Sunday, June 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ቆሞ ማንቀላፋት!

እነሆ መንገድ ከአዲሱ ገበያ ወደ ፒያሳ። የእንጀራ ነገር ሆነና ሠልፍ ይዘናል። ዳዋ የሚበላው መሬት አጥቶ፣ ጎዳናው እግር በእግር ተጨናንቆ ሥጋ ላይ መብቀል ያስባል። እንዲህ ያለ ሐሳብ አለእኩይ ሐሳብየሚባል። ሰውነት ሳይሸመግል ለጋነቱን የመንገድ ድውይ ይጫወትበታል።ድኩማንይላል ተራ አስከባሪው።ማንን ነው?” የወይን ፍሬ የመሰለች ሸጋ ልጅ ትጠይቃለች።እኛን ነዋ። ማላገጡ ነው በእሱ ቤት፤ይላታልሪዙን እያፍተለተለ ከኋላዋ የቆመ ወጣት።ድኩማን እባካችሁ ሠልፉን አስተካክሉት። አጣመማችሁት እኮ፡፡ ምሳ አልበላችሁም እንዴ?” የሠልፉ ጌታ።ወቸው ጉድ። ደግሞ ብለው ብለው በሠልፍ አመካኝተው ሆዳችንን መሰለል አመጡ?” አንዲት ወይዘሮ ግራ እየተጋባች ትጠይቃለች።መቼ እነሱ ናቸው መንገዱ ነው እንጂ፣ የማያሳየን የማያመጣብን የለ። እኛም ተሰብረን የማንታሽበት ጥግ የለ፤ከወይዘሮዋ ፊት የተሰየመ ጎልማሳ ይናገራል።

ወዲያ ደግሞ አንዲት ጠምበለል በስልኳ ስታወራ እንሰማታለን።ዘፈን ለመምረጥ ነበር የደወልኩት፤ትላለች።እሰይ! ያንችው ይሻላል አንደኛውን…” ሲል ጎልማሳው ጢማሙ ወጣት፣ቂልነት ነው እንጂ አሁን ለዘፈን ምርጫ በምናጠፋው ካርድ ፈንታ፣ አጠራቅመን በስንዴ ዱቄት ዳቦ ብንደፋበት ስንት ቀን አንበላውም?” ይላል።አንተ ደግሞ መቼ እኛ ከተደፋንበት ተነሳንና ነው ዳቦ የምንደፋው?” አለችው የወይን ሐረጊቱ። “ . . . ደማም ሰው ደማም ሰው ስምህን ልዋሰውየሚለውን ጋብዝልኝ፤የዘፈን ምርጫው ቀጥሏል። ይኼን የሰማ አንድ ዋዘኛ ጉሮሮውን ጠራርጎ፣ማነው የሚያውሳት? ሰው ካልተደራጀ ለሥራ ማስኬጃ የሚያበድረው ቢያጣ በተናጠል ስም ወደ መዋስ ገባ እንዴ?” ይላል።ስም ኑሮ ይሆናል እንዴ?” ብሎ አንዱ ቢጠይቅእንጃ!” እያለ ሁሉም ተከታትለው ወደመጡት ታክሲዎች በየተራ ተሳፈሩ። ዋስና ገላጋይ ያጣ ሁላ!

ጉዟችን ተጀምሯል። ወያላው ጋቢና የተሰየመውን ወጣት ያንገራግራል።ከፈለግክ ወርደህ በባቡር መሄድ ትችላለህ፤ይለዋል።ብፈልግ በባቡር ብፈልግ በታክሲ ብፈልግ በፐብሊክ ሰርቪስ የመጓዝ መብቱ የእኔ ነው። ዕድሜ ለለውጡ መንግሥቴ። አርፈህ ሥራህን ሥራ። በሰው ምርጫ አትግባ፤ይለዋል ወጣቱ ተሳፋሪ።እግዚኦ! ብሎ ብሎ መንግሥት የግል ሆነ?” ወይዘሮዋ ናት ከሾፌሩ ጀርባ ተሰይማ የምታሽሟጥጠው። ከጎኗ ጎልማሳው አለ።ምን ታደርጊዋለሽ? አንዳንዱ እኮ በብብቱ የሚታቀፈው እሳት ይሁን ውኃ አያውቅም፤ሲላት መሀል መቀመጫ ከጎኔ የተሰየመችዋ የወይን አምባ፣ምናልባት ቅኔን ለባለ ቅኔ ቢተውት? እሳት ይለኮሳል፣ ውኃ ይቀዳል፣ ወይ ይደፋል እንጂ በብብት ይያዛል? እግዜር ያሳይህ እስኪ፤ትለኛለች። ይኼን ስትል የሚሰማት ከጀርባችን የተሰየመ ተሳፋሪ ደግሞ፣ሁሉም ሰው የፈለገውን የመናገር ነፃነት አለው የእኔ እህት። የአለቃነትና የተቆጣጣሪነት መንፈስ ነው አንድም ዴሞክራሲያችንና የመናገር ነፃነታችን እንዳሰብነው እንዳያብብ እያደረገው ያለው፤አላት። አንዳንዱ ደግሞ ምኑን ከምኑ እንደሚያገናኘው እንጃ!

ይኼ የድኅረ ዘመናውያንመንገዶች ሁሉ ሮም ያደርሳሉይሉት አስተሳሰብ እኮ በጠበጠን እናንተ!” ትላለች መጨረሻ ወንበር አንገቷ ላይ ስስ ጨርቅ የጠመጠመች ወጣት።ልክ ምንድነው? ልክ እንዴት ያለ ነው?” እያለ ከጎኗ የተቀመጠ አውቆ አበድ መሰል ትክን ሲያደርጋት እያየ ወያላው፣የተሳፋሪዎቼን በሰላም የመጓዝ መብት የሚተናኮል ወደ ሠልፉ ይመለሳልእያለ የማስፈራሪያ ጥቅስ ይጽፋል።አታስፈራሩና! አንገት የደፋነው የምር መሰላችሁ እንዴ?” ይላል መጨረሻ ወንበር በጥግ በኩል የተቀመጠ።ሰው ጨዋታ ጠፋበትሳ በአፉ የሚስተውና የሚያስተው በዛ፤የምትለኝ ደግሞ ከጎኔ የተቀመጠችዋ ቀዘባ ናት።የሚጨበጥ ነገር ሲጠፋ ታዲያ ምን ይደረግ?’ እንዳልላት ኋላ አጉል ተግባብቼ የምይዘው የምጨብጠው ባጣስ ብዬ ዝም። ያውስ እንዲህ የሚጨበጥ የሚያዝ ሲጠፋና ቆርጦ ቀጥሉን፣ የሰይጣን ተላላኪውንና ደም የጠማውን ዕብድ ሃይ የሚል በጠፋበት ጊዜ?! ኧረ ጎመን በጤና ያሰኛል!

ሒሳብ ወጣ! ወጣ!” ወያላው በሙሉ ዓይኑ ለማየት ተፀይፎ ያጣድፈን ጀመረ።አወይ ሥልጣን!” ይላል ከኋላ አንዱ።ከላይ ካልተሰጠ በቀር ሥልጣን የለምብለህ እመን ልጄ፤ወይዘሮዋ መነሻውን በደንብ ሳታጣራ ታማታን ትጀምራለች።አምነናል!” ይላል ወጣቱ በሽሙጥ። ወያላው ፈገግ እያለ፣ማን ላይ ቆመሽ ማንን ታሚያለሽ?” በሚል አስተኔያዊ ዕይታ እየገረፈን ሒሳቡን ይሰበስባል።እንኳንም ግብር ሰብሳቢ አላደረጉህ፤ትለዋለች ከጎኔ። ዘወር ብዬ ሳያት ጠቀሰችኝ።እጅና እግር ይዘን እንዳልተፈጠርን ዕድሜ ልካችንን ወንበሩ ላይ የተቀመጡትን ሰዎች ተጠያቂ ማድረግ መቼ ይሆን የምናቆመው?” ሲል ጎልማሳው፣ምነው ሆድን ዘለልከው?” ብሎ አንዱ ያስታውሰዋል። ‹‹ሆድ መስሎን የአዳምን ልጅ አውሬ አድርጎት ልቡን የነሳው…›› ትለኛለች ቀዘባዋ ጎሸም እያደረገችኝ፡፡ ዘንድሮ እኮ እህ ካሉ አናጋሪ በሽ ነው!

ይኼው በሥራ እንዳንከበር በምግባር እንዳንመሠገን የሚያደርገን ማን ሆነና?” ሲለው፣እስኪ አሁን በሰው ቦርጭ ከመቅናት ሰው የራሱን አያይም?” ትላለች መጨረሻ ወንበር የተቀመጠችው።ምን ትላለች? ምን አጠላለፈን ታዲያ? በታጋይነት ስም መስሎኝ ይኼው መንገዱ የመንታፊና የቀማኛ ብቻ ሆኖ የቀረው፤ሲላት ደግሞ አጠገቧ የተሰየመው አኳኋኑ የሚያስፈራው ወጣት፣የጭቆናው ብዛት አይመስልህም የነፃነት ትግሉን ሜዳ ለጥጦ ጉድ የሠራን?” አለው። ወይዘሮዋ በስጨት ብላ፣አንዴ ሥልጣን ትላላችሁ፣ አንዴ እጅና እግር፣ አንዴ ደግሞ ሆድ፣ ደግሞ አሁን ነፃነትና ጭቆና። ወደ ገደለው ግቡ እንጂ፤ከማለቷ ውቢት ከአፍዋ ተቀብላ፣መግደል ኃጢያት ነዋ፤አለቻት።የለም እንግዲያስ በቁም ማሰቃየትና ማስታመም ነዋ የሚሻለው? የት ሄጄ ልፈንዳ አሉ እማማ?” ብላ ወይዘሮዋ ተንተከተከች። ተሳፋሪው እየተያየ፣ለካ የሰው ልጅ በል ካለው ከብርቱካንነት ወደ ቦምብነት ይሸጋገራል?› እየተባባለ መሳለቅ ጀመረ። ስላቁ ቀርቶብኝ ከፍንጣሪው ባዳነኝ ማለት ይኼኔ ነው!

ጉዟችን ቀጥሏል።ቅርብ ወራጅ አለ?” ወያላው ጠየቀን። ዝም፣ ዝም።ደርቤባችሁ እስከ መጨረሻው ከምትጓዙ ንገሩኝ፤አለ ደገመና።ደርብብና። አዲስ ነገር ነው እንዴ መደረብ?” ቆንጅት መለሰች።ደግሞ ዘመኑ የመጠጋጋትና የመተቃቀፍ ነው፤ቀጠለች። ወያላው በመዳፉ መዝጊያውን ነረተና ታክሲዋን አስቆማት። በስልኩ የሚነጋገር አንድ ጎልማሳ ገባ።እንዲያው ከየትም ብለህ አንድ ሰላሳ ሺሕ ብር የሚያበድረኝ ሰው ፈልግልኝ፤ይላል።ወይ! አንድ ሺሕ ብር ወረቀት በሆነበት ጊዜ ገንዘብ አበዳሪ ጠፋ?” ሦስተኛው ረድፍ ላይ የተሰየመው ወጣት ነው።የዘንድሮ ብር ንፋስ እንዳየ ዱቄት እንደሚበተነው መሰለህ የሚገኘው? እንደ አወጣጣችን መቼ ይገባና?” ይለዋል ከኋላ የተቀመጠ።ሄዶ ሄዶ የት ነው የሚገባው ግን?” ስትልስካርፍየጠመጠመችው፣የእኛን አትጠይቂም? ገንዘብማ ሲፈጥረው ኑሮው አየር ላይ ነው። ካላመንሽ አየር ወለዶቹን መጠየቅ ነው። ሥራ ፈጠራ እያሉ አየር በአየር ሲያጣፉ መሬት የረገጠው ገርጥቶ አለቀ፤ይላታል። እንዲህ ነው እንግዲህ መጨረሻችን!

ወደ መዳረሻችን ተጠግተናል።ወይ አዲስ አበባ!” ትላለች ወይዘሮዋ።እንደ ቀልድ 140 ዓመት?” ብላ ስትገረም፣ምን ዘንድሮ እኮ ሰውም ከተማውም እኩል ዕድሜ መቁጠር ብቻ ሆነ። እንዲያውም የከተሞቹ ይሻላል ኧረ። እያደር ብሶብናል እኛማ፤ሲል ጋቢና የተሰየመው ሳይታሰብ አወራ።ምን ይላል ይኼ? ህያውን ከግዑዝ ጋር ያነፃፅራል እንዴ?” ጎልማሳው ያብዳል።ዘመኑ የንፅፅርና የፉክክር ቢሆን ነዋ፤ትላለች ቆንጂት። ወያላው በበኩሉ፣አዳሜ ባቡር ባቡር ብለሽ ባቡራችሁን አየንላችሁ። መሀል ወገቡን እንደ ተመታ እባብ እንደዚያ እየተጎተተ በዚህ የጥንቸሎች ዘመን የኤሊ ሞተር ገጥመው ተሳፈሩበት ሲሏችሁ እሺ ይባላል?” ይላል።ታዲያ ምን ምርጫ አለ? የተገኘውን መጠቀም ነው፤ስትል ወደ መጨረሻ፣ደግሞ አንሳፈርም በሉ እያላችሁ አድማ ማስመታት ጀመራችሁ? ቆይ፤ብሎ አንዱ ወያላው ላይ ይዝታል።ዛቻን ምን አመጣው?” ሲለው አንዱ ጠጋ ብሎጥጋብ!” ይላል።

እንዲህ በየመንገዱ እየተዛተብን እንዴት ነው ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብታችን ሊጠበቅ የሚችለው?” ብሎ የቅድሙ ወጣት ሲጠይቅአቤት? ወዴት? በማለት እንጂለምን? እንዴት?’ መሥራታቸውን እንጃ፤ትላለች ወይዘሮዋ።ወይ አዲስ አበባ። እዚህ አራዳ ላይ እዚህ ፒያሳ ሁሉ ነገር ተጀምሮ ዛሬ ማቆሚያ ጠፋ። በዚህ ቢሄዱ ግንባታ ነው፣ በዚያ ቢዞሩ ጥርጊያ ነው። መካብ ነው፣ ማፍረስ ነው። እንዴት ደስ ይላል ግን?” ሲል ጎልማሳው ቆንጂት ተራዋን ቀበል አድርጋ፣ምን ዋጋ አለው? ከተማው ሲቆረቆር ከነበረበት ቅርፅና ገጽታ ተቀየረ። ሰው ደግሞ ከተማዋን ሲቆረቁር ከነበረው መልካም ሥነ ምግባርና ይሉኝታ ፈቀቅ አለ። ቦታ ተቀያየርን። አዋክቦ መንጠቅ፣ ፍርፋሪ ለመለቃቀም ሰብዓዊ ክብርን ማዋረድ፣ ሌብነት፣ ዘረኝነት፣ ጥጋበኝነት፣ ሴረኝነትና ክፋት ይኼው ይጫወቱብናል። ከተማው የሁላችንም የጋራ ቤት መሆን ሲገባው የራስ ለማድረግ አጥንት ላይ እንደሚናጠቁ ውሾች ላያችን ላይ ይፋጃሉ…” እያለች ሳለ ወያላውመጨረሻብሎ በሩን ከፈተው። ይህን ጊዜ ነው ራቅ ካለ ሥፍራ፣ ‹‹ሁለተኛው ጥፋት ቆሞ ማንቀላፋት…›› የሚል ድምፅ የሰማነው›፡፡ መልካም ጉዞ! 

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት