግጅት አስመልክቶ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ሚያዚያ 6 ቀን 2013 ዓ.ም. በሐያት ሬጀንሲ ሆቴል ባደረገው ምክክር እንደተነገረው፣ የገጠመው ችግር ከመጀመርያው ዕቅድ ላይ የአሥር ቀናት ጊዜ የበላ ውጣ ውረድ እንደነበረ የቦርዱ ሰብሳቢ ወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳ ተናግረዋል፡፡ ለዚህ ችግር መንስዔ ከሆኑ ጉዳዮች አንዱ በአገሪቱ ያለው የፀጥታ ችግር እንደሆነም አልሸሸጉም፡፡
ስለዚህም በአዲስ አበባ ይከፈታሉ ተብለው ከታቀዱ 1,848 የምርጫ ጣቢያዎች መካከል የተከፈቱት 1,662፣ በአፋር ከ1,432 ጣቢያዎች ምንም ጣቢያ አልተከፈተም፣ በአማራ ከ12,199 የምርጫ ጣቢያዎች የተከፈቱት 6,558፣ በቤንሻንጉል ከታቀዱ 699 የምርጫ ጣቢያዎች የተከፈቱት 286፣ በጋምቤላ ይከፈታሉ ተብለው ከታቀዱ 431 ጣቢያዎች የተከፈቱት 383፣ በኦሮሚያ ከታቀዱ 17,623 ጣቢያዎች የተከፈቱት 8,545፣ በሐረሪ ካታቀዱ 285 ጣቢያዎች የተከፈቱት 120፣ በድሬዳዋ ከተማ ከታቀዱ 431 ጣቢያዎች የተከፈቱት 209፣ በደቡብ ክልል ከታቀዱ 8,281 ጣቢያዎች የተከፈቱት 5,271፣ በሲዳማ ከታቀዱ 2,247 የምርጫ ጣቢያዎች የተከፈቱት 2,117፣ በሶማሌ ክልል ከታቀዱ 4,057 የምርጫ ጣቢያዎች ምንም እንዳልተከፈተ ተገልጿል፡፡ የዚህ ድምር ከታቀዱ 50,000 የምርጫ ጣቢያዎች መካከል የተከፈቱት የምርጫ ጣቢያዎች 25,151 ብቻ እንደሆኑ ያሳያል፡፡
ከዚህ ውጪም በስደተኞ መጠለያ ጣቢያዎችና በመከላከያ ሠራዊት ካምፖች ሊቋቋሙ የታሰቡ የምርጫ ጣቢያዎች ሊመሠረቱ እንዳልተቻሉ ተጠቅሷል፡፡ በተፈናቃይ ጣቢያዎች በጣቢያዎቹ አስተባባሪዎች አማካይነት የምርጫ አስፈጻሚዎች ከተፈናቃዮች መካከል ተመርጠው ምርጫ እንዲያስፈጽሙ ቢታቀድም፣ የተፈናቃይ ጣቢያዎችን አስተባባሪዎች ስልክ በመደወል ለማስተባበር ተሞክሮ እንዳልተሳካ ተነግሯል፡፡ የተወሰኑትም ስልኮች የማይሠሩ እንደነበሩና ይኼንን ለማሳካት ለአንድ ወር ከግማሽ ያህል ጥረት እንደተደረገ ሰብሳቢዋ አስታውቀዋል፡፡
በመከላከያ ካምፖች ሊቋቋሙ የታሰቡ የምርጫ ጣቢያዎችን በተመለከተ፣ መከላከያ ሠራዊት ካምፖቹ የሚገኙባቸውን ጣቢዎች ቢያሳውቃቸውም አስፈጻሚ ከመከላከያ ተመርጦና ተመድቦ እንዲገለጽላቸው ጠይቀው ይኼንን ማድረግ እንዳልተቻለም በማስታወቅ፣ ቦርዱ የምርጫ ጣቢያዎችን ማቋቋም እንዳልቻለ ተነግሯል፡፡
‹‹የፀጥታ ችግር ባለበት እንደሌለ ልናልፍ አልቻልንም፤›› በማለት የተናገሩት ሰብሳቢዋ፣ የአገሪቱን የፀጥታ ሁኔታ የተመለከቱ የተለያዩ ጥያቄዎችን በተደጋጋሚ አቅርበው ምላሽ ማግኘት እንዳልተቻለ አስታውቀዋል፡፡
ክልሎች በተናጠል የፀጥታ ሁኔታን የተመለከቱ ትንታኔዎችን ለቦርዱ የላኩ መሆኑን የተናገሩት ወ/ሪት ብርቱካን፣ በትንታኔዎቹ መሠረት ወደ ተግባር ሲገቡ ግን የተባሉት ችግሮች የታዩባቸው አካባቢዎች መኖራቸውን፣ እንዲሁም መካከለኛ ችግር ነው ያለባቸው የተባሉ አካባቢዎች ደግሞ ትልቅ ግጭት ተፈጥሮባቸው የምርጫ እንቅስቃሴዎችን አስተጓጉሏል ብለዋል፡፡ በዚህም ምክንያት አስቸጋሪ በተባሉና የፀጥታ ችግራቸው ጉልህ በሆኑ እንደ ምዕራብ ወለጋ ዞኖች የመራጮች ምዝገባ ቢደረግ ችግር ሊገጥም ይችላል በሚል ሥጋት ምዝገባ አለመደረጉ፣ በዚህም ሥጋት በ4,126 የምርጫ ጣቢያዎች በፀጥታ ችግር የመራጮች ምዝገባ መዘግየቱ፣ በኦሮሚያ ክልል በአንድ የምርጫ ጣቢያ ላይ በተፈጸመ ጥቃት ከእነ ዕቃው የተቃጠለ መሆኑን፣ በዚያው አካባቢ አንድ የኤክስቴንሽን ጽሕፈት ቤት የምርጫ ጣቢያ በመሰላቸው አጥቂዎች መቃጠሉም ተነግሯል፡፡
የምርጫ ጣቢያዎችን ከማቋቋምና የመራጮች ምዝገባን ከማከናወን ባለፈም ለምርጫ ጣቢያዎች የሚደረግ ጥበቃ አዳጋች እንደሆነባቸው ያወሱት ሰብሳቢዋ፣ ክልሎች ሁሉንም የምርጫ ጣቢያዎች በፖሊስ ማስጠበቅ አንችልም፣ ኃይልም የለንም እያሉ መሆኑን አክለው፣ በሚሊሻ ለማስጠበቅ አዝማሚያ እንዳለና ቦርዱ ግን ይኼ ኃላፊነት የፖሊስ በመሆኑ በፖሊስ ካልሆነ አይቻልም እንዳለ ተነግሯል፡፡
የዕጩዎች መታሰርና በፀጥታ ችግር ብዙ ጣቢያዎች አለመከፈታቸው በሁለቱ ዋና ዋና የምርጫ ሒደቶች ወቅት መታየታቸውን የጠቀሱት ወ/ሪት ብርቱካን፣ በእነዚህ ችግሮች ሳቢያም የመራጮች ምዝገባ መቀዛቀሱን አስታውቀዋል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ ለምርጫ የተመዘገቡ መራጮች 200,906 ብቻ እንደሆኑ ተነግሯል፡፡ በአጠቃላይ ምን ያህል መራጮች ለምርጫው እንዲመዘገቡ ታቅዶ ይኼንን ያህል እንደተመዘገቡ ባይገለጽም፣ በእያንዳንዱ የምርጫ ጣቢያ እንዲመዘገብ የሚፈቀደው ከፍተኛው የመራጮች ቁጥር 1,500 ብቻ በመሆኑ፣ በአዲስ አበባ ባሉ 1,662 የምርጫ ጣቢያዎች 2.5 ሚሊዮን ገደማ መራጮች ይመዘገባል ተብሎ እንደሚጠበቅ መገንዘብ ይቻላል፡፡
የምርጫ አስፈጻሚዎች በበኩላቸው ሥልጠና ከወሰዱ በኋላ የሚከፈለው ገንዘብ አይበቃንም ብለው ትተው እየሄዱ እንደሚገኙ፣ ክፍያው በጊዜ አልደረሰንም የሚል ቅሬታ ያላቸው አስፈጻሚዎች እንደነበሩ አልሸሸጉም፡፡ ገንዘቡ በቶሎ አለመድረሱ የቦርዱ ችግር መሆኑን በማመንም፣ ‹‹ቀልጣፋ ሥርዓት መዘርጋት ነበረብን፣ ግን ባለማድረጋችን ጥፋቱ የእኛ ነው፤›› ሲሉ ሰብሳቢው አምነዋል፡፡ ሆኖም ገንዘቡ አነሰን ለሚሉ አስፈጻሚዎች ይኼ ሥራ እንደ አገራዊ ኃላፊነት እንዲታይና እንደ ሥራ ፈጠራ መታየት እንደሌለበት አሳስበዋል፡፡
በምክክር መድረኩ ላይ ከተገኙ የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች በዋናነት የቀረቡ ጥያቄዎች የፀጥታ ችግሮችን የተመለከቱ ናቸው፡፡ እስካሁን በተከናወነው የምርጫ ዝግጅት እንደታየው በዚህ ሁኔታ በተቀመጠለት የጊዜ ሰሌዳ መከናወን ይችላል ወይ ሲሉ የጠየቁ አልጠፉም፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች ዕጩዎች ላይ ማስፈራሪያና ዛቻ፣ እንዲሁም ሐሰተኛ መረጃዎች እንደሚሠራጩ በመጥቀስ ቅሬታቸውን ለቦርዱ አሰምተዋል፡፡
የብልፅግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ብናልፍ አንዷለም በበኩላቸው፣ የፀጥታ ችግሮች ያለባቸው ሥፍራዎች እንደሚታወቁና መንግሥት በበኩሉ ችግሮቹን ለመፍታት ጥረት እያደረገ ነው በማለት፣ የተፈቱና የተሻሻሉ ችግሮች አሉ በማለት ተከራክረዋል፡፡ ሆኖም የፖለቲካ ፓርቲዎች የበኩላቸውን እንዲወጡ በመጠየቅ፣ በግጭቶቹና በብጥብጦቹ እጃቸው ያለበት የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዳሉ ይታወቃሉ ብለዋል፡፡ ‹‹ስለዚህም ፓርቲዎችም የበኩላችንን ድርሻ እንወጣ፤›› ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ሆኖም ቦርዱ በአስፈጻሚዎች ላይ የሚቀርቡ በርካታ ቅሬታዎች ስላሉ በተቋም ደረጃ ትኩረት ሰጥቶ መፍታት ያለበትን እንዲፈታ፣ ይኼ ችግር በተለይ በሶማሌ ክልል ጎልቶ እንደሚታይና በተቃዋሚ ፓርቲ ደጋፊነት የሚታወቁና ዝምድና ያላቸው አስፈጻሚዎች እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡
ነገር ግን በዕጩዎች ላይ የሚደርስ እስርን በተመለከተ የቀረቡ ጉዳዮችን አስመልከተው በሰጡት አስተያየት፣ ‹‹እዚህ ቁጭ ብዬ ይኼንን መስማት ያሳፍረኛል፣ ይኼ መሆን የሌለበት እንደሆነ እናምናለን፤›› በማለት አቶ ብናልፍ ያስታወቁ ሲሆን፣ መደገም የሌለበት ጉዳይ ነው ብለው እንደሚያምኑ ገልጸው ለክስተቶቹ ይቅርታ ጠይቀዋል፡፡ ስለዚህም የዕጩዎች እስርን በተመለከተ ትልቁ ጉዳይ ቀድሞ አለመፈጠሩ ነው እንጂ፣ ከተፈጠረ በኋላ መፈታቱ መሆን እንደሌለበትም አስምረዋል፡፡
ነገር ግን በተቃዋሚዎች ላይ ይደርሳሉ ስለሚባሉ በደሎች የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት መሬት ወርዶ፣ መረጃ ሰብስቦና አጠናቅሮ አቅርቦ መወያየት እንዲቻል ጠይቀዋል፡፡
‹‹አስረግጬ መናገር የምፈልገው ገዥው ፓርቲ ምርጫ እንዲደረግ አይፈልግም በሚል በዚህ ደረጃ ባትጠራጠሩን ጥሩ ነው፡፡ ምርጫ ቦርድ፣ ተቃዋሚዎችም ከእናንተ በላይ ወይም እኩል ቁርጠኝነት አለን በታቀደለት የጊዜ ሰሌዳ እንዲፈጸም፤›› ሲሉ አቶ ብናልፍ ገልጸዋል፡፡
በመድረኩ የቀረቡ የተለያዩ ቅሬታዎችን መዝግበው እንደያዙና ለመፍታት እንደሚሠሩም አስታውቀዋል፡፡
‹‹ሁላችንም አማራጭ ነን እንጂ ጠላቶች አይደለንም፤›› ያሉት አቶ ብናልፍ፣ ቦርዱ የድሬዳዋንና የሐረሪ፣ ብሎም የአፋርና የሶማሌ ክልሎች ጉዳዮችን ዳግም እንዲመለከታቸውና በተቻለ መጠን ከአካባቢው ማኅበረሰብ ጋር እየተነጋገረ ዕልባት እንዲሰጥባቸው፣ ካልሆነም መተማመን መፍጠር በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ደግሞ መተማመን እንዲፈጠር ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ወ/ሪት ብርቱካን በአጠቃላይ የተመዘገቡ መራጮች ቁጥር እጅግ አነስተኛ ነው ብለው፣ ይኼንን ተከትሎም የሚመጣ ተጠያቂነት ካለም ለመቀበል ዝግጁ ነን፤›› ሲሉ አስታውቀዋል፡፡ የሐረሪ ክልልን በተመለከተ ቦርዱ ያስተላለፈውን ውሳኔ ተከትሎ፣ ክልሉ ትብብር እያደረገላቸው እንዳልሆነ ወ/ሪት ብርቱካን ተናግረዋል፡፡