Wednesday, June 19, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የሲሚንቶና የአርማታ ብረት ፋብሪካ በ350 ሚሊዮን ዶላር ለመገንባት የመሠረት ድንጋይ ተቀመጠ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ኢስት አፍሪካ ሆልዲንግ ከአንድ ወር በፊት በሰሜን ሸዋ ዞን በለሚ ከተማ ከቻይናው ዌስት ኢንተርናሽናል ሆልዲንግ ጋር በጥምረት የሚሠራውን የኢንዱስትሪ ኮምፕሌክስ ግንባታ ሲያስተዋውቅ ከግንባታዎቹ መካከል አንዱ ሲሚንቶ ፋብሪካ መሆኑን አሳውቆ ነበር፡፡

ከሁለት ቢሊዮን ዶላር በላይ በሚጠይቀው የኢንዱስትሪ ኮምፕሌክስ ግንባታ ውስጥ የሚጠቃለለው የለሚው ሲሚንቶ ፋብሪካ በቀን ወደ አሥር ሺሕ ቶን የማምረት አቅም ያለው በመሆኑ ከአፍሪካ ግዙፍ ፋብሪካዎች መካከል አንዱ ያደርገዋል፡፡ ይህ ከተነገረ ከአንድ ወር በኋላ ደግሞ ፊቱን ወደ ምሥራቅ በማዞር ከዚሁ የቻይናው ሸሪክ ጋር በቀን ከአምስት ሺሕ ቶን በላይ የማምረት አቅም ያለው አዲስ የሲሚንቶና የአርማታ ብረት ማምረቻ በድሬዳዋ ለመገንባት የመሠረት ድንጋይ እሑድ ሚያዝያ 10 ቀን 2013 ዓ.ም. አኑሯል፡፡

የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አቶ ሙሐመድ ድሪር፣ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበልና ሌሎች ከፍተኛ የፌዴራልና የክልል ባለሥልጣናት በተገኙበት የመሠረተ ድንጋይ ማስቀመጥ ሥርዓት ላይ እንደተገለጸው፣ ኢስት አፍሪካና የቻይናው ተጣማሪ ኩባንያዎች በድሬዳዋ የሚገነቡት ዘመናዊ የሲሚንቶና የአርማታ ብረት ፋብሪካ አጠቃላይ ወጪ 350 ሚሊዮን ዶላር ነው፡፡ ከሲሚንቶ ፋብሪካው ጎን ለጎን የሚገነባው የአርማታ ብረታ ማምረቻው ደግሞ 300 ሺሕ ቶን የማምረት አቅም ይኖረዋል፡፡

ኩባንያዎቹ የሚገነቧቸው የድሬዳዋውና የለሚው ሲሚንቶ ፋብሪካዎች በቀን 15 ሺሕ ቶን ሲሚንቶ የማምረት አቅም የሚኖራቸው ሲሆን፣ የናሽናል ሲሚንቶ አራት ሺሕ ቶን የቀን ምርት ሲተከል በጋራና በተናጠል ከእነዚህ ፋብሪካዎች በቀን ወደ 19 ሺሕ ቶን ሲሚንቶ ለማምረት ይቻላል ተብሎ የሚጠበቅ ነው፡፡ ይህም በአገሪቱም ሆነ በአፍሪካ ደረጃ ከፍተኛ የሲሚንቶ አምራች ያደርጋቸዋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

በድሬዳዋው የሲሚንቶና የአርማታ ብረት ፋብሪካዎች የመሠረተ ድንጋይ ማስቀመጥ ሥርዓት ላይ እንደተገለጸው ደግሞ፣ አዲሱ ፋብሪካ የወጪ ንግዱን ታሳቢ ያደረገ ነው፡፡ የለሚው ፕሮጀክት የአገር ውስጥ ገበያ ላይ ሲያተኩር፣ የድሬዳዋው ፕሮጀክት ደግሞ የወጪ ንግድ ላይ እንደሚያተኩር የኢስት አፍሪካ ሆልዲንግ ሊቀመንበር አቶ ብዙአየሁ ታደለ ገልጸዋል፡፡

ሁለቱ ፋብሪካዎችም በተመጋጋቢነት እንዲሠሩ ታስበው የተቀረፁ ፕሮጀክቶች ናቸው፡፡ ፋብሪካዎቹ እጥረት የሚታይባቸውን ምርቶች በጥራት በማምረት ለአገር ውስጥ ያቀርባሉ የተባለ ሲሆን፣ በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ የሚገቡ ብረታ ብረቶችን አገር ውስጥ በማምረትና ምርቶቹን ወደ ውጭ በመላክ የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት ተጨማሪ አቅምን እንደሚፈጥር አቶ ብዙአየሁ ተናግረዋል፡፡

ከጎረቤት አገሮች ጋር ያለውን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ትስስር የሚያሳድግና የንግድ ልውውጡን በማሳለጥም የውጭ ንግድ ሚዛንን የማስተካከል አስተዋጽኦ ያለው የድሬዳዋው አዲሱ የሲሚንቶ ፋብሪካ፣ ምርቱን ለሶማሊ ላንድ፣ ለሶማሊያ፣ ለጂቡቲ የሚያቀርብ ይሆናል፡፡ ይህንን ታሳቢ በማድረግ ዝግጅት ሲደረግ እንደቆየም ታውቋል፡፡ እንደ አቶ ብዙአየሁ፣ የኢስት አፍሪካ አማካሪ ቦርድ አባል የሆኑት አምባሳደር መሐመድ ድሪር በአካባቢው የገበያ ትስስሩን ለመፍጠር የተሳካ ሥራ ሠርተዋል፡፡    

የመሠረት ድንጋይ ከተቀመጠለት የሲሚንቶ ፋብሪካ ቀደም ብሎ ኢስት አፍሪካ ሆልዲንግ የናሽናል ሲሚንቶ ፋብሪካን በባለቤትነት ያስተዳድራል፡፡ የናሽናል ሲሚንቶ ፋብሪካ ዕድገትና ትርፋማነት እንደ ኢትዮጵያ ከሚኮሩባቸው ድርጅቶች ዋነኛ የሚያደርገው፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ ያመጣው ዕድገትና ትርፋማነት ብቻ እንዳልሆነ የገለጹት አቶ ብዙአየሁ፣ ፋብሪካው አሁን ያለበት ነባራዊ ትርፋማነት ለረዥም ጊዜ የሚያስቀጥል ቢሆንም፣ ለክልሉ ወይም ለአገር ዕድገት ካለው መንፈሳዊ ቅናትና ጉጉት ግዙፍ ኢንቨስትመንት ውስጥ እንዲገቡ እንደገፋፋቸው አስረድተዋል፡፡

‹‹የናሽናል ሲሚንቶ ፋብሪካም ሆነ አዲስ የሚገነባው ፋብሪካ ስኬቱ ከድርጅታችን በላይ በድሬዳዋ ኮሪደር ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ላይ የሚፈጥረው አዎንታዊ ለውጥ በቀላሉ የሚታይ አይሆንም፤›› ያሉት አቶ ብዙአየሁ፣ የኢንቨስትመንት ትስስር ከማሳደጉም በላይ የፋብሪካዎቹ መከፈት በቀጣናው አብላጫውን የሲሚንቶ ገበያ ለመቆጣጠር ያግዛል የሚል እምነት እንዳላቸውም አመልክተዋል፡፡

የድሬዳዋውን የሲሚንቶ ፋብሪካ ለየት የሚያደርገው ተብሎ የተጠቀሰው በሲሚንቶ ማምረት ሥራ ከፍተኛ ወጪ ተደርጎ የሚወስደውን የኃይል አቅርቦት ለመቀነስ የሚያስችል አሠራር የሚከተል መሆኑ ነው፡፡ ከውጭ የሚገባው የድንጋይ ከሰል ከ200 ሚሊዮን ዶላር በላይ እንደሚወጣ ያስታወሱት አቶ ብዙአየሁ፣ ይህ አኃዝ አሁን ከሚታየው የኢኮኖሚ ዕድገት ጋር ተያይዞ ሊጨምር እንደሚችል ስለሚታመን ይህንን ሥጋት ለመቅረፍ አማራጭ የኃይል ምንጭ ማደራጀት የግድ ይላል፣ በመሆኑም በሳይንሳዊ ስሙ ፕሮፖሊስ በሚባል የሚታወቀውን መጤ ዓረም በኃይል ምንጭነት በመጠቀም ኩባንያው ተግባራዊ እንቅስቃሴ ጀምሯል ብለዋል፡፡ ይህንን ሥራ የሚሠራው ኩባንያም የተለያዩ የምርምር ሥራዎችን እያካሄደ ሲሆን፣ መጤ አረሙን ለኃይል ለማዋልና በናሽናል ሲሚንቶ ተሞክሮ ሌሎች ፋብሪካዎች እንዲጠቀሙት የማድረግ ውጥን እንዳለ ታውቋል፡፡  

በአፋርና በሶማሌ ክልል በስፋት ተንሠራፍቶ የሚገኘውን መጤ አረም በግብዓትነት ለመጠቀም መታሰቡ አረሙ በኅብረተሰቡ ላይ የሚያሳድረውን ጫና የሚያቃልል ስለሆነ ትልቅ የምሥራች እንደሆነ የሶማሌ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙስጠፌ መሐመድ ተናግረዋል፡፡

የዕለቱ የክብር እንግዳ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አቶ መሐመድ፣ ናሽናል ሲሚንቶ ከፍተኛ የግንባታ ዕቃዎች እጥረት በተከሰተበት ወቅት አጋጣሚውን ያላግባብ ሳይጠቀም፣ ሕግና ሥርዓቱን በጠበቀ አኳኋን በመሥራት የአገር አለኝታነቱን ያስመሰከረ ኩባንያ ነው፡፡

የዌስት ኢንተርናሽና ሆልዲንግ ተወካይ ዣንግ ፑንግ፣ ኩባንያቸው በሲሚንቶ ማምረት ሥራ ከቀዳሚዎቹ አንዱ መሆኑን በመግለጽ፣ በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት እንድናደርግ ያነሳሱን ምክንያቶች ምቹ ኢንቨስትመንት፣ ትልቅ የገበያና ቀና አመለካከት ያላቸውን የኢስት አፍሪካ ቦርድ ሊቀመንበር የሥራ አጋር በማግኘታችን ነው ብለዋል፡፡ አሁን ኢንቨስት ያደረጉበት የሲሚንቶ ፋብሪካ ኃይል ቆጣቢ ሆኖ የሚገነባ ሲሆን፣ ከሸሪካቸው ጋር በሌሎች የምሥራቅ አፍሪካ አገሮች ተመሳሳይ ሥራ እንደሚሠሩ አመልክተዋል፡፡ የለሚውንም ሆነ የድሬዳዋውን ፋብሪካዎች ግንባታ የሚያከናውነው ሲኖማ የተባለው የሥራ ተቋራጭ ነው፡፡

የተቋራጩ ተወካይ ሚስተር ቻንግ እንደገለጹት፣ ኩባንያቸው በሲሚንቶ ኢንዱስትሪ በዓለም ላይ ውጤታማ የሆነ ሥራ መሥራቱን ጠቁመዋል፡፡ ሲኖማ ከ500 በላይ የሲሚንቶ ፋብሪካዎችን ግንባታ ያከናወነ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥም ለተመሳሳይ ሥራ ከመጣ አሥር ዓመታትን ያስቆጠረ ነው፡፡ በዚህም ቆይታው ዳንጎቴ ሲሚንቶ ፋብሪካን የምሕንድስና የግዥና ግንባታ ሥራ ውል ወስዶ ያጠናቀቀ መሆኑንና በተመሳሳይ የሁለት ሲሚንቶ ፋብሪካዎችን የምርት ሒደት አስተዳደር ሥራ እየሠራም የሚገኝ ነው፡፡ የለሚውንም ፕሮጀክት የሚሠራው ይኼው ተቋራጭ ነው፡፡ ሚስተር ቹንግ በለሚ ከ2.2 ቢሊዮን ዶላር በላይ የሚፈጀው ኮምፕሌክስ በአፍሪካ ግዙፍ የሲሚንቶ ስለመሆኑም ጠቅሰዋል፡፡ ፋብሪካውን በተያዘለት የጊዜ ሠሌዳ ለማጠናቀቅ እንደሚሠሩም አመልክተዋል፡፡

ናሽናል ሲሚንቶ ፋብሪካው አሁን ካለበት ስትራቴጂያዊ አቀማመጥና ከ80 ዓመታት በላይ ባካበተው ልምድ አንፃር የአዲሱ ፋብሪካ ምርት ከኢትዮጵያ አልፎ ኤክስፖርት የሚደረግ፣ የውጭ ምንዛሪ ሊያስገኝ እንደሚችል ተስፋ እንደሚያደርጉና ደግሞ ጥሩ ተወዳዳሪ ይሆናል የሚል እምነት እንዳላቸው አቶ መላኩ ተናግረዋል፡፡

ለሲሚንቶ ምርት የኤሌክትሪክ ኃይል፣ መንገድና ትራንስፖርት በአካባቢው እየተጠናከረ መገኘት ለፋብሪካው ተወዳዳሪነት በእጅጉ አስተዋጽኦ ያደርጋሉ ብለዋል፡፡  

ኢስት አፍሪካ ሆልዲንግ ከቻይናው ተጣማሪ ጋር በለሚና በድሬዳዋ የሚገነባቸው ኮምፕሌክሶች በጠቅላላ ከ2.55 ቢሊዮን ዶላር በላይ የሚፈጁ ሲሆን፣ ኩባንያዎቹ ከሚያወጡት ሌላ ከተለያዩ የፋይናንስ ተቋማት በሚያገኙት ብድር የሚገነባ ስለመሆኑ ታውቋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች