Sunday, June 4, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

መንግሥት ሕዝብን ከጥቃት መከላከል ካልቻለ መዘዙ የከፋ ይሆናል!

ኢትዮጵያ እጅግ በጣም አደገኛ የሆነ የታሪክ ምዕራፍ ውስጥ እየገባች ነው፡፡ መንግሥት ባለበት አገር ውስጥ ንፁኃን ሲገደሉና ሲፈናቀሉ ተከርሞ፣ አሁን ደግሞ ከተሞች በጠራራ ፀሐይ እየነደዱና እየወደሙ ነው፡፡ ችግሩ ምንድነው ተብሎ ሲጠየቅ አፍታቶ የሚናገር የመንግሥት አካል የለም፡፡ ነገር ግን ታጣቂዎች በግልጽ ሕዝብ እየፈጁ አገር እያወደሙ ነው፡፡ መንግሥት በተደጋጋሚ ማንነትን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶችን ባለማስቆሙ፣ በጭካኔ የተሞሉ ነውረኛ ድርጊቶች እየተበራከቱ ነው፡፡ ማንነትን መሠረት ያደረጉ ግድያዎች እየተፈጸሙ፣ መንግሥት ተጠያቂነት የለሌበት ይመስል ዝምታው ከፍቷል፡፡ ኢትዮጵያዊያን በተለያዩ ዘመናት ክፉና ደግ ወቅቶችን በጋራ አሳልፈዋል፡፡ አኩሪ በሆኑ የጋራ እሴቶቻቸው አማካይነት ተደጋግፈው ኖረዋል፡፡ ለእናት አገራቸው በነበራቸው ከመጠን ያለፈ ፍቅር ምክንያት፣ ወራሪዎችና ተስፋፊዎች እንዳይደፍሯት አድርገዋል፡፡ ለእናት አገራቸው ክብር ሲሉም አንድ ላይ ተሰውተዋል፡፡ ይኼንን የመሰለ ኩሩ ታሪክ ባላት አገር ውስጥ፣ ማንነትን እየለዩ መግደልና ማፈናቀልን ማስቆም አለመቻል ያሳዝናልም፣ ያሳፍራልም፡፡ መንግሥት ንፁኃንን ከጥቃት ማዳን ባለመቻሉ በአሁኑምወደፊቱም ትውልድ ይጠየቃል፡፡ ንፁኃንን በጭካኔ መግደል፣ ማፈናቀልና አገር ማውደም የከፋ መዘዝ አለው፡፡ ኢትዮጵያዊያንን በብሔር፣ በሃይማኖት፣ በቋንቋ፣ በባህል፣ በመልክዓ ምድር፣ በፖለቲካ አቋምና በመሳሰሉት በመከፋፈል አገርን ማዳከም የሚጠቅመው ለጠላት መሆኑ እየታወቀ፣ በቀላሉ ሊቆሙ በሚችሉ ነውረኛ ጥቃቶች ሳቢያ ኢትዮጵያዊያን ያለ ኃጢያታቸው እየተፈጁ ነው፡፡ አገርም ከድጡ ወደ ማጡ እየተሸጋገረች አደገኛ ቀውስ ውስጥ እየገባች ነው፡፡ መንግሥትም ዳተኛነቱ ከቀጠለ መዘዙ የከፋ መሆኑ አይቀርም፡፡

በቤተሰብ ደረጃ እንኳ ተደጋጋሚ ችግር ሲያጋጥም መፍትሔ ለማግኘት በቁጭት መነሳሳት የተለመደ ነው፡፡ ችግሩ በአገር ደረጃ አድጎ በተደጋጋሚ ሲያጋጥም ደግሞ አደጋው ስለሚከብድ፣ መንግሥትና ሕዝብ አንድ ሆነው ለመፍትሔ ይማስናሉ፡፡ አሁን ግን አስፈሪ ነገር ነው የሚታየው፡፡ የአፄ ኃይለ ሥላሴ ሥርዓተ መንግሥት በየካቲት 1966 .. አብዮት እንዲያከትም ከተደረገ ወዲህ ያሉትን 47 ዓመታት ብናስታውስ፣ እርስ በርስ ከመፋጀት ጀምሮ በርካታ አስጨናቂ ክስተቶች አጋጥመዋል፡፡ ከዘመነ ነጭና ቀይ ሽብር እስካሁን ድረስ ያሉት የንፁኃን ግድያዎች፣ እስራቶች፣ ማሰቃየቶች፣ ማፈናቀሎች፣ ማሳደዶች፣ የንብረት ውድመቶችና የመሳሰሉት ትክት ይላሉ፡፡ በእርስ በርስ ጦርነት ምክንያት ያለቁት ወገኖች፣ የወደሙ መሠረተ ልማቶች፣ ድህነትና ኋላቀርነት፣ ወዘተ የኢትዮጵያ የበርካታ ዓመታት ቁጭቶች ናቸው፡፡ ከአንዱ አምባገነን ወደ ሌላው አምባገነን የተደረጉት ሽግግሮች የመከራና የሥቃይ አዋላጆች ነበሩ፣ አሁንም እየሆኑ ነው፡፡ የመንግሥት ሥልጣን በያዙ ፖለቲከኞች ጭምር የመነጋገርና የመደማመጥ ባህል ባለመኖሩ ምክንያት ብቻ፣ በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ የደረሰው መከራ ተቆጥሮ አያልቅም፡፡ አሁንም ከዚህ መርገምት ውስጥ ለመውጣት ጠንከር ያለ ፍላጎትና መተማመን ስለሌለ፣ ከተስፋ ይልቅ ሥጋት እየበረታ ነው፡፡ ለአገር የሚጠቅሙ በርካታ የጋራ ጉዳዮች እያሉ፣ ለአገር በማይጠቅሙ አፍራሽ አጀንዳዎች ምክንያት የውድመት መንገድ እየተመረጠ ነው፡፡ መንግሥት ሕዝብን ከጥቃት ካልተከላከለ አደጋው የባሰ ይሆናል፡፡

ማንም ጤነኛ ሰው በሚገባ እንደሚገነዘበው ከየሥርቻው ችግር እየፈለፈሉ ቅራኔ መፍጠር ለአገር አይጠቅምም፡፡ ስንትና ስንት ጠቃሚ ነገሮችን ከታሪክ ማኅደር እያገላበጡና የሚጠቅሙትን እየመረጡ በጋራ አገርን ማሳደግ እየተቻለ፣ የማይረቡትን ብቻ እያግበሰበሱ በኢትዮጵያውያን መካከል ቅራኔ በመዝራት አገር ለማጥፋት እንቅልፍ አጥተው የሚያድሩ በዝተዋል፡፡ በርካታ የዓለም አገሮች ያለፉባቸውን ዓይነት የታሪክ ክስተቶች በጋራ በመቀበል የተሻለች አገር ለመፍጠር ከመትጋት ይልቅ፣ የኢትዮጵያ ልዩ ገጽታ ይመስል በአሳዛኝ መንገድ የታሪክ ሒሳብ ለማወራረድ ታጥቆ መነሳት ያሳዝናልም፣ ያሳፍራልም፡፡ በአራቱም ማዕዘናት የሚኖረው ሕዝባችን ለአገሩ ብሩህ ተስፋ ሲመኝ፣ በየቦታው የሚሰሙ አፍራሽ አጀንዳዎች ሥጋት እየደቀኑ ነው፡፡ ቀኑ መሽቶ ሌሊቱ እስኪነጋ ለሰላምና ለአገር መፃኢ ዕድል ማማር የሚተጉ ያሉትን ያህል፣ የመንግሥት ሥልጣን የያዙ ጦር የጠማቸው አፍለኞች ሳይቀሩ አገሪቱን በጭንቀት እየወጠሩ ነው፡፡ የተገኘውን አጋጣሚ በሙሉ ግጭት ለሚቀሰቅሱ አገር አፍራሽ ድርጊቶችያዋሉ ነው፡፡ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን በዚህ ሁኔታ እስከ መቼ ይቀጥላሉ? ይህንን አደገኛ ወቅት በሚገባ አጢኖ አገርን ከተደቀነባት አደጋ የመታደግ ኃላፊነት የኢትዮጵያዊያን ነው፡፡ ካልሆነ ግን የከፋ ቀውስ ይከተላል፡፡

በኢትዮጵያ የፖለቲካ ሰማይ ሥር ውርውር ከሚሉ ፋይዳ ቢሶች መካከል ከሥልጣን በመለስ፣ አገር ለማፍረስ ታጥቀው የተነሱ ክፉዎች እየተስተዋሉ ነው፡፡ አገር አተራምሰው ዓላማቸውን ለማሳካት የማይፈነቅሉት ድንጋይ የለም፡፡ ለዚህ ደግሞ አመቺው ጎዳና አገርን ማስጨነቅና ሕዝብን ግራ ማጋባት ነው፡፡ ብሔር፣ ሃይማኖት፣ ቋንቋ፣ ባህልና የመሳሰሉትን የሚታከኩ ኃይሎች ፍላጎታቸው ሕዝቡን እርስ በርስ ማጋጨትና አገር ማፍረስ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም ለፍትሕ፣ ለእኩልነትና ለነፃነት ይጮሁ እንደነበር በግልጽ የሚናገሩ ጭምር፣ መንግሥት ውስጥ ተሰግስገው ችግር ፈጣሪዎች ሆነዋል፡፡ ለእያንዳንዱ ተራ ጉዳይ ጭምር አጀንዳ እየፈበረኩ ለሰላምና ለመረጋጋት ጠንቅ የሆነ ቅራኔ በማስፋፋት ላይ ናቸው፡፡ ታሪክን በራሳቸው ፍላጎት እየተረጎሙ የጠገጉ ቁስሎችን ጭምር ያመረቅዛሉ፡፡ ኢትዮጵያውያን የጋራ እሴትና መስተጋብር የሌላቸው ይመስል፣ አንዱ በሌላው ላይ እንዴት እንደሚነሳ ይቀሰቅሳሉ፡፡ ሐሰተኛ ወሬዎችን እየፈበረኩ ግርግር በመፍጠር ሁከት ያስነሳሉ፡፡ ይህ ሁሉ ጥረት ግን ለኢትዮጵያዊያን የሚያመጣው በረከት ሳይሆን፣ ለፀፀት የሚዳርግ ጥፋት ነው፡፡ አሸናፊና ተሸናፊ የሌለበት ውድመት ነው፡፡ ይህንን አስከፊ ሁኔታ በፍጥነት መቀልበስ ያስፈልጋል፡፡ መንግሥት ኃላፊነቱን ካልተወጣ ግን አደጋው ይባባሳል፡፡

ለኢትዮጵያ የሚያዋጣው በሕዝብ ፈቃድ ላይ የተመሠረተ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት፣ በሰላማዊና ሁሉንም በሚያግባ ምርጫ አማካይነትመገንባት መነሳት ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ ሥርዓት ማንም ማንንም የማይጨቁንበት፣ ማንም የማንም ሎሌ የማይሆንበት፣ አምባገነንነትና ዕብሪት ሥፍራ የሚያጡበት፣ የበዳይና የተበዳይ ትርክቶች የሚያቆሙበት፣ በእኩልነትና በነፃነት የሚኖሩበት፣ የሕግ የበላይነት ተረጋግጦ ሕገወጥነት የሚከስምበት፣ ወዘተ ነው፡፡ ሥርዓቱን በአስተማማኝ ለማቆም ግን ቁርጠኝነት ያስፈልጋል፡፡ ይህ ቁርጠኝነት በጋራ ለመነጋገር መቻል፣ መከባበር፣ ዕውቅና መሰጣጠት፣ ፍትሐዊና አስቻይ የፖለቲካ ምኅዳር መፍጠርና በኃላፊነት ስሜት መሥራት ከብዙ በጥቂቱ ይጠቀሳሉ፡፡ ይህንን ተግባራዊ ለማድረግ ደግሞ በአስተማማኝ ምርጫ ኢትዮጵያን ከጭንቀት መገላገል የግድ ይላል፡፡ ለዚህም ሰላምና መረጋጋት በመላ አገሪቱ ተፈጥሮ፣ ለሕዝብ የተሻለ አማራጭ አጀንዳ አለን የሚሉ የፖለቲካ ኃይሎች በነፃነት መንቀሳቀስ አለባቸው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከዳር እስከ ዳር በነፃነት የፈለገውን የሚመርጥበት ዓውድ መፍጠር የመንግሥት ኃላፊነትና ግዴታ ይሆናል፡፡ ሚዲያዎች፣ ሲቪክ ማኅበራት፣ የዴሞክራሲ ተቋማትና የመሳሰሉት በነፃነትና በገለልተኝነት የሚሠሩበት አመቺ ሁኔታ መፈጠር አለበት፡፡ የፀጥታ ኃይሎች ከማንኛውም የፖለቲካ ኃይል ነፃ ሆነው ኃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል፡፡ ከማንም በላይ ኃላፊነቱ የመንግሥት እንደሆነ ግን መታወቅ አለበት፡፡

ከዚህ ውጪ አገሪቱን እንደ ውጋት እየቀሰፉ መላወሻ በማሳጣት በነጋ በጠባ ጭንቅ እየፈጠሩ፣ ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ የሚደረገውን ሽግግር ማጨናገፍ ታሪክ ይቅር የማይለው ወንጀል ነው፡፡ ለኢትዮጵያ እንዴት ቢደረግ ነው በታሪኳ ዓይታው የማታውቀው በሕዝብ ፈቃድ ላይ የተመሠረተ ሥርዓት መፍጠር የሚቻለው የሚለው ጉዳይ፣ ከምንም ነገር በላይ ትኩረት ያስፈልጋዋል፡፡ ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ የነበሩ ኃይሎችም ችቦውን ለአዲሱ ትውልድ በማስተላለፍ፣ የእነሱ የብሽሽቅና የጥላቻ ታሪክ እንዲያበቃ ቢያደርጉ ከህሊና ፀፀት ይድናሉ፡፡ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ በዋና ተዋናይነትም ሆነ በረዳትነት፣ እንዲሁም ተደብቀው  ሴራ የሚጎነጉኑ ኃይሎችም አገር ለማፍረስ መከራ ከሚያዩ፣አገር ዕድገትና ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ቢሰማሩ ታሪካቸውን ያሳምራሉ፡፡ ታሪክ እንደሆነ ማንንም አይምርም፡፡ ጊዜ ሰጠኝ ብሎ በክፋት መንገድ የሚጓዘውንም ሆነ ተባባሪውን ዕርቃኑን አጋልጦ የትውልድ ማፈሪያ ያደርጋል፡፡ ከዚህ ቀደም ማማው ላይ ቆመው ሲፎክሩ የነበሩ የት ደረሱ? ከእነሱ በላይ ጉልበት ያለው እንደሌለ በመለፈፍ ሲያቅራሩ የነበሩ የት አሉ? በእነሱ እግር የተተኩት ምን እያሰቡ ነው? ካለፈው ስህተት አለመማር ታሪክን በከፋ መንገድ ለመድገም ያስገድዳል፡፡ አሁን ሕዝብ በጭካኔ እየታረደና አገር እየወደመ ነው፡፡ ሕዝብ መንግሥትን የት አለህ እያለ ነው፡፡ መንግሥት ደግሞ ለሕዝብ ተገቢውን ምላሽ መስጠት ይጠበቅበታል፡፡ መንግሥት አገርን የመጠበቅና ሕዝብን ከማንኛውም ጥቃት የመከላከል ግዴታ እንዳለበት ማወቅ አለበት፡፡ ካልሆነ ግን መዘዙ የከፋ ነው!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ኢትዮጵያ በ2023 የሚኖራት የውጭ ምንዛሪ ክምችት ለ18 ቀናት ግዢ መፈጸሚያ ብቻ እንደሚሆን አይኤምኤፍ ተነበየ

ኢትዮጵያ በ2023 የሚኖራት የውጭ ምንዛሪ ክምችት ለ0.6 ወር ወይም...

የኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ባንክ ከ100 ቢሊዮን ብር በላይ ተቀማጭ ያለው ሦስተኛው ከግል ባንክ ሆነ

የኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ባንክ የተቀማጭ ገንዘብ መጠኑን ከ100 ቢሊዮን...

በወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የተሰበሰበው ከፍተኛ ሀብት ጥቅም ላይ እየዋለ አይደለም ተባለ

በኢትዮጵያ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የተሰበሰበው የተቀማጭ ገንዘብ መጠን...

መንበሩ ካለመወረሱ በስተቀር መፈንቅለ ሲኖዶስ መደረጉን ቤተ ክህነት አስታወቀ

ቅዱስ ሲኖዶስ ከነገ ጀምሮ ውይይት እንደሚጀምር ተነገረ ‹‹እኛ ወታደርም ሆነ...
- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

አወዛጋቢው የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ጉዳይ

በኢትዮጵያ የሕገ መንግሥት ማሻሻል ጉዳይ ከፍተኛ የፖለቲካ ውዝግብ የሚቀሰቀስበት...

 መፍትሔ  ያላዘለው  የጎዳና  መደብሮችን  ማፍረስ

በአበበ ፍቅር ያለፉት ስድስት ዓመታት በርካቶች በግጭቶችና በመፈናቀሎች በከፍተኛ ሁኔታ...

የተናደው ከቀደምቱ አንዱ የነበረው የአዲስ አበባ ታሪካዊ ሕንፃ

ዳግማዊ አፄ ምኒልክ በ19ኛው ክፍለ ዘመን መገባደጃ መናገሻ ከተማቸውን...

የአከርካሪ አጥንት ሕክምናን ከፍ ያደረገው ‘ካይሮፕራክቲክ’

በአፍሪካ ከጀርባ ሕመም ጋር በተያያዘ በርካታ ሰዎች ለከፍተኛ የአካል...

ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ለመስጠት የተቋቋመው ራሚስ ባንክ ዛሬ ሥራ ይጀምራል

በኢትዮጵያ ሙሉ ለሙሉ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ለመስጠት የተቋቋመው...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ሕገ መንግሥት ለማሻሻል ባህሪን መግራት ያስፈልጋል!

በሥራ ላይ ያለው አወዛጋቢ ሕገ መንግሥት ከፀደቀበት ከ1987 ዓ.ም. ጀምሮ እስካሁን ድረስ ከተለያዩ አቅጣጫዎች ወቀሳዎችና ተቃውሞዎች ይቀርቡበታል፡፡ ከተቃውሞዎቹ መካከል በሕገ መንግሥቱ መግቢያ ላይ ኢትዮጵያዊነትን...

የፖለቲካ ምኅዳሩ መላሸቅ ለአገር ህልውና ጠንቅ እየሆነ ነው!

የኢትዮጵያ ፖለቲካ ምኅዳር ከዕለት ወደ ዕለት የቁልቁለት ጉዞውን አባብሶ እየቀጠለ ነው፡፡ በፖለቲካ ፓርቲዎች የእርስ በርስ ግንኙነትም ሆነ በውስጠ ፓርቲ ዴሞክራሲ የሚታየው መስተጋብር፣ ውል አልባና...

የመኸር እርሻ ተዛብቶ ቀውስ እንዳይከሰት ጥንቃቄ ይደረግ!

ክረምቱ እየተቃረበ ነው፡፡ የክረምት መግቢያ ደግሞ ዋናው የመኸር እርሻ የሚጀመርበት ጊዜ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ከእርሻው ክፍለ ኢኮኖሚ 70 በመቶ ያህሉን የሰብል ምርት የምታገኘው በመኸር እርሻ...