በአዲስ አበባና በኦሮሚያ 28 ንዑስ የምርጫ ጣቢያዎች እንዲከፈቱ ወሰነ
መንግሥት ለፖለቲካ ፓርቲዎች ከፈቀደው የበጀት ድጋፍ ውስጥ በእኩል የሚከፋፈለውን የተወሰነ ድርሻ፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለፓርቲዎች በተናጠል ማከፋፈል መጀመሩን አስታወቀ።
ምርጫ ቦርድ መንግሥት ከመደበው የፓርቲዎች የበጀት ድጋፍ ውስጥ የተወሰነውን ድርሻ ለሁሉም ሕጋዊ ፈቃድ ላላቸው ፓርቲዎች የሚከፋፈልበትን ሥርዓት ያመቻቸ መሆኑን፣ በዚህም መሠረት 24.6 ሚሊዮን ብር ለሁሉም ፈቃድ ያላቸው ፓርቲዎች እንዲከፋፈል መወሰኑንና በዚህም አግባብ ከተጠናቀቀው ሳምንት ጀምሮ ለፓርቲዎች ማከፋፈል መጀመሩን ቦርዱ አስታውቋል።
ለሁሉም ፓርቲዎች በእኩልነት እንዲከፋፈል ከተመደበው 24.6 ሚሊዮን ብር ለሁሉም ሕጋዊ ፈቃድ ላላቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች በተናጠል 483,452 ብር ማከፋፈል መጀመሩን የገለጸው ቦርዱ፣ በጀቱን ማከፋፈል ከተጀመረበት ቀን አንስቶም ለ32 ፓርቲዎች ክፍያ መፈጸሙን አስታውቋል።
እስከ ዘንድሮ ድረስ በኢትዮጵያ በአጠቃላይ 107 የፖለቲካ ፓርቲዎች ይንቀሳቀሱ የነበረ ሲሆን፣ በአዲሱ የምርጫና የፖለቲካ ፓርቲዎች አዋጅ መሥፈርቶችን በማሟላት ሕጋዊ ዕውቅና ማግኘት የቻሉት ግን 53 መሆናቸውን የቦርዱ መረጃ ያመለክታል፡፡ ከ53 የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል ዘንድሮ ለሚካሄደው አጠቃላይ ምርጫ ለመወዳደር አመልክተው የምርጫ ምልክት የወሰዱ 49 ፓርቲዎች ናቸው።
ነገር ግን ሁለት ፓርቲዎች በተለያዩ ምክንያቶች ከውድድሩ ራሳቸውን በማግለላቸው፣ በአሁኑ ወቅት ለምርጫ ውድድር የቀረቡት 47 የፖለቲካ ፓርቲዎች ናቸው።
ተግባራዊ መሆን በጀመረው አዲሱ የምርጫና የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ አዋጅ፣ መንግሥት ከራሱ ካዝና፣ ከውጭ ድጋፍ፣ እንዲሁም በአገር ውስጥ ከሚገኝ ድጋፍ ለፖለቲካ ፓርቲዎች በጀት እንዲያዘጋጅ እንዲያደርግ ይደነግጋል፡፡
መንግሥት ለፖለቲካ ፓርቲዎች የሚመድበው የበጀት ድጋፍ በምርጫ ቦርድ አማካይነት የሚከፋፈል ሲሆን፣ ምርጫ ቦርድ የተለያዩ መሥፈርቶችን መነሻ ያደረገ ቀመር በማዘጋጀት የበጀት ድጋፉን የማከፋፈል ሥልጣን በአዋጁ ተሰጥቶታል።
የማከፋፈያ ቀመሩን ለማዘጋጀት መነሻ ከሆኑት መሥፈርቶች መካከል፣ ፓርቲዎቹ ቀደም ብሎ በነበረው ምርጫ ያገኙት የመራጮች ድምፅ ቁጥር፣ ከአባላትና ከደጋፊዎች የሚሰበስቡት የገቢ መጠን፣ ለምርጫ በሚያቀርቧቸው ሴት ዕጩዎች ብዛት፣ በፓርቲው ውስጥ ባሉ ሴት አባላትና አመራሮች ብዛት የመሳሰሉት ይጠቀሳሉ።
ምርጫ ቦርድ ዘንድሮ ለሚያስፈጽመው ምርጫ ለሕዝብ የተወካዮች ምክር ቤት ካቀረበው 3.7 ቢሊዮን ብር በጀት ውስጥ 2.5 ቢሊዮን ብር በ2012 ዓ.ም. ፀድቆለት እንደነበር ይታወሳል፡፡ በኮቪድ ወረርሽኝ መከሰት ምክንያት ምርጫው ወደ ዘንድሮ ከተሸጋገረ በኋላ የወጪ ፍላጎቱ በመጨመሩ 1.1 ቢሊዮን ብር በተጨማሪነት እንዲመደብለት ጥያቄ አቅርቦ የፓርላማውን ውሳኔ በመጠባበቅ ላይ መሆኑን፣ ከጥቂት ሳምንታት በፊት መዘገባችን ይታወሳል።
ከመንግሥት ከተመደበለት በጀት በተጨማሪ ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም (ዩኤንዲፒ) በዓይነት 40,004,000 ዶላር ድጋፍ የሚደረግለት ሲሆን፣ የዚህም ዓላማ ቦርዱን ብቁ፣ ግልጽና የሚታመን ተቋም ለማድረግና አካታች፣ ግልጽና ተዓማኒነት ያለው ምርጫ ማድረግ እንዲችል ለማገዝ ነው፡፡
በሌላ ዜና ምርጫ ቦርድ ቀደም ብሎ በአዲስ አበባ ከተማና በኦሮሚያ ክልል እንዲቋቋሙ ከፈቀደው የምርጫ ጣቢያዎች በተጨማሪ፣ በአዲስ አበባ 15 እና በኦሮሚያ 13 በድምሩ 28 ንዑስ የምርጫ ጣቢያዎች እንዲቋቋሙ በዚሁ ሳምንት ወስኗል።
በምርጫ ሕጉ መሠረት አንድ የምርጫ ጣቢያ የሚያስተናግደው ከፍተኛው የመራጮች ቁጥር 1‚500 መሆን እንዳለበት የሚደነግግ ሲሆን፣ በአዲስ አበባና በኦሮሚያ ክልል የሚገኙ የተወሰኑ የምርጫ ጣቢያዎች ከተጠቀሰው ቁጥር በላይ የመራጮች የምዝገባ ፍላጎት በመታየቱ ነው ንዑስ የምርጫ ጣቢያዎቹ እንዲቋቋሙ የወሰነው።
በየትኛውም አካባቢ ተመሳሳይ ሁኔታ በቀጣይ የሚታይ ከሆነ፣ ተጨማሪ ንዑስ የምርጫ ጣቢያዎች እንዲቋቋሙ ሊወስን እንደሚችልም ቦርዱ አስታውቋል።