በጥበበ ሳሙኤል ፈረንጅ
“ሐሰትና ስንቅ እያደረ ያልቅ” አገራዊ ብሂል። በርካታ ጥናቶች እንደሚያስረዱት የተለያዩ አገሮች መንግሥታት ሕዝባቸውን በተደጋጋሚ ስለሚዋሹ፣ ሕዝብ በመንግሥት ላይ እምነት አጥቷል። በአገራችንም ከዚህ የተለየ አይደለም። በተለይ ከደርግ የአገዛዝ ዘመን ጀምሮ ሕዝብ በመንግሥት ላይ እምነት ከማጣቱ የተነሳ፣ ሕዝቡን በተለያዩ መንግሥታዊ ዕቅዶች (ፕሮጀክቶች) ላይ ለማሳተፍ የተደረጉ ጥረቶች ከሽፈዋል። በዘመነ ሕወሓትም ከደርግ ጊዜ በባሰና መንግሥት “የረቀቀ” በሚመስለው ውሸቱ፣ ሕዝቡ በመንግሥት ላይ ምንም ዓይነት እምነት እንዳይኖረው አድርጎታል። የመንግሥት ባለሥልጣናት ዛሬም ድረስ ያለተረዱት ነገር ሕዝብ የማያውቀው ነገር የለም። የሚያውቀውን ሕዝብ መዋሸት ግን ለምን ያስፈልጋል?
ሕወሓት ከሥልጣን ማማው ላይ ሲወረወር አንዱ ተስፋችን እውነት የሚነግረን መሪ ይኖረናል የሚል ነበር። ዶ/ር ዓብይም ወደ ሥልጣን ሲመጡ ከተናገሩትና ቀልቤን ከሳበው አንዱ ነገር፣ “ሁሌም እውነቱን እነግራችኋለሁ፤” ማለታቸው ነበር። ከሁለት ዓመታት ገደማ በፊት ለኅትመት በበቃችው “ሕዝቡ ከመሪዎቹ እውነት እንዲነገረው ይጠብቃል” በሚል ርዕስ በጻፍኩት ጽሑፍ፤ “አንዳንዴ እውነቱን መናገር መሪር ሊሆን ይችላል፣ ዋጋም ሊያስከፍል ይችል ይሆናል። ግን ውሸት ተነግሮ፣ ውሸትነቱ ቆይቶም ሲጋለጥ የበለጠ መሪር ይሆናል፣ የበለጠም ዋጋ ያስከፍላል፤” ብዬ ነበር። ዛሬ በማያስፈልግ ውሸት እነሆ አገራችን በዲፕሎማሲው መድረክ ላይ ከፍተኛ ዋጋ የምትከፍልበት ወቅት ላይ ተገኝተናል።
የሕወሓት መራሹ ቡድን በትግራይ በተመደበው የሰሜን ዕዝ የኢትዮጵያ የመከላከያ ሠራዊት ላይ አሳዛኝና ዘግናኝ ጥቃት በመፈጸሙ፣ የፌዴራል መንግሥቱ በትግራይ ክልል በወሰደው ሕግ የማስከበር ዘመቻ የኤርትራ ወታደሮችም መሳተፋቸውን አስመልክቶ ለተነሳው ጥያቄ፣ የኢትዮጵያና የኤርትራ መንግሥታት የሰጡት ምላሽ የኤርትራ ወታደሮች በዚህ ዘመቻ አለመሳተፋቸውን ነበር። አንዳንዶቻችንም በምንችለው መንገድ እውነቱን ለመረዳት ባደረግነው የግል ጥረት በተለያየ የኃላፊነት ቦታ ላይ ካሉ የኤርትራም ሆነ የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት በእርግጠኝነት የተነገረን፣ የኤርትራ ወታደሮች በዚህ ዘመቻ እንደተሳተፉ ነበር። ይህንንም መረጃ በመቀበል ነበር ይህ ጸሐፊ ለአሜሪካ ኮንግረስ የብላክ ኮከስ ሊቀመንበር ለሆኑት ለኦሃዮ ስቴት የሕዝብ ምክር ቤት ተወካይዋ ወ/ሮ ጆይስ ቤቲ፣ እንዲሁም ለሜሪላንዱ የሕዝብ እንደራሴ ቤንጃሚን ካርድንና ሌሎች ተቋማት የኢትዮጵያ የፌዴራል መንግሥት በትግራይ ክልል እየወሰደ ባለው ሕግ የማስከበር ዕርምጃ፣ የኤርትራ ወታደሮች አልተሳተፉም በማለት ለኢትዮጵያ ድጋፋቸውን እንዲሰጡ የጠየቀው።
በጣም የሚገርመውና በተለይም በዓለም አቀፍ መድረክ አገራችንን ተዓማኒነት ያሳጣው፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ የኤርትራ ወታደሮች ትግራይ ክልል ስለመግባታቸው የኢትዮጵያን መንግሥት ለጠየቁት ጥያቄ ዶ/ር ዓብይ ሽምጥጥ አድርገው መካዳቸው ነው። ይህ ግን ፍፁም አስፈላጊ ያልሆነ ውሸት ነበር። ኢትዮጵያ የፈለገችውን አገር በመጋበዝ በሕግ የማስከበር ዘመቻው ተባባሪ ማድረግ ትችላለች። ይህንን የሚከለክል ምንም ዓይነት ዓለም አቀፍ ሕግ የለም። ይህ ጸሐፊ በተደጋጋሚ እንደገለጸው፣ ኃያሏ አሜሪካ ኢራቅንና አፍጋኒስታንን የወረረችው ከሌሎች 49 አገሮች ጋር በመተባበር ነው። የሶሪያ መንግሥት በሩሲያ እየታገዘ ነው ከተቃዋሚዎቹ ጋር ጦርነት የሚያካሄደው። የመን ውስጥ የሳዑዲ ዓረቢያና የተባበሩት ዓረብ ኢምሬትስ እጅ አለበት። ሌላው ቀርቶ በ1970ዎች በሶማሊያ መንግሥት በተደረገብን ወረራ ለድል የበቃነው በሶቪየት ኅብረት ወታደራዊ መኮንኖች አማካሪነት፣ እንዲሁም በየመንና በኪዩባ ወታደሮች ቀጥተኛ የጦርነት ተሳትፎ ነው። ታድያ የኢትዮጵያ መንግሥትም ሆነ የኤርትራ መንግሥት በትግራይ ስላለው ዘመቻ በዓለም መድረክ ላይ ምን አስዋሻቸው?
በርካታ ኢትዮጵያውያን በተለያየ መድረክ ላይ የኤርትራና የኢትዮጵያ መንግሥታት የሰጡትን የተሳሳተ መረጃ እንደ እውነት በመቀበል፣ የኤርትራ ወታደሮች ወደ ኢትዮጵያ አልገቡም ሲሉ ተከራክረዋል። ዛሬም እየተከራከሩ ነው። “የዘፈን ዳርዳሩ እስክስታ ነው” እንዲሉ፣ የኤርትራ ወታደሮች በትግራይ ክልል መኖራቸው መረጃዎች ሲወጡ የኢትዮጵያ ወታደራዊና ሲቪል ባለሥልጣናት የሐሰት ሙዚቃቸውን በመቀየር፣ የሰሜን ዕዝ በሕወሓት ሲመታ ድንበር ላይ በተፈጠረ ክፍተት ‘የኤርትራ ወታደሮች ወደ ኢትዮጵያ ድንበር ገብተዋል” የሚል አሳሳች ከበሮ መደለቅ ጀመሩ። በዚህም ወቅት አንዳንዶቻችን የኢትዮጵያ መንግሥት በዚህ ጉዳይ ላይ ግልጽ የሆነ ነገር ለሕዝብ እንዲያሳውቅ ጠይቀን ነበር። ይህ ግን አልሆነም። ይህ ጽሑፍ እስከተጻፈበት ቀን ድረስ የኢትዮጵያ መንግሥት፣ የኤርትራ ወታደሮች ለምን ወደ ኢትዮጵያ ዘልቀው እንደገቡ፣ ምን ያህል ወታደሮች እንደገቡ፣ ተሳትፏቸው ምን ያህል እንደሆነ ለሕዝብ ይፋ ያደረግው ነገር የለም። ለምን?
ለመሆኑ ዛሬ ከማንም በላይ የትግራይ ሕዝብ የኤርትራ ወታደሮች በክልሉ እንደሚንቀሳቀሱ እያየ የኢትዮጵያ መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት፣ “የኤርትራ ወታደሮች ትግራይ ውስጥ የሉም” እያሉ ሲዋሹ እየሰማቸው በሌላው ነገር እንዴት ሊያምናቸው ይችላል? የትግራይ ሕዝብ በፌዴራል መንግሥቱና በተቀረው ኢትዮጵያዊ ላይ እምነት መጣል በሚያስፈልገው በዚህ አሳቻ ወቅት ዓይኑን ያፈጠጠ ውሸት ስንዋሸው ምን ይሰማው ይሆን? የሕዝቡንስ ልብ እንዴት ማሸነፍ ይቻላል?
“እውነት ትቀጥን እንደሁ እንጂ አትሰበረም” ይባላል። በኢትዮጵያና በኤርትራ መንግሥታት ከአምስት ወራት ክህደትና ድብብቆሽ በኋላ፣ የኤርትራ መንግሥት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ተወካይ ሰሞኑን ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት በጻፉት ጽሑፍ እውነቱን አፍርጠውታል። በዚህ ደብዳቤያቸውም የኤርትራ ወታደሮች ኢትዮጵያ ውስጥ መግባታቸውን አምነዋል። ሆኖም የኤርትራ ወታደሮች በትግራይ ፈጽመውታል ስለተባለው ዘግናኝ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ሙሉ በሙሉ ክደዋል። ትናንት የካዱትን ዛሬ ሲያምኑ እያየን ዛሬ የሚክዱትስ እውነት ላለመሆኑ እንዴት ልናምናቸው እንችላለን?
በተለይ በዚህ የፌዴራል መንግሥቱ በትግራይ የሕግ ማስከበር ሒደት መንግሥት በዓለም አቀፍ ደረጃ በሕዝብ ግንኙነት በኩል ያሳየው ድክመት ከፍተኛና አሳፋሪ በመሆኑ፣ እንደዚህ ጸሐፊ ዓይነት ደቂቅ ዜጎች ይህንን ክፍተት ለመሙላት በተለያየ መድረክ ብዙ ተሟግተዋል፣ ዛሬም እየተሟገቱ ይገኛሉ። ዜጎች “የአገራቸው አምባሳደር” በመሆን በሚያደርጉት ሙግት ግን፣ ሙግታቸው በሐሰት መረጃ የተደገፈ ከሆነ ዛሬ ብቻ ሳይሆን ወደፊትም ተዓማኒነት ስለማይኖራቸው ድካማቸው ከንቱ ሆኖ ይቀራል። ትናንት “ባለማወቅ የዋሸናቸውን” ሰዎች ዛሬ እንዴት ትብብራቸውን ልንጠይቅ እንችላለን?
የኢትዮጵያ መንግሥት መዋሸት በማያስፈልገው አገራዊ ጉዳይ ላይ በመዋሸት በዓለም መድረክ ላይ ውርደት አከናንቦናል። በጉዳዩ በቀጥታ ተጎጂ የሆነውን በተለይ የትግራይን ሕዝብ፣ በአጠቃላይም የኢትዮያን ሕዝብ እምነት አጥቷል ለማለት ያስደፍራል። ሕዝቡ በመንግሥት ላይ እምነቱ እንዲጎለብትና ያለ ምንም ማመንታት የተለያዩ መንግሥታዊ ዕቅዶች ላይ እንዲሳተፍ ለማድረግ፣ መንግሥት ግልጽ በሆነና በማያሻማ ሁኔታ በዚህ የሕግ ማስከበር ዘመቻ የኤርትራ ወታደሮች እንዴት ወደ ትግራይ ሊገቡ እንደቻሉ፣ የተሰጣቸው ሚና ምን እንደነበር፣ ምን ያህል ወታደሮች እንደገቡ አሁን ምን ያህል የኤርትራ ወታደሮች እንዳሉ፣ እንዲሁም መንግሥት በዚህ ጉዳይ ላይ ለምን ለሕዝቡም ሆነ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ እውነቱን እንዳልተናገረ ማብራርያ መስጠት ይኖርበታል።
ከመንግሥት በተጨማሪ በዚህ ጉዳይ ተወቃሽ ሊሆኑ የሚገባቸው “የኢትዮጵያ የአገር ውስጥ ጋዜጠኞች” ናቸው። በአንድም ወቅት የኤርትራ ወታደሮችን አስመልክቶ ጥልቅ ምርመራና መረጃ የያዘ ዘገባ አልሠሩም፡፡ በተለያዩ የመንግሥት ባለሥልጣናት ጋዜጣዊ መግለጫ በሚሰጥበት ጊዜ፣ የኤርትራ ወታደሮችን አስመልክቶ ጠበቅ ያለ ጥያቄ አቅርበው አያውቁም፡፡ ይህ ለምን ሆነ? ጋዜጠኞች እንደ ባለሙያ ሙያቸውን አክብረው፣ ሳያዳሉና ያለ ፍርኃት እውነት ብቻ ሊዘግቡ ይገባል። ይህ ሲሆን መንግሥትም ጥንቃቄ ያደርጋል፣ እኛም ከእንዲህ ዓይነት ብሔራዊ ውርደት እንተርፋለን። ቸሩ እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ይባርክ!
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካካት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡