በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ተከታዮቹን በሰፊ የነጥብ ልዩነት እየመራ የሚገኘው የፋሲል ከነማ እግር ኳስ ክለብ ደጋፊዎች፣ በቡድኑ ወቅታዊ ‹‹አቋም›› ከመደሰትና ድሉን ከመጠበቅ ባለፈ የኮቪድ-19 መስፋፋት ምክንያት ዕድሉን እንዳያጣ ሥጋት ውስጥ ገብተዋል፡፡
ፋሲል ከነማ በዓምናው ሊግ በተመሳሳይ እየመራ በነበረበት ወቅት የተከሰተው ኮቪድ-19 ከድሉ ያሰናከለው መሆኑ ይነገራል፡፡ ዘንድሮም እየጨመረ የመጣው የኮቪድ መስፋፋት በተለይ ደግሞ አሁን ላይ ውድድሩን እያስተናገደች በምትገኘው ድሬዳዋ ከተማ ያለው የወረርሽኙ መስፋፋት ምክንያት ሁኔታው የቡድኑን አቋም በማወደስና ‹‹ዕድሉን›› በመውቀስ የሚዋልል ሆኗል፡፡
13 ክለቦች የሚሳተፉበት ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ውድድሩ ሊጠናቀቅ በአሁኑ ወቅት የአምስት ሳምንት የጨዋታ መርሐ ግብር መጠበቅ ግድ ብሎታል፡፡ ከተከታዩ ኢትዮጵያ ቡና በ12 ነጥብ ልዩነት በ45 ነጥብ ሊጉን እየመራ የሚገኘው ፋሲል ከነማ የዋንጫ ባለቤት ሆኗል ለማለት በሒሳባዊ ስሌት ትክክል ባይሆንም፣ የዋንጫውን አንድ እጅ ጨብጧል ማለት ግን ይቻላል፡፡
18 ጨዋታ ያደረገው ፋሲል ከነማ ሊጉን በ45 ነጥብ ሲመራ፣ ተከታዩ ኢትዮጵያ ቡና በተመሳሳይ ጨዋታ 33 ነጥብ ይዟል፡፡ ሦስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ባህዳር ከነማ 18 ጨዋታ አድርጎ 31 ነጥብ ሲይዝ፣ ተከታዩ ቅዱስ ጊዮርጊስ በበኩሉ አንድ ተስተካካይ ጨዋታ እየቀረው በ30 ነጥብ አራተኛ እንዲሁም ሐድያ ሆሳዕና በጎል ልዩነት ተብልጦ በ30 ነጥብ አምስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል፡፡
ወላይታ ድቻ በ24 ነጥብ እንዲሁም ሀዋሳ ከነማ 17 ጨዋታ አድርጎ በጎል ልዩነት ተበልጦ 24 ነጥብ ስድስተኛና ሰባተኛ ሲሆኑ፣ ሰበታ ከነማ በ17 ጨዋታ 22 ነጥብ፣ ወልቂጤ ከነማ በ18 ጨዋታ 20 ነጥብ፣ ድሬዳዋ ከነማ በ18 ጨዋታ 17 ነጥብ፣ ሲዳማ ቡና በ17 ጨዋታ በጎል ልዩነት ተበልጦ 17 ነጥብ፣ ጅማ ከነማ በ18 ጨዋታ 11 ነጥብ እና በደረጃ ሰንጠረዡ መጨረሻ የሚገኘው አዳማ ከነማ በ17 ጨዋታ ስምንት ነጥብ ይዘው ይገኛሉ፡፡
ከፋሲል ከነማ የዋንጫ ግስጋሴ ባልተናነሰ በድሬዳዋ ከተማ አስተናጋጅነት እየተካሄደ የሚገኘው ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ በአስገራሚነቱ እየተጠቀሰ የሚገኘው የኮቪድ ምርመራ ጉዳይ ተዓማኒነት ማጣቱ ይጠቀሳል፡፡ የደም ናሙና ምርመራ በድሬዳዋ ተደረጎላቸው ኮቪድ በደማቸው እንዳለባቸው የተነገራቸው ተጫዋቾች ወደ ሐሮማያ ዩኒቨርሲቲ ሄደው ሲመረመሩ ነፃ መሆናቸው ተረጋግጦ የተነገራቸው ተጫዋቾች አጋጣሚም ታይቷል፡፡