Friday, May 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ኪንና ባህል‹‹ታንታዊ›› - እንደ ዘበት ባይረሳ

‹‹ታንታዊ›› – እንደ ዘበት ባይረሳ

ቀን:

‹‹ታንታዊ›› የጉራግኛ ቃል ነው፡፡ ትርጉሙም ባይተው፣ ባይቀር፣ እንደዘበት ባይረሳ እንደ ማለት ነው፡፡ ይህን ቃለ ጉራጌ ነው ብርሃነ ዓለሙ ገሣ ባህሎች፣ ሥነ ቃሎች፣ እሴቶችና መልካም የሆኑ ልማዶች እንደዘበት ተረስተው እንዳይቀሩ በአጽንዖት ለማሳሰብ ፈልጎ ላዘጋጀው መጽሐፍ ርዕስ አድርጎ ያመጣው፡፡

መጽሐፉ በምዕራቡ ቤተ ጉራጌ ይከወኑ ከነበሩት ባህላዊ ቅርሶች በተጓዳኝ የተለያዩ መጣጥፎች፣ ቃለ ምልልሶችና ግጥሞችን በሁለተኛ ክፍሉ ይዟል፡፡

ደራሲው በመግቢያው እንደገለጸው፣ ትኩረቱ በምዕራቡ ቤተ ጉራጌ ውስጥ ይከወኑ ከነበሩት ባህሎች በጥቂቱ ለማሳየት ነው፡፡

- Advertisement -

‹‹መረጃዎች ለማግኘት ብዙ ውጣ ውረዶች ነበሩ፡፡ ተወልጄ ያደግኩበት አካባቢ ቢሆንም መረጃውን በቀላሉ ለማግኘት አልቻልኩም፡፡ ባህሎቹን በሚመለከት ብዙዎች ማስረጃን ሳይዙ በስሜታዊነት መጥፎ ጥላሸት ቀብተዋቸው ስለነበር ይህንን ማጥራት በማስፈለጉ ጊዜ ሊወስድ ችሏል፤›› ሲልም ሒደቱ ምን እንደሚመስል አውስቷል፡፡

‹‹ባህሎቹን ስንመረምር እጅግ የሚያስደንቅ እውነት በውስጣቸው ይዘው እናገኛቸዋለን፡፡ አንዳንዶች ስሜታዊ ሆነው እንደሚፈርጇቸው ሳይሆኑ ለብሔረሰቡ ባለውለታ ናቸው፤›› የሚለው አቶ ብርሃነ ዓለሙ ገሣ፣ ከአፍላው የወጣትነት ዘመኑ ጀምሮ የጉራጌ ብሔረሰብ ባህልን በአግባቡ ተረድቶ በአግባቡ ለማስተላለፍ ከፍተኛ ጉጉት እንደነበረው ገልጾ ‹‹የጉጉቴን ያህል ባይሳካልኝም ቅሉ ይኼ እንደ ማሟሻ ነውና አንብባችሁ ተነጋገሩበት፡፡ በማስረጃና በመረጃ አስደግፋችሁ ተከራከሩበት፡፡ ነበርን የማያውቅ ነውን ሊረዳ አይችልምና በጥሞና መርምሮ መረዳት ተገቢ ይመስለኛል፤›› ሲል አስገንዝቧል፡፡

‹‹ታንታዊ›› - እንደ ዘበት ባይረሳ

 

የጉራጌ ብሔረሰብ ባህል በብሔረሰቡም ጭምር ትኩረት መነፈጉንም ጠቅሶ ባህሎቹ ከጠፉ በኋላ ግን፣ ‹‹እንዲህ ዓይነት ባህሎች እኮ ነበሩን›› ብለው ቢፀፀቱ ዋጋ አይኖረውም ሲል ያሳስባል፡፡ በምሳሌነትም የሚጠቅሳቸው የተዘነጉ በዓላትን እንዲህ አውስቷቸዋል፡፡

‹‹የእናቶች በዓል አንትሮሸት፣ የልጃገረዶች በዓል ነቆ፣ የምዕራቡ ቤተ ጉራጌ የዘመን መለወጫና የእንሰት በዓል ግሩየ እንከን የሚወጣላቸው አይደሉም፡፡ ግና ባለቤቱ ያቀለለው አሞሌ ባለዕዳ አይቀበልም ሆነና ባህሎቹ የሚቆረቆርላቸው አላገኙም፡፡ የብሔረሰቡ ተወላጅ የሆኑ ምሁራን ብዙዎቹ ተምረው ወደ መጡበት መመለስ አይፈልጉም፡፡ በባህላቸው፣ በማንነታቸውና በቋንቋቸው ይሸፍታሉ፡፡ በባህላቸው፣ በማንነታቸውና በቋንቋቸው ያፍራሉ፡፡››

መጽሐፉ ለውይይት መነሻ እንዲሆን መዘጋጀቱንና ሌሎች እንዲያዳብሩት መንገድ የሚከፍት እንደሚሆን እምነቱን አንፀባርቋል፡፡ የጸሐፊው ግብ ባህሉ ላይ ማተኮር ቢሆንም በተጓዳኝ ኢሕአፓ በሰባት ቤት፣ ስብሐት ገብረ እግዚአብሔር፣ ሥነ ልሳናችን ሲወድቅ ሲነሳ፣ ዌየግ፣ የቃቄ ወርድወት ከዠርመነ እስከ ብሔራዊ ቴአትር እና ከሎሚ ሜዳ – ወገፐቻ መጣጥፎች፣ የይልማ ገብረአብና የቴዲ አፍሮ ኢንተርቪዎች፣ ማንዋሌን ተመልከት (ግጥም) እና የፀሐይ ቤተሰቦች በሚል ርዕስ የሰፈሩ መጣጥፎች ለመረጃነት እንደሚጠቅሙ በማየት ማካተቱንም ገልጿል፡፡

ደሟሚት እምን ላይ ይገኛል?

ታንታዊ በጉያው ከያዛቸው ባህላዊና ትውፊታዊ እምነታዊ መገለጫዎች መካከል ደሟሚት ይገኝበታል፡፡ ደሟሚት ‹‹ባዕድ አምልኮ›› በሚል ቅጥያ ምክንያት ሥርዓተ ክዋኔው እየቀነሰ መምጣቱ ደራሲው ገልጿል፡፡ ስለደሟሚት ከጻፈው ውስጥ የሚከተሉት ዐረፍተ ሐሳቦች ይገኙበታል፡፡

‹‹ቀደም ባሉት ዓመታት በይበልጥ ደግሞ 1970ዎቹ በፊት በምዕራቡ ቤተ ጉራጌ የደሟሚት ታላቅነት፣ ተከባሪነትና ተፈሪነት ላቅ ያለ ነበር፡፡ የተለያዩ ሃይማኖቶች እንደዚሁም የተማረው ወገን ሳይቀር በአብዛኛው የባህሉን እሴቶች ኋላ ቀርና ባዕድ አምልኮ ብሎ በመፈረጁ ዛሬ ዛሬ የተከታዮቹ ቁጥር እየቀነሰ መጥቷል፡፡ አሁን ባህሉ ሲጠፋ ምንም ላይመስለን ይችላል፤ የኋላ ኋላ ግን ማንነት ወደመፈለግ ሲኬድ ትልቅ ሐዘንና ፀፀት እንደሚያስከትል እርግጠኛ ሆኖ መናገር ይቻላል፡፡

‹‹ባዕድ አምልኮ ብሎ ከመደምደም በፊት ደጋግሞ ቆም ብሎ ማሰብ ተገቢ ይመስለኛል፡፡ ባዕድ አምልኮ ማለት ምን ማለት ነው? ከጥንት ጀምሮ ብሔረሰቡ ሲተዳደርበት የነበረና ከማንነቱ ጋር የተያያዘው ነው ባዕድ አምልኮ ወይስ ከጊዜ በኋላ ከሌሎች የተቀበለው ነው? የማይመስል ነገር ለሚስትህ አትንገር ይላል የአገሬ ሰው፡፡ ስሜታዊ ሆኖ ሳይሆን ከስሜታዊነት ተላቅቆ ዓይንን በደንብ ገልጦ ማየትና ጆሮን አቅንቶ ማዳመጥ ያስፈልጋል፡፡ በጥናትና በምርምር ታግዞ መወሰኑና አቋም መያዙ ተገቢ ይሆናል፡፡ 

‹‹የደሟሚትን ሥርዓት ባዕድ አምልኮ ነው ብለን ታርጋ ከለጠፍንለት የብሔረሰቡ በርካታ እሴቶችን አብሮ መደምሰስን ያስከትላል፡፡ በየዓመቱ ኅዳር ወር ላይ የሚከበረውን የእናቶች በዓል (አንትሮሸት) በጥር ወር የሚከበረውን የልጃገረዶች በዓል (ነቈ) ይዳር ሙየትን፣ ሁለት ጎሳዎች ተጣልተው ጠባቸው ከፍተኛ ደረጃ ሲደርስ መሀል ገብተው የሚያስታርቁ ሙየቶችን ወዘተ. ሁሉ መጥፋት አለባቸው ማለት ነው፡፡ እያንዳንዱ እሴታችን ከቦዠ፣ ከደሟሚትና ከዋቅ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ የጆካ ታሪክን ወድደን ዋቅን አግልለን አይሆንም፡፡

ሚያዝያ 9 ቀን 2013 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር የተመረቀው ታንታዊ በ120 ብር ለሸመታ ቀርቧል፡፡

ደራሲው በምረቃው ወቅት በመጽሐፉ አማካይነት ያንፀባረቀው ምክረ ሐሳብ የሚከተለው ነው፡፡

‹‹ተነግሮ፣ ተፅፎና ተተርኮ የማያልቀው ባህላችን በአሁኑ ዘመን ከማወቁ ወይም ከማሳወቁ በተጨማሪ የቱሪዝም ምንጭ ሊሆን ይችላልና በእጅጉ ልናስብበትና ልንጨነቅለት ይገባል፡፡ ሥነቃሎቻችንና የተለያዩ እሴቶቻችን በዘጋቢ ፊልም (በዶክመንተሪ) ደረጃ ቢሠሩ፣ በመጽሐፍ መልክ ቢታተሙ፣ የገቢ ምንጭ ከመሆናቸው በተጨማሪ የኢትዮጵያንና የኢትዮጵያውያንን መልክ የማሳየት አቅም እንደሚኖራቸው አያጠራጥርም፡፡››

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የማዳበሪያ አቅርቦትና ውጣ ውረዱ

በቅፅል ስሙ “The Father of Chemical Warfare” እየተባለ የሚጠራው...

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የትርፍ ምጣኔውን ከ70 በመቶ በላይ አሳደገ

ከሁለቱ መንግሥታዊ ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ...