በዓባይ ውኃ የመጠቀም መብቷን በአስገዳጅ ስምምነት ስም አሳልፋ እንደማትሰጥ አስታወቃለች
ኢትዮጵያ የህዳሴ ግድቡ የውኃ ሙሌትና አስተዳደርን አስመልክቶ ከግብፅና ሱዳን ጋር ስታደርግ በነበረው ድርድር፣ ከአንድም ሁለት ጊዜ አስገዳጅ ስምምነት እንዲፈረም ጥያቄ አቅርባ፣ በሁለቱ አገሮች ውድቅ መደረጉን የኢትዮጵያ ተደራዳሪ ቡድን አባል ገለጹ።
የህዳሴ ግድቡ ድርድር ውጤት አስገዳጅ እንዲሆን ቢጠይቁም፣ ኢትዮጵያ ፈቃደኛ ባለመሆኗ ስምምት ላይ መድረስ እንዳልተቻለ ግብፅና ሱዳን በተደጋጋሚ የሚያስተጋቡት ክስ ሐሰተኛና እውነታውን የሚገልጽ እንዳልሆነ፣ አንድ የኢትዮጵያ ተደራዳሪ ቡድን አባል ለሪፖርተር ገልጸዋል።
ከአንድም ሁለት ጊዜ ኢትዮጵያ አስገዳጅ ስምምነት ለመፈራረም ጥያቄ አቅርባ ሁለቱ አገሮች ጥያቄውን ውድቅ እንዳደረጉት ተደራዳሪው ገልጸዋል።
የህዳሴ ግድቡ የመጀመሪያ ምዕራፍ የውኃ ሙሌትና ዓመታዊ አስተዳደር በ2015 በሦስቱ አገሮች መሪዎች በተፈረመው የትብብር መግለጫ መርሆችን መሠረት ያደረገ አስገዳጅ ስምምነት እንዲፈረም ጥያቄ አቅርባ የነበረ ቢሆንም፣ በግብፅና በሱዳን ተቀባይነት አለማግኘቱን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ አስገዳጅ ስምምነት እንዲፈረም በመጀመሪያ ያቀረበችው ጥያቄ በሦስቱ አገሮች መሪዎች የተፈረመውን የትብብር መግለጫ መርሆዎች መሠረት ያደረገ በመሆኑ ግብፅና ሱዳን እንዳልተቀበሉት ገልጸዋል።
ምክንያቱን ሲያስረዱም፣ የዓባይ ውኃ ተለዋዋጭ የፍሰት መጠንን መሠረት በማድረግ የግድቡ ባለቤት የመጀመሪያ ምዕራፍ የውኃ ሙሌትና ዓመታዊ የግድቡ አስዳደርን እንዲመራ በመሪዎቹ በተፈረመው የትብብር መግለጫ ስምምነት፣ መብት የሚሰጥ በመሆኑና ይህም ኢትዮጵያ ከግድቡ በላይ በሚገኘው የዓባይ ተፋሰስ ላይ ወደፊት ልታከናውን ከምትችለው መሠረተ ልማት ጋር የማይቆራኝ መሆኑን ስለተገነዘቡ ግብፅና ሱዳን እንዳልተቀበሉት አስረድተዋል።
ኢትዮጵያ በዚህም ሳታበቃ ሌላ የአስገዳጅ ስምምነት ጥያቄ ማቅረቧንም አመልክተዋል።
ኢትዮጵያ ለሁለተኛ ጊዜ ባቀረበችው ጥያቄ በተፋሰሱ ተጋሪ አገሮች መካከል ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ አስገዳጅ የሆነ የውኃ ክፍፍል እንዲደረግ የሚጠይቅ ሲሆን፣ ግብፅና ሱዳን ይህንን ጥያቄም ውድቅ እንዳደረጉት ገልጸዋል።
በተቃራኒው ግብፅና ሱዳን የግድቡን የውኃ ሙሌትና ዓመታዊ አስተዳደርን አስመልክቶ በሦስቱ አገሮች ስምምነት የተደረሰባቸውን የድርቅ ወቅትና የተራዘመ ድርቅ ወቅት አመላካች ተብለው የተቀመጡ የውኃ መጠን ምጣኔዎች (ለአብነት ወደ ግድቡ የሚመጣው የውኃ መጠን 37 ቢሊዮን ሜትር ኩብ ከሆነ የድርቅ መከሰትን ያመለክታል የሚለውን) በመውሰድ ይህ የውኃ መጠን የተከሰተው ኢትዮጵያ ከግድቡ በላይ ውኃውን የሚጠቀም አዲስ መሠረተ ልማት በመገንባቷ ቢሆንም፣ ድርቅ ተብሎ ከግድቡ ውኃ እንድትለቅ ሐሳብ ማቅረባቸውን ገልጸዋል።
በዚህ መሠረትም ስምምነት እንዲፈረምና የሚፈረመውም ስምምነት አስገዳጅ እንዲሆን መጠየቃቸውን የሚገልጹት ተደራዳሪው፣ ኢትዮጵያ ይህንን ተቀበለች ማለት ህዳሴ ግድቡ ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ የምታካሂደው የመጨረሻ ልማት እንደሚሆንና ይህም የወደፊት የመጠቀም መብቷን አሳልፋ እንደመስጠትና በመጪው የኢትዮጵያ ትውልድ ላይ መወሰን እንደሆነ ያስረዳሉ።
በመሆኑም ይህንን ኢትዮጵያ መቼም እንደማትቀበል በማስረገጥ እንዲያውቁት መደረጉን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በህዳሴ ግድቡ ድርድር ላይ ስምምነት ያልተደረሰበትን ምክንያት የተመለከተና የኢትዮጵያን አቋም የሚያስረዳ ደብዳቤ ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታ ምክር ቤት ሰሞኑን ልኳል።
በዚህ ደብዳቤ ላይም ከላይ የተገለጸውን በማስረገጥ ኢትዮጵያ በዓባይ ውኃ የመጠቀምና ከግድቡ በላይ ውኃውን የሚጠቀም ልማት የማካሄድ መብቷን በአስገዳጅ ስምምነት ስም አሳልፋ እንደማትሰጥ አስታውቋል።
ግብፅና ሱዳን በኢትዮጵያ ላይ ጫና ለመፍጠርና የአፍሪካ ኅብረትን ከአደራዳሪነት ለማስወጣት እየጣሩ መሆናቸውን በመግለጽም ይህ አካሄድ በሦስቱ አገሮች መካከል አለመተማመንን ከመፍጠር ያለፈ ፋይዳ እንደማይኖረው አስታውቀል።
የኢትዮጵያ መንግሥት የሁለተኛውን ዓመት የውኃ ሙሊት ከማከናወኑ አስቀድሞ የመረጃ ልውውጥ ለማድረግ ለግብፅና ሱዳን ጥያቄ ቢያቀርብም ሁለቱም አገሮች ጥያቄውን ሳይቀበሉት እንደቀሩ አስገንዝቧል።