Monday, April 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊበችላ ባይነት የሚደርሱ የእሳት አደጋዎች

በችላ ባይነት የሚደርሱ የእሳት አደጋዎች

ቀን:

ከከተሞች መስፋፋትና ማደግ ጋር ተያይዞ ሊከሰቱ የሚችሉ አደጋዎችን ሊመክትና ምላሽ ሊሰጥ የሚችል አቅም ማስፋትን ይጠይቃል፡፡ ይህ ግን ለብዙዎቹ በማደግና በድህነት ውስጥ ላሉ አገሮች ቀላል አይደለም፡፡

በኢትዮጵያም ድንገተኛ አደጋዎች ከደረሱ በኋላ እንጂ ቀድሞ የመዘጋጀት ልምድና ዝግጁነት የእሳትና ድንገተኛ አደጋው ደግሞ ከጊዜ ወደ ጊዜ ጨምሯል፡፡  

ለአደጋዎቹ መበራከት የኅብረተሰቡ ስለሚቀጣጠሉ ቁሶች በቂ ግንዛቤ አለመኖርና የአኗኗር ዘይቤው ዓይነተኛ ሚና አላቸው፡፡ የማኅበረሰቡ ተጠጋግቶ የመኖር ልምድም ለአደጋ ተጋላጭ ያደርጋል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

በቅርቡ በተለያዩ የገበያ ሥፍራዎች ላይ ከደረሱ ድንገተኛ የእሳት አደጋዎችም ብዙዎቹ ከችላ ባይነት መነሳታቸውን መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

የሚነዱና የሚቀጣጠሉ ቁሶች አንድ ላይ ማስቀመጥ፣ የተሰኩ የኤሌክትሪክ መስመሮች ባለመንቀልና በሌሎች የግንዛቤ ክፍተቶች መሆኑን የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን የአደጋ የመንስዔዎች መረጃ ዝርዝር ያሳያል፡፡

በሌላ በኩል ቆሻሻ በማቃጠል ጊዜ፣ የተለኮሰ ሻማ በመርሳት፣ ማሳ ለማፅዳትና ለሌሎችም የተለኮሱ እሳት ቁጥጥር ሳይደረግበት በመቅረቱ የደረሱ የእሳት አደጋዎች በርከት ያሉ ናቸው፡፡

በጋራ መኖሪያ ቤቶች ላይ የእሳትና ሌሎች አደጋዎችን ለመከላከል በሚያስችል ሁኔታ እንደማይገነቡ በየክፍላተ ከተሞች ያሉ መኖሪያ ቤቶች ማሳያ ናቸው፡፡ እነዚህ  መኖሪያ ቤቶች በየአካባቢያቸው የድንገተኛ እሳት አደጋ መከላከያ የሌላቸው፣ አደጋዎች ቢከሰቱ እንኳን ድንገተኛ አደጋ ጊዜ መውጫ የሌላቸው መሆናቸውን ኮሚሽኑ ያስረዳል፡፡

ከእሳት አደጋዎች ሥጋት በተጨማሪ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ጥራታቸው እጅግ ዝቅተኛ በመሆኑ፣ የመደርመስ አደጋ እንዳይከሰት ሥጋት አለ፡፡ ከጋራ መኖሪያዎች በተጨማሪ በመዲናዪቱ የሚሠሩ ሕንፃዎች በሠራተኛና በአካባቢው ለሚያልፍ መንገደኛ ጭምር ሥጋት ናቸው፡፡

በቅርቡ ቦሌ መድኃኔዓለም ሰላም ሲቲ ሞል አካባቢ የአንድ ወጣት ሕይወት ማለፍ የዚሁ ሕንጻዎች ሲሠሩ የአካባቢን ደኅንነትና የሠራተኞችን ደኅንነት ሥጋት ላይ የሚጥል መሆኑ ማሳያ ነው፡፡ 

በአዲስ አበባ ከተማ የሚደርሱ ድንገተኛ የእሳት አደጋዎች በአብዛኛው የሚከሰቱት እጅግ በተፋፈጉና አደጋውን ለመቆጣጠር አስቸጋሪ በሆኑ ሥፍራዎች መሆናቸውም ሌላው ችግር ነው፡፡

ከዚህ ጋር ተያይዞ የመዲናይቱ የእሳትና አደጋ ሥራ አመራር ኮሚሽን ከጊዜው ጋር የዘመነ አሠራር፣ ቴክኖሎጂና ብቁ የሰው ኃይል እጥረት እንደሚያጋጥመው በተደጋጋሚ ይገልጻል፡፡

ኮሚሽኑ ያለውን ቴክኖሎጂና የሰው ኃይል በአግባቡ እንዳይጠቀምም የአሠራርና ከሌሎች ዘርፎች ጋር በጋራ የመሥራት ልምድ ማነስም እንደ ችግር ይነሳል፡፡

ከመንገዶች ባለሥልጣን፣ ውኃና ፍሳሽ፣ የኤሌክትሪክ አገልግሎትን ጨምሮ ሌሎች የመንግሥት ተቋማትን የማስተሳሰር ቴክኖሎጂ አለመኖር ዘርፉ በተፈለገው ፍጥነት እንዳያድግ ካደረጉ ምክንያቶች ውስጥ ይጠቀሳሉ፡፡

በሌላ በኩል ኅብረተሰቡ እሳትና ድንገተኛ አደጋዎች ቅድመ መከላከልና አደጋው ሲከሰት ማድረግ ስለሚገባው ነገር ያለማወቅ ችግር እንዳለ ኮሚሽኑ የገለጹ ሲሆን፣ ያልሠለጠነ የአኗኗር ዘይቤ ላይ የአየር ፀባይ (ወቅት) ተዳምሮ በመዲናይቱ ያለው የእሳት አደጋዎች መበራከታቸው እየታየ ነው፡፡

ኮሚሽኑም ራሱን ለማሻሻል መመርያ በማዘጋጀት፣ በዘርፉ የሠለጠኑ ባለሙያዎች በማፍራትና ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም አደጋዎች ከመድረሳቸው በፊትና ከደረሱም በኋላ ዘመናዊ የአደጋ መከላከያና መቆጣጠሪያ ተቋም ለማድረግ እየሠራ እንደሚገኝ አስታውቋል፡፡

የኮሚሽኑ የ2013 ዓ.ም. የዘጠኝ ወር ሪፖርት እንደሚያሳየው፣ ከተከሰቱ 249 የእሳት አደጋዎች 236 የሚሆኑት አደጋዎች መንስዔአቸው የሚታወቅ ሲሆን፣ የተቀሩት አይታወቅም፡፡

በዘጠኝ ወር በድንገተኛ እሳት ምክንያት 249 አደጋዎች ሲከሰቱ በዚህም የ35 ሰዎች ሕይወት አልፏል፡፡ 28 ሰዎች ላይ ደግሞ የአካል ጉዳት እንደደረሰባቸው ሪፖርቱ ያሳያል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ በአማካይ በወር 27 አደጋዎች የሚደርሱ ሲሆን፣ በሳምንት ደግሞ ከስድስት በላይ ድንገተኛ አደጋዎች ይደርሳሉ፡፡

የእሳትና ድንገተኛ አደጋዎች መቆጣጠር አገልግሎት ዳይሬክተር አቶ ወንድምአገኝ አልታዬ ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ በዘጠኝ ወር ውስጥ ለተቋሙ የደረሰው ጥሪ 659 ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ የእሳት ቃጠሎ 481 ነው፡፡ 

2013 ዓ.ም. የዘጠኝ ወር ሪፖርት ከዓምናው ጋር ሲነፃፀር አንድ የእሳት አደጋ ጭማሪ አሳይቷል፡፡ አቶ ወንድምአገኝ፣ ከደረሱት እሳት አደጋዎች የተቋሙ ሠራተኞች ሳይደርሱ በኅብረተሰቡ ትብብር በቁጥጥር ሥር የዋሉ መኖራቸውን ጠቁመዋል፡፡

የቃጠሎ አደጋዎች የደረሱት በ85 የመኖሪያና በ43 የንግድ ቤቶች ላይ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡ በመዲናዪቱ በአንድ ቀን የተከሰተው ስድስት ድንገተኛ የእሳት አደጋ ከፍተኛ ሆኖ መመዝገቡን አቶ ወንድምአገኝ ተናግረዋል፡፡

ካሉት አሥሩ ክፍላተ ከተሞች ውስጥ ቦሌ ክፍለ ከተማ ቀዳሚ ነው፡፡ በክፍለ ከተማው 43 የእሳት አደጋዎችና 23 ሌሎች ድንገተኛ አደጋዎች ተመዝግበዋል፡፡

የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ በሁለተኛ ደረጃነት የሚገኝ ሲሆን፣ በዘጠኝ ወራት ውስጥ 33 የእሳትና 15 ሌሎች ድንገተኛ አደጋዎችን አስተናግዷል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር የጨረታ ማስታወቂያ

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር በገቢ እና በውጭ ንግድ እንዲሁም...

ያልተቃናው የልጆች የንባብ ክህሎት

አንብቦና አዳምጦ መረዳት፣ የተረዱትን ከሕይወት ጋር አዋህዶ የተቃና ሕይወት...

እንስተካከል!

ሰላም! ሰላም! ውድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ እንዲሁም የሰው ዘር በሙሉ፣...

የሙዚቃ ምልክቱ ሙሉቀን መለሰ ስንብት

የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ በ1950ዎቹ እና በ1960ዎቹ በኪነ ጥበባትም ሆነ...